ግንቦት 19 2008 ዓ.ም
ከአምሳለ ዓለሙ
ዘረኛው ወያኔ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት አልሞ የተንቀሳቀሰው ገና እንደ ድርጅት ሳይዋቀር ሳይቀፈቀፍ በዕንቁላልነቱ እያለ ነበር። የማንን ዓላማ የማንን ምኞት ለማስፈጸም ነው የሚለው ጥያቄ የሃገሩን ታሪክ በገረፍ ገረፍ ለሚያውቀው እንኳ የተሰወረ አይደለም። ወያኔነት ፀረ አገር፣ ፀረ ሕዝብ፣ ፀረ ታሪክ፣ ፀረ ሃይማኖት፣ ፀረ ሁሉም ጥሩ፣ ደግ ነገር ሲሆን፤ የመጨረሻ ደረጃው (ለመከሰቱ ምንም ጥርጣሬ የማይኖረን) ደግሞ በአሰቃቂ ሁኔታ ይህ ከይሲ ቡድን ሊጠፋ፣ እንደ ጉም ሊበን፣ እንደ አዋራ ሊበተን ጉዞው መጀመሩ ነው። ግንቦት 19 ብለን ወደ 21 እንዳንዘልና ግንቦት 20ን ወደ ቀን መቁጠሪያው ለመመለስ ከመቼውም በበለጠ አንድ ሆነን ኃይላችንን አስተባብረን ፀረ ወያኔ ትግላችን መፋፋም አለበት።
ገና ከጅምሩ የተባበረ ክንድ ድል የመንሳቱ እውነት ያሳሰበው ወያኔ በ-የአውቅልሃለሁ ብሂል ሽፋን ሁሉም ብሄር የራሱን ከፈሎ ከጣራ በታች እንዳለ አምፑል ለራሱ ቤት ብቻ እንዲጠቅምና እርሱነቱ እንዲገደብ፣ ተከልሎ እንዲኖርና የእኔ የበላይነት ስሜትን በማጫር የህብረትን ዓላማ አዳክሞ አመለካከትን ልምሾ የማድረግ ስልቱ ጥቂት የጠቀመው ቢመስልም፤ የሰፊው ሕዝብ የእርሱነቱ መለያ፣ የመኖሩ ዋስትና፣ ማንነቱ ያዋሐደው እርሱነት አለውና ልክ የአንድን ሰው አካል በየክፍሉ ገነጣጥሎና ለይቶ በሕይወት ኑር የማለት ያህል አዳጋች ሆኖበታል።
የወያኔ አገዛዝ በአሜሪካና በምዕራብ መንግሥታት ሙሉ ድጋፍና ትብብር የኢትዮጵያን ሕዝብ በአጠቃላይ፤ በተለይ ደግሞ ተቃዋሚዎች፡ ጋዜጠኞች፡ ለሰብአዊ መብት መከበር በሚንቀሳቀሱ ኢትዮጵያዊያን ላይ የሚያደረጋቸው ወከባ፣ እንግልት፣ እስራትና ግድያዎች የተነሳ በርካቶች ለስደት ተዳርገዋል። ወያኔ ይህንን ድርጊቱን በመፈጸም ላይ የሚገኘው በጠመንጃ ኃይል የያዘው ሥልጣን ላይ ተፈናጦ ለመቆየት በመሆኑ ይህ ደግሞ ያለ ባዕዳን የፖለቲካና የኤኮኖሚ ድጋፍ ላለፉት 25 ቀርቶ የአንድ ቀን እንኳ የሥልጣን እድሜ ለማግኘት የማይቻለው መሆኑ የአደባባይ ሚስጢር ነው። ሙስናውንና የሰብዓዊ መብት ረገጣውን ለመሸፈን ኢትዮጵያ የታሪክ ማህደርነትዋን የአልሸነፍ የጀግንነት ምንጭ መሆንዋ ከሚቆጠቁጣችው ጋር በመሻረክ በአጥንት መከስከስ ተመትራ በደም የተገዛች የማንነት ምድርን እጅ መንሻ አድርጎአል። ስለሆነም ወያኔንን ከሥልጣን ለማስወገድ የምናደርገው ትግል ኢፍትሃዊ የሆነውን የባዕዳንን ጣልቃ ገብነትም አብሮ ማስወገድ የሚኖርበት በዚሁ ምክንያት ነው።
