ዴሞክራሲያ ቅጽ 42 ቁ. 3 ታኅሣሥ 2009
ከፋሽስት ጣሊያን ወረራ በኋላ የመጣው ኢትዮጵያዊ ትውልድ በተለይም ፊደል ለመቁጠርና ዘመናዊ ትምህርት ለመቅሰም
እድሉን ያገኘው ክፍል፤ የወገኑና የአገሩ ችግርና ብሶት እጀግ ያንገበገበው፤ ያሳሰበው ነበር። ለውስብስብ ችግሮቹ መፍትሔ
ለመሻት ብዙ ጥሯል። በአፍላ የወጣትነት ዘመኑም የራሱን ጥቅምና ፍላጎት ለአገርና ለወገኑ አሳልፎ የሰጠ፤ ወደር የማይገኝለት
ትውልድ በመሆኑ ታሪክ ዘወትር ሲያስታውሰው ይኖራል።
በ1950ዎቹ መጨረሻና በ60ዎቹ መጀመሪያ የነበረው ወጣት ትውልድ የአገሩን ሁኔታ እንዴት መለወጥ እንደሚችል አበከሮ
በመጠየቅ፤ የወቅቱን አገር አቀፍና የዓለም አቀፉን ተጨባጭ ሁኔታ በማገናዝብና ተገቢውንም ትምህርት በመቅሰም፤ አገራችን
በተሻለ የእድገት፣ የልማትና የፍትኅ ጎዳና እንድትራመድ አቅሙ በፈቀደ መጠን ኃላፊነቱን ለመወጣት ጥረት አድርጓል።
ወጣቱ
ትውልድ በሀገራችን ትምህርትን፣ ህክምናንና ሥራን ለሁሉም ዜጋ ለማዳረስ፤ እጅግ አስከፊ የነበረውን ድኽነት ለመቅረፍ ፤
የብዙኅኑን መብትና ጥቅም ለማስከበር፤ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለማስረጽ፣ የመደብና የብሔር
ጭቆናን ለማስወገድ፤ ማኅበራዊ ፍትህን ለማስገኘት፣ ፈጣን ኢኮኖሚያዊና የቴክኖሎጂ እድገትን ለማምጣት የብሔር፣
የሃይማኖትና የፆታ ልዩነት ሳይገድበው እጅ ለእጅ ተያየዞ ከዳር እስከዳር ተንቀሳቅሷል።
ይህ የሀገሩን ኋላ ቀርነት የተረዳው የትናንቱ ለውጥ ናፋቂ ኢትዮጵያዊ ወጣት ትውልድ፤ “ሰማይ አይታርስ ንጉሥ አይከሰስ”
ይባልለት የነበረውን ሥርዓት ለመለወጥ በተደረገው ሕዝባዊ ትግል የግንባር ቀደምትነት ሚና ተጫውቷል። የዘውዱን አገዛዝ
ለመቀየር በተደረገው ሕዝባዊ አመጽና እንቅስቃሴ የሕዝብን ድል በጠብ-መንጃ አፈሙዝ ጠልፎና ነጥቆ ሥልጣኑን
የተቆጣጠረውንና ከእግር ጥፍሩ እሰከ ራስ ጠጉሩ ታጥቆ ከፍተኛ በደል ሲፈጽም የነበረውን ፋሽስታዊ የደርግ አገዛዝም ፍትኅ
እና እኩልነት እውን ይሁኑ፤ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም፤ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ይከበሩ፤ ... ወዘተ በማለት፤
ኢትዮጵያዊ ወኔን ተላብሶ፤ በአንድነት ተሰባስቦና የምልአተ ሕዝቡን ጥያቄዎች አንግቦ ፊት ለፊት ተጋፍጧል።
ዛሬ ወርሃ ታኅሣሥን ስንዘክር፤ የኢትዮጵያ ወጣቶች ገድልና የታኅሣሥ ወር በኢትዮጵያ ወጣቶች ታሪክ ውስጥ
የማይነጣጠሉ ቁርኝት ያላቸው መሆኑን በመገንዘብ ነው። የኢትዮጵያ ወጣት ምሁራንና ተማሪዎች ትናንት መሬት ለአራሹ
ለላብ አፍሳሹ፤ ድኽነት ወንጀል አይደለም፤ ዳቦ ለተራበው፤ የዲሞክራሲ መብቶች ያለገደብ፤ የሃይማኖትና የፆታ እኩልነት
ይከበር፤ ሕዝባዊ መንግሥት ይመሥረት ሲሉ በወርሃ ታኅሣሥ የለኮሱት የአመጽ ችቦ ለየካቲት 66ቱ ሕዝባዊ አብዮት
መቀጣጠልና መወለድ ራሱን የቻለ ዓብይ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ሕዝባዊ ትግሉም የጠየቀውን ከባድ መስዋዕትነት ሳያመነቱ
ከፍለዋል። ታኅሣሥ 20 የኢትዮጵያ ወጣቶች የሰማዕታት ቀን ሆኖ እየታወሰ እንዲኖር በዓለም አቀፍ ተማሪዎች ማኅበራት
