የካቲት ፳፫(ሃያሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢትዮጵያውያን የጣሊያንን ወራሪ ሃይል ድል የመቱበትና ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቁሮች በነጮች ላይ የአሸናፊነት ታሪክ የጻፉበት የአድዋ ድል 119 አመት በአል በአዲስ አበባ ተከብሮአል።
በርካታ አርበኞችና ወጣቶች ፣ የአድዋን ድል በመሩት በአጼ ሚኒሊክ ሃውልት ዙሪያ በመሰባሰብ ቀኑን አክበረው የዋሉ ሲሆን ወጣቶች የጀግንነት መገለጫ የሆነውን ባህላዊ ሽለላ ሲያሰሙ፣ ባልተጠበቀ ሁኔታ በፖሊስ እንዲበተኑ ተደርጓል። ፖሊሶች ያልተፈቀደ ሰልፍ ነው በማለት ወጣቶችን መበተናቸውን በስፍራው የነበረው የኢሳት ወኪል ቀርጾ ከላከው ቨዲዮ ለመመልከት ይቻላል
የዛሬ 119 ዓመት በጄ/ል ባራቴሪ የተመራው የጣሊያን ጦር ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ታጥቆ መላ ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር ህልም የነበረው ቢሆንም፣ በአጼ ሚኒሊክና በባለቤታቸው በእቴጌ ጠሃይቱ የተመራው ጦር፣ ከአዲስ አበባ ገስግሶ በመሄድ የጣሊያንን ወረራ በማክሸፍ ፣ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቁሮች ነጮችን ድል ያደረጉበትን ታሪክ አስመዝግቧል። የአድዋን ድል ተከትሎ በጣሊያን የጠ/ሚኒስትር ክርስፒ መንግስት ፈርሷል። አውሮፓውያን ደግሞ ኢትዮጵያን እንደ አንድ ነጻ አገር እንዲቆጥሩ ተገደዋል። ድሉ በመላው የጥቁሮች ዘር የፈጠረው ስሜት በሁዋላ ላይ ለታዩት የጸረ ቅኝ ግዛት ትግሎች ከፍተኛ እገዛ አድርጓል።
በእለቱ በተደረገው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ጣሊያውያን ሲገደሉ፣ ብዙዎችም ተማርከዋል። በኢትዮጵያ በኩልም በሺዎች የሚቀጠሩ ዜጎች መስዋት ሆነዋል።
No comments:
Post a Comment