ወያኔ በጫካ ዘመኑም ምዕራባዊያን መንግሥታት በተለይም አሜሪካ የደርግን ፖለቲካ ለመቃወም ሲባል ብቻ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ወደጎን በማድረግ አድርገውለት የነበረው ድጋፍ እጅግ ግዙፍና ካቅሙ በላይ ነበር። በኋላም በትግራይ ለደረሰው የረሃብ ጉዳት በሚል የጎረፈለት በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር የገንዘብ እርዳታ አሳብጦት አሁን ላለንበት የሃገር አድን የሞት ሽረት ትግል ሁኔታ አብቅቶናል። የግንቦት ወር በመጣ ቁጥር ሃዘናችንን ብቻ እያሰብን እስከመቼ እንኖራለን? እስከመቼ ወያኔዎች መሬታችንን ለሱዳን እየሸጡና ለመሸጥ እያስፈራሩን ይኖራሉ? እስከመቼስ ጎረቤት አገሮች የኛን መብራት እየገዙ እኛ በጨለማ እንጨናበሳለን? እስከመቼስ ወጣት እህቶቻችን በየአረብ አገሩ፣ ሕጻናቶቻችን በምዕራቡ አገር እየትሸጡ ዝም እንላለን? እረ ወያኔ እስከመቼ?
አናሳው ወያኔ እንዴት በላያችን ይህን ያህል ዘመን ቆየ ስንል የተለያዩ ሰንካላ ምክንያቶችን እንደ መልስ ልንቀበል እንችል ይሆናል። ጊዚያዊ ጥቅም፣ አልጠግብ ባይነት፣ ወያኔያዊ በሽታ (በጎጥ ማሰብ)፣ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን መፍትሔ መሻት…ወዘተና ከመሳሰሉት ርቀን ራሳችንን መርምረን የስካሁኑን ጉዟችንን ገምግመንና በጎውንና ክፉውን ለይተን የትግላችንን መስመር ካልቀየስን የዘረኞች መጫወቻ ሆነን የነሱን ዕድሜ ቆጣሪ ሆነን ባልተኖረበት ዘመን እየዘመንን እንቀራለን።
ትውልድ ሊረከበው የሚገባውን ታሪክ ጥላሸት የመቀባትና የማጣጣል ሽንፈት፣ የሰው ልጅ የመኖሩ መገለጫ ስለ ነጻነቱ እንዳይናገር የመታፈኑና የአትተንፍስ ኑሮው፣ ከባለቤቱ ጉሮሮ በመንጠቅ በ- አጉርሰኝ ለአጉርስህ ለሽርኮች በመላክ፤ ሕዝብ የበይ ተመልካች ሆኖ በጠኔ እየተቆራመደ፣ የሃገር ህልውና ተከብሮ እንዳይኖር የጥፋት ዘመቻው . . . . . . እነዚህ ሁሉ የለውጥ ማነቆ ውጤቶች ግንቦት 20 ተብሎ 1 ሲባል ጀምሮ 25ቱንም ዓመታት ያልተኖረባቸው ዓመታት ያሰኛቸዋል።
የትግሉ ሂደትና አቅጣጫ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ግንዛቤ ቢያገኝም አስፈላጊው ተሞክሮ አሁንም ተወስዷል ለማለት የሚያስደፍር ግን አይደለም። ለዚህም ነው በወያኔ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም የተቃውሞ እርምጃዎች በነዚሁ አቅፈው ደግፈው ከሥልጣን ለማቆየት በሚጥሩት ባዕዳን ላይም ያነጣጠረ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከምንጊዜውም በበለጠ ግንዛቤ አግኝቶ በራስ ሕዝብ ላይ እምነትን ያሳደረና የተመሰረተ እልህ አስጨራሽ ትግል ማካሄድ ተገቢና ወሳኝነቱ ግልጽ መሆን የሚያሻው። አንድ ሆነን
ዘረኛውን አገዛዝ እናስወግድ!!
No comments:
Post a Comment