ዴሞክራሲያ ቅጽ 42 ቁ. 2 ጥቅምት/ ኅዳር 2009
በማንኛውም የሥርዓተ ማኅበር ልውውጥና ሂደት የሚተላለፍ ኅብረተሰብ፣ ተወደደም ተጠላ፤
የሽግግር ወቅት የሚያስፈልገው መሆኑ አያከራክርም። ለዚህም በቂ ምክንያቶች ይኖራሉ። በቅርቡ
የሀገራችን ታሪክ እንኳን ሦስት ተፃራሪ ሥርዓቶች፣ ባለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት ሲለዋወጡ
የተመለከትን ሲሆን በሥርዓቶቹ ልውውጥ መካከል ለተተኪው ሥርዓት መተላለፊያ፣ ማስተናገጃና
መቆጣጠሪያ ሊሆኑ የሚገባቸው በቂ ዝግጅቶችና መሰናዶዎች ሳይደረጉ ቀርተዋል። ሂያጁውን
ማስወገድ እንጅ፤ መጭው ምን እንደሚመስል እንኳን በቅጡ ሳይታወቅ በመታለፉ ፤ በሁሉም መስክ
አገራችን መጎዳቷን ሁሉም ዜጋ የሚያውቀው ዕውነታ ነው። የዚህ ውጤትም የማያቋርጥ ፀፀትና ቁጭት
ሆኖ ቀርቷል። "አርቆ ማሰብ አቅቶኝ፤ በግብታዊነት እጄን በእጄ ቆረጥኩት" የሚያሰኝ ትካዜን ጥሎ
ሄዷል።
ያለፉት ሦስት ፅንፈኛ ሥርዓቶች የተፈራረቁት አንዱ ሌላውን በማስወገድና ሥልጣኑን በመተካት
ቢሆንም ሕዝቡ የበይ-ተመልካች በመሆን ተበደለ፤ ተጎዳ እንጅ፤ የመፃዒ ዕድሉ ቀያሽም ሆነ የመብቱ
ወሳኝ አልሆነም። እያንዳንዱ ሥርዓት ከአንዱ ወደሌላው በሚተላለፍበት ወቅት የለውጡ ሂደት
የፈጠረው ክፍተኛ ግርግር፤ ሕዝቡ የሚመኘውን የለውጥ ረድዔትም ሆነ በረከት እንዳያገኝ አድርጎታል።
ዕድሉን ተነጥቋል፤ ተስፋው የምድረ-በዳ ውልብልቢት ሆኖ ቀርቷል ። ያም በመሆኑ፤ ሽግግሩ የጥቂት
ሥልጣን ጥመኞች ማርኪያ ሆኖ አልፏል። ሕዝቡ ተሳታፊ ሊሆን ባለመቻሉም የብሩኅ ተስፋ ዕድሉ፤
ተሰናክሎ ቀርቷል። የዚህ አንደምታ፤ እስካሁን ድረስ ሀገሪቱን እያማቀቃት ይገኛል።
ይህ ችግር በሦስቱም ተከታታይ ሕዝባዊ አመፆች ተፈጽሟል - ተደጋግሟል። ከዐፄው ሥርዓት እስከ
ወያኔ አገዛዝ ተሰልሷል። በተለዋዋጮቹ ሥርዓቶች ሂደት ውስጥ ሕዝብ የሥልጣን ባለቤትና ተጠቃሚ
ባለመሆኑና የሕዝብ ተሳትፎ ተግባራዊ እንዲሆን ባለመደረጉ፤ የተጠበቀው የሀገር ተስፋ መክኗል።
1ኛ/ የ1966ቱ የካቲት ሕዝባዊ አመፅ ሲፈነዳ፤ የነበረውን ሥርዓት ለመለወጥ ተችሎ ነበር። ግን መተኪያው
አልነበረም። በዘውዳዊ የአገዛዝ ሥርዓት የፖለቲካ ነጻነት በመታፈኑ የተጀመረውን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ
አቅጣጫና መልክ አስይዞ ሊያስኬድ የሚችል ህጋዊነት ይዞ በይፋ የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ኃይል
አልነበረም። በህቡዕ የተደራጁ የፖለቲካ ክፍሎች አመጹ መልክ ይዞ ሕዝብ የሥልጣኑ ባለቤት እንዲሆን
