BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

Friday, 4 July 2014

ትግል እምብይታ እንጅ አቤቱታ አይደለም


የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብታዊፓርቲወጣትክንፍድርጅተ(ኢሕአፓ ወክንድ) 
መጋቢት 2006 ዓ.ም
ምንም እንኳን ወያኔን እንቃወማለን የሚሉ ድርጅቶች ሁሉ ተቃዋሚ ሃይሎች በመባል በአንድ ጎራ ተጠቃለው ይታወቁ እንጅ
በውስጣቸው የተሰሉፉት ሃይሎች አንድ አይነት የትግል ስልትም ሆነ ብሄራዊ ራዕይ ያላቸው እንድልሆኑ ግልፅ ነው። ከነዚህ ውስጥ
አንዳንዶቹ በጥገና ለውጥ ስርዓቱ እንዲሻሻል ማስገደድ ይቻላል የሚሉ፣ ሌሎች ደግሞ ስርዓቱ መቀየር አለበት የሚሉ፣ ነገር ግን
የሃገሪቱን ሉአላዊነት ግምት ውስጥ የማያስገቡና የባዕዳንን የቆየ ተፅዕኖ በአዲስ ቀለም ለማስቀጠል የሚፈልጉና ዴሞክራሲን
ከይስሙላ ምርጫ ጋር ቀላቅለው የሚያዩ፤ ጥቂቶች ደግሞ መገንጠልን በግልፅ እሚያራምዱ ወይም ይህንኑ ዓላማ በአዲስ ቋንቋ
አለዝበው ሁኔታው እስኪመቻች የሚጠብቁና ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች ነን ቢሉም እነዚህኑ ክፍሎች የሚያግዙና የሚያበረታቱትንም
ያጠቃልላል። ከነዚህ ሁሉ ተለይተው የቆሙት ሃይሎች ደግሞ፣ ያለው አገዛዝ ከስረ መሰረቱ መነቀል ያለበት ብሄራዊ ጠላት በመሆኑ
የሚያምኑና፤ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚገነባው፣ ህዝብ የስልጣን ባለቤት መሆኑ የሚረጋገጠው፣ እንዲሁም የሀገሪቱ አንድነትና
ሉአላዊነነት የሚጠበቀው ስር-ነቀል በሆነ ለውጥ ብቻ ነው በሚል የሚገፉትን በሌላ በኩል የያዘ ሰፊ ጎራ ነው።

