ኧረ ጉድ ነው !!!
በረከት ስምዖንና አዲሱ ለገሰ ወደ ባህር ዳር አቅንተው ነበር። መቸስ በረከት ስምዖን አማራ ካልሆንኩ ሞቼ እገኛለሁ ብሎ አለመንደሩ የአማራ ህዝብ መሪ እኔ ነኝ ብሎ ከአማራ ህዝብ ፊት ሲቆም አለማፈሩ ያስገርማል። አዲሱ ለገሰም እንደ በረከት ራሱን የአማራ ህዝብ ወኪል እኔ ነኝ ይላል።እነዚህ ሁሉት ህወሃት የሠራቸው ፍጡራን ባህር ዳር እንዲወርዱ ያደረጋቸው ብአዴን ተዳክሟል ተብሎ መታሠቡ ነበር።
እንግዲህ በእንበረከት የአስተሳሰብ ደረጃ ብአዴን ተዳከመ ሲባል ምን ማለት ይሆን?
ከጥቂት ደካማ ካድሬዎች በቀር ሌሎች እንደ ሰው ማሰብ የሚችሉ የብአዴን አባላት አገሪቷ እየሄደች ያለችበት መንገድ ያሳስባቸዋል። ህወሃት በአማራ ህዝብ ላይ እያደረሰ ያለው ግፍ የሚያንገበግባቸው በርካታ ናቸው። ጉርፋርዳ እና ቤንሻንጉል አገራችሁ አይደለም ተብለው አማሮች ከኖሩበት ቀየ ተፈናቀለው ሜዳ ላይ የመውደቃቸው ድርጊት የእግር እሳት ሁኖ የሚለበልባቸው ብዙዎች አሉ። በዚህ ሁኔታ ያዘኑና የተቆጡ የብአዴን ካድሬዎች ድርጅቱ ቆሜለታለው የሚለው ፍትህ የት አለ፤ እኩልነትስ ከወዴት አለ፤ ኢትዮጵያስ የሁላችን አገር ነች የምትባለው መገለጫው ምንድ ነው እያሉ ይጠይቃሉ። እነዚህ ጥያቄዎች በካድሬዎች መካከል መመላለስ ሲጀምሩ ድርጅቱ ተዳክሟል ተብሎ ግምገማ ይካሄዳል።
በረከት እና አዲሱ ነፃነትን ሳያውቁ ራሳቸውን ነፃ አውጪ አድርገው የሚቆጥሩ የህወሃትን ዙፋን ከመጠበቅ የዘለለ ምንም ሚና የሌላቸው ያልሆኑትን ለመሆን የሚውተረተሩ ደካሞች መሆናቸውን እናውቃለን። እነዚህ ግለሰቦች ስለ አማራ ህዝብ ነፃነትና ክብር ይሠራሉ ብሎ ማሰብ የሚቻልበት ሁኔታ የለም። በረከትና አዲሱ በህዝብ መካከል እየኖሩ የህዝብ ፍቅር የሌላቸው፤ ከህዝቡ ጋር መኖርንም የማያውቁ፤ እለት ዕለት በሚፈጥሩት የፍርሃት አረንቋ ውስጥ የሚኖሩ እና ሠላም የራቃቸው ግለሰቦች ናቸው። ከእነዚህ ግለሰቦች እውነትን ፈልጎ ማግኘት፤ ነፃነትን ጠይቆ መቀዳጀት፤ ለፍትህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት የሚቻል አይደለም። የአማራ ህዝብ ከጉራፋርዳ እንዲወጣ የተደረገበት ምክንያት ምንድ ነው ተብለው ሲጠየቁ የጠባቦች ጥያቄ ብለው ይሳደባሉ። አያቶቻችን በደምና አጥንታቸው ያቆዩልንን ድንበር አፍርሳችሁ ለባእዳን ለምን ትሰጣላችሁ ሲባሉ የጦርነት ናፋቂ ጥያቄ እያሉ ይዘባበታሉ። እንደምን ሁኖ ከሁለት ሚሊዮን በላይ አማራ ከቁጥሩ ጎድሎ ተገኘ ሲባሉ የትምክህተኞች ወሬ እያሉ ይሳለቃሉ። አዎን እነበረከት ስምዖን የሚፈልጉት ዜጎች ስድባቸውን ተሸከመው እንዲኖሩላቸው እንጂ እውነትን፤ ፍትህን እና እኩልነትን እንዲጠይቁ አይደለም።