የታቻላቸውን ቢያደርጉም ተደራጅቶና ታጥቆ የነበረው ወታደሩ ክፍልና ተባባሪዎቹ ሥልጣኑን
በቁጥጥራቸው ስር አደረጉ። በአስራ ሰባት ዓመት የፋሽስት አገዛዝ ዘመናቸው፣ ምሁራኑን፣ አርበኛውን፣
ወጣቱን፣ አዛውንቱን፣ ….ወዘተ ፈጁት። በመጨረሻም የሕዝቡን አመፅ ከንቱ አስቀርተው፤ ሀገሪቱን
አራቁተው፤ በየፊናቸው ተበታትነው ፈረጠጡ። ኢትዮጵያንም ለሌላ ሀገር አጥፊ ቡድን አሳልፈው
አስረከቧት። በአዲስ ጥርስ ለሚግጥ፤ ለሌላ በላዒ ሰብ አጋለጧት። ንጉሡን አስወግደው በጊዜያዊ
ወታደራዊ መንግሥት መሸጋገሪያ ሽፋን የነጠቁትን ሥልጣን ለማደላደል ሲሞክሩ በዚህ መልክ የታቀደው
ሽግግር ወደ ሕዝብን ሌላ አምባገነንና ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ይዳርጋል እንጅ ሕዝብን ሥልጣን ሊያቀዳጅ
ወደሚችል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አያሸጋግርም በማለት በወቅቱ ኢሕአፓና ሌሎች የለውጥ ኃይሎች
ታግለዋል። ተገቢው የሽግግር ሂደት ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት መሆኑንም በማሳየት ሕዝብ በዚህ ዙሪያ
እንዲታገል አድርገዋል። ኢትዮጵያ፤ ከነበረችበት የፊውዳል ሥርዓት ወጥታ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት
ልትሸጋገር የምትችለው በዚህ መንገድ ብቻ መሆኑ ግልጽ ነበር። ይህ ሳይሆን ቀርቶ የደርግ ፋሽስቶች
"የወታደራዊ መንግሥት ኅበረተሰባዊነት”፤ “ሳይንሳዊ ሶሻሊዝም” ...ወዘተ ወደሚል ቅዠት ሄደው ሀገሪቱን
የመሃይም ቤተ ሙከራ አድርገዋትና አጥፍተዋት ጠፉ።
2ኛ/ ሌላው የታሪክ ግንዛቤ የ1983-ኡ ሁኔታ የፈጠረው፣ ክፍተት ሲሆን በ1966- 67 ሕዝባዊ ድልን
የነጠቁት ወንጀለኞች፤ ፈርጥጠው በሚሸሹበት ወቅት በተፈጠረው ክፍተትና ውዥንብር፤ አሁንም
አጋጣሚውን፤ የራሳቸውን የግል ዓላማ ብቻ ለማሳካት አድፍጠው የጠበቁ ፀረ-ኢትዮጵያ ጎሰኞች
በባዕድ ትዕዛዝ እየተመሩ ፤ የሕዝቡን ድል ለመንጠቅ ችለዋል። ቀደም ሲል በነበሩት 17 ዓመታት
አንዳችም ዝግጅት ሳይደረግ በመቅረቱ፤ አድፋጭ ኃይሎች በትረ-ሥልጣኑን በቀላሉ ለመያዝ በቅተዋል።
ለጥቅማቸው ካሰፈሰፉ የፀረ-ኢትዮጵያ ኃይላት ትብብርንና እርዳታንም በገፍ አግኝተዋል።
ኢትዮጵያን የሚወክል ድርጅት ቀርቶ፤ ገለልተኛ ታዛቢ እንኳን ባልተገኘበት የሎንዶን ስብሰባ ተብየው፤
ሀገራችንን በዘለቄታ መልኩ የሚጎዳ ውሳኔ አስተላልፎ ተደመደመ። ታጋይ ኢትዮጵያውያን ድርጅቶችንና
ግለሰቦችን በማግለል በጸረ-ኢትዮጵያ ኃይላት በጥንቃቄ የተመረጡ ቡድኖችና ግለሰቦች ተሳተፉበት