በትግል ታክቲክ ደረጃም እነዲሁ ከሰላማዊ መንገድ ውጪ ያሉ ሌሎች የትግል አማራጮችን ውድቅ የሚያደርጉ ሃይሎች በአንድ
በኩል፣ ትግሉ የሚቻለውን አማራጭ ሁሉ ከመጠቀም መገደብ የለበትም ስለዚህ ሁለገብ የሆነ የትግል ስልት መያዙ ያዋጣናል
የሚሉ በሌላ በኩል ይገኙበታል። በመጀመሪያው ስልት ላይ የሚነሳው ጥያቄ ግን ለምን ይህን አካሄድ መረጣችሁ ሳይሆን፣
በያዛችሁት መንገድ ቆርጦ ለመታገል ዝግጁ ናችሁ ወይ? የሚል ነው። ሰላማዊ ትግልስ ከመቸ ወዲህ ነው መጀመሪያውና
መጨረሻው በአምባገነኖች ፈቃድ የሚወሰነው? የሚለውንም ጉዳይ መጠየቅ ያሻል። ለሰላማዊ ትግል፡ ስብሰባዎችን፣ ተቃውሞ
ሰልፍን፣ ስራ ማቆምን፣ የኢኮኖሚ እቀባን፣ የሙት ከተማን፣ ወዘተ የመሳሰሉትን ሁሉ መጠቀም ግድ የሚል ከሆና በፈቃድ ውጣ
ውረድ ከታሰረ፣ ቃሉ ራሱ አዲስ ትርጉም ሊያስፈልገው ነው።
ዲሞክራሲያዊ መብቶቹን በመጠቀም በመረጠው አስተዳደርና ባፀደቀው ህገ ደንብ በሚተዳደር አገር ያለውን አቀራረብ ወያኔ
ከሚፈነጭባት ኢትዮጵያ ጋር ማምታት ወደድንም ጠላንም ለገዥው ቡድን አጋዥ አሰላለፍ እነጅ ሌላ ሊሆን አይችልም። ለትግል
ስልታችን ወሳኝ ከሆኑት ጉዳዮች ውስጥ አይነተኛና ዋነኛ የሚሆነው የአገዛዙን አጠቃላይ ባህሪ በትክክል መረዳት ነው። ወያኔ
አገሪቱን እንደ ወራሪ ሃይል በሚያደባይበት፣ ህልውናዋን በጥያቄ ውስጥ ባስገባበትና ሰላማዊ መፍትሄ በሚሹ ላይ እያፌዘ ያለ
የዘረኞች መንጋ ፈቃድ መለመንንና እንዲለወጥ እናስገድደዋለን የሚለውን ምን አገናኘው። ይልቅስ ይህ አገዛዝ ህዝባዊ አመፅን
የማይቀር ክስተት እያደረገው እንደመጣ በመረዳት “ህጋዊ ተቃዋሚ” የሚለውን አሰላለፍ በተጨባጭ መመርመር ወቅቱ ግድ እያለ
እንደመጣ መገንዘቡ ተገቢ ነው። ስለሆነም የትግል አቅጣጫን በተገቢ ማጤን፣ ያሉትን እውነታዎች መረዳትና ደፍሮ መቆም ለአንድ
ተቃዋሚ ድርጅት የፖለቲካ ህልውና ወሳኝ ሁኔታ ነው።
አገር ለማጥፋት የመጣን ጠላት በፈቀደልን መንገድ ብቻ ነው የምንቃወመው የሚለው አባዜ ቆመንለታል በምንለው ህዝብ ፊት
አመኔታ ያሚያሳጣና አዝጋሚ የተባለው ጉዞ በተግባር ሲፈተሽ አዘናጊ ሚናው እየተከሰተ ነው። ይህ ወንጀለኛ ስርዓት በፈቀደው
መንገድ ብቻ ለመጓዝ የመረጡ ድርጅቶች ቁጥር መራባት ሌላው አስቸጋሪ የተቃዋሚው ገፅታ ሆኗል። ያሉትን ደርጅቶች አጠናክሮ
ከማስኬድ ይልቅ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ ሌላ ስም ይዞ ብቅ ማለት ልምድ እየሆነ መጥቷል። ድርጅቶች መብዛታቸው በራሱ ችግር
ሆኖ ባይታይም የሚፈጠሩት ድርጅቶች ከነበሩት ጋር አብረው እንዳይሰሩ ያደረጋቸው ግልፅ የመርህም ሆነ የስልት ልዩነት
አለመታየቱ ነው። እነዚህ በተመሳሳይ አወዛጋቢ ግለሰቦች እንደ በራሪ ወረቀት የሚባዙ ስብስቦች የፖለቲካ ሀ ሁ ለሀገርና ለወገን
ፍትህ የተዋደቀውን ትውልድ ታሪክ በማጥቆር መሆኑ ደግሞ የህብረትን ጥያቄ የበለጠ እያወሳሰበው እንጅ እያቀለለው አልሄደም።
በእርግጥ በስርዓቱ ተመዝግበን ህጋዊ ሆነን ስለምንሰራ ከፈቃድ ውጭ መንቀሳቀስ አንችልም የሚል መከራከሪያ እንዳለ ቢታወቅም፤
የህግ የበላይነት በሌለበት አገር እንዴት “ህጋዊ” ሆኖ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል በራሱ አወዛጋቢ እንደሆነ ቀጥሏል። ለዚህም
ነው ተቃዋሚው ክፍል እስካሁን የተጓዘበትን መንግድ መለስ ብሎ መርምሮ ሁኔታው ግድ ከሚለው የትግል ዘዴ ጋር ራሱን ማዛመድ

