ልጄ አስራ ሁለተኛ ክፍል ስለጨረሰ የደስታዬ ተካፋይ ትሆኑ ዘንድ… የሚል ግብዣ ደርሷችሁ አያውቅም? እናንተም ፋሽኮ ቪኖ ወይንም እናትና ልጅ አረቄ ይዛችሁ ድግሱን ለማድመቅ ሳትሄዱ አልቀራችሁም – የዚያን ዕለት ጎረምሶቹ የቀለጠ ፓርቲ ደግሰው እስኪነጋ ይጨፍራሉ አሉ… ይህስ ይሁን።
ድህረ ምረቃ ፕሮግራም ላይ መሆኑን አንድም ቀን ሲናገር ሰምታችሁ የማታውቁት በቅርብ የምታውቁት ሰው ፣ እንዲያውም በመደበኛ ትምህርት ከስንተኛ ክፍል ነበር? አቋርጦ ወደ ሄደበት ሄዶ (ጫካ ወይንም ምርኮ) ግን የዛሬ ‘ሹም’ ‘የማስተርስ ፣ ዶክትሬት ዲግሬዬ በፖሰታ ስለደረሰኝ የደስታዬ ተካፋይ እንድትሆን ብሎ ቢጠራችሁስ? ይኼ ሰው ድሮ ትምህርት ቤት የተመዘገበበት ስም ሌላ ነበር… አሁን ደግሞ አዲስ ስም ብቻ ሳይሆን አዲስ ማዕረግ ፣ አዲስ ቤት ፣ አዲስ መኪና… ምኑ ቅጡ… ባናቱ ላይ ዲግሪ ሸምቶበታል።
ይድረስ ለተከበሩ… አስፈላጊውን ክፍያ ስላጠናቀቁ የ ማስተርስ ዲግሪዎን አያይዘን ልከናል – ለዶክተሬት ዲግሪዎ ተመልሰው እንደሚመጡ ተስፋ እናደርጋለን – የዋጋ ቅናሽም እናደርግሎታለን – ስለ ደንበኝነታችን ሲሉ አገልግሎታችንን ለስራ ባልደረቦችዎ እንዲያስተዋውቁልን ትብብሮን እንጠይቃለን – ለዚህም ተገቢውን ወሮታ እንከፍላለን – ያስታውሱ ‘ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ’ – ሴንቸሪ ዩንቨርሲቲ
ታዲያ እርሶም ለምርቃቱ ተጋብዘዋል – በተጠራው ድግስ ላይ ‘…ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትህን የት ነበር የጨረስከው ፣ ማትሪክ ውጤትህስ ስንት ነበር ፣ የመጀመሪያው ዲግሪህስ… ያጠናኸው ፣ የተመራመርከው እና መቸ ያዘጋጀኸው መመሪቂያ ቴሲስ ነው ለዚህ ያበቃህ?…’ ብላችሁ ትጠይቃላችሁ ወይስ ድግሱን ተቋድሳችሁ …እንኳን ለዚህ አበቃህ ብላችሁ መርቃችሁ ትመለሳላችሁ?
አነሳስቶ ላስጀመረን ፣ አስጀምሮ ላስጨረሰን ተብሎ ባደባባይ በግልፅ ሳይተያዩ ማስትሬት እና ፒኤችዲ እንደ መለዋወጫ እቃ ‘…ኦን ላይን ኦርደር…’ ማድረግ የወቅቱ የወያኔ ሹማምንት ልዩ መታወቂያ መሆኑን ስናይ
‘ኦ ዲግሪ ሆይ ከስምሽ ጀርባ ስንት ደደብ መሸገ’ እንድንል ያስገድደናል። ባንድ ጀምበር ሚሊየነር ፣ ባንድ ጀምበር ጄነራል እናም ባንድ ጀምበር ዶክተር እገሌ መባል ወያኔአዊ ተፈጥሮ ያመጣብን በሽታ ነው። እነኝህ ሰዎች በየመስኩ በሚፈጥሩት ስፍር ቁጥር የሌለው የተዛባና ህገ ወጥ አሰራር ጉዳቱ ውሎ አድሮ አገሪቱ ላይ በሁለንተናዊ መልኩ እየተንፀባረቀ መሆኑን ለመናገር የሚያስቸግር አይመሰለኝም። አዲሱ ሚሊየነር በሙስና እና ነጠቃ ላይ የተገነባ መሆኑ ፣ ጄነራሉ ችግር ሁሉ የሚፈታው በጠመንጃ ብቻ ነው ሲል የቁጩ ማስተርስ እና ዶክተርም የነሲብ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መፍትሔ ሲያረቅ ሲያማክር… እንዲያው ተያይዞ ገደል መግባት መሆኑ ቁልጭ ብሎ አይታያችሁም?