ተወስኖ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ተማሪ ማኅበራት ጭምር ለረዥም ጊዜ ሲታሰብና ሲከበር ቆይቷል። ለዚህም ነው
ዛሬም ወርሀ ታኅሣሥ የኢትዮጵያ ኩሩ ወጣት ምሁራንና ተማሪዎች እንቅስቃሴ ባለታሪክ ወር ሆና የምትዘከረው።
የ1960ዎቹ የኢትዮጵያ ወጣት ተማሪዎች በተለይም በዩኒቨርስቲ አካባቢ የነበሩ ወጣት ምሁራን፣ በወቅቱ በጭሰኝነት በረሀብና
በደዌ በድህነት ለሚቆራመተው አርሶ-አደር፤ በዘመናዊ እርሻ ተቋማትና ኢንዱስትሪዎች ውስጥ አድካሚ የጉልበት ሥራን
እየሰራ ተመጣጣኝ ክፍያ ለማይደረግለትና ጉልበቱን ለሚበዘበዘው ላብ አደር ፤ በአጠቃላይ በገዛ አገሩ የበይ ተመልካች
ለሆነው ብዙኅኑ ዜጋ መድህን በመሆን፣ የጭቁኑን ብሶት ከፍ አድርገውና አስተጋብተው ታግለዋል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች እንቀስቃሴ በጨቋኞች ላይ በአሻፈረኝ ባይነት ብቻ አልተወሰነም። የተበደለውን ዜጋ መብት ለማስከበር
በአስቸጋሪ የትግል ጉዞ ተሳትፈው ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን አፍርቷል። ይህ ጎጥ፣
ሃይማኖትና ፆታ ሳይገድበው በመላው የአገሪቱ ክፍሎች የተቀጣጠለው የወጣት ተማሪዎችና የወጣት ምሁራን እንቅስቃሴ
በአገር ውስጥ ብቻ የተገደበ ሳይሆን በውጭ አገር በነበሩ ወጣት ኢትዮጵያውያን ተቀጣጥሎ የቀጠለ ነበር። ቀደም ብሎ
ለከፍተኛ ትምህርት የሄዱትም ሆነ በአገዛዙ የስለላ መዋቅር ለእስራት ለግድያ ተጋልጠው ወደ ውጭ የወጡ ተማሪዎች ትግሉ
እንዳይቋረጥ በውጭ አገሮች የበኩላቸውን አስተዋፅኦን አበርክተዋል። የተለያዩ ቀስቃሽ ፅሁፎችን በማዘጋጀትና በህቡዕ ወደ
አገር ውስጥ በማስገባት፤ የተቃውሞ ሰልፎችንና የረሀብ አድማዎችን በማድረግ ፤ በውጭ አገር የሚገኙ ኤምባሲዎችን
በመውረርና በመያዝ አገዛዙ በወጣት ምሁራንና ተማሪዎች ላይ የሚያደርሰውን እንግልት፣ እስራትና ግድያ ለዓለም ሕዝብ
ያለማቋረጥ አሰምተዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ ወጣት ምሁራንና ተማሪዎች የሚያደርጉትን ፖለቲካዊና ማኅበራዊ እንቅሰቃሴንም
በመደገፍ የትግል አጋርነታችውን በሚገባ አረጋግጠዋል።
በ1950-ዎቹና 1960-ዎቹ በአገሪቱ መናገሻ ከተማ፣ በአዲስ አባባ፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተጀመረው የተማሪዎች
እንቅስቃሴም ውጪ ካለው የወጣት እንቅስቃሴ ጋር ተቀናጅቶ አገሪቱን በመላ ያዳረሰ ከመሆኑ ሌላ እያደር ሕዝባዊ መሠረትና
ድጋፍን ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እያገኘ በመጠናከሩ አገዛዙን ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል።
በወጣት ምሁራንና በተማሪዎች ተቀስቅሶ፤ በከተማና በገጠር በስፋት በተቀጣጠለው የለውጥ እንቅስቃሴ የተደናገጠው አገዛዝ
የተለያዩ እርምጃዎች ከመውሰድ አልተቆጠበም። ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ታጋዮች ፤ የሥራ ማቆም አድማ ያደረጉ ላብ-አደሮች፤
ለባለ እርስቶች አንገብርም በማለት ያመፁ አርሦ-አደሮች እንደተጋዙና እነደተረሽኑ ሁሉ፤ የሕዝባዊ ትግሉ ግንባር ቀደም አካል
