-ፓርቲዎች በድርጅታዊ ፕሮግራሞቻቸው ውስጥ እንዲያካትቱት ጠይቋል ሰማያዊ ፓርቲ በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ በርካታ ምሁራን ተወያይተውበት ብዙ ጥናትና ምርምር አድርገውበታል ያለውንና ‹‹የዜጎች የቃል ኪዳን ሰነድ ለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ›› በሚል መጠሪያ ያዘጋጀውን ሐምሌ 18 ቀን 2006 ዓ.ም. ይፋ አደረገ፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ ይፋ ያደረገው የዜጎች የቃል ኪዳን ሰነድ ዜጎች በጋራ አንድ ሆነው ሊስማሙባቸው የሚችሉ፣ አጠቃላይ በአገራቸው ሁኔታ ላይ የሚግባቡባቸው ጉዳዮችን የያዘ የጋራ ሰነድ መሆኑን አስረድቷል፡፡ ከፕሮግራም፣ ከፖለቲካ ሐሳብ፣ ከአስተሳሰብና ለወቅታዊ ችግሮች መፍትሔ ከመስጠት ልዩነት ባሻገር፣ ኢትዮጵያዊያን እንደ አገር የሚግባቡበት አንድ የጋራ ሰነድ አስፈላጊ መሆኑን ፓርቲው ገልጿል፡፡ ይህም ሰነድ ፓርቲው ብቃት ባላቸው ምሁራን ተጠንቶና ውይይት ተደርጎበት፣ ሕዝብ ውይይት አድርጎበት አንድ የሚሆንበትና ‹ሕገ መሠረት› (የሕገ መንግሥት ማርቀቂያ መነሻ መሠረት) ሲል የጠራው ሰነድ መሆኑን የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር) ገልጸዋል፡፡