‘ኦ ዲግሪ ሆይ ከስምሽ ጀርባ ስንት ደደብ መሸገ’ እንድንል ያስገድደናል። ባንድ ጀምበር ሚሊየነር ፣ ባንድ ጀምበር ጄነራል እናም ባንድ ጀምበር ዶክተር እገሌ መባል ወያኔአዊ ተፈጥሮ ያመጣብን በሽታ ነው። እነኝህ ሰዎች በየመስኩ በሚፈጥሩት ስፍር ቁጥር የሌለው የተዛባና ህገ ወጥ አሰራር ጉዳቱ ውሎ አድሮ አገሪቱ ላይ በሁለንተናዊ መልኩ እየተንፀባረቀ መሆኑን ለመናገር የሚያስቸግር አይመሰለኝም። አዲሱ ሚሊየነር በሙስና እና ነጠቃ ላይ የተገነባ መሆኑ ፣ ጄነራሉ ችግር ሁሉ የሚፈታው በጠመንጃ ብቻ ነው ሲል የቁጩ ማስተርስ እና ዶክተርም የነሲብ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መፍትሔ ሲያረቅ ሲያማክር… እንዲያው ተያይዞ ገደል መግባት መሆኑ ቁልጭ ብሎ አይታያችሁም?
‘…ለኢህአዴግ ታማኝ እስከሆነ ድረስ ማይም እንኳ ሚኒስትር መሆን ይችላል…’ ያለው ማን ነበር? ሙት ወቃሽ እንዳልሆን ብዬ እንጂ ይኼ ድኩም ራዕይ የተሰነቀው ገና ከጠዋቱ እንደነበር አትዘንጉ ለማለት ነው። የአሳ ግማቱ ከወደ አናቱ!!
አንኳንስ ዶክተሬት ስምንተኛ ክፍል ሲጨርሱ ካባ ለብሶ ፎቶ መነሳት ፣ የምርቃት ቀን ደግሞ ሽክ ባለ ልብስ ፣ ባጌጠ አደራሽ ፣ ሞቅ ደመቅ ባለ ስነስርዓት ዘመኑን መቋጨት እዚህ በምእራቡ አለም ጭምር የተለመደ ነው። ከዩንቨርሲቲ ሲመረቁ ደግሞ ስርዓቱ ለየት ይላል – ይኼ ሁሉ የሚደረገው ግን አንድም ትምህርት በአግባቡ የተሰጠ ለመሆኑ ይፋዊ ማረጋገጫ ለመስጠት ሲሆን – ሽፍንፍን ፣ ድብቅብቅ ተመርቂያለሁ ማለት ባካዳሚው አለም ሆነ በህብረተሰቡ ውስጥ ተቀባይነት የሌለው ጉዳይ መሆኑን ለማሳየት ጭምር ነው። ይህን ስል በወያኔ ተቋማት አደባባይ የተመረቀ ሁሉ ብቃቱ ተረጋግጧል ማለቴ አይደለም።
ወያኔ ሁሉንም ዘዴ እንደ አስፈላጊነቱ ይጠቀምበታል። ከገበያ መሸመት ያለባቸው ሹሞች በጀት ተይዞላቸዋል – በተጠረቡ ቤቶች ውለው አድረው ‘የሚመረቁ’ ደግሞ አሉ… ከሲቪል ኢንሲቲትዩት… ከዚህ ሰፈር ከዚያ ሰፈር ኮሌጅ… ከዚህ ከዚያ ህዝቦች ዩንቨርሲቲ… ኮብል ስቶን ጠራቢ ምሩቃን ከታማኝ የወያኔ ካድሬ ምሩቃን ጋር ተማክረው ስለጉዳዩ የበለጠ ሊነግሩን ይችላሉ።