 መቻል አለበት የሚባለው። ወያኔ በፈቀደው መንገድ እሰከተቆመለት ድረስ ምንም ነገር እንዲቀይር አይገደድም። አንድ ድርጅት፣
ድርጅታዊ ይዞታውን፣ ፖሊሲዎቹንና የትግል ስልቱን በየጊዜው እየመረመረ ካልተጓዘና ለዓላማው ስኬት አስፈላጊውን መስዋዕት
መክፍል ካልደፈረ የፖለቲካ ህልውናው ይጠፋል በመጨረሻም ጭራሽ የስርአቱ መናጆ ሆኖ ይቀራል።
ሰላማዊ ትግል ትክክለኛ ትርጉሙ ከመሳሪያ አመፅ በመለስ ያሉትን ማንኛውንም የትግል አማራጮች መጠቀም ማለት ነው።
የአገዛዙን ስስ ብልቶች እየፈለጉ ማዳከምና በዚህ ጉዞም ትግሉ የሚጠይቀውን ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ቆርጦ መነሳት
ማለት ነው። የተቃውሞ ሰልፎችን ለማካሄድ የአምባገነኑን ስርአት ይሁንታ መጠየቅ የት ቦታ እና መቸ እነደምንቃወመው አውቆ
እንዲዘጋጅ ቀጠሮ እንስጠው ከሚል አስቂኝ ትርኢትነት ሌላ ውጤት አልታየበትም። ተቃዋሚ ድርጅት ነን እየተባለ በወያኔው
የምርጫ ድራማ ያለመሳተፍ መብት እንኳ መቆም ያዳገተበት ጉዞ በእውነት ሊመረመር ይገባል። እንዲህ ከሆነ ደግሞ ሰላማዊ ትግል
ሳይሆን ከንቱ አቤቱታ ከመሆን አያልፍም። አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ ሌላ ተቃዋሚው የሚገኝበት ጎራ ሌላ ሆነና፣ “በቅሎ አባትህ
ማን ነው ቢሉት ፈረስ አጎቴ ነው አለ” እነደተባለው እየሆነ ነው። አገራችን የምትፈልገው ከገባችበት ዘርፈ ብዙ ችግር ሊታደጓት
ቆርጠው የተነሱ ዜጎቿን እንጅ ለአሮጌው ስርዓት አዲስ አጃቢ መሆን የሚፈልጉትን አይደለም።
የደቡብ አፍሪካንና ህንድን ተመክሮ ብንመለከት ትግላቸው የቅኝ ገዥዋን የእንግሊዝን ወይም የዘረኛው አፓርታይድን ፈቃድ
በማግኘት ላይ የተመሠረተ አልነበረም። “ሰላማዊ” የሚል ቃል ስላለበት ብቻ ወደ ልመና/ተማፅኖ ደረጃ ዝቅ አላደረጉትም። የደቡብ
አፍሪካ ታጋዮች ሰላማዊ ትግል አልሰራልንም ብለው ዘረኛውን ስርዓት ወደ መማፀን አልሄዱም፤ እንዲያውም “የኛም ጣቶት እኮ
ቃታ መሳብ ይችላሉ” በማለት ትግሉ ወደሚጠይቀው ደረጃ አሸጋገሩት እንጅ። በቅርቡ አምባገነን አጋዛዞችን መተንፈሻ አሳጥቶ
ከስልጣን ያባረረው የቱኒዚያና ግብፅ እንቅስቃሴ ሰላማዊ ነበር።
ብዙም ሳንሄድ በሀገራችን እየተካሄደ ካለው የዕስልምና ሃይማኖት ተከታይ ወገኖቻችን እንቅስቃሴ እንኳን ብዙ መማር የሚቻልበት
ገንቢ ተመክሮና አጋር የሆነውን እንቀስቃሴ መጥቀስ ያቻላል። እነዲሁም በሀገራችን የቅርብ ታሪክ ዝነኛው የኤትዮጵያ ተማሪዎች
