ነዋሪነቴ በሰበታ ከተማ አስተዳደር ወለቴ 03 ቀበሌ ጎጥ አራት ነው፡፡ የጎጥ ሰብሳቢ ሆኜ ለሁለት ዓመት ሰርቻለሁ፡፡ የቀበሌው የምክር ቤት አባል እና የኦህዴድ ኢህአዴግ አባል ሆኜ አገልግያለሁ፡፡ ድርጅታዊ እና ማንኛውንም ከላይ የሚወርደውን የመንግሥት መመሪያና ደንብ በህገ መንግሥቱ መሰረት እንደ ዝቅተኛ አመራር ከድጋፍ ሰጪ አመራሮች በሚሰጠኝ መመሪያ እና ደንብ መሠረት በመፈጸም እና በማስፈፀም ሰርቻለሁ፡፡የህዝብን ጥቅም ለማስከበር ለአካባቢ ፀጥታ፣ ልማት እና የህዝብን አደረጃጀት በቀበሌው ውስጥ ከየትኛውም የጎጥ አመራሮች በበለጠ ስሰራ ቆይቻለሁ፡፡ በ23/07/06 ዓ.ም ለቀበሌው የፀጥታ ዘርፍ በጎጡ ውስጥ ባለው ከፍታ ቦታም መሬት እየተወረረ ነው በማለት ሪፖርት ባደርግም የሚሰማኝ አላገኘሁም፡፡ የሚሰማኝ በማጣቴ መሬት እየወረሩ የነበሩትን ‹‹እየተሰራ ያለውን አቁሙ!›› ስላቸው ‹‹አንተ ምንድነህ? ከአንተ የበላይ የሚገኙት ባለስልጣናት ናቸው ያዘዙን!›› በማለት ስራቸውን ቀጠሉበት፡፡
በማግስቱ ዓርብ ቀን 25/07/06 ዓ.ም ጧት 2፡00 ሰዓት አካባቢ ለቀበሌ 03 ሊቀመንበር ደውዬ ስለሁኔታው አስታውቄያለሁ፡፡ሊቀመንበሩም ለደንብ አስከባሪዎች ደውሉላቸው በማለት መልስ ሰጥተውናል፡፡ ይህም በእንዲህ እንዳለ አንድ ምንም የሥራ ዓይነት የሌለው ደላላና የግንባታ ፈቃድ ሌላቸው የመንግስትና የህዝብ ሀብት የሆነውን መሬት በመቸብቸብ ሀብት ያካበተ ግለሰብ ረቡዕ ማታ የደንብ አስከባሪዎች እየጠራ ገንዘብ ሲያፍስ እንደዋለ በዓይኔ አይቻለሁ፡፡ ይህ በሆነበት ማግሥት እርስ በእርሳቸው ጀርባ በመግጠም አራቱ ቤቶች ወደ ሰሜን፣ አራቱ ቶች ደግሞ ወደ ደቡብ፣ አራቱ ተዋቅረው አልቀው ቆርቆሮ ሊመቱ ሲል፣ አራቱ ደግሞ ገና ጉድጓድ ተቆፍረው እያሉ ተደረሰባቸው፡፡ ዓርብ ቀን በ25/07/06 ዓ.ም ከሰበታ ከተማ አስተዳደር የቀበሌያችን ደጋፊ ሰው አመራር የሆነውን ግለሰብ ደውዬ በግምቱ 5፡00 ሰዓት አካባቢ በህገ ወጥ መንገድ የተሰሩት ቤቶች አስፈርሻለሁ፡፡
ይህንን የመንግስትና የህዝብ ሀብት የሆነውን መሬት ከመሬት ወራሪዎች እጅ አስፈርሼ ስላስመለጥኩ የጥቅሙ ተካፋይ የቦታዎቹ ባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ እና ምንም ዓይነት የግንባታ ፈቃድ የሌላቸው ግለሰቦችና ባለስልጣናት ሥልጣናቸወን ተጠቅመው በደል አድርሰውብኛል፡፡ የመሬት ወረራ ያደረጉ ግለሰቦች በእኔ ላይ ተደራጅተው በደል እያደረሱብኝ ይገኛሉ፡፡ ዐቃቤ ሕግ፣ ፖሊስ እና አስተዳደር እና ፀጥታ ከፍተኛ አድማ፣ ተፅዕኖ፣ ማዕቀብ እና በኑሮዬ ላይ ችግር በመፍጠር ከቤቴ እንድወጣ አድርገውኛል፡፡ አሁን ተባባሪ ሆኛለሁ፡፡ ህገ ወጥ ቤትን በማስፈረሴና የመሬት መቀራመቱን ለማስቆም በጣርኩ በ8/8/06 ዓ.ም ስምንት ኦሮሚያ ልዩ ኃይል አባላት እንዲሁም 11 አባላት የያዘ የከተማዋ ፖሊሶችን በመያዝ እንዲሁም 10 የሚደርሱትን የቀበሌ 03 ደንብ አስከባሪዎችን ግደሉት ተብለው መኖሪያ ቤቴን ከበው ውለዋል፡፡ እነዚህ አካላት የታዘዙት ከከተማው የፖሊስ አዛዥ ሲሆን በእኔ ላይ የሚወሰደው እርምጃ ምክንያታዊ ባለመሆኑ ‹‹ለምን እንገድለዋለን?›› ብለው ከአዛዡ ጋር የተከራከሩ የፖሊስ አባላት እንዳሉም ሰምቻለሁ፡፡ ባለቤቴ ‹‹ባልሽን አምጭ!›› ተብላ ያለአግባብ የዋስትና መብትዋን በመንፈግ ያለምንም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ታስራ ትገኛለች፡፡ ‹‹የመንግስት ያለህ›› በማለት ለህዝብ እና ለሀገር ታማኝ ሆኜ መሥራቴ፣ ከኪራይ ሰብሳቢዎች ጋርለመተባበር ህገ-ወጥ ግንባታዎችን ማስፈረስ፣ አጥፉት፣ ግደሉት ያስብላል ወይ?
የአስተዳደር ፀጥታ ኃይሉ በሙሉ በእኔ ላይ ከፍተኛ አድማ፣ ተፅዕኖ፣ በመፍጠር ሊያጠፉኝ ተነስተዋል፡፡ ዛሬ ባለቤቴ ከመንግሥት ስራ ተፈናቅላ፣ እኔም እንዳይገሉኝ ሸሽቼ እገኛለሁ፡፡ ለአቅመ አዳም ያልደረሱ