በአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ በነጭ ሳር ግቢ የሚማሩ ከ25 ያላነሱ ተማሪዎች መታሰራቸው ታወቀ
ታህሳስ ፲፮( አስራ ስድስት )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ተማሪዎቹ የታሰሩት ካለፈው አርብ ጀምሮ ሲሆን፣ እስካሁንም በእነርሱ ላይ እየደረሰ ያለው እንግልት አለመቆሙ ታውቋል። በግቢው ውስጥ ተማሪዎች የሚጠቀሙበት መጸዳጃ የተበላሸ መሆን፣ የምግብ ጥራት መጓደል፣ የውሀ እጥረት፣ የመብራት ለረጅም ጊዜ መቋረጥ፣ የትምህርት ስርአቱ በተገቢው መልኩ አለመከናወን፣ የመጽሀፍት እጥረት፣ የኮምፒዩተር አለመኖር እና በተማሪዎች ላይ እየደረሰ ያለው የጤና መቃወስ ተማሪዎች ተቃውሞ እንዲያነሱ ግድ ብሎአቸዋል።
ተማሪዎች ባስነሱት ተቃውሞ የዩኒቨርስቲው የመማሪያ ክፍሎች መስታውቶች የሰባበሩ ሲሆን፣ የዩኒቨርስቲው አስተዳዳሪዎች ፖሊሶችን በመጥራት እርምጃ እንዲወሰድባቸው አድርገዋል። በርካታ ተማሪዎች ወከባና እስሩን በመፍራት ወደ የቤተሰቦቻቸው መመለሳቸውም ታውቋል።
የዩኒቨርስቲው አስተዳዳሪዎች ” የሌላ ብሄር ተወላጆች ንብረታችሁን እያወደሙ ነው የሚል ቅስቀሳ በማካሄድ” ተማሪዎችና የአካባቢውን ነዋሪዎች ለማጋጨት ያደረጉት ሙከራ እንዳልተሳካ ተማሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።
ዩኒቨርስቲው በእስር ላይ የሚገኙትን ተማሪዎች ለማባረር በዝግጅት ላይ መሆኑ ታውቋል። የአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ከአስተዳዳራዊ ችግሮች ጋር በተያያዘ በተለያዩ ጊዜዎች ተቃውሞ ሲያሰሙ ቆይተዋል።
No comments:
Post a Comment