በምዕራቡ የትምህርት አለም ግን ልጆቻችሁን አስተምረን እዚህ አድርሰናል ፣ አዘጋጅተናል ፤ ኑ ተረከቡን የሚል ጥሪ ለወላጆች ሲቀርብ – ወጣቶቹ ለመጪው የከፍተኛ ትምህርት ዘመን ወይንም ለላቀ ሀላፊነት መዘጋጀታቸውን ለማብሰር ብቻ ሳይሆን ጠንክረው በጥሩ ውጤት ያጠናቀቁትን በአርአያነት በአደባባይ በመሸለም ሌሎችም እንዲተጉ ለማበረታታት ጭምር ነው። ይህም የሚደረገው አለምክንያት አይደለም።
የትምህርት ደረጃ የማይዛነፍ ራሱን የቻለ እርከን ፣ አድማስ እና ጥልቀት አለው – በትምህርት ገበታ የተወሰነ አመታት ማሳለፍ በራሱ የተጠና ፣ የተወጠነ ግብአት ያለው መሆኑንም መረዳት አያዳግትም። እያንዳንዱ እርከን ከዕድሜና የአይምሮ መጎልመስ ጋር ተቀናጅቶ ፣ በጥንቃቄ ተመጥኖ እየተለካ ዕውቀት የመመገብ ዘዴ ተዘርግቷል – መደመር እና መቀነስ ብለው ሳይጀምሩ ፣ ረጅሙን የሂሳብ ጎዳና ሳይጓዙ ካልኩለስ ስሌት ውስጥ መግባት እንደማይቻል ሁሉ ወግ ያለው መደበኛ ትምህርት በተገቢው መንገድ ሳይታለፍ ባቋራጭ ማስተርስ እና ፒኤችዲ አገኘሁ ማለት ራስን ከማጃጃል አልፎ ጦሱ የት እየለሌ ነው።
የረባ ዕውቀት ሳይጨብጡ ድሀ አገርን ያህል ለመምራት መድፈር ፣ ‘ድህነትን ታሪክ እናደርጋለን’ ከሚል ባዶ መፈክር የዘለለ ፋይዳ የለውም – ውጤቱ ከባዶ ጣሳ ወደ ተቀደደ ጣሳ ውሀ አገላብጥኩ እንደ ማለት ያህል ነው። ይሄም ባዶ ያም ባዶ – ከባዶ ለባዶ!! Blank of blank ይሉታል ፈረንጆቹ።
በመጀመሪያ ዲግሪ ለመመረቅ አራት ዓመታት የሚፈጀው በሚሰጡት ኮርሶች የሚገኘው ዕውቀት ብቻውን ያን ያህል ዘመን ይፈጃል ተብሎ አይመስለኝም። ተማሪው አራት ዓመታት በዚያ የእውቀት ማዕከል ሲመላለስ ከመደበኛው ትምህርት ሌላ ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊ ፣ አለም አቀፋዊ እና ቤተሰባዊ ልምድ እና እውቀት አጣምሮ በመቅሰም አይምሮውን ያጎለምሳል። ካንድ ደረጃ ወደሚቀጥለው ለመሻገር የትናንቱ ለዛሬው ፣ የዛሬው ለነገው የሚያወርሱት መሰረት እጅግ አስፈላጊ ናቸው። መደበኛ ትምህርት ወደ ስራ አለም ሲሰማሩ ሀላፊነትን በብቃት ለመወጣት የሚያስችል ስንቅ መደቆሻ አምባ ነው። በወጉ ሳይሰንቁ ሩቅ ለመጓዝ አይታሰብም ፣ በድፍረት የመጣው ይምጣ ብሎ መጓዝ ይቻል ይሆናል ውጤቱ ግን ባዶ መፈክር እያመረቱ ማደናገር ይሆናል – ከባዶ ጭንቅላት የሚመነጩ መፈክሮች መሬት ላይ ካለው ውነት ጋር የሚጣረሱ ለመሆናቸው ያለፉትን 23 ዓመታት ብቻ ማስተዋል ይበቃል – በቀን ሶስት ጊዜ ትበላለህ አይነት!!
ትምህርት እውቀት ነው ፣ እውቀት ደግሞ ሀይል ነው። የትምህርት ማዕረግ ሸምቶ ባልሰለጠኑበት ደረጃ እና ብቃት ሀላፊነት ላይ መቀመጥ ‘ሆድን በጎመን ቢደልሉት ጉልበት ዳገት ላይ ይለግማል’ እንዲሉ ፈታኙን የህብረተሰብ ሁለንተናዊ ችግሮች ለመጋፈጥ እና ለማቃለል ከቶውንም ማጠፊያው ይቸግራል። ይህንነም በተጨባጭ እያየነው ነው – እቅድ ተነደፈ ተብሎ ወረቀት ላይ የሚለቀልቁት ቅዠት ከዕውቀት ማነስ የሚመነጭ መደናበር ነው። በየዘመኑ ማክተሚያ ‘እቅዳችን ያልተሳካው …’ 99 ሰበብ መደርደር።
በቅርቡ ይፋ ሆነው ባነበብናቸው የምርመራ ዘገባዎች እንደተገነዘብነው አገራችን ከቶውንም የዩንቨርሲቲ ደጃፍ መርገጥ ቀርቶ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በወጉ ያላጠናቀቁ ባለስልጣናት የተሸከሙትን የሙያ ማረጋገጫ ምስክር ሰነድ እያየን ነው። ሳይማሩ የጠመጠሙ ዳውላ ሹማምንት እየበረከቱ መሆኑን በማስረጃ ተደግፎ የቀረበው ዘገባ አረጋግጧል። ይኼ ዜና አሳፋሪነቱ ድርጊቱን ለፈፀሙት ቱባ ባለስልጣናት ብቻ ሳይሆን እነዚህን ታቅፎ ተመርኩዞ አገር እየገዛ ላለው የወያኔ ስርአት ጭምር ነው።
ወያኔ ግን ሀፍረት ያውቃል እንዴ?
ይችን አስተያየት ለመክተብ ያነሳሳኝ ዋና ምክንያት ድንቅ ጋዜጠኛ አበበ ገላው ባቀረበው በዚህ ጥናታዊ ዘገባ ከተጋለጡት (ቅሌት ከተከናነቡት ብል ይሻላል) ግለሰቦች አንዱ አቶ ቆስጠንጢኖስን ባንድ አገጣሚ የማውቀው በመሆኑ ነው። ሰውዬውን ያገኘሁት እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር 1971 – 72 አብረን ማዕከላዊ ብሎም ከርቸሌ በቆየንባቸው የእስር ዘመናት ነበር። ያንን የእስር ዘመን በሚመለከት በቃለ መጠይቅ የተናገረውንም ሰምቻለሁ… ቆስጤ ያው እንደ ጥንቱ ነው – ሲናገር ሳግ አያንቀውም – የሴንቸሪው ዶክተሬት በባህሪው ላይ ለውጥ አላመጣም።
በሰኔ ወር 1971 ዓም በደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢ ደርግን የሚያሰጋ አንዳች ህቡዕ እንቅስቃሴ በደህንነት መስሪያ ቤት የተደረሰበት መሆኑ ይወራል። በዚህ እንቅስቃሴ ተሳትፈዋል የተባሉ አስራ ዘጠኝ ያህል የጂጌሳ እና ሰንቀሌ እንጨት መሰንጠቂያ ወዛደሮች (በደን ልማት ባለስልጣን ስር የነበሩ ፋብሪካዎች ናቸው) የፋብሪካዎቹ ዋና ስራ አስኪያጅ አለማየሁ ዘውዴ እንዲሁም በሻሸመኔ እና አካባቢው በልዩ ልዩ መስክ የተሰማራን ግለሰቦች በአካባቢው የደርግ ተጠሪ ኮሎኔል አባተ መርሻ አዝማችነት ከያለንበት ታድነን ደቡብ ጦር ሰፈር በሚገኝ እስር ቤት ገባን። በማግስቱ በከፍተኛ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች አጀብ አዲስ አበባ ተጓጉዘን ማዕከላዊ እስር ቤት እንታጎራለን። የተከሰስንበት ጉዳይ መንግስትን በወታደራዊ ሀይል ለመገልበጥ ዝግጅት ማድረግ የሚል ነበር። ‘… ጦር መሳሪያ አከማችታችሁዋል ፣ ወታደራዊ ስልጠና እየወሰዳችሁ ነው..’ ይላል የክሱ ቻርጅ። ከታሰርነው መካከል አንድም ወታደር የለም – እርግጥ ነው እሳት ከሌለ ጭስ የለም… እሳቱ ግን የነደደው ሌላ ሩቅ ሩቅ ሰፈር ነበር… ዝርዝሩ ወደ ሌላ ታሪክ ስለሚወስደን ለጊዜው እዘለዋለሁ።
ይህ በንዲህ እንዳለ አዲስ አበባ የደን ልማት ሰራተኞች ማህበር ሊቀመንበር ሀይሉ ዳኜ ተይዞ በኛ የክስ ሰነድ ተካተተ ፤ ብዙም ሳይቆይ ቀንደኛው ተጠርጣሪ ቆስጠንጢኖስ በረኼ ነው በሚል እሱም ተይዞ መጣ።
ቆስጤን በዝና እንጂ እስከዚያ ድረስ በአካል አላውቀውም ነበር… ደን ልማት ውስጥ ማለፊያ ስልጣን ያለው ሰው ሲሆን ተወዳጅ ተክለሰውነትም ነበረው… ረጋ ብሎ መናገር… ግን ሳያቋርጥ የመናገር ችሎታ አለው። ምንም ርዕስ ስጡት ቆስጤ እንደ ልዩ ባለሙያ ይተነትነዋል ፣ ያብራራዋል… ልዩ ተስጥኦ ነው። ታዲያ ከሚናገራቸው ነገሮች ውስጥ አብላጫው መጨበጫ መያዣ የሌለው ነገር ነበር… የቱ ውነት የቱ ውሸት መሆኑን እንኳ ለመለየት ይቸግራል። ያኔ እኔ ገና የ12ኛ ክፍል የህብረተሰብ ትምህርት ተማሪ ስለነበርኩ ቆስጤ የሚተነትነው የፊዚክስ ንድፈ ሀሳብ ሚስጥር ሆኖብኛል። በዚህ የተነሳ በጣም አደንቀዋለሁ – በብዙሀኑ እስረኛ ዘንድ በዚያን ዘመን ማዕከላዊ ከነበሩ ምሁራን እንደ አንዱ ይቆጠር ይከበርም ነበር።
ቆስጤን በዝና እንጂ እስከዚያ ድረስ በአካል አላውቀውም ነበር… ደን ልማት ውስጥ ማለፊያ ስልጣን ያለው ሰው ሲሆን ተወዳጅ ተክለሰውነትም ነበረው… ረጋ ብሎ መናገር… ግን ሳያቋርጥ የመናገር ችሎታ አለው። ምንም ርዕስ ስጡት ቆስጤ እንደ ልዩ ባለሙያ ይተነትነዋል ፣ ያብራራዋል… ልዩ ተስጥኦ ነው። ታዲያ ከሚናገራቸው ነገሮች ውስጥ አብላጫው መጨበጫ መያዣ የሌለው ነገር ነበር… የቱ ውነት የቱ ውሸት መሆኑን እንኳ ለመለየት ይቸግራል። ያኔ እኔ ገና የ12ኛ ክፍል የህብረተሰብ ትምህርት ተማሪ ስለነበርኩ ቆስጤ የሚተነትነው የፊዚክስ ንድፈ ሀሳብ ሚስጥር ሆኖብኛል። በዚህ የተነሳ በጣም አደንቀዋለሁ – በብዙሀኑ እስረኛ ዘንድ በዚያን ዘመን ማዕከላዊ ከነበሩ ምሁራን እንደ አንዱ ይቆጠር ይከበርም ነበር።