የሆነው እንቡጥ የወጣቶች እንቅስቃሴ አካል ታሳታፊ የነበሩት በአገዛዙ የተጋረጠባቸው አደጋ ጭካኔ የመላበትና እጀግ የከፋም
ነበር።
የአፄው ሥርዓት ለጥገና ለውጥ እንኳን ክፍት ባለመሆኑ የተነሳ በጊዜው በርካታ ለውጥ ፈላጊ ክፍሎች የኃይል እርምጃ
በመውሰድ አክሽፏቸዋል። በ1943 እነቢትወደድ ነጋሽ፤ በ1953 እነ መንግስቱና ገርማሜ ንዋይ ያካሄዱት የመፈንቅለ
መንግሥት ሙከራ በተጨማሪም በ1957 በተወሰኑ መኮንኖች እና በ1960 ዎቹ መጀመሪያ ላይ በእነ ደጃዝማች ታከለ ወልደ
ሓዋርያት የተደረጉት ሙከራዎች በእስራትና በግድያ እንዲሁም በሌሎች አፋኝ እርምጃዎች እንዲከሽፉ ተደርገዋል። በዚሁም
ዘመን እነ ጥላሁን ግዛው፣ ዋለልኝ መኮንን፣ ማርታ መብራቱና ሌሎች ብርቅዬ ወጣት ምሁራን ሥርዓቱን ለመለወጥ ሲታገሉ
ህይወታቸውን ለአገራቸው ሰጥተዋል።
በተማሪዎች ላይ የተካሄዱት ግድያዎች እስራቶችና አፈናዎች የሕዝቡን ቁጣ በመቀስቀሳቸው ተቃውሞ ተባብሶና ተጋግሎ
ቀጥሎ፣ አገዛዙ የተማሪዎቹን አመጽ ማፈንና ማስቆም የማይችልበት ሁኔታ ውስጥ ገባ። እንደቆሰለ አውሬም መወራጨቱን
ተያያዘው። አገሪቷንም ካላችበት ኋላቅርነት ጎዳና ለማላቀቅ ሥር-ነቀል የሆነ ለውጥን ማካሄድ እንደሚያስፈልግ የተገነዘቡትና
ይህን የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት ትግሉን ከፍ ወዳለ እርከን ማሸጋገር አስፈላጊ መሆኑን የተረዱት ክፍሎች ታጋዩን
ሊያሰባስብ የሚችል የፖለቲካ ድርጅት ለመፍጠር እንቅስቃሴ ጀመሩ። መሠረታዊ ለውጥ ውድና ክቡር ህይወት የሚከፈልበት፤
ከባድ መከራን መቀበል የግድ የሚልበት መሆኑን በመገንዘብና አልፎም ለምን ዓላማ ፤ ማንን መታገል እና እንዴት መታገል
እንደሚገባ በመረዳት የትግል መሣሪያ ሆኖ እንዲያገለግል የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ(ኢሕአፓ) በመባል
የሚጠራውን የፖለቲካ ድርጅት በሚያዚያ ወር 1964 ዓ.ም ለመመስረት ቻሉ።
በወጣትነት እድሜያቸው ኢሕአፓን የመሠረቱትም ሆነ በኋላም የድርጅቱ አባልና ደጋፊ በመሆን በትግሉ ውስጥ የተሳተፉት
ወጣት ምሁራንና ተማሪዎች ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በኢትዮጵያዊነት የተሰባሰቡ፤ በአንድ ዓላማና ፍላጎት (በአገር ፍቀር
ስሜት) የተሳሰሩ ለመሆናቸው፣ በጊዜው የከፈሉት መከራና ስቃይ ይመሰክራል። በትግሉ ሂደት ያለፉትም ሆነ እስከዛሬም
ትግሉን በፅናት ያስቀጠሉ አባላትና ደጋፊዎች ገድልም ይህንኑ አስረግጦ ይናገራል። ይህ በአያሌ ኢትዮጵያውያን የህይወት
መሰዋዕትነት የተከፈለበት የለውጥ እንቅሰቃሴ ምላሽ ባላማግኘቱ ዛሬም የሕዝብን ትግል ማስፋፋትና ማጠናከር ግድ ሆኖ
ይገኛል። በየወቅቱ የነበሩትን የአምባገነንና የፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ሥርዓትን በማስወገድ፣ በምትኩ ፍትህ እኩልነትና
ዴሞክራሲ እውን የሚሆንበት ሥርዓት እንዲሰፍን ለማድረግ የተደረገው የትግል ጉዞ እጅግ አስቸጋሪ፤ ወጣገባና ውስብስብ
ነው። ከበርካታ ዓመታት በላይ የፈጀውና አሁንም ቢሆን ለውጥን አርግዞ በጉዞ ያለው ሕዝባዊ ትግል ያሳለፈውን ውጣ ውረድ