የተባለው የአዲስ አበባው የሽግግር ጉባዔ በሻዕቢያና በወያኔ ሴራ አገር አፍራሽ ፕሮግራም አጽድቆ
ተለያየ እንጅ ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ የሚበጅ ውጤት አላመጣም። የይስሙላው የሽግግር ጉባዔና ተከትሎ
የመጣውም የሽግግር ወቅት ኤርትራን በመነጠል ኢትዮጵያን አዳከመ፤ ሕዝቧንም በጎሳ ከፋፍሎ
ለአምባገነኑና ለዘረኛው የወያኔ ቡድን ጥቃትና ባርነት ዳረገ እንጅ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን እንዲሆን
አላደረገም። አሁንም የኢትዮጵያ ሕዝብ በዳግመኛ፤ ዠሮው እየሰማ ዐይኑ እያየ፤ ጥቃት ተፈፀመበት።
ለአስራ ሰባት ዓመታት የተካሄደው ትግልና የተከፈለው መሥዋዕት መና ሆኖ ቀረ።
3ኛ. የዛሬይቱ ኢትዮጵያ የፖለቲካ መልከዐ ምድር፤ ልክ ከስድሳ ስድቱ የካቲት ጋራ ተመሳሳይነት
አለው። ተጨባጩና ኅሊናዊ ሁኔታዎች፤ (ኦብጀክቲቭ - ሳብጀክቲቭ ሁኔታዎች) ያንኑ ዋዜማ
ያንፀባርቃሉ። ሀገሪቱ አሁንም ልክ እንደ ትላንቱ፤ በአንድ አምባገንን አገዛዝ ሥር ትማቅቃለች። ያሁኑ
ከቀደምት አምባገነኖች የሚለየው ግን፤ በምንም ዓይነት መስፈርት ቢለካ፤ ለሀገሪቷም ይሁን ለሕዝቧ
ያልቆመ ጎሰኛ ቡድን መሆኑ ነው። ይህ መሠረታዊ ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ሌሎቹ ሁኔታዎች ከሞላ- ጎደል፤ የለውጥ ግብዓቶችን አዝለው በሀገሪቱ ሰማይ ላይ ያንዥብባሉ። በምድር ላይ ያሉት ተጨባጭ
ዕውነታዎች የሚከተሉትን ያስነብባሉ ፡-
-ከአስር ሚሊዮን ያላነሰ ሕዝብ የረሃብ ሰለባ ሆኗል። የኑሮ ዋጋ ሰማይ ነክቷል። ላብዛኛው ነዋሪም፤
መሠረታዊ የሆኑ የኑሮ አቅርቦት የህልም እንጀራ ሆነውበታል። ለድሃው ሁሉም ነገር አጥሮበታል ።
መኖር ያንገፈገፈው ዜጋ በብዛት በመሰደድ ላይ ነው። ብዛታቸው በትክክል በማይታውቅ እስር ቤቶች
ውስጥ የሚማቅቀው የሀገሪቱ ዜጋ፤ በተለያዩ ማሰቃያ ቅጣቶች እየተንገበገበ ይገኛል። ወጣቱ በአደባባይ
ይረሸናል። የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ በመታወጁ፤ ፅልመተ-ሲዖል በመላው ሀገሪቱ ሰፍኗል። "ለመግደል
ተኩስ !" የሚል ዐረመኒያዊ ቋሚ ትዕዛዝ የተሰጣቸው ወታደሮች በጅምላ ዜጎችን እየገደሉ ያሉበት ሁኔታ
ውስጥ ነው ያለነው።
በትላንትናዎቹ የመሬት ከበርቴዎች ቦታ ዛሬ የሀገር ሀብት ዘራፊዎቹ ወያኔዎች ተተክተዋል። ታይቶ
በማይታወቅ ደረጃ ዛሬ ሀብታሞቹ የወያኔ አባላትና ተከታዮቻቸው ቢሊየነሮች እየተባሉ ነው። በአንፃሩ
