ዘመነ አስተምህሮ
በቤተ
ክርስተያናችን የዘመን አቆጣጠር /አከፋፈል/ መሠረት ከኀዳር 6 ጀምሮ እስከ ታኀሣሥ 13 ድረስ ያለው ወቅት ዘመነ አስተምህሮ
ይባላል፡፡
መሀረ ማለት ይቅር አለ ማለት ሲሆን፤ ዘመነ አስተምህሮ ማለት ይቅርታ የመጠየቅ /የምልጃ/ ዘመን ማለት ነው፡፡ ዘመኑ ቤተ
ክርስቲያን ስለ ልጆቿ ይቅርታ የምትጠይቅበት፤ ምዕመናንንም ስለ በደላቸው ይቅርታ የሚጠይቁበት፤ ስለዚህም በስፋት ትምህርት
የሚሰጥበት ዘመን ነው፡፡
በዚህ
ዘመን ያሉት አምስት እሑዶችና በእነዚህ እሑዶች የሚጀምሩት ሳምንታት አስተምህሮ፣ ቅድስት፣ ምኩራብ፣ መጻጉዕ፣ እና ደብረ ዘይት
በመባል ይጠራሉ በየሳምንቱ ቤተ ክርስቲያን የምታቀርበውን ትምህርት በየጊዜው እናከብራለን የመጀመሪያውን ሳምንት /የአስተምህሮ/
ትምህርት እነሆ: -
እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፤ በደላችንን ይቅር በለን /ማቴ.6-12/
ይህ ቃል የተወሰደው ጌታችን በደቀ መዛሙርቱ በኩል እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ለሚኖሩ /ዛሬም ላለን/ ክርስቲያኖች እንዲህ
ብላችሁ ጸልዩ ብሎ ካስተማረው ፀሎት ነው፤
በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ ስምህ ይቀደስ መንግሥትህ ትምጣ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን፤ የዕለት
እንጀራችንን ዛሬ ስጠን፤ እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን፤ ከክፉም አድነን እንጂ ወደ ፈተና
አታግባን፤ መንግሥት ያንተ ናትና ኃይልም ክብርም ለዘለዓለም አሜን/ ማቴ.6. 9-14/
ይህ ጸሎት በጥንታውያን የቤተ ክርስቲያን አባቶች እና ሊቀውንት «የጌታ ጸሎት» ተብሎ ይጠራል፡፡ በእኛ ቤተ ክርስቲያን
የጸሎቱን የመጀመሪያ ሐረግ በመያዝ «አባታችን ሆይ» ወይም በግእዝ «አቡነ ዘበሰማያት» እንለዋለን፡፡
ይህ ጸሎት ጌታችን ራሱ ያስተማረው በመሆኑ በቤተ ክርስቲያን ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ የሌሎች ጸሎታት ሁሉ ማሰሪያ /ማሳረጊያ/
ሆኖም ያገለግላል፡፡ በውስጡም «አባታችን ሆይ» ከምትለው ከመጀመሪያዋ ሀረግ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ እጅግ ጥልቅ የሆኑና
ነፍስን የሚያጠግቡ ወደ ሰማይ ከፍ የሚያደርጉ መንፈሳዊና ነገረ መለኮታዊ መልእክቶችን ያዘለ ነው፡፡
ይህ የዘመነ አስተምህሮ የመጀመሪያው ሳምንት ስለ ይቅርታ የሚሰበክበት ነውና በጸሎቱ ውስጥ ስለዚህ የሚናገረውን አንቀጽ መሠረት
አድርገን እንማራለን፤
«እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን» ከዚህ ቃል በርካታ ነገሮችን እንማራለን፤
1. እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን እንደሚወድ
አምላካችን ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ባይወድ ኖሮ ይቅርታን እንድንጠይቅ አይነግረንም ነበር፡፡ አዎ እኛ ከተመለስን ምንም ያህል
በደለኛ ብንሆን ይቅር ሊለን፤ ምንም ያህል ብንቆሽሸ ሊያድነን ዝግጁ ነው፡፡ እንዲህ እያለ ይጠራናል፤ «እናንተ ሸክማችሁ የከበዳችሁ፤
ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ»፡፡ ስለዚህ በዚሀ ጸሎትም ላይ «በደላችንን ይቅር በለን» ብለን እንድንጠይቀው አስተማረን፤
ይቅር ይለን ዘንድ፡፡
2. ይቅር ለመባል ምን ማድረግ እንዳለብን፤
ይቅር ሊለን ስለ ወደደም ይቅርታን ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለብን በዚሁ ቃል ነግሮናል፤ ማድረግ ያለብን ምንድን ነው?
-
ኀጢአታችንን ማወቅ፣ ማመን፣ ማስታወስ
-
የበደሉንን ይቅር ማለት
-
ይቅርታን መለመን
ኅጢአታችንን ማወቅ /ማመን/
ጌታ «በደላችንን ይቅር በለን» ብለን እንድንጸልይ ሲነግረን በመጀመሪያ ደረጃ በደለኛ እንደሆንን እያስታወስን /እንድናስታውስ
እያደረገን/ ነው፡፡
ሁልጊዜም በማሰብ፣ በመናገርና በማድረግ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የሆነውን ልባችንን /ኅሊናችንን/ እና ሰውነታችንን
እናቆሽሻለን፤ መድኃኔዓለም ክርስቶስ የሞተለትን ማንነታችንን እናጎድፋለን፡፡ ይህም የሰው ልጆች በቅድስና እርሱን መስለን
እንድንኖር በኋላም የተዘጋጀልንን የዘለዓለም መንግሥት እንድወርስ ብቻ ፈቃዱ የሆነውን እግዚአብሔርን ያሳዝናል፤ በአርአያውና
በአምሳሉ ለክብር የፈጠረው ሰውነታችን መጉደፍ ያስቆጣዋል፤ ንጹሐ ባሕርይ የሆነ እርሱ ኀጢአት አይስማማውምና፡፡
እንግዲህ ይቅር ለመባል በመጀመሪያ እንዲህ ኀጢአት እየሠራን መሆኑን ማወቅና ማመን ያስፈልገናል፡፡ ወደዚህ ዕውቀት ለመድረስም
የቅዱሳት መጻሕፍትን ቃል መማር የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም ስህተት የሚታወቀው ያለውን ሁኔታ /ድርጊታችንን
ንግግራችንን፣ ሀሳባችንን.. / መሆን ከነበረበት /ከትክክለኛው/ ጋር በማነጻጸር በሚዛን ላይ በማስቀመጥ ነው፡፡ የማነጻጻሪያ
ሚዛኖቻችን ደግሞ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉ ሕግጋትና ትዕዛዛት ናቸው፡፡ እነዚህን ስናውቅ ጉድለቶቻችን፣ ድካሞቻችን ፍንተው
ብሎ ይታዩናል፡፡ አሊያ ግን እየበደለን ያልበደልን ሊመስለን ይችላል፡፡
የበደሉንን ይቅር ማለት