እንዲሁም በትግሉ ውስጥ የተከፈለውንና ዛሬም ጭምር እየተከፈለ ያለውን መስዋዕትነት በአንክሮ ማሰብና ትልቅ ክብርም
መስጠት ይገባል።
ያ ለአገር ቀናኢ በሆኑ ወጣት ምሁራንና ተማሪዎች የተመሰረተው ኢሕአፓ፣ ሲጸነስም ሆነ ሲወለድ ይዞት የተነሳውን አገራዊና
ሕዝባዊ ራዕይ ሳያጥፍና ሳይሰርዝ ፤ ለመጣው ሁሉ ሳያጎበድድ፤ ሹመትና ሽልማት ሳያታልለው፤ በክህደትና በባዳነት ጎዳና
ሳይነጉድ፤ ትናንት የምርጦቹን አምባገነናዊ አገዛዝ በጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ይተካ፤ ዛሬም በጽናት የወያኔን ዘረኛ ከፋፋይና
አምባገነን አገዛዝ እየታገለ ያለ የሕዝብ ድርጅት ነው፡፡ የዛሬው ወጣት ትውልድ ካለፈው ወጣት ትውልድ የትግል ተመከሮና
ታሪክ የሚወርሰውና የሚማረው በርካታ ቅርሶች አሉት። ወጣቱ ትውልድ ባገሩ ጉዳይ ላይ ፀንቶ ለመቆም በመጀመሪያ ሀገሩን
ማፍቀር፤ ሕዝብን መውደድ ስለዕውነት መቆም ይጠበቅበታል። ብቃት በተመከሮ ሊመጣ የሚችል ነው። የሀገር ፍቅር
በቅጽበት የሚፈጠር ጉዳይ አይደለም። ሀገር ወዳድ ዜጋ እንደባለሙያ ከማሰልጠኛ ተቋም የሚመረት ሳይሆን ከትውልድ
ትውልድ በተወረሰ ታሪክ ፤ ወግና ባህል ውስጥ በማለፍ የሚገኝ ቅርስ ነው። ከልጅነት ጀምሮ በአስተዳደግ ሂደት ውስጥ
የሚሰርጽ ስሜት ነው። በመሆኑም አዲሱ ትውልድ ከኅብረተሰቡ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ታሪክ፣ ወግና ባህል
ይወርሳል። ሀገሩ ስትደፈርና ክብሩ ሲነካ የሚያስቆጣው ፤ ወኔና ድፍረት በህሊናው ውስጥ ይሰርጻል። ጀግናን ማክበር
ማወደስና ማሞገስ በተፃራሪው ደግሞ ፊሪን፣ አጎብዳጅንና ባንዳን መኮነንና ማጋለጥ የብቁ ዜጋን ሰብዕና ለመገንባት ይረዳል።
አንድ ኅብረተሰብ ተተኪውን ትውልድ ኮትኩቶና ተንከባክቦ ለአገርና ለሕዝብ ፍቅር ፀንቶ መቆም የሚያስችለውን የሥነ-
ምግባርና የሥነ-ልቦና መሠርትን መጣል ይኖርበታል። ለዚህም ነው ኢሕአፓ ስለቀጣይ ትግሉም ሆነ ስለቀጣይ የትግል ቃል
ኪዳን ሲያወሳ፤ የነገው አገር ተረካቢ ትውልድ ይህንን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ኢትዮጵያዊ እሴቶቹንና የጀገኖችን ታሪክ
ተረክቦ ተንከባክቦና ጠብቆ በተራው ለተተኪው ትውልድ ሊያወርስ ይገባል የሚለው። ያኔም ነው ቀጣዩ ትውልድ ባለ-
ራዕይና ጀግና ትውልድን ያለማቋረጥ ማፋራት የሚችለው። ለዚህ ማስረጃው ትናንት ኢሕአፓን በጠላትነት ፈርጀው
ሊያጠፉት ጦር የሰበቁበት ሳይቀር የዛን ወጣት ትውልድ ጀግንነትና ቆራጥነት ጀንበር ከጠለቀች ቢሆንም እንኳ ሳይክዱ
መመስከር መጀመራቸው ነው። ያ ! ወጣት ትውልድ ደሙን ያፈሰሰውና አጥንቱን የከሰከሰው ለሚወዳት አገሩና ለተበደለው
ወገኑ ክብር ሲል ለመሆኑ በአደባባይ ጭምር የምስክርነት ቃላቸውን መስጠት ተገደዋል።
ኢሕአፓ መሠረቱ ሕዝባዊና አገራዊ ስለነበር ራዕዩም ጥቂቶች ብቻ ባለመብትና ተጠቃሚ የሆኑበትን ሁኔታ በትግል ለውጦ
ሁሉም በዜግነቱ እኩል የሚሰተናገድባትን አገር ዕውን ለማድረግ እንደነበር በትግሉ ሂደት ያሳየው ቆርጥነትና የከፈለው
መስዋዕትነት በሚገባ ያረጋግጣል። ትናንትና የዚያን ወጣት ትውልድ ሀቀኛ ታሪክ ለመበረዝና ለማርከስ ብሎም ለማጥቆር