አወይ ማዕከላዊ! እኛ በታሰርንበር ዘመን እስር ቤቱ ተጨናንቆ እና ገንፍሎ ከቤት ውጭ መተላለፊያው ላይ ሰሌን ዘርግተን መተኛት ነበረብን። ማዕከላዊ ስንገባ እነ ጋሼ አሰፋ ጫቦ በጨለማ ቤት እንደታሰሩ ነው ፣ እኔ የደረሰኝ ላይኛው ግቢ 8 ቁጥር ሲሆን ብዙ ሰዎችን የመተዋወቅ ዕድል አጋጥሞኛል። እዚህ አሜሪካ ባለፈው ዓመት ዋይት ሀውስ ተጋብዞ ከፕሬዘደንት ኦባማ ልዩ ክብር የተቸረው ሳይንቲስቱ ዶር ሰለሞን ቢልልኝ የ8 ቁጥር ባልደረባዬ እንደነበረም አስታውሳለሁ።
የቼዝ ጨዋታ ስልት አስተምሮ ለውድድር እንድሰለፍ ያበቃኝ ሙባረክ ሸሪፍ (የሸሪፍ ላውንደሪ ባለቤት ልጅ) ከዚያው ከ8 ቁጥር ነበር ሌሊት ሌላ ክፍል ታስረው ከነበሩ ጓዶቹ ጋር ተወስዶ የተረሸነው (ከብርሀነመስቀል ረዳ ጋር ከጫካ የተያዙ ወጣቶች ናቸው)። እስከዛሬ ድረስ በቤተሰብ ደረጃ ግነኙነታችን ተጠብቆ የሚገኝ የዚያን ጊዜ የ8 ቁጥር እስረኛ ባልደረባዬ በቀለ ተፈራ ዛሬ ከነቤተሰቡ ጀርመን አገር ይኖራል… አዲስ አበባ ታዋቂ ኮማሪቶች ፔጆ 504 ወርቅና ውድ ጌጣ ጌጥ እየሸመተ ሲያንቆጠቁጣቸው የነበረው የመንግስት እርሻ ልማት ሀላፊ የነበረውን በርሔ ተመልሶንስ ታስታውሱታላችሁ? እሱም 8 ቁጥር ነበር። ስንቱ ይነገራል።
አለም በቃኝ ሲወስዱን ደግሞ የልጅነት ጓደኛዬን የሽመልስ ኦላና ታናናሽ ወንድሞች ሀይለልዑል እና ዳኜ አገኘሁዋቸው። ሽመልስ ኦላና አምቦ አካባቢ በግፍ መገደሉ ሳይበቃ ደርግ መላ ቤተሰቡን ለረጅም ጊዜ በእስር አሰቃይቷል ፣ ቤት ንብረታቸውን ቀምቶ ባዶ አስቀርቷቸዋል። አባቱ አንጋፋው ኦቦ ኦላና ባቲ በወያኔ ዘምንም ቢሆን ከመንገላታታት አላመለጡም። አንዳንድ ቤተሰብ ላይ የወረደውን ግፍ ሲያስቡት ይዘገንናል።
ከርቸሌም ቢሆን በየቤቱ ከታጎረው እስረኛ ሌላ አለም በቃኝ ክልል ሜዳው ላይ የላስቲክ ጎጆ ቀይሶ የሚያድረው ቁጥሩ እጅግ ብዙ ነበር። የመጀመሪያ ቀን አዳሬን ያደረኩት የ8 ቁጥር ባልደረባዬ ከነበረው ከመሐመድ ኢዛም ጋር ሲሆን – (መቸም 8 ቁጥር ኖሮ መሀመድ ኢዛምን የሚዘነጋው ያለ አይመስለኝም)። ተናግሮ የሚያስቅ ፣ ፈገግታ ከፊቱ የማይለይ ፣ ጨርሶ እስር ቤት መሆኑን ለመዘንጋት እና ሌሎችም እንዲዘነጉ ለማድረግ የነበረው ተሰጥኦ የሚገርም