ድንግል ማርያም-የማራኪ ክርስቲያናዊ ሕይወት ምሳሌ
መጽሐፍ ቅዱስ ድንግል ማርያም ከዳዊት ዘር መወለዷን ይመሰክራል፡፡ (ማቴ. 1፡1-18)፡፡ የቤተክርስቲያን የትውፊት ትምህርት ደግሞ ከኢያቄምና ከሐና በሕግ በሆነ ሩካቤ እንደተወለደች፤ በንፅህናና በቅድስና በመቅደስ እንዳደገች ያስተምራል፡፡ (ቅዳሴ ማርያም ቁ. 38 ገጽ 169)፡፡ ድንግል ማርያም መድኃኒት ወደ ዓለም የገባባት በር ናት፡፡ እግዚአብሔር ዓለምን ለማዳን የቀጠረው ቀን ሲደርስ የአንድያ ልጁ ዙፋን አደረጋት፡፡ ብርሃናዊው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ወደ እርሷ ተልኮ መጣ፡፡ ከእግዚአብሔር የሠማውን የምስራች ሰበከላት፤ የሰውን ልጅ የመዳን ዜና አበሰራት፡፡ (ሉቃ. 1፡26-36፡፡ ቅዳሴ ማርያም ቁ. 45 ገፅ 170)
በራማው መልአክ የሰላምታ ቃል ውስጥ የድንግል ማርያም ውበት ተብራርቷል፡፡ ከተለዩ የተለየች፤ ከከበሩት የከበረች፤ ከተመረጡት የተመረጠች እንደሆነች ተገልጧል፡፡ መልአኩ “አባቶችሽ ሱባኤ የቆጠሩለት፣ ትንቢት የተናገሩለት መሲህ ካንቺ ይወለዳልና ደስ ይበልሽ፡፡ ሕይወትን የሚደግፋት፤ ሁሉን የሚያድን፤ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡ አባቶችሽ በጽድቅ ያመለኩት እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነውና፡፡ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ (ለክብሩ ዙፋን የተለየሽ) ነሽ” አላት፡፡
እመቤታችን ቅድስት
ድንግል ማርያም የአካላዊ ቃል (የመለኮት) ማደሪያ ሆናለች፡፡ አባቱ በዙፋኑ ሆኖ ሲያይ በትሕትናዋ ልቡ አረፈ፤ በትህትና ለሚገለጠው ልጁ እናት አደረጋት፡፡ ድንግል ማርያም የአምላክ እናት ናት፡፡ በ431 ዓ.ም በጉባኤ ኤፌሶን ንስጥሮስ ከተወገዘባቸው ሃይማኖታዊ ጉዳዮች አንዱ ክርስቶስ አምላክ መሆኑን እናቱ ድንግል ወላዲተ አምላክ መሆኗን ስለካደ ነው፡፡ በጊዜው የነበሩት የክርስትናው ዓለም ሊቃውንት ንስጥሮስን አውግዘው “ክርስቶስ የዘላለም አምላክ መሆኑን፤ እናቱ ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ (Theotokos) መሆኗን መስክረዋል፡፡ የእመቤታችን ትልቅ ክብር አምላክን ለመውለድ መመረጧ ነው፡፡ የመንፈስ ቅዱስ እሳት የነካው ትውልድ የጌታዬ እናት ብሎ ይጠራታል፡፡ ሉቃ. 1፡43፡፡ የወለደችው ልጇም ክብሯ፣ ጌታዋ፣ አምላኳና መድኃኒቷ ነው፡፡ በልጇ ቀልድ አታውቅም፡፡ (ሉቃ. 1፡47)፡፡
ድንግል ማርያም የደስታ መፍሰሻ ናት፡፡ የመላእክትን ተድላ ደስታ የምእመናንን ፋሲካ ኢየሱስ ክርስቶስን ወልዳለችና፡፡ ሀዘን የወጋውን ልብ በደስታ የሚያፈካው፣ አልቃሻውን ዓለም የደስታ ዘይት ያፈሰሰበት፤ የናዝሬቱ ኢየሱስ የማይወሰድ ደስታ፤ የማይነጠቅ በጎ እድል ነው፡፡ ዳዊት በአባቱ ቀኝ ያለ ፍሰሀ ብሎ ተመክቶበታል፡፡ (መዝ. 15፡11)፡፡
እመቤታችን ቅድስት
ድንግል ማርያም የክርስትና ትልቅ ፊደል ናት፡፡ “ድንግል ማርያም የማራኪ ክርስቲያናዊ ሕይወት ምሳሌ ናት፡፡” አምብሮስ (Ibid 2:2:6, p116:208) እግዚአብሔር በድንግል ማርያም ሕይወት ውስጥ የልጁን መልክ ስሏል፡፡ ከሕይወቷ ገጽ የምናነበው አርአያነት አላት፡፡ እስኪ እናንብባት፡-
1. የእምነት ሕይወት፡- ከመልአኩ በድንግልና የመውለድን ዜና ስትሰማ “እንዴት ይሆናል?” የሚል ጥያቄ አነሳች፡፡ መልአኩም “ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም፡፡” በማለት የእምነትን መሰረት ሰበከላት፡፡ እርስዋም በእምነት “የጌታ ባርያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” ብላ መለሰች፡፡ በእግዚአብሔር መቻል ተደገፈች፡፡ ፀሐፊው ሉቃስም “ያመነች ብፅዕት ናት” ብሎ መሠከረላት፡፡ (ሉቃ. 1፡36-46)፡፡ ሴት ያለወንድ ዘር ወለደች የሚል የዓለም ዜና የለም፡፡ የዓለም ሥርዓት በተፈጥሮ ሥርዓት ግዛት ሥር ነው፡፡ ድንግልን መልአኩ ያለ ወንድ ዘር በድንግልና ትወልጃለሽ፤ ይህም በእግዚአብሔር መቻልና ማስቻል ይከናወናል፤ ሲላት በእምነት ተቀበለች፡፡ በቃና ገሊላ ሠርግም ሁሉን እንደሚችል አምና ጠየቀችው ሁሉን ቻይነቱንም ሰበከች፡፡ “የሚላችሁን አድርጉ” ብላ አዘዘች (ዮሐ. 2፡1-11)፡፡ የማይሆን ያልነው በእግዚአብሔር መቻል እንደሚሆን ካመንን ድንግልን በእምነት መስለናታል፡፡ ዛሬ በእምነት ሳይሆን በማየት የሚመላለሱ፤ በራሳቸው ማስተዋል የተደገፉ፣ በእግዚአብሔር መቻል የማይተማመኑ ሰዎች እየበዙ ነው፡፡ ከድንግል ማርያም ሕይወት እምነትን እንዲማሩ እንጋብዛለን፡፡
2. የድንግልና ሕይወት፡- ድንግል ማርያም ኢሳይያስ ቀድሞ የተናገረላት ድንግል ናት፡፡ ኢሳ. 7፡14፡፡ ሕዝቅኤልም በምስራቅ ያያት የተዘጋች ደጅ፤ የታጠረች ተክል ናት፡፡ ድንግል በድንግልና ወለደች፡፡ የወለደችው ከእርሷ በፊት የነበረውን ፈጣሪዋን ነው፡፡ ቅዱስ ቄርሎስ “ድንግል ፈጣሪዋን ወለደች” እንዳለ፡፡ ስለዚህ የድንግልና ሕይወት አርአያ ናት፡፡