BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

Tuesday, 3 March 2015

ሰማያዊ ፓርቲ የቅስቀሳ መልእክቱን እንዲለውጥ ተጠየቀ።

የካቲት ፳፬(ሃያ አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ፣ ኤፍ ኤም 96.3፣ ሰማያዊ ፓርቲ ለምርጫ ቅስቀሳ ያቀረባቸውን መልእክቶች እንዲለውጥ፣ ካልለወጠ ግን እንደማያስተላልፍ ገለጸ።
ጣቢያው እንዲወጡ ከጠየቃቸው መልእክቶች መካከል ‹‹ሀገራችን ዛሬ በቀሪው ዓለም የምትታወቀው በእርስ በርስ ጦርነት ነው›› የሚለው የሚገኝበት ሲሆን፣ መልእክቱ ለአመጽና ለሁከት የሚያጋልጥ ነው የሚል ምክንያት አቅርቧል።

ሌላው እንዲወጣ የተጠየቀው ‹‹ህዝቧ የዘር፣ የኃይማኖት፣ የቋንቋና የባህል ልዩነቶችን ተቀብሎ ለበርካታ ዘመናት ተቻችሎ የኖረ ቢሆንም ዛሬ ግን እርስ በርስ በጥርጣሬ እንዲተያይና አንድነቱ እንዲላላ እየተደረገ ነው›› የሚለው መልእክት ሲሆን፣ መልእክቱ ብሔር፣ ብሔረሰቦችን የሚያጋጭ ወይንም የእርስ በርስ ግጭት የሚያስነሳ፣ አመፅና ጦርነት የሚቀሰቅስ ነው ተብሎአል።
ዝግጅቱ  የታጀበበት ሙዚቃ የድምጻዊውን ፍቃድ መያዝ እንዳለበትም የሬዲዮ ጣቢያው ለመስተዳድሩ በላከው ደብዳቤ ላይ ጠቅሷል።
የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ የቅስቀሳ ፕሮግራሙ ውስጥ እንዲስተካከሉ የላካቸው ሀሳቦች የሰማያዊ  ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ  ያፀደቃቸው ፣ የፓርቲው ፕሮግራም አካልና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም የተቀበላቸው መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ራዲዮ ጣቢያው በፓርቲው የውስጥ ጉዳይ ገብቶ ቅድመ ምርመራ እያደረገ ነው ሲሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።
ሙዚቃውን በተመለከተም ‹‹መብቱ የሙዚቀኛው እንጂ የራዲዮ ጣቢያው አይደለም፡፡ ሙዚቀኛው ደስተኛ ካልሆነ ካስተላለፍነው በኋላ ሊከሰን ይችላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ጣቢያው የሚያገባው ነገር የለም›› ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።
“በሚናገሩት ቋንቋ መነሻነት ብዙ ዜጎች በተደጋጋሚ ከቀያቸው እንደሚፈናቀሉ ፣ በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ባለው ዘርን ያማከለ ሹመት ምክንያት በርካቶች የጎሪጥ እንደሚተያዩ ፣ የጎሳ ፌደራሊዝሙ ለተደጋጋሚ ግጭት መዳረጉን መንግስት በሚያሰራቸው ጥናቶችም ጭምር መረጋገጡን የገለጹት የሰማያዊ ፓርቲ ም/ሊቀመንበርና የምርጫ ጉዳይ ኃላፊው አቶ ስለሽ ፈይሳ ፣  ራዲዮ ጣቢያው የቅስቀሳ ፕሮግራሙ ላይ እንዲቀየሩ የጠየቃቸው ሀሳቦች በመረጃ የተደገፉ ናቸው ሲሉ ለጋዜጣው ተናግረዋል፡፡ አቶ ስለሽ አክለውም ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ፕሮግራሙ ላይ ያለውን ሀሳብ አውጣ እየተባለ ቅድመ ምርመራ ሲደረግበት፣ ኢህአዴግ ግን ተቃዋሚዎችን ‹‹ህገ-ወጥ›› ከሚላቸው አካላት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው እየከሰሰና እያንቋሸሸ ቅስቀሳ እያካሄደ ነው ፡፡ ይህ ደግሞ ራዲዮ ጣቢያው በግልጽ አድሎአዊነቱን እያሳየ እንደሆነ ትልቅ ማስረጃ ነው›› ሲሉ አክለዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ሰማያዊ ፓርቲ  ዛሬ በአዲስ አበባ በጀመረው ይፋ የምርጫ  ቅስቀሳ አባላቱ  ሲታሰሩ አንድ የፓርቲው አመራር አባል ደግሞ  በአማራ ክልል ከተሞች ልማትና ግንባታ ውስጥ ከነበራቸው ኃላፊነት ተነስተዋል።