ነው። የኮሜርስ ምሩቅ እና የባንክ ሰራተኛ ነበር – ታዲያ የዚያን ዕለት ሜዳ ላይ አነጣጥፈን ከመተኛታችን ዝናም መንጠባጠብ ይጀምራል – መጠለያ የሚሉት ነገር የለም ምክንያቱም ቤት ውስጥ የሚተኙት በሙሉ ተቆልፎባቸዋል – መሀል ላይ ያለው በረንዳ ለጠጠር መወርወሪያ የሚሆን ክፍተት አንኳን የለውም – እስረኛው እንደ ርስቱ የሚቆጥረው የመኝታ መደብ አጨናንቆታል። እናማ ከዝናም መሸሻ ቦታ የለም። መሐመድ ኢዛም ግን እንዲህ አለኝ ‘አይዞህ አትስጋ ዝናም በአስማት የማቆም ችሎታ አለኝ… ብቻ የሚሆነውን ጠብቅ’ ሲል በማይገባኝ ቋንቋ መለፍለፍ ጀመረ…. ውነትም አስገምግሞ የመጣው ዝናብ በመንጠባጠብ ቀስ በቀስ በረደ – እኛም አንቀላፋን። ሁዋላ ውጭ ከመተኛት የታደጉኝ የሸመልስ ወንድሞች ናቸው።
ብዙ ትዝታ ያተረፍንበት ዘመን። … ወደ ቆስጤ ልመልሳችሁ።
እንዳልኩት በዚህ ጉዳይ ላይ ለመፃፍ ያነሳሳኝ የቆስጤ ነገር ነው። ትምህርቱን ከአዲስ አበባ ዪንቨርሲቲ ያውም በአፄው ዘመን ያጠናቀቀ ማለፊያ ጭንቅላት የነበረው ቆስጤ ምን ሲያደርግ የዩንቨርሲቲ ደጃፍ ረግጠው ከማያውቁ እነ አባዱላ ገመዳ ተርታ የሚያስልፈው ድርጊት እንደ ፈፀመ ሳስበው ይገርመኛል? በውነቱ በፖለቲካ እምነቱ ከወያኔ ጎን ቢሰለፍ ፣ እሱም እንደነሱ የዘር ሐረግ መዝዞ ይህን እና ያንን ስልጣን ቢጨብጥ ለምን ይህን አደረክ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ላይሆን ይችላል – ሰልጣን በዘር መስፈርት እንደ ቆሎ በሚታደልበት ዘመን እሱም ከዚያ ሰልፍ ውስጥ መግባቱ ቢያስቆጭም ትምህርትን ያክል ታላቅ ነገር የዘረኞች ማላገጫ ሲደረግ ግን ለምን እሱ ራሱ ግንባር ቀደም አድራጊ ፈፃሚ ሆነ? ውሻ በቀደደው…
ቆስጤ ይበልጥ ትዝ የሚለኝ ከርቸሌ ወደኛ ክፍል ተዳብሎ መኖር ከጀመረ በሁዋላ የሆነው አጋጣሚ ነበር። ዘመኑ 1972 ወሩ ትዝ አይለኝም ለሆነ የእስልምና ብሔራዊ በአል ቀን ወህኒ ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ጫት በይፋ እንዲገባ ይፈቀዳል – በዕለቱ ከውጭ በገባልን ጫት ምርቃና ሞቅ ደመቅ ያለ ውይይት ተከፍቶ ብዙም ሳይቆይ መድረኩ ለቆስጤ ይሰጠዋል። የንግግሩ ርዕስ ስለ ፊዚክስ የትምህርት መስክ ሲሆን በወቅቱ በመስኩ ስለተገኙ አዳዲስ ግኝቶች ምን ሊነግረን እንደሚችል ከቤቱ ጥያቄ ቀረበ። ቆስጤ ትንተናውን ጀመረ – ያኔ እኔ የ12ኛ ክፍል የሶሻል ሳይንስ ተማሪ ስለነበርኩ ስለፊዚክስ ብዙም ዝንባሌ አልነበረኝም። ይሁንና ቆስጤ ከሚሰጠው ትንታኔ በተለይ ስለ ህዋ ምርምር የተደረሰበትን ጭብጥ ሲያብራራ ሁላችንም ፈዘን በተመስጦ ‘በምርቃና’ መንፈስ እንከታተለው ነበር። አገላለፁ ቴክኒካል ተርም የሚበዛበት በመሆኑ ይመስለኛል አብዛኛው ነገር አልገባኝም – ሁላችንም ግን ባድናቆት ተከታትለነዋል። ያን ያህል ራሱን መግለፅ የሚችል ሰው ፣ የመጀመሪያ ዲግሪውን አንቱ ከተባለው የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ለፍቶ ደክሞ ያገኘ ሰው እንዴት መደበኛ ትምህርታቸውን በወጉ እንኳን ካላገባደዱት እነ አባዱላ ገመዳ ተራ ለመሰለፍ መረጠ? መልሱን በጨዋ ደንብ ሊሰጠን የሚችለው ቆስጤ ብቻ ነው።
ዛሬ አለም ያለበትን የቴክኖሎጂ ዕድገት ደረጃ ስናይ የሰውን ዘር ለዚህ ምጥቀት ያበቁ ሳይንቲስቶች በየዘመኑ ተጠበው በምርምር ባስገኙት ውጤት መሆኑ ግልፅ ነው። ከጥንት እስከ አሁን ደረጃ በደረጃ እየበለፀገ እየዳበረ ዕውቀት ይበልጥ እየረቀቅ ብሎም እያንዳንዱ መስክ ዳብሮ ልዩ የሙያ ዘርፍ መፍጠር አስፈላጊ የሆነበት ዘመን ላይ ነን። የስራ ክፍፍል ለብቃት መጎልበት አይነተኛ መሣሪያ እንደሆነ ሁሉ ካንድ የጠቅላላ ዕውቀት ዘርፍ ወደ ሰፔሸላይዜሽን ሽግግር የሚደረገው ያው ብቃትን ለማጎልበት ሲባል ነው። ይኼ ደግሞ በድህረ ምርቃ የትምህርት ዘርፍ ስልጠና እና ምርምር በማድረግ የሚጨበጥ ውጤት ነው። ታዲያ ከምድር ተነስቶ የድህረ ምረቃ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት መሸመት ባጠቃላይ ባገሪቱ እና በተለይ በትምህርት ገበያ ዘንድ ያለውን ሚዛን ምን ያህል እንደሚያዛባው የሚጠፋው ማነው? ቆስጤ ኦን ላይን ኦርደር የተደረገ ዲግሪ መሸመት ትምህርትን በቁሙ ለመግደል ከተሰለፉ ማይማን ተርታ እንደሚያሰልፈው እንዴት ጠፋው?
አገርን ለመግደል የትምህርት ስርዓቱን መግደል ፣ የትምህርትን ብቃት ዋጋ ማሳጣት እና ስልጣንና ሀላፊነት ዘር መዝዞ ለተጠጋ ሆዳም ማስታቀፍ – ይኼ ነው ከወያኔ አንቀፅ 39 ያተረፍነው – ትምህርት እና በተግባር የተፈተነ የሙያ ብቃት ሳይሆን ከዚህ ከዚያ ዘር መምጣት… እናም ስለ ዲግሪው ሴንቸሪ ዩንቨርሲቲ ይጨነቅበት።
ዶክተሬት በፖሰታ ልኬልሀለሁ
የድሮ ስምህን ደልዠዋለሁ…. አጅሬ ዶክ…
የድሮ ስምህን ደልዠዋለሁ…. አጅሬ ዶክ…
No comments:
Post a Comment