እንቅስቃሴ በ1959 ዓ.ም የዓፄው መንግሠት ሰላማዊ ሰልፍን የሚያግድ ህግ ባወጀበት ጊዜ ህጉን ራሱን በመቃውሞ ሰለፍ ወጣ አንጅ
ፈቃድ እስኪሰጠው አልጠበቀም። በዚህ መንፈስ የተነሳሳው እንቅስቃሴ ነበር እነደመለኮት ይታይ የነበረውን የዘውድ አጋዛዝ ገዝግዞ
የጣለው። በዃላም ወታደራዊ ጁንታውን ለእብደት የዳረገው- እስከ 1968 ዓ.ም ድረስ የተካሄደው ሰላማዊ ትግል ነበር። ነገር ግን
ሁሉንም የሰላማዊ ትግል ስልቶች የተጠቀመና እምብይ! ለአምባገነን መንግስት አንገዣም ያለ ቆራጥ ትግል እንጅ የዘውዱንም ሆነ
የደርግን ፈቃድ በመጠየቅ የተካሄደ አልነበረም። መሠረታዊና ስር ነቀል ጥያቄዎችን አንግቦ ያልተቋረጡ ሰላማዊ ሰልፎች፣ በስራ ላይ
ከመለገም አስከ ስራ ማቆም አድማዎች፣ ከተማዎችን በበራሪ ወረቀቶችና አርማዎች ማጥለቅለቅ፣ የፀጥታውን ክፍል እመቃ የሚበትኑ
ኡኡታዎችን መልቀቅ፣ በተወሰኑ የገዥው ፓርቲ ሸቀጦቹ ላይ እቀባ ማድረግ እና ማንኛውንም ሰላማዊ የትግል መንገዶችን ሁሉ
በመጠቀም ነበር። ሰላማዊ ትግል እምብይ አንገዛም እንጅ ህገ ወጡ ስርዓት ሲፈቅድ የምናስኬደው ሲከለክል የምንጥለው ማለት ግን
ፍፁም ሊሆን አይችልም።
ዋናው ነጥብ ድርጅቶች ራሳቸውን በመገምገም ስህተታቸውንና ድክመታቸውን መርምረው መፍትሄ መፈለግ እንዳለበቸው
ለመጠቆም ነው። እናት ድርጅታችን አሕአፓ በ1971 ዓ.ም ባካሄደው የዓመራር (ፖሊት ቢሮንም ይጨምራል) ጉባዔ ቀጥሎም
በ1976 ዓ.ም በተካሄደው 2ኘው የጠቀላላው ዓባለት ጉባዔ (ኮንግረስ) ራሱን በጥልቅ ገምግሞ ድክመቶቹንና ስህተቶቹን ይፋ
በማድረግ ራሱን ወቅሷል። አያይዞም በመርህ ደረጃ መሪ ፓርቲ ነኝ የሚለውን ሠርዞ ሁሉንም ተቃዋሚ ሃይል የሚያሳትፍ የመደብለ
ፓርቲ መተክል ማፅደቁንና ለኤርትራ ችግር የፌዴሬሽን መፍትሄ ማቅረቡን ከሌሎች ብዙ ጉዳዮች ሁለቱን ለአብነት መጥቀስ
ይቻላል። ይሀ ራስን ትሁት አድርጎ ከስህተቶች መማርና መታረም ነው ለተቃዋሚው ጎራ ባዕድ እንደሆነ የቀጠለው።
ስለሆነም የኢወክንድ መሠረታዊ መልዕክት ተቃዋሚ ነን የሚሉ ድርጅቶች አካሄዳቸው የዜጎችን አመኔታ ወደሚያስገኝ፣ የትግል
ወኔን ወደሚያነሳሳና ለመሠረታዊ ለውጥ አቅጣጫ ሰጭ እንዲሆን በወንጀለኛው ወያኔ በጎ ፍቃድ ላይ ከመንጠላጠል ይልቅ በራስ
ተነሳስቶ ሰላማዊ ትግሉን ማጧጧፍ ፍሬ ያስገኛል በሚል ምክር መለገስ እንወዳለን። አለዚያ ምንም አይነት ህግ የማይገዛውን ዘረኛ
ስርዓት በህግ እንደሚዳኝ የሃሰት ሺፋን መስጠት መሆኑንም መረዳት ያስፈልጋል።