ግን ዕልፍ አዕላፍ ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ ፤ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ረሃብተኞች እንደቅጠል ይረግፋሉ።
በዚህ ምክንያት መላው ሕዝብ፤ የወያኔን አገዛዝ ተቃውሞ ቆሟል። ተቃውሞውንም፤ ከነባቢት አልፎ
በተግባር እየገለፀ ነው። በበርካታው የሀገሪቱ ክፍሎች፣ መሣሪያ ያነገቡ አማፅያን በትጥቅ ትግል ወያኔን
እየተፋለሙ ናቸው። የዛሬ ወጣት ትውልድ እንደ ቀደምት ተራማጅና ሀገር ወዳድ ትውልድ፤ የራሱን
ታሪካዊ ግዴታ ለመወጣት መሥዋዕት በመክፈል ላይ ይገኛል። በመሆኑም የነገዋን አንድነቷን የጠበቀችና
እኩልነትን የምታስተናግድ፤ ዴሞክራሲንና ነጻነትን የተላበሰች ኢትዮጵያን ለመረከብ እንደተዘጋጀ
ያረጋግጣል። ይህም ብሩህ ተስፋን አንፀባራቂ በመሆኑ፤ ሁሉም ዜጋ ትንሣዔ-ኢትዮጵያን ለማየት
በጉጉት እየተጠባበቀ ነው ቢባል ከእውነት የራቀ አይደለም። ዘረኛው አገዛዝ፤ እንደተመኘውና፤
እንዳቀደው ሀገሪቱን ለመሰነጣጠቅ ያለው እድል ተሰናክሎበታል። የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት፤ የወያኔን
አገዛዝ ግብዐተ-መሬት እያጣደፈው መምጣቱን ያረጋግጣል።
ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት አንኳር አንኳር የሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታዎች በአንድ በኩል ሊመዘገቡ ቢችሉም፤
ተጨባጩ የዓለም አቀፍ ሁኔታ ግን ከየካቲቱ 66 ዓም ሁኔታ ጋር ሲተያይ፤ የተለየ ገፅታን ያሳያል።
የዛሬይቱ ዓለም፤ በአንድ ልዕለ-ኃያል ዕይታ ሥር መሆንዋን እንዲሁም ምዕራባያውን ሆኑ ተመጣጣኝ
ኃይል ያላቸው ሌሎች አገሮች ጥቅማቸውንና ፍላጎታቸውን ከማስቀደም ውጭ ለሌላው ሕዝብ ግድ
እንደሌላቸው ማጤን አግባብነት ይኖረዋል። ወቅቱ ለነፃነታቸው ለሚታገሉ ሕዝቦችና ሀገሮች፤ አጋርና
አማራጭ በማግኘት በኩል ያላቸውን ዕድል የሚያጠብብ ከመሆኑ በላይ ለአምባግነኖች የተራዘመ ዕድሜ
ምቹ ሁኔታን ፈርጥሎቸዋል። ይሁን እንጅ ሕዝብ በራሱ ተማምኖ ካለምንም ዕርዳታና ትብብር ድል
አድራጊ የሆነበት በዓለም ታሪክ በተደጋጋሚ የተከሰተ በመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ አለምንም ድጋፍ
በራሱ ኃይልና ጉልበት በሚያደርገው ትግልና በሚከፍለው መስዋዕት የነጻነቱ ባለቤት ሊሆን እንደሚችል
ማንም ሊጠራጠር አይችልም። ይህ ኃላፊነትና ተግባር፣ የታጋይ ድርጅቶችና የወጣቱ ትውልድ ዓይነተኛ
ተልዕኮ ነው።
አምባገነንን ታግሎ በመጣል መንግሥታዊ ሥልጣን መውሰድ አስፈላጊና ወሳኝ ቢሆንም ከሕዝባዊ አመፅ
