ከመምህራን ከፍተኛ ተቃውሞ ሊገጥመው ይችላል ተብሏል በ2006 ዓ.ም መጨረሻ ሳምንታት ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ለነዋሪዎች መስጠት የተጀመረው የግዳጅ ስልጠና ዛሬ ለመምህራንና ለሁለተኛ ዙር ሰልጣኝ ተማሪዎች መሰጠት መጀመሩ ታውቋል፡፡
ምንጮች ለነገረ ኢትዮጵያ እንደገለጹት ለሰባት ተከታታይ ቀናት ለመምህራን ይሰጣል በተባለው ስልጠና ላይ መምህራን ያሉባቸውን ችግሮች በማንሳት ለኢህአዴግ አሰልጣኞች ከፍተኛ ፈተና ሊሆኑባቸው እንደተዘጋጁ አስረድተዋል፡፡ ከደመወዝ ማነስ ጀምሮ እስከ አጠቃላይ የትምህርት ፖሊሲው ድረስ ያላቸውን ቅሬታ በማንሳት ኢህአዴግ ሊሰጠው ያሰበውን ስልጠና የብሶታቸው ማሰሚያ መድረክ ለማድረግ መዘጋጀታቸው ታውቋል፡፡
‹‹ኢህአዴግ የመምህራንን ብሶት ያውቀዋል፤ ስልጠናው ላይ ችግሮቻችንን በሰፊው እናነሳለን፡፡ ይህ በመሆኑም የእኛን ድምጽ ለማፈን በማሰብ አባላቱን ቀድሞ አሰልጥኖ በመሃላችን እንደሚሰገስግ እናውቃለን፡፡ ሰዎቹን አዘጋጅቷል፡፡ ቢሆንም ግን እኛ ችግሮቻችንን ከማስተጋባት ወደ ኋላ አንልም›› ሲል አንድ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጹዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሁለተኛው ዙር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ስልጠና በተመሳሳይ ዛሬ መጀመሩ ታውቋል፡፡ በሌላ በኩል ግን መምህራንና ተማሪዎች የግዳጅ ስልጠና እንዲገቡ በተደረገበት በአሁኑ ሰዓት መንግስት ዛሬ በመላ ሀገሪቱ ትምህርት ቤት መከፈቱን በይፋ መናገሩ ይታወሳል፡፡ ነገረ ኢትዮጵያ በስልጠናው ሂደት የሚነሱ አብይ ጉዳዮችን በተመለከተ ምንጮቿ የሚያደርሱትን በመከታተል ለማቅረብ ትሞክራለች፡፡
No comments:
Post a Comment