የተሯሯጡት ሁሉ ተልኳቸው ተጋልጦ የሀሰት ሸማን ተከናንበዋል። ሰልፋቸው ከማን ጋር እንደሆነ በሂደት ታይቷል። በዛሪዋ
የዴሞክራሲያ እትም ይህንን እንድናንሳ የተገደድነው ባለፈው ታሪካችን ለመመፃድቅ ሳይሆን ዋናው መልዕክታችን፤ የኢትዮጵያ
ወጣቶችን የትግል ሚና ለማስታውስና ቀጣዩ/ተተኪው ትውልድ ያለፈውን ወጣት ትግል ታሪክ ጠንቅቆ እንዲረዳ የትግል
ታሪክ ተመክሮ ሊቀስምበት ይችላል ከሚል ቁም ነገር ተነስተን መሆኑን አበክረን ለመግለጥ እንወዳለን።
የዛሬው ወጣት ትውልድም ካለፈው ትውልድ የቀጠለውን ትግልና ቃል ኪዳን እንዲረከብ ታሪክ ኃላፊነትን ጥላበታለች።
የዛሬው ወጣት ትውልድ የተሸከመው አገራዊና ሕዝባዊ አደራ ከትላንትናው ትውልድ ሸክም የከበደ፤ የትግሉም ጎዳና
የተወሳሰበ ነው ብንል ከሐቅ የራቅን አይመስለንም። ለዚህም ዋነኛው ማጠየቂያ የሀገር ህልውና ጥያቄ ውስጥ የገባበት የትግል
ምዕራፍ ውስጥ መገኘቱ ነው። ይህ የዛሬው ትውልድ ኢትዮጵያን ከአደጋ ለማዳን ህልውናዋንም ለማስጠበቅ ከአድዋው ጊዜ
የበለጠ ኅብረትና ጀግንነትን አጣምሮ በዘረኞች/በጎጠኞችና በተባባሪዎቻቸው የተቃጣውን አደጋ መከላከልና ታሪኩንና
ማንነቱን ማስከበር ግድ ይለዋል።
በወያኔ እየተራገበ ያለው የጎጠኝነት እሳት የሚጠፋው የአንድነት መሠረቱ ምን መሆን እንዳለበት ታውቆ ይህንን ዕውን
ለማድረግ የሚያስችል አገራዊ የሆነ ትግል መካሄድ ሲቻል ብቻ ነው። ለዚህም ነው ወጣቱ ትውልድ እንዳለፈው ሁሉ
ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ የብሔረተኞች/የዘረኞች ማርከሻ በሆነው አገራዊ ትግል ውሰጥ የግንባር ቀደምትነት ታሪካዊ ሚናውን
መጫወት አለበት የምንለው።
የዘመኑ ፖለቲከኞች ከሁለት ፅንፍ ሆነው እየጎተቱ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ሊያጠፏት የሚከጅሏት ኢትዮጵያ፤ አንድነቷ
ሊጠበቅና ሊጠናከር ህልውናዋ ሊከበር የሚችለው የሕዝብ የጋራ አንድነት ከተመሠረተ ብቻ መሆኑ መታመን ይኖርበታል።
ከጠባቦችና ከግንጠላ አራማጆች ጎራ እንደሚስተጋባው አጉል ታሪክ፤ አገራችን ኢትዮጵያ እንዲያው በድንገት የተከሰተች
ሳትሆን የዘመናት የትውልድ የመስዋዕትነት ትግል ውጤት ናት። ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ ለማድረግ የብዙ ሚሊዮንና የአያሌ
ትውልድ ህይወት ተገብሮበታል። ይነስም ይብዛ፤ ይጉላም ይደብዝዝ ሁሉም ሕዝብ ለዚች አገር ግንባታ አስተዋጽኦ
አደርጓል። ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ታሪክ ለአገር ግንባታ ታሪካቸው፤ ለዘመናት ለቆየው አንድነታቸውና ውህደታቸው፤
እንዲሁም ለማንነታቸው መገለጫ ነው። ኢትዮጵያውያን በፍልሰት አማካኝነት የፈጠሩት መስተጋብር ደግሞ መወሳት ያለበት
አብይ ክስተት ነው። በተለያዩ ወቅቶች ዜጎች ከሰሜን ወደ ደቡብ ፤ ከደቡቡ ወደሰሜን ፤ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ፣
በመዘዋወር ተቀላቅለዋል፤ ተወራርሰዋል። ዛሬ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት ከማይሹ ጠባቦች እየሰማነው እንዳለው የተዛባ