ሰማያዊ ፓርቲ እንዳስታወቀው ዛሬ ከማለዳ ጀምሮ በአዲስ አበባ  በሁሉም ክፍለ-ከተሞች  በመዟዟር የምርጫ ቅስቀሳ በይፋ ጀምሯል።
ይሁንና በቅስቀሳ ሥራ ላይ የነበሩ ሁለት የፓርቲው አመራሮችና ሌሎች አባላትም  ረፋዱ ላይ   ከሽሮሜዳ አካባቢ  በፖሊስ ታፍነው መወሰዳቸውን ፓርቲው አስታውቋል።
ታፍነው ወደ “ላዛሪስት” ፖሊስ ጣቢያ የተወሰዱት የፓርቲው አመራሮች፦  የምርጫ ክልል 12/13 እጩ የሆነው ዶ/ር ዘላለም ደሳለኝ እና የምርጫ ክልል 10 እጩ  የሆነው አቶ ይድነቃቸው አዲሱ ናቸው፡፡
ከነሱ ጋር አብረው የነበሩት  የቅስቀሳ ቡድኑ አባላት አቶ ሳምሶን ግዛቸው፣ ወ/ሪት ምዕራፍ ይመር፣ አቶ ፍሬው ተክሌ ፣ የቴክኒክ ባለሙያዎች፣ ሹፌሩና ረዳቱም አብረው መታሰራቸውን ፓርቲው አስታውቋል፡
በፖሊሶች በታገተው መኪና ውስጥም ከአስር ሺህ በላይ በራሪ ወረቀቶች  አብረው መታገታቸውንም ሰማያዊ ፓርቲ አመልክቷል።
ይህ በ እንዲህ እንዳለ የአማራ ክልል ከተሞች ልማትና ግንባታ ፤የሰማያዊ ፓርቲ የምዕራብ ጎጃም ዞን ተወካይ እንዲሁም የምዕራብ ጎጃም፣ ምስራቅ ጎጃምና አዊ ዞን የምርጫ ግብረ ኃይል አባል የሆኑትን  አቶ አዲሱ ጌታነህን ‹‹ማኔጅመንቱን ያውካል፣ የስራ ተነሳሽነት የለውም›› በሚል ከኃላፊነታቸው  እንዳነሳቸው በደብዳቤ አሳውቋል፡፡ መስሪያ ቤቱ አቶ አዲሱ ጌታነህን  “ባሳዩት ብቃት” በሚል  የዛሬ አምስት ወር፤ ማለትም  ጥቅምት 23/2007 ዓ.ም  አሁን በሻራቸው የኃላፊነት ቦታ ላይ  እንደመደባቸው  ከቢሮው የወጣው የምደባ ደብዳቤ ያመለክታል።
በብቃት ሀላፊነት ላይ በመደባቸው በአምስት ወር ጊዜ ውስጥ ፣ “ማኔጅመንቱን ያውካል፣ የሥራ ተነሳሽነት የለውም” በማለት የወሰደባቸውን እርምጃ እንደማይቀበሉት የገለጹት አቶ አዲሱ፤ የተወሰደባቸው እርምጃ ፖለቲካዊ መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ አዲሱ አክለውም፦‹‹ባህርዳር ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ኃይል እየተፈጠረ ነው፡፡ በተለይ የአንድነት መዋቅር ሰማያዊን ከተቀላቀለ በኋላ ከፍተኛ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ይህንም ተከትሎ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች ጋር ያደረግናቸው ውይይቶች ብአዴንን አስደንግጦታል››ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የምዕራብ ጎጃም ዞን የሰማያዊ ፓርቲ መዋቅር በአካባቢው ህዝብ ላይ የሚደርሰውን በደል፣ እንዲሁም ምርጫ ቦርድ ከዕጩ ምዝገባ ጋር በተያያዘ የሚፈጥራቸውን ችግሮች ለሚዲያ እያጋለጡ መሆናቸው ከኃላፊነታቸው ለመነሳት አንድ  ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ አብዛኞቹ የአማራ ክልል ከተሞች ልማትና ግንባታ የቦርድ አባላት የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች ናቸው።ከእነዚህም መካከል የባህርዳር ከተማ ከንቲባ አቶ ላቀ አያሌው፣ የክልሉ ም/ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ያለው አባተ እና የክልሉ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ኃላፊ አቶ አየነው ይገኙበታል፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት በኢትዮጵያ አየር መንገድና በንግድ ባንክ ውስጥ ይሰሩ የነበሩ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች በተመሳሳይ መንገድ ከስራቸው እንዲባረሩ መደረጋቸው አይዘነጋም።

No comments:

Post a Comment