በኋላ ሕዝብን የሥልጣን ባለቤት ለማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ግን ፤ ሕዝብን ማዕከል ያደረገና
የሁሉንም ዜጋ ተሳትፎ ያካተተ ሁኔታ መፈጠር፤ ሌላ አማራጭ የሌለው ብቸኛው መንገድ ነው።
የሽግግር ወቅት መታለፍ የሚገባው የመጀመሪያ ምዕራፍ እንጅ የግብር-ይውጣ መቆያ ሊሆን
አይችልም። ይህንን መሠረታዊ ሐቅ ታሳቢ አድርጎ መታገል ፤ ለድል ዋስትና መሆኑ አያጠራጥርም።
በሚፈጠሩት ግርግሮችና ምስቅልቅሎች ወቅት የመንግሥትን ሥልጣን በመንጠቅና፤ የሽግግርን ሂደት
በሥርዓት አካሂዶ፤ ሕዝብ በተሳተፈበት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ መንግሥት በመመስረት መካከል ያለው
ልዩነት፤ የጨለማና የብርሃን ያህል ነው።
አኩሪ ታሪክና ባህል ያለውን ሕዝብ እወክላለሁ የሚል ሁሉ፤ አርቆ ተመልካች ባኅርይ ከሌለው፤ ለሀገር
ዘላቂ ጥቅምን የሚያስመዘግብ ውጤት አያመጣም። የሀገሪቱ ፖለታካዊ ኢኮኖሚያዊ, ማኅበራዊ
ችግሮች ብቻ ሳይሆኑ የህልውናዋም ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን ጭምር ሁሉም ዜጋ አምኖበት
ተቀምጧል። የመሠረታዊ ለውጥ መምጣት ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ መሆኑንም ማንኛውም
ኢትዮጵያዊ ይስማማበታል። ለሽግግር ወቅት የሚሆን ዝግጅት ማድረግ የቅድሚያ ቅድሚያ መሆኑንም
ይገነዘባል። "ታድያ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ነውን?" ለሚለው ጥያቄ ግን አስተማማኝ መልስ
ለመስጠት አልተቻለም።
ሀገራችን ወደ አልታወቀ ሌላ አዙሪት የምትገባበት አደጋ አፍጥጦ-አግጦ መጥቷል። የውጭ ኃይላትም
ይሁኑ የሀገር ውስጥ የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎችና ሊሂቃን፣ ወያኔ እየተንገዳገደ ነው ከሚል ግምት
አንድ ነገር መደረግ አለበት ብለው በማሰብ፤ "የሠርገኛ መጣ ቃሪያ ቀንጥሱ" ዓይነት ጥድፊያና
እሽቅድድም ውስጥ መግብታቸው በገሃድ እየታየ ነው። ጣምራ ዕይታዎችና አሰላለፎች በመሸረብ ላይ
መሆናቸው ይነገራል፣ ይሰማል፣ ይታያልም። ባንድ በኩል የባዕዳንን ጥቅም አስከባሪ ቡድኖች፣ በሌላ
በኩል የሀገር ተቆርቋሪ ኃይላት በተፃራሪ ረድፍ ተሰልፈው ቆመዋል ማለት ይቻላል።
ባዕዳኑ "ኢትዮጵያን ማጣት የለብንም " በሚል ስሌት ሲቆሙ፤ ኢትዮጵያውያን ኃይይላቱ በበኩላቸው፣
ሀገራቸውን ከሌላ ዙር ጥፋት ለመታደግ መቆማቸው የሚታበል አይደለም። ይህ አሰላለፍ ደግሞ፤ ደርግ
