ቀን ፡ ግንቦት ፲፭ ቀን ፪ ሺህ ፮ ዓ.ም. (May 23, 2014)
ከ«ያ ትውልድ ተቋም» የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
የከበረ ሰላምታችንን በቅድሚያ አያቀረብን፤
May 23, 2014 (ግንቦት ፲፭ ቀን ፪ ሺህ ፮ ዓ.ም.) በሰሜን አሜሪካ
ዳንቨር ኮልራድ የአረመኔውን ከፍተኛ 15ቱ ቀይ ሽብር ተሳታፊ
ከፋለኝ ዓለሙን ጉዲይ የመጨረሻ ፍርድ ውሳኔ ለመስጠት የፍርድ ቤቱ
ችሎት ከጠዋቱ 9፡30 ተሰየመ። ጉዳዩን ሲከታተሉ የነበሩት ጠበቆችና
የሚመለከታቸው ተገኝተዋል። ከፋለኝ ዓለሙን ለመጀመሪያ ጊዜ
በዳንቨር ኮልራድ በመመልከት ወደ ፍርድ ይቀርብ ዘንድ ከፍተኛውን
ድርሻና ኃሊፊነት የተወጣው የዳንቨሩ ነዋሪ አቶ ክፍለ ከተማን ጨምሮ
በነሐሴ ፬ ቀን ፪ ሺህ ፭ ዓ.ም. በዳንቨር በተካሄደው የፍርድ ቤት ውሎ
በአካል በመገኘት በከፋለኝ ዓለሙ በከፍተኛ 15 እሥር ቤት በ1970/71
ዓ.ም. በጊዜው ወጣቶች፣ ሕፃናትና አዛውንቶች ላይ የፈጸመውን
አሰቃቂ ግርፋት፣ ግፍና ግድያ በመመስከር ተገኝተው የነበሩት ወ/ሮ
አበበች ደምሴ ከሳንሆዜ፣ አቶ ብርሃን ዳርጌ ከዋሽንግተን ዲሲ፣ ድር ሳሙኤል ከተማ
ከዳንቨር እና አቶ ነሲቡ ስብሐት ከቨርጂንያ ሲገኙ አቶ አሳየኸኝ ፈለቀ ከቦስተን በሥራ
ምክንያት አልተገኙም።
በፍርድ ሂደቱ የከፋለኝን ጉዳይ የያዙት ጠበቃ ከፋለኝ ዓለሙ የአሜሪካንን መንግስት
በማጭበርበር ባደረገው ማንነትን የማታለል ጉዳይ የ22 ዓመት እስራት እንደሚገባው ፍርድ
ቤቱን ጠየቁ። የፍርድ ቤቱ ዳኛ ጉዳዩን ከተለያየ አቅታጫ ካደመጡና ከተመለከቱ በኋላ
በዛሬው ዕለት በከፋለኝ ዓለሙ ላይ የ22 ዓመት እስራት ብያኔ ሰጥተዋል።
ነሐሴ ፲፰ ቀን ፪ ሺህ ፬ ዓ.ም. (August 24, 2012) ከፍያለኝ ዓለሙ በሰሜን አሜሪካ
ዳንቨር ኮልራድ የአሜሪካን ደህንነት ኃይልች ቁጥጥር ሥር በመዋል ወደ እስር ቤት
መግባቱ ይታወቃል። የከፋለኝ ዓለሙን ጉዳይ ሳትሰለቹ በመከታተል እዚህ ላደረሳችሁና
የመጨረሻውን ብይን ላሰጣችሁ የከፍተኛ 15 ወገኖችና የያ ትውልድ አባላት ምስጋናችን
ይድረሳችሁ። እናመሰግናለን። የያ ትውልድ አባላትና የቀይሽብር ቀጥተኛ ተጠቂ ወገኖችና
ቤተሰቦች በመላ እንኳን ደስ አላችሁ።
በአድራጎቱና በአረመኔነቱ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ይህ ግለሰብ፡ በትዕቢት ያፈሰሰው የንጹሃን
ወንድምና እህቶቻችን ደም፤ ዛሬ ከ36 ዓመት በኋላ ተፋራጅና ተሟጋች በማግኘት ከፍያለኝ
ዓለሙን በፍርድ በማቅረብ የመጨረሻውን ብይን እንዲያገኝ ተደርጓል። የያ ትውልድ
ሰማዕታትን ጨምሮ የከፍተኛ 15ቶቹ ብርዬ ሀ/ማርያም፣ ክፍሌ ቄስ፣ ታደሰ ቢፍቱ፣ ግዛው
ወረሳ፣ አፈሳ በቀለ፣ በዛ ገ/ሕይወት፣ አሸናፊ በቀለ፣ አሰለፈች፣ ሶፊያ አየለ፣ ዮሐንስ ስዩም፣
ዳንኤል አንጋጋው ወዘተ እና የበርካታ ወጣቶች ደም ምንጊዜም ቢሆን ተፋራጅ እንዳለው
እንረዳለን። የበርካታ ወጣቶችንና ጎልማሶችን ደም እንደውሃ አፍስሦ ምንም እንዳልሰሩ