የፈጠራ ታሪክ ፤ ኢትዮጵያውያን በረዥም ዘመን የጋራ ታሪካቸው ውስጥ አንዱ ሁሌ አጥቂ ሌላው ሁሌ ተጠቂ፤ አንዱ ሁሌ
ጉልበታማ፤ ...ወዘተ በሆነ ግንኙነት ውስጥ የኖሩ ሳይሆን፤ ማጥቃቱንም ሆነ መጠቃቱንም በርካታዎች ተጋርተውታል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በረዥም ታሪኩ አብሮ ከመኖሩ የተነሳ የጎሳ፣ የሃይማኖት፣ የክልል፣ ...ወዘተ መለያቸው የጠፋባቸው
ቁጥራቸው እጀግ ብዙ ነው። በጋብቻ ብቻ የተለየዩ ጎሳዎች አባል የሆኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን እንኳን ትተን በሕዝብ
ደረጃ ጠቅላላ ውህደት ያደረጉት በጣም ከፍተኛ መሆናቸውን ታሪክ የመዘገበው ሐቅ ነው።
የቋንቋና የባህል ጉራማይሌነት የሰፈነበትን ጨምረን ከቆጠርነው ኢትዮጵያዊያን ጥልቅ የሆነ መቀላቀል መፍጠራቸውን
እንረዳለን። አንዱ የሌላውን ይዞታ በመውረስ ፤ ተቻችሎ በጋራ ይዞታ ሥር በመኖር ወይም በመዋሃድ ሀገሪቱ በአብዛኛው
የሁሉም ሕዝብ የወል መንደር ሆናለች። ይህንን የሕዝብ የውህደት ታሪካችንን በመካድና አዲስ የፈጠራ ታሪክ በመፈብረክ
የዛሬው ወጣት ትውልድ አገሩን ፈፅሞ እንዳያውቅና እንዳይወድ የሥነ- ልቦና ዘመቻቸውን ከፍተውበታል። እኛ
ኢትዮጵያዊያን ከሚለያዩን ይልቅ የሚያስተሳስሩን ድርና ማጎች ይልቃሉ። ይህንን በጽኑ የሚያምነውን በተለይም በኢሕአፓ
ዙሪያ የተሰባሰበውን ትውልድ ይፈሩታል። ይጠሉታል፤ አልፎም በትምክህተኝነት ይከሱታል። "ለታላቋ ኢትዮጵያ" የሚታገል
የሚል ሥያሜም ሰጥተውታል። በዕኩልነት ላይ ለተመሠረተ አንድነት በጋራ እንታገል ሲባሉም ጨርሶ ጥያቄው እንዲነሳ
አይሹም። በመቀራረብ በመጋባትና በመዋለድ ኢትዮጵያዊነቱን በጋራ አረጋግጦ መገኘቱንም በመካድ፤ አዲስ የፈጠራ ታሪክ
እያቀነቀኑ የተበረዘ ታሪክ ለትውልድ ለማውረስ የሚደረገው ጥረት ጎጂ ብቻ ሳይሆን በትውልድ የሚያስጠይቅ መሆኑንም
መረዳት ያስፍልጋል።
ሕዝብ፣ ባዕድ ነን፤ ቅኝ ተገዥ ነን፤ ወይንም ኢትዮጵያዊነታችንን በአዲስ መንገድ እንደራደር በሚል በደሙ የጻፈውን የራሱን
ታሪክ ሲበርዝና ሲክድ አልተደመጠም - ኢትዮጵያዊነታችን በማንም ሊካድ አይችልም በማለት ድምጹን ሲያሰማ ኖረ እንጂ !
በዚህ ዕውነታ ላይ በመመሥረት ጎጠኝነትን በማስወገድ የሕዝብ ዕኩልነትንና አንድነትን በዴሞክራሲ አረጋግጦ፤ የሀገር
አንድነትን ማስጠበቅ ሲገባ፤ በፀረ- አንድነት ዛር በመተብተብ ጥላቻን ቀፍቅፈው መገነጣጠልን በማራገብ ጎዳና እየሰመጡ
ያሉት ቡድኖች ለአንድነትና ለሕብረት ደንቃራ ናቸውና ለዘላለም በታሪክ የሚወቀሱ፣ የሚወገዙ ይሆናሉ።
ኢትዮጵያውያን ሙሉ ነፃነት ፍለጋ ከባእዳን ብቻ ሳይሆን የራሳቸውን ገዥዎች በጋራ ሆነው በጽኑ ታግለዋል። በተወሰኑ
የሀገሪቱ ከፍሎች ተጥሎ የነበረውን የገባር ሥርዓት ለመለወጥ በተደረገው ትንቅንቅ ሁሉም የሕዝብ ክፍል በትግሉ ተሳትፏል።
በዛን ዘመን የተከናወነው የገበሬው፣ የላብ አደሩ፣ የጭቁን ወታደሩ፣ የሴቱ ፣ የልዩ ልዩ ሃይማኖት ተከታዩ፣ የምሁራኑና
የተማሪዎች አመፅ ክልላዊ ሥርጭትና የአማጽያን የጎሳ ስብጥር ይህንን ሐቅ ቁልጭ አደርጎ ያሳየናል። ባጭሩ በ1966ቱ ሕዝባዊ
አመፅም ሆነ በኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ የሕዝብ ወገኖች ዘር፣ ሃይማኖትና ፆታ ሳይገድባቸው እጅ ለጅ ተያይዘው
