BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

Saturday, 28 January 2017

" ሀገርንና ሕዝብን ባለመክዳታችን ፤ አብሮን የሚኖረው ኅሊናችን ሲያመስግነን ይኖራል ! " የኢሕአፓ ታጋዮች

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ታጋዮች፤ ካነገቧቸው መሠረታዊ መርሆች አንዱ ፤ለሕዝብና ለሀገር ታማኝነት ነው። ይኽ ዕምነታቸው ዘመን ተሻጋሪ ፤ ትውልድ አስከባሪ፤ ታሪክ መስካሪ ሆኖ አብሯቸው ዘልቋል ። በዘለቄታ ቀጥለው እንዲዘልቁ ያስቻላቸውም ይኽው የማይበገር ፅኑ ዕምነታቸው ነው። ለሕዝብና ለሀገር ጠንካራ ታማኝነታቸው ፤ በቦታ ፤ በጊዜና ፤ በሁኔታ የሚለወጥ የሚበረዝና የሚከልስ አለመሆኑን ያውቁታል ። ታማኝነት የሚጀመረው ከራስ በመሆኑ፤ በራስ ዕምነት መተማመን፤ የአላማና የመርኅ ታማኝነትን ይወልዳል፤ ዕምነትን ያጠነክራል፤ አዕማደ-ትግል ሆኖ ፀንቶ ያፀናል ። ያበረታል -ያበረታታል ። ብርቱ ዕምነት፤ ፅኑ ዓላማ ካለ ደግሞ፤ ማነኛውንም የማሳናክያ ዓለት ሁሉ ፤ የመረማመጃ ድንጋይ አድርጎ ረግጦ ያልፋል ። የኢሕአፓ ታጋዮች፤ ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ፤ የሚያስፈራቸው ነገር ቢኖር፤ ራሱ ፍርሃት ብቻ ነው። በትግላቸው ሂደት ለፍርሃት ስከንዶች አይኖራቸውም ። ይኽን ባኅርይ ፤ ለአለፉት ግማሽ ምዕተ ዓመት በሚገባ አስመዝግበዋል ፡፡
የኢትዮጵያ ባላንጣዎችም ቢሆኑ ይኽንን ሀቅ ሊክዱት አልቻሉም ። በዚህ አይበገሬ ባኅርይ ምክንያት፤ የሀገሪቱ ጠላቶች፤ ኢሕአፓን አምርረው ይጠሉታል ። ይፈሩታል። የርግሙታል። ጠልተው ፤ ያስጠሉታል ። እርሱን "ካላጠፉ" ደግሞ፤ ዕንቅልፍ አይተኙም ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ንፅጹህ ደም፤ በምንም ካሣ የማይደርቅ በመሆኑ፤ ይዘገያል እንጅ፤ አንድ ቀን ተፋራጅ እንደሚያገኝ መጠራጠር አይቻልም። ወገኑ -ዘመዱ የሞተበት ሁሉ፤ ባለደሙን ለይቶ ያውቀዋል ። እስካሁን ሀገሪቱን የከዷትና አሁንም እየከዷት ያሉ ሰዎች፤ ከክህደት ላይ ክኅድት እያጨመሩ ከመሄድ ሊታቀቡ አልቻሉም ። ይኽም ሊሆን የቻለው ፤ኢትዮጵያ ተቆርቋሪ ጀግና አልባ በመሆኗ ነው።ጀግና ያለቀበት ሀገር ደግሞ ፤ይናቃል ። የተናቀ ሀገር በበኩሉ፤ በአህያ የወረራል። የአህያ ባል ከጅብ ስለማያስጥል፤ ከፍርሃቱ የተነሳ፤ሀገሪቱን ለወራሪ ቡድን አስላፎ በመስጠት፤ ሸሽቶ ያመልጣል። ሀገሪቱም ፤ በግድ- የለሾቹ ወራሪዎች ትበዘበዛለች። 