ዘረኛው የወያኔ ቡድን የሥልጣን ርካቡን በጠመንጃ ኃይል ከተቆናጠጠበት ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ስለደረሰው ግፍ፤ሥቃይና መከራ እንዲሁም አገሪቱን በቋንቋና በጐሣ ሸንሽኖ ህልውናዋን እየተፈታተነ ለመሆኑ በልዩ ልዩ አጋጣሚዎች በተደጋጋሚ ተገልጿል።
የዚህን ጠባብ ብሄረተኛ ቡድን እኩይ ተግባር በቡድንም ሆነ በተናጠል በብዕራቸው የተዋጉ፤በድርጅት ዙሪያም ተሰባስበው ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ትግል ያካሄዱ ኢትዮጵያውያን በነቂስ እየተለቀሙ ለእሥር ተዳርገዋል።ከፊሉንም ቤት ይቁጠረውና የደረሱበት ሳይታወቅ እንደወጡ ቀርተዋል።
ሰሞኑንም ይህ መንግሥት ነኝ ባይ ጠባብ ብሄረተኛ ቡድን ከየመን መንግሥት ጋር በመመሳጠር ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብትን ድንጋጌ ጥሶ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የግንቦት ሰባት የፍትህ፤የነጻነትና የዴሞክራሲያው ንቅናቄ መስራች አባልና የንቅናቄውን ዋና ጸሐፊ በማገት ጠልፎ እንደ አንድ ነጻ ዜጋ በየትኛውም አገር የመዘዋወር መብታቸውን ረግጦ በማፈን ወደ ኢትዮጵያ ውስዶ እያሰቃያቸው ይገኛል።
መብቴ ተረገጠ፤ ነፃነቴ ተደፈረ፤በሀገሬ ጉዳይ የመናገር፤የመጻፍና የመደራጀት ዜግነታዊ ሕልውናየ ተጣሰ…ወዘተ ብሎ የሚያምን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከምን ጊዜውም በላይ ይህ የሰሞኑ በወንድማችን ላይ የተፈፀመው ድርጊት አስቸኳይ መልስ የሚጠይቅ ፈተና ከፊቱ ተደቅኖ ይገኛ
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መባቻ ላይ የሂትለርን አገዛዝ አጥብቆ የሚያወግዝ ማርቲን ኒሞለር የተባለ ጀርመናዊ የፕሮቴስታንት ቄስ በወቅቱ ሰፍኖ የነበረውንና ናዚስቶች ደረጃ በደረጃ ይፈጽሙ የነበረውን ግፍና መከራ አስመልክቶ የተናገረውን ያስታውሷል፦ይኸውም
“የናዚ አገዛዝ በመጀመሪያ በሶሻሊስቶች ላይ ሲዘምት ምንም አልተናገርኩ ምክንያቱም እኔ ሶሻሊስት ስለአልነበርኩ ።ቀጥለውም በትሬድ ዩኒየን ላይ የግፍ በትራቸውን ሲሰነዝሩ አልተናገርኩም።ምክንያቱም እኔ ትሬድ ዩኒየኒስት አልነበርኩምና። ከዚያም በኋላ በይሁዶች ሲነሱ ዝም አልኩ ምክንያቱም እኔ ይሁዲ አልነበርኩምና።በመጨረሻም ወደ እኔ መጡ ሆኖም ግን ስለ እኔ የሚናገር የቀረ ማንም አልነበረም።”
አሁንም ይህ በአንድ ታጋይ ኢትዮጵያዊ ላይ የተፈጸመውን ዘግናኝ ድርጊት መግለጫ በማውጣት ፤ሰልፍ በመሰለፍ ብቻ ልንወጣው አይቻለንም።በመሆኑም እኛ በኮሎምቦስ ኦሀዮ የምንገኝ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ የደረሰው በደል በዝምታና በለሆሳስ ልናስተናግደው በጭራሽ አይቻለንም።ይህ ዓይነት መረን የለቀቀ ግፍ ተራ በተራ በእያንዳንዱ የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎችና የዴሞክራሲ ጠበቃዎች ላይ ከመድረሱ በፊት በድርጅት መጠናከርንና በመረጃ ልውውጥ ውጤታማ ሆኖ መገኘት አስፈላጊ እንደሆነ የወቅቱ አጠቃላይ ሁኔታ ስለሚያሳይ ለእውነተኛ የኢትዮጵያ ልጆች የሚከተለውን ጥሪ አቅርበናል።
vየየመን መንግሥት በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ የፈጸመችው አሳልፎ የመስጠት ክህደትን ማጋለጥ። የእንግሊዝ መንግሥት የዜጋዋን መብት ለመታደግ በመጀመሪያው ረድፍ መገኘት ስላለባት የሚፈለገውን ሁሉ ስልት በመጠቀም ለጉዳዩ ትኩረት እንድትሰጥበትጫና ማድረግ።