 ለሃያ ሶስት ዓመታት ተመሳሳይ ሽንፈት ካበቃን አዙሪት እንዴት እንወጣለን ብሎ እነደመጠየቅ አዲስ ስም ይዞ ያንኑ ማስቀጠል
ውጤት አያመጣም። በተመሳሳይ ብልሹ አሠራር አዲስ ውጤት እንደማይገኝ ለመረዳት የባከነው ዘመንና ብሄራዊ ህለውና ላይ
የደረሰው ጉዳት ከዚህ መለስ ነው የሚባል አይደለም። በ1997 ብዙሃን የተጋዙበት የምርጫው ህግ ይሻሻል ጥያቄስ የት ደረሰ
ለማለትም ሆነ ድሉ የተነጠቀበትን ሁኔታ ካለመመርመራቸውም ሌላ በወቅቱ ጎጅ ሚና የተጫወቱ ክፍሎች እሰከዛሬ ድረስ መለስ
ብለው ራሳቸውን ለመገምገምና ስህተት ሰርተናል ለማለት ቅንነቱ እንደራቃቸው ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ህዝብ የቁርጥ ቀን ልጆቹን
የአዞ እንባ ከሚያነቡለት ለይቶ የሚያውቅ መሆኑን ደግሞ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ይህን ስንል ግን በነዚህ ድርጅቶች ውስጥ
ብዙ ሀገር ወዳድ ዓባላት እንዳሉና የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ እንደሆነ በመዘንጋት አይደለም።
ኢወክንድ በትግል ብዙ መማር ያለበት የወጣቶች ድርጅት መሆኑን ብንረዳም የእናት ድርጅቱ ኢሕአፓን አንጋፋ ተመክሮ መሠረት
ያደረገና የጀግኖቹ የነ ኢሕአወሊን ቆራጥ መንፈስ የወረሰ በመሆኑ ተቃዋሚው ክፍል ቆም ብሎ አቋሙን እነዲመረምር፣ አቅጣጫ
ለማሳት የተቀላቀሉትን ከወዲሁ እንዲለይና ብሎም ትግል ምንን እንደሚጠይቅ ደፍሮ ቢጠቁም በሁሉን አውቃነት የሚያስፈርጀው
አይሆንም። የነገውን ጉዞ የተስተካከለ -ትግላችንን የሠመረ ለማድረግና ሀገር አድን ትግሉን ወደ ድል ለማምራት ወደ ትናንት መለስ
ብለን ሂደታችንን በሚገባ መመርመር ከስህተታችንና -እንዳንደግመውም መማር ያስፈልገናል። ይህ ሲሆን ብቻ ነው የተቃዋሚው
ጎራ የሀገሪቱን ዜጎች እምነት ሊያተርፍና ከአለበት የፖለቲካና ሞራል ቀውስ ወጥቶ አይነተኛ ህዝባዊ ሃይል በመሆን ትግሉን
በአስተማማኝ ደረጃ መምራት የሚችለው ብሎ ኢወክንድ ያምናል።
በመጨረሻም በግልም ሆነ የተለያዩ ስብስቦችን ተቀላቅለው በአገር ውስጥና በውጭ እየተደረጉ ባሉ እንቅስቃሴዎች ለወገን ነፃነትና
ፍትህ የሚቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ ላሉ ሀገር ወዳድ ወገኖቻችን አድናቆታችንና ወገናዊነታችንን እየገለፅን፣ በዚህ ተጋድሏቸው
ኢወክንድ አብሮ ለመስራት ምንጊዜም ዝግጁ እንደሆነ መግለፅ እንወዳለን።

ለሀገር አድን ትግል ተባብረን እንነሳ!

No comments:

Post a Comment