ወድቆ፤ ወያኔን ለመተካት እንደታቀደው፤ እንደ 1983 ዓም የሎንዶን ዓይነት ስብሰባ ሊመጣ ይችላል
በሚል ስሌት ውስጥ እንደተገባ ተቆጥሯል። ሁሉም የየራሱን ተሳትፎ ለማድረግ በተዋናኝነት እየተዘጋጀ
እንደሆነ በየአቅጣጫው የሚነፍሱት ወሬዎች፤ መድረኮቹን ሁሉ እያጣበቡ ይገኛሉ።
በየቦታው እየተካሄዱ ያሉት ውጣ ውረዶች፤ የየቡድኖቹንና ጥቅሞቻቸውን በየግል ደረጃ ከማንፀባረቅ
አልፈው ተርፈው፤ መሠረታዊ፣ ሁለንተናዊ፣ ሀገራዊ፣ እስትራተጂያዊ እና ሁሉንም አሳታፊ የሆነ የሽግግር
ወቅት መሰናዶ ለማድረግ የሚያስችሉ አይደሉም። አንዱ ሌላውን ጠልፎ በመጣል ፤ አግልሎ
በማስቀረት፤ በዚህም ሂደት በሚከሰተው የፖለቲካ ትርፍ፤ የአንበሳውን ድርሻ ለመውሰድ የሚደረግ
እሽቅድድም ፤ የሕዝብና የሀገር ዘላቂ መፍትሔ አያመጣም። ይልቁንም፤ ለሌላ አለመረጋጋትና ብጥብጥ
በር-ከፋች ከመሆን አልፎ-ተርፎ፤ ሀገሪቱን ሌላ የአደጋ አዙሪት ውስጥ ይጨምራታል።
ይህ ሁኔታ ከተፈጠረ፤ ተጠቃሚ የሚሆኑት የሀገራችን ጠላቶች ብቻ ናቸው። “ሲሸበር ገዳይ ! " በሚል
መርኅ፤ "የሀገሪቱ ዕድል ወሳኞች" እኛው ብቻ ነን፤ ምንስ የረባ ተቃዋሚ አለ ?" ብለው በማመን ፤
በትዕቢት አነጋገር ተኮፍሰው እራሳቸውን የሀገሪቱ ብቸኛ መድኅን አድርገው ይቆጥራሉ። ዛሬም
እንደትላንቱ፤ ባለቤት ያጣች ሀገር በመሆኗም፤ እንደ አራጊ-ፈጣሪ ሆነው በኢትዮጵያ የወደፊት ዕድል
የመወሰን ኃይል እንዳላቸው ይገምታሉ። ይህን ቢያደርጉ ፤ አይፈረድባቸውም። ለዚህ ክስተት መፈጠር
ተጠያቂነቱ ከኛ ራስ አይወርድም። ምክንያቱም እኛ የራሳችንን የቤት ሥራ ሠርተን ሀገራችንን ማዳን
አልቻልንምና ! ታዲያ፤ በለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ፤ እንዴት ባለ ዕዳ ሊቀበለው ይችላል ?
የ1983 ዓም የነበረው ሁኔታ በአዲስ መልክ በሀገራችን የፖለቲካ መልከዐ - ምድር አዲስ ምዕራፍ
ከፍቶ፤ የኢትዮጵያ ጠላቶች ምኞታቸውን ለማሳካት ይችሉ ይሆናል። ይህንን ስጋት በቁርጠኝነት
ማስተናገድ ቢያዳግትም፤ በአንፃሩ ደግሞ በፖለቲካ ሂደትና ዕይታ "ይህ ወይም ያ ሁኔታ ፈፅሞ ሊሆን
አይችልም ወይም ይችላል" ብሎ በእርግጠኝነት መደምደም፤ አዘናጊ ሊሆን ይችላል። የፖለቲካ ዕውነታ፣
በመሬት ላይ የሚታየውን መረዳት መቻል እስከሆነ ድረስ፤ በሀገራችን ያለውን/ያሚያንዥብበውን
ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መስተጋብሮችን ያገናዘበ መፍትሔ መፈለግ የወቅቱ አንገብጋቢና
አጣዳፊ ተግባር ሊሆን ግድ ይላል።
በእርግጥ የወቅቱ አጣዳፊ ብሔራዊ አጀንዳ፤ የሽግግር ወቅት መስናዶ እንደሆነ ማንም ሊከራከር