አድፍጦ መቀመጥና ይባስ ብሎ ያንን ትውላድ ተጠያቂ ለማድረግ የሚደረገው ሩጫና ታሪክ
ብረዛ ተከላካይና ሀቁን አስረጂ ወገን እንዳለው ጥርጣሬ የሚገባን አይመስለንም። ጊዜው ምን
ቢርቅ ታሪካችን ተዳፍኖ እንደማይቀመጥና ለትውልድ እንደሚተላለፍ የምናደርገው ጥረት
ፍሬ እንደሚያሳይ በያ ትውልድ ስም እያደረግን ያለው እንቅስቃሴ ውጤት መስካሪ መሆኑን
«ያ ትውልድ ተቋም» ያምናል።
የከፍተኛ 15ን ቀይ ሽብር ተሳታፊ ከፍያለኝ ዓለሙ ያለበት ቦታ ከታወቀ ጀምሮ ጉዳዩን
በመከታተል ሙሉ ትብብርና ድጋፍ ላደረጋችሁ ሁሉ ልናመሰግን እንወድለን። በተለይ
ከፍያለኝ ዓለሙ የዛሬ 36 ዓመት የሰራውን ወንጀል የምታውቁትንና ያያችሁትን ለመመስከር
ምንም ሳታወላውሉ ፈቃደኛ በመሆን ለተባበራችሁ ዛሬ ከፍያለኝ ዓለሙ ማንነቱ እንዲታወቅ
ፍርድ ማለት ምን እንደሆነ ይመለከት ዘንድ ያበረከታችሁት አስተዋጽዎ ውጤት ነውና
በሰማዕታት ወንድምና እህቶቻችን ስም ከ«ያ ትውልድ ተቋም» ምስጋችን ይድረሳችሁ።
በከፍተኛ 15 ለምትገኙ በደርግ ያንድ ትውልድ መመተር ቀይ ሽብር ጥቃት ሰለባ ለሆናችሁ
ቤተሰቦችና ወገኖች በሙሉ የዛሬ 36 ዓመት በማንአህሎኝነት በየእሥር ቤቱና በየመንገዱ
የፈሰሰው የልጆቻችሁ ደም ሰሚ ሊያገኝ ችሏል። ጊዜው ምንም ቢርቅ ጉዳዩ ዛሬም
ያንገበግባልና ወንጀላቸውን ተሸክመው ማንነታቸውን ደብቀውና አድፍጠው ያለ መሰል
ከፋለኝ ዓለሙ ገዳዮች ምንጊዜም፣ ዛሬም ወደ ሕግ መቅረቡ ለሌሎች ትምህርት ሊሰጥ
ይገባዋል እንላለን። ጊዜ የሰጠውን ጉልበትና ኃይል ተጠቅሞ ያለአግባብ የሚፈስ የንጹሐን
ደም ሌላ ጊዜ የፍትህ ያለህ ብሎ ወደ ሕግ እንደሚያቀርበው ትምህርት ሊወሰድበት ይገባል።
ዛሬ ዓለም የወንጀለኞችና የገዳዮች ዋሻ አለመሆኗን በትንሹም ቢሆን ግንዛቤ እንድንወስድ
ይገባል እንላለን።
በ1969/70/71 ዎቹ የደርግ ቀይሽብር ተሳታፊዎች ጉዳይ የሁላችንም የያ ትውልድ አባላትና
ቤተሰቦች የጋራ ኃላፊነት ነው ብለን እናምናለን። በመሆኑም በየቦታው አድፍጠው
የተቀመጡትን በደም የተነከሩ ወንጀለኞች ቢያንስ በኅብረተሰቡ ሊታወቁ የሚገባቸው በመሆኑ
የጉዳዩ ባለቤት ሁላችንም ነንና፤ ድጋፍና ትብብራችን ለግለሰቦችና ለተወሰኑ አካላት ሳይሆን
ለሚነሳውና ለተነሳው ጉዳይ መሆኑን በማገናዘብ ድምጻችንን በጋራ እናሰማ እንላለን።
«ያ ትውልድ ተቋም» ከፋለኝ ዓለሙን ለፍርድ ለማቅረብ የሚደረገውን ሂደት ሙሉ ድጋፍ
በመስጠት እንደተባበረ ሁሉ በቀጣይነትም በየቦታው አድፍጠው የተቀመጡ የደርግ ቀይ
ሽብር ተሳታፊዎችን ከያሉበት በማውጣት ሕዝብ እንዲያውቃቸው ማድረግ ይጠበቅብናልና
እንተባበር እንላለን።
እናመሰግናለን።
“ያ ትውልድ” ተቋም
Email : yatewlid@yahoo.com, yatewlid@gmail.com, yatewlid@hotmail.com
web site : http://www.yatewlid.com , http://www.yatewlid.org
Facebook: yatewlid
No comments:
Post a Comment