በውጭ አገር የሚገኘው ኢትዮጵያዊ በያለበትና በሚገኝበት ሥፍራ የተገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅሞ ለተወካዮች ምክር ቤትና ለሴነተሮች ለማሳወቅ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ።አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የእንግሊዝ ዜጋ መሆናቸው እየታወቀ የየመን መንግሥት ዓለም አቀፉን የሰብዓዊ መብት ሕግጋትን ፤ የኮመን ዌልዝ ኔሽንን ፓክት ጥሶ ለዘረኛው መንግሥት አስልፎ የሰጠበትን ምክንያት አጥጋቢ ምላሽ ከሁለቱም መንግሥታት እንዲሰጥ አበክረን እንጠይቃለን።
የወያኔ የዜና አውታሮች የሚያሰራጩትን ነጭ ወሬ የሚያስተጋቡ ግለሰቦች እንዳሉ ይታወቃል። እነዚህ ግለሰቦች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚያሰራጩት ወሬ እርባና ቢስ ቢሆንም የአንድነት ኃይሉን የሚጎዳ በመሆኑ ከዚህ ጸረ-ሕዝብ ተግባራቸው መቆጠብ ይኖርባቸዋል። በሌላም በኩል በየአካባቢያችን የሚገኙ የዘረኛው መንግሥት ሰላዮች፤ደጋፊዎችም ሆነ ተባባሪዎች የቆሙበት ዓላማ ርካሽ ሀገርንና ወገንን የሚጎዳ በመሆኑ በመረጃ ላይ የተደገፈ ተግባራቸውን በማረጋገጥ ከማህበራዊ ግንኙነት ማግለል በእነርሱ በኩል የሚከናወኑ ማናቸውንም ነገሮች ቦይ ኮት ማድረግ።
የአንድነት ኃይሎ ተበታትኖ መገኘቱ ለጥቃት በር እንደከፈተ ይታመናል በመሆኑም ሁኔታው ትግላችንንም እየጎዳው የጠባብ ብሄረተኛውን የወያኔን እድሜም እያራዘመው በመገኘቱ የአንድነት ኃይል ነን ብለው የሚያምኑ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ ንቅናቄዎች በአስቸኳይ በመገናኘት የኢትዮጵያ አንድነት የተቃዋሚ ኃይልን መመስረት ይገባቸዋል።የዚህ የኢትዮጵያ አንድነት ኃይል መመሥረት ለመንግሥታትም እንደ አማራጭ ኃይል ሆኖ ስለሚቀርብ ይህንኑ ዓላማ ገቢራዊ ለማድረግ የየድርጅቶችም ሆነ የየስብስቦቹ መሪዎች ከዚህ በፊት በባዶ ጉዳይ የሚያናቁራቸውን ሁሉንም ነገር ከበስተጀርባቸው በመተው ለአዲስ ትንሳኤና የድል ጉዞ እንዲነሱ ታፍራና ተከብራ በኖረችውና በእኛ ዘመን ለውርደት በተዳረገችው ታላቋ ሀገራችን በኢትዮጵያ ስም እንጠይቃለን።
በወንድማችን ላይ የተፈፀመውን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት በጥሞና ተመልክተን መደረግ ስለሚገባው ልዩ ልዩ የትግል እንቅስቃሴ ስልቶችን የሚነድፍ፤ የሚያጠናና በተግባር የሚተረጉምና የሚመራ ውጤታቸውንም የሚገመግም፤ ራሱን የቻለ በስደት ላይ የሚገኘውን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚያሳትፍ አንድ ለስደተኛው የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ማዕከል መፍጠር እንደሚገባው እናምናለን።የዚህ ማዕከል መፈጠር በተለያየ መልክ ጸረ-ሕዝብ የሆነው ህወሃት በተቃዋሚ ኃይሎች ላይ የሚያደርሰውን በደል፤ ሰቆቃና መከራ በባለቤትነት ወስዶ መምራት ይሆናል።ይህንን ሀሳብ ግምት ውስጥ በማስገባት ዳብሮ አንድ ውጤት ላይ እንዲደርስ አበክረን እንጠይቃለን።
ኢትዮጵያ ለዘላዓለም ትኑር!!
በአሸባሪውና ጠባብ ብሄርተኛው ወያኔ ከርሰ መቃብር ላይ ህዝባዊት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ትግትነባለች!!!
No comments:
Post a Comment