አይችልም። ከወያኔና ከአጫፋሪዎቹ በስተቀር ! ይኸንን ሐቅ በመገንዘብ ይመስላል ፤ ዛሬ ሁሉም
በየፊናው - የስደት መንግሥት ፣ የአደራ መንግሥት ፣ ጊዚያዊ መንግሥት ፣ የዓለም አቀፍ ሽግግር
መንግሥት ፣ የአስራ አንደኛው ሰዓት መንግሥት ፣ ዘውጋዊ የሽግግር መንግሥት ፣ የቅብብል መንግሥት፣
...ወዘተ እያለ ሁሉም ይሽቀዳደማል። የሀገራችን ሕዝብ፣ የአሳላፊዎች ጋጋታ ድግሱን ያሳምረዋል ብሎ
አያምንም።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢ አንድ የሚነገር ቀልድ እንዳለ ይደመጣል፤ ይኸውም አስራ አንድ
ዲፕሎማዎች አንድ ድግሪ አይመዝኑም/ አይሆኑም" ነው። ኢትዮጵያን የቸገራት አሁን ከወደቀችበት
የሚያድኗት ድርጅቶች ቁጥር ማነስ፤ የመንግሥታቱ ድግስ ጉድለት፤ የአሳላፊዎች ሽር-ጉድ እጥረት፤
የውጭ ባዕዳን መንጎራደድ አለመከሰት፤ ...ወዘተ አይመስልም። ችግሩ የልጆቿ አለመተባበር እንደሆነ
ተደጋግሞ የሚነገር ሆኗል። ይኽ ተግዳሮት ካልተወገደና ለትብብሩ ቅድሚያ ካልተሰጠው ሌላውን
ዝርዝር ማዥጎድጎዱ ፤ አንድ ምዕራፍ መንገድ አያስኬድም። ተቀዳሚው ጉዳይ ታጋይ ኃይሉ ክንዱን
አስተባብሮ ሥር ሰዶና ተጠናክሮ ያለውን ኃይል ከሥልጣን ማስወገድ ሲሆን ይህን ተግባር ማከናውን
ከተቻለ ተገቢ ትክክለኛና ሕዝባዊ የሆነውን የሽግግር ወቅት እውን ማድረግ ብዙ የሚከብድ አይሆንም።
በሁሉም ዘንድ ቅን ፍላጎትና እምነት ካለ በውይይትና በድርድር በሚደረግ ስምምነት የሽግግር ጉባዔ
ማድረግም ሆነ የሽግግር ሰነድ ማዘጋጀት ይቻላል። በኢሕአፓ በኩል ይህ እንዲሳካ ከልብ የሚጥር
መሆኑን በተደጋጋሚ ገልጿል። ሥልጣን በሕዝብ አመንጭነት፣ ባለበትነት ዕውን ወደሚሆንበት ሥርዓት
ለመሸጋገር የሚከተሉት ፍሬ ነገሮች መሠረታዊ ናቸው ብለን እናምናለን ።
1ኛ. በዝግጅቱ ያገባኛል የሚለው ሁሉ ከመጀመሪያው አንስቶ ተሳታፊ ሊሆን ይገባል።
2ኛ. የኢትዮጵያ ሀገራዊ ሉዓላዊነት፤ የዜጎቿ አንድነትና ነፃነት እንዲሁም የሕዝቧ እኩልነት፤ ለድርድር
መቅረብ አይኖርበትም።
3ኛ. ዴሞክራሲያዊ ሥርዓተ- መንግሥት መተኪያ ሊኖረው አይገባም።
ከላይ ከአንድ እስከ ሦስት በተጠቀሱት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ከሚስማሙ ጋር ኢሕአፓ አብሮ
ለመሥራትና ለመተባበር ምን ጊዜም ዝግጁ መሆኑን እየገለጸ በአሁኑ ወቅት የዘረኛና የአምባገነን ሥርዓትን
ከሥሩ ለመገርሰስ በኅብረት ትግላችንን እናፋፍም በማለት ጥሪውን ያስተላልፋል።
ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያቸንፋል !
No comments:
Post a Comment