2 ይክ ክስተት የሀገራችን አሳፋሪ ታሪክ ሆኗል ። ዜጎቿም የደም ዕምባ እያለቀሱ ይኖራሉ ። መኖር አይበለውና ! የኢሕአፓ ልጆች፤ ደቂቀ ኢትዮጵያ በመሆናቸው፤ በተማኝነታቸው ፀንተው የሀገራቸውን ሕዝብ ዕምባ ለማድረቅ ፤ወደ ኋላ አይሉም ። አሳፋሪ ታሪክ የሰሩ፤ አፍረው ሲቀሩ ፤ ኢሕአፓ ግን በአክሪ ታሪኩ እየታገለ፤ የኢትዮጵያን ታሪክ እያስከበረ መታገሉን ይቀጥላል ። በአሁን ወቅት ፤ ሰማይ ምድሩ የተደፋበት በመሆኑ ይመስላል፤ ሁሉም ቢሰበሰብ፤ ሀገሩን ለማዳን አልቻለም። ተስማምቶ በጋራ ሊቆም አልተሳካለትም። ለመስማማት መስማማቱ ቀርቶ፤ ላለመስማማት እንኳ ሊስማማ አልቻለም ። ለኢትዮጵያ እቆረቆራለሁ የሚለው ሁሉ፤ መቆርቆሩን የሚገልጽበት የጋራ መግባቢያ ቋንቋ ቸግሮት፤ እንደ ባቢሎን ግምብ ሰሪዎች፤ እርስ በእርሱ የነታረካል ። በሆነ ባልሆነው ይወቃቀሳል ። በረባ ባልረባው ይካሰሳል ። ዳኛና ታዛቢ፤ እማኝና ዋስ ፤ ጠበቃና ሽማግሌ በሌለበት ሀገር፤ ቁም ነገር መስራት ቀርቶ፤ ማንነትን ለማወቅ እንኳ ያስቸግራል ። ጥረት ለማድረግ ቢሞክርም፤ ሙከራው ሁሉ፤ የጨረባ ተስካር ከማውጣት ያለፈ ፋይዳ አያስገኝም ። ይኽ ሊሆን የቻለው፤ የዕወቀት ማጣት ሳይሆን፤ የባኅርይ ጉድለት ፤ የሀገር ፍቅር ዕጦት፤ የሥልጣን ጥማት፤ የራስ መውደድ ልክፍትና ለተተኪው ትውልድ መፃኢ እድል ካለመሰብ የተነሳ እንደሆነ ፤ ብዙ ታዛቢዎች ይስማሙበታል ። ሀገሪቱ የተማረ የሰው ኃይል የላትም እንዳይባል ፤ ምናልባት በአፍሪካ አህጉር ደረጃ ሲነፃፀር፤ "ምሉዕ በኩለሄ " ባይባልም እንኳ ፤ ዘርፈ-ብዙ ችሎታን ያካበተ፤ የተማረ ኃይል እንዳላት ተደጋግሞ የሚነገር ሆኗል ። ትምህርትና ዕውቀት ተባብረው ፍቅርንና ስምነትን ካላስገኙ፤ ታዲያ የመማር ጥቅሙ እምኑ ላይ ነው ? ብለው የሚጠይቁ ዜጎች ብዙ ናቸው ። መልሱን ግን እስካሁን አላገኙትም ። ቅጥ-አምባሩ ጠፍቶባቸዋል ። ብቃት ያለው መሪ አውጥተው፤ መሪያቸውን ተከትለው ፤ በቅደም- ተከትል አካሄድ መራመድ አቅቷቸው፤ጎን -ለጎን በጎሪጥ እየተያዩ ያዘግማሉ። ይኽ ሊሆን የቻለው፤ እርስ በእርስ መተማመን ቢጠፋ ነው ቢባል፤ ከዕውነት የራቀ አይሆንም ። " የጨነቀው ሙቅ አነቀው " ሆኖ ነው ምሰል፤የራስን ሀገር ችግር፤ ሌሎች ይፈቱታል ተብሎ ፤ በዕርጎ ባኅር የሚዋኙ ክፍሎች እንዳሉ ይደመጣል ። ቅድሚያውና ትኩረቱ በራስ ሀገር ችግር ላይ ማድረግ እየተሳነ፤ ስለ ባኅር ማዶ ሀገሮች የምርጫ ውድድርና ስለ መሪዎቻቸው መምጣትና መሄድ ላይ ከፍተኛ ውይይት ይደረጋል ። ከሥልጣን የወረደው መሪ፤ የወያኔ ደጋፊ ስለነበር፤ ኢትዮጵያን በድሎ እኛንም አሳዝኖናል ። " አዲሱ ተሿሚው ፕሬዝደንት ግን ምናልባት ሀገራችንን አስመልክቶ የተሻለ የፖሊሲ ለውጥ ሊያሳይ ይችላል " እየተባለ የኅልምዣት ማስተናገድ ተጀምሯል ። " ኦባማና ትራምፕ ሁሉም አንድ ናቸው ፤ ምን አለያያቸው ? ባገራቸው ጥቅም ወይ ፍንክች ባይ ናቸው፤ ስለሌላው ችግር ግድም የሌላቸው ። " 3 የሚለውን የዩናትድ ስቴትስ ብሄራዊ / መሠረታዊ ጥቅም አስጠባቂ ፖሊሲ ካለመረዳት የመጣ የዋኅነት መሆኑ መገንዘብ በተገባ ነበር ፡፡ ይኽ የዋህነት " ከባልሽ ባሌ ይበልጣል፤ ሽሮ አበድሪንኝ ። " የሚለውን ተረት ከማስታወስ የለፈ እርባና አያመጣም ። ይኽ አዲስ የገባው የፈረንጆች ዓመት፤ ለሀገራችን ሊያመጣ የሚችለው የተለይ ነገር አይኖርም ። የችግሩ ፈጣሪዎችም ሆነ፤ የመፍተሄው ፈላጊዎች እኛው እራሳችንን መሆናችንን ተረድተን ፤አዳዲስ የመፍተሄ ኃስቦችን ማፍለቅ ካልቻልን፤ በየዓመቱ በውሃ ቅዳ-ውሃ መልስ አዙሪት እየተሽከረከን የዓለም መሳቂያ መሳለቂያ ልንሆን አይገባንም ። ከእንግዲህስ በቃ ! ብለን መነሳት አለብን ። " ያልተገላበጠ፤ ያርራል፤ " እንዲሉ፤ እያረርን ከስለን እንዳንቀር መፍተሄውን ሳይመሽ መፈልግ ይኖርብናል ። ወያኔዎች ቁመው አይጠብቁም ። " "ዉሾቹ ይጮሃሉ፤ ግመሉችም ይራመዳሉ " እያሉ፤ ምፀት በተመላበት ትዕቢት ተወጥረዋል ። ይኽን ትዕቢታቸውን ማስተንፈስ አለብን ! የመኖር ትርጉም የማይታይበት ባዶነትን ታቅፈን መኖሩ ሊያከትም ይገበዋል ። ለሚሟገቱለት ሀቅ ፤ ውድ ዋጋ መክፍሉ የማይቀር ዕዳ መሆኑን እያንዳንዳቸን ልንገነዘበው ይገባናል ። ሀቅን በድፍረት የመናገር ባኅል፤ ለታሪኩ ባለቤት ለሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ መግለፅ የተማኝነታችን ዐብነት መሆኑን መረሳት የለብንም ። ወደድንም ጠላን ፤ ሀገራችን ዛሬ ሁለት ተደራራቢ ፈታኝ የሆኑ ሁኔታዎች (ተግዳሮት) እፊቷ ላይ ተደቅነውባታል ። የማንነትና የኅልውና ጥያቄ ! ሁለቱም የተያያዙ ስለሆኑ ፤ ምናልባት ፤ አንዱን አስቀድሞ ሌላውን በይደር ለማቆየት የሚያስቸግር መስሎ ሊታይ ይችላል ። ያ እንዳለ ሆኖ ግን፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ጠላቶቹ እንደሚወሽክቱት የማንነት ጥያቄ /ችግር የለበትም። ኖሮትም አይውቅም ። ምክንያቱም እንደ ሕዝብ / እንደ ዜጋ፤ ለአያሌ ዓመታት በነፃነት፤ አብሮ ተባብሮ የኖረ መሆኑን ፤ የማይሞት ታሪኩ ይመሰክርለታልና ! ይኽ ከታወቀ፤ ዛሬ አፍጥጦ አግጥጦ የመጣበት የህልውና ጉዳይ ነው ። የመኖር /ያለመኖር ጉዳይ ሆኗል ። በአብሮነት መኖር ፤ ወይም ተግነጣጥሎ መበታተን ! እንደ ዘመነ መስፍንት ፤ በጎጥ በክልሉ በንዑሳን የጎሣ አባዎራዎች መገዛት ! ይኽ አደጋ በኢትዮጵያ ሰማይ ካንዣበበ ቆይቷል። ሀገሪቷን በአደጋ ለማጥለቅለቅ አስፈላጊ ዝግጅቶቹ ሁሉ ተጥናቅቀው፤ " ያየ ያላየ ያግባሽ " የሚለውን ዐዋጅ ሁሉም ተጠንቅቆ ይጠባበቃል ። የመጀመሪያ ዐዋጅ ተግባራዊ የሚሆነው ክልል ቁጥር 1/ አንድ ተብሎ በተሰየመው በትግራይ ክልል አይሆንም ማለት አይቻልም ። የባኅር ምድር የሆነችው የኢትዮጵያ አካል ፤ በፈር - ቀዳጅነት ሄዳለች ! ወገኖቻችንም አብረው ሄደዋል ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን፤ " ንዑናይ ነጆ፤ ሕዝቢ መረብ - ምላሽ፤ ደቅ ባኅር- ነጋሽ " እናንት፤ በመረብ ምላሽ ያለችሁት ሕዝቦች ፤ እናንት የበኅር-ነጋሽ ልጆች፤ ወደ እኛ ኑልን " እያለ በተስፋ ይጠራቸዋል ። ይዋል- ይደር እንጅ፤ ጥሪው ሰሚ ጆሮ ማግኘቱ አይቀርም ተብሎ ተስፋ ይደረጋል ። ይኽ ተስፋ በኢትዮጵያ ሕዝብ አዕምሮና ልብ የተመዘገበ ቢሆንም፤ አሁን የቀሩት የሀገሪቱ ክፍሎች ከወያኔ የብተና አደጋ ያመልጣሉ ብሎ መዝናጋት የሚያዋጣ አይሆንም ፡፡ የወያኔ አንቀጽ 39 በተግባር የሚተረጎምበት ሃቅ ፤ ጊዜውንና አመች ሁኔታውን እየጠበቀ መሆኑን ፤ አለመከታተል አያዋጣም ። ሊሆን አይችልም ብሎ መዘናጋት፤ የትላንቱን ጥፋት እና ጉዳት መልሶ እንዲደገም መፍቀድ ይሆናል ። 4 ይኽን አስተውህሎ፤በግንዛቤ ማሰላሰል እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በእኛ ዕምነት ግን ፤ ጠላቶቿ ሊያጠፏት ቢመኙም፤ የሀገራችን ኅልውና ግን አይደበዝዝም፤ አይጠወልግም፤ አይቀጭጭምም ! የኢትዮጵያ ሀገራዊ ኅልውና፤ ዘመን ባለፈ ዘመን በተተካ ቁጥር፤ እያፈካ የሚሄድ አበባ ነው። አበባው እንዳይበቅል፤ የበቀለውም ከስሞ እንዲቀር ግን ፤ የኢትዮጵያ ጠላቶች ምኞት መሆኑን በሚገባ እንረዳለን ። ለዚህም ነው፤ ስለ ኢትዮጵያ ሀገራዊ ነፃነትና ስለ ዜጎቿም አንድነት ፤ የለመታከት የምንጮኸው ! ይኽም ሊሆን የቻለው ፤ የትግላችን አልፋ-ዖሜጋ በመሆኑ ነው። በዚኽም መሠረታዊ አቋማችን ምክንያት ፤ ከገንጣይ -አስገንጣዮችና የሀገራችንን አንድነት ከማይፈልጉ ክፍሎች ጥርስ ወስጥ አንድነገባ ያደረገን ! በብዙ አንገቶች ላይ፤ አንድ ጭንቅላት የተሸከመ ሰው፤ ወሳኝ ለመሆን እንዳማይችል ሁሉ ፤ በብዙ አንገቶች ላይ የሚሽከረክር የተቃዋሚው ጎራ ፤ ኢትዮጵያን ከአንዥበበባት አደጋ ሊያድነት ከሚችል ውሳኔ ላይ መድረስ አልሆነለትም ። "የቅማል ስደት፤ ከራስ ወርዶ አንገት " ከሚል ፉተታ መዳን የምንችለው፤ ከችግር ለመሸሽ ብለን፤ ከሀገራችን መሰደዱን ስናቆም ብቻ ነው። በስደት ላይ ሆኖ የስደት መንግሥት ለማቋቋም መመኘት የሀገራችንን ስር የሰደደ ችግር ሊፈታልን አይችልም ። ባዕዳን፤ የሀገራችንን ችግር እንድንፈታ የተባበሩናል ብልን ተስፋ ማድረግ፤ " የሀብታም አሽቃባጭ የሽንብራ ቆሎ ያሻል " ከመባል አያድንም ። በራስ መተማመን፤ በራስ ዕምነት መቆምና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ታማኝነትን መግለፅ ጊዜ የማይለውጠው ዕምነታችን ሆኖ ይኖራል ።በዚህ ዕምነታችን ደስተኞች ነን ። ነፃነትን የወርሰው ትውልድ አካል በመሆናችን፤ ባርነትን ለተተኪው ትውልድ ለማውረስ አንፈቅድም ። ነፃነቱን ወርሶ፤ ነፃነቱን እያስከበረ እንዲኖር እንፈልጋለን ። ወጣቱ ትውልድም ይኽንን ያውቃል ። ይቀበላል ! ይኽንን ቃል ኪዳን ለመቀበል ተዘጋጅቷል ። በአፍላ ዕድሜው ምክንያት፤ አፍለኝነት እንዲያጠቅውም አንመኘም ። የወጣቱ ትግል፤ ውሉን ሳይስት የትግሉ ባቡር ሀዲድ አቅጣጫውን ሳይቀይር ፤ሳይሰናከል እንዲቀጥል የተቻለነን ያኽል እንደክማለን ። ሀገራችንም የማንም መጫወቻ ሆና አትቀርም ። የኢሕአፓ ታጋዮች፤ እንደ አብረሐም ቤት የሌላቸው፤ እንደ ሙሴ መቃብራቸው ያልታወቀላቸው፤ የቤተስብ ባይታዎሮች ፤ የዓለም ተንከራታቾች መሆናቸውን ያውቃሉ። በዚህ አይቆጩም። ነገር ግን፤ ፓርቲያቸው የወቀሳ ዶፍ እንጅ፤ የምስጋና ካፊያ ያልተቸረው በመሆኑ ቅር ይሰኛሉ። ይከፋሉ። ያም ሆኖ፤ የተመስጋኝ ሳይሆን፤ ያመስጋኝ ዕጥረት ያለባት ሀገር መሆኗን ስለምንረዳ አመስጋኝን አንጠብቅም ። ሀገራችንንና ሕዝባችንን ባለመክዳታችን፤ ባለመጎዳታችን ፤ አብሮን የሚኖረው ሕሊናችን እያመስግነን ስለሚኖር ግን ደስተኞች ነን ። ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኖራለች !

No comments:

Post a Comment