በማመጽ ነበር ሥርዓቱን ያስወገዱት።
ዛሬም ወጣቱ፣ እናት አገሩ ካለችበት ማጥ እንድትላቀቅ በአንድነት ኃላፊነቱን መወጣት ያለበት መሆኑ ሁኔታው ግድ ይላል።
ይህንን አገራዊ ግዳጅ ወጣቱ በግምባር ቀደምትነት እንዲወጣ ለማስቻል ፤ ያለመታከት ደረጃ በደረጃ ማደራጀት፤ አገራዊና
ሕዝባዊ ዓላማዎች/መተክሎች ፖሊሲዎችና አቋሞችን ማስረዳትና ማስጨበጥ፤ የትግል ታክቲክና እስትራቴጂን ቀይሶ ወጣቱን
ማታገል ያስፈልጋል ብሎ ኢሕአፓ ዛሬም እንደትናንትናው በጽኑ ያምናል። ተተኪው ወጣት በኢትዮጵያዊነት ሥነ-ምግባር
የታነጸና ያለፉትን ቆራጥ ታጋይ ጀግኖች ገድል የሚያከበር ፤ ለአገርና ለወገን አለኝታና መከታ ከመሆን አልፎ በራሱ ላይ
የሚተማመን ትውልድ ማድረግ ይቻላል ብሎም ያምናል።
እነሆ ዛሬ በከፋፋዩና ዘረኛው የወያኔ ቡድን የጭቆና፣ የብዝበዛ፣ የአድሎና አግላይ አገዛዝ የተንገፈገፈውና የተንገሸገሸው
ሕዝብ የተጠራቀመ ብሶቱንና በደሉን በመግለፅ ተቃውሞውን በማሰማትና የወያኔን አገዛዝ ለማስወገድ ሕዝባዊ አመጽ
እያካሄደ የሚገኝበት ምዕራፍ ላይ እንገኛለን። በመላው አገሪቱ ከፍሎች በተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ዓመጽ የተደናገጠው አገዛዝ
የሕዝቡን አመፅ ለመደምሰስ አፋኝ ወታደራዊ አገዛዝ አስፍኖ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ እየረገጠና እያሸበረ ይገኛል። በመላው
ኢትዮጵያ ከትናንትናው የወታደራዊ ደርግ ቀይ-ሽበር ያልተናነስ ግድያ፣ አፈናና ስየል በወጣቱ ላይ እየፈፀመ ነው። በወያኔ
ከፍተኛ በደል የደረሰበት ወጣት ብሶትና ቁጣው ከልክ ሲያልፍ ማናቸውንም ዓይነት ግብታዊ እርምጃዎች ከመውሰድ
የማይቆጠብ መሆኑን መገመት ይችላል።
ወቅቱ የወጣቱን ግብታዊ ትግልና እርምጃ በስልት ማቀናጀትና ማደራጀት ግድ የሚልበት ወቅት ነው። በደልና ጭቆና ከልክ
ሲያልፍ በወጣቱ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን የሰነልቦና ጫናና የሚያስከትለውንም ተጽእኖ የዚያ አይበገሬ ትውልድ ታሪክ
በተገባር አረጋግጦልናል። ያኔ፣ በተለይም ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ፣ ኢሕአፓ ወጣቱን በኢሕአወሊ ውሰጥ በስፋት አደራጅቶ
የሥነልቦና መሠረት ጥሎ፤ በሥነምግባር አንፆ ታካቲክና እስትራቴጅ ነድፎ የዕለት ተዕለት አመራር እየሰጠ በስፋት በመላው
አገሪቱ ክፍሎች በህቡዕ አደራጅቶ እንዲታገል አድርጓል። ሞትን፣ ሰቆቃን፣ ግርፋትን፣ ረሃብን፣ እርዛትንና ድካምን የማይፈራ፤
ለዓላማና ለቃሉ የፀና ፤ በአጠቃላይ የጀግንነት ሥነ- ምግባር የተዋሀደው ወጣት ትውልድን ማፍራት ትችሏል። ይህም ሊሆን
የቻለው በድርጅታዊ ጥረትና በአደራጆች ጥንካሬ መሆኑ ጥርጥር የለውም። ዛሬም ይህ ዕውን የማይሆንበት ምከንያት
አይኖርም። ይህ በአሁኑ ትውልድ ላይ የምንዘራው የአንድነት፣ የሀገር ፍቅር፣ የነፃነት የቆራጥነትና የፅናት መንፈስ እንዳለፈው
ትውልድ ሁሉ በዛሬዎቹ በርካታ ወጣቶች ልቦና ውስጥ እየሰረጸም ነውና አገራዊ ትግሉን በስፋት እንዲቀላቀሉ አስተዋፅኦ
ይኖረዋል ብለን እናምናለን።
ወጣቱ የወያኔን የዘር ፖለቲካ በአደባባይ እርቃኑን ማስቀረቱ የሚያረጋግጠው “የኦሮሞው ደም ደሜ ነው!”፡ “የአማራው ደም
ደሜ ነው!”፡ “የኮንሶውም ደም ደሜ ነው!” ፡ “ደሜ ኢትዮጵያዊ ነው !” በሚል በቁጣ ስሜቱን መግለጹና አገዛዙን ማውገዙ
ነው። ይህ ሊከበር ሊወደስ አርዓያ ሊሆን የሚችል ቆራጥ እርምጃ ነው። ኢትዮጵያዊው ወጣት ዛሬም መሠረታዊ ለውጥ
ፈላጊ ፤ የሁሉም የዜጎች መብት አስክባሪ ነኝ ብሎ ከፋፋይ ኃይሎችን ሊያሳፍር ይገባል። ትናንት የኢትዮጵያ ወጣቶች
ለሀገራቸው ሉዓላዊነት ለሕዝባቸው ዕኩልነት፤ ለፍትህና ለዴሞክራሲ ያደረጉት ትግልና የከፈሉት መስዋዕትነት ለዛሬው
ወጣት ትውልድ መልካም ምሳሌ ሆኖ ሊጠቀስና በአጽንኦት የትግል ተመክሮም ሊቀሰምበት ይገባል የምንለውም ለዚህ ነው።
የተከፈለውን መስዋዕትነት ለማርከስና ትግሉን ለመበረዝ፤ መልካቸውንና ስማቸውን እየቀያየሩ ፤ እንደእስስት በፖለቲካው
መድረክ የሚርመሰመሱትንና የሚቆምሩትን ደንቃራ የፖለቲካ እንክርዳዶች ሁሉ ወጣቱ ትውልድ ሊያጋልጣቸውና ወጊዱ
ሊላቸው ይገባል።
ወያኔ ከኢትዮጵያውያን ወጣቶች የሀገር ፍቅር ስሜትና የነፃነት ቀናኢነት ጋር መተዋወቅ ተስኖታል። ሰላም ፈላጊነቱን እንደ
ፍርሃት፤ ሆደ ሰፊነቱን እንደ ደካማነት ፤ ትዕግሥቱን እንደሞኝነት ቆጥሮታል። ወጣቱ ትውልድ ኢትዮጵያን አትንኩ ፤ ሕዝብን
በጎጥ አትከፋፍሉ፤ አገርን ለባዕዳን አትሽጡ፤ ክብሯን አታስደፍሩ በማለቱ እንደ ግራዚያኑ ዘመን አዋጅ ታውጆበታል ጦር
ተሰብቆበታል። ትናንት የነበረው ጠላታችን “ያለምንም ደም፣… ” እያለ መላውን አገር በደም እንደለወሰው ዛሬ የተተካው
ወያኔ ደግሞ ”ሰላም ዴሞክራሲና ልማታዊ መንግሥት” እያለ ፋሽዝምን ዳግም በአገራችን ለማስፍን እየተቅነዘነዘ ይገኛል።
ይሁን እንጅ የቀድሞ ትንታግ ወጣቶቹን ፈለግ ተከትሎ የሕዝባዊ ትግሉ ችቦ ተለኩሷል። ያለፈው ወጣት ትውልድ ቅርስ
የጉራጌ፣ የአደሬ፣ የአማራ፣ የትግሬ፣ የኦሮሞ፣ የአፋር፣ የከንባታ፣ የሀዲያ፣ የቅማንት፣ የአገው፣ የኩናማ፣ የሽናሻ፣ ... ወዘተን
ኢትዮጵያዊ ወጣት የዓላማ ጽናትንና የትግል ወኔን አስርክቧል። ዛሬም እንደትናንትናው ኢትዮጵያዊ ወኔ የተጎናፀፉ የአገር
ተረካቢ ቆራጥና የዓላማ ፅናትን የተላበሱ ወጣቶች፤ ያልተገባደደውን ሕዝባዊ ትግል የማስቀጠል ታሪካዊ አደራ እንዳለባቸው
ኢሕአፓ በጽኑ ያምናል። ለዚህም የበለጠ መጠናከርና የዋናው ዓላማ ዕውን መሆን የበኩሉን አስተዋፃኦ ያደርጋል።
ኢትዮጵያን እያፈረሰ፤ ሕዝብን እየበደለና እየረገጥ የሚገዛውን ዘረኛውንና ከፋፋዩን የወያኔ አገዛዝ በጽኑ መታገልና ሳይታክቱ
ማጋለጥ፤ በሕዝብ መካከል መቃቃርና ጥላቻ፤ እንዲሰፍን ሳይታከቱ የሚቆሰቁስትን፤ የኢትዮጵያዊነት ጠንቅ የሆኑትን አረሞች
ሁሉ እየመነገሉ ፀሐይ ላይ ማስጣት፤ ለመጭው ትውልድ የማይለጋ የዛሬው ትውልድ ግዴታና ኃላፊነት ነው።
ወርሃ ታኅሣሥ የቀድሞዎቹ ወጣቶች፣ የዚህ የዚያ ጎሣ፤ የዚህ የዚያ ሃይማኖት፣ ...ወዘተ ሳይሉ ለሀገርና ለሕዝብ ውድ
ህይወታቸውን በመስዋዕትነት የሰጡበት ወቅት በመሆኑ ሊታወስና ሊዘከር ይገባል።
በኢትዮጵያዊነት የተጣመረ የወጣቶች ትግል ለድል ዋስትና ነው!
የተባበረ የሕዝብ ክንድ ጠንካራ ነው!
እናቸንፋለን!!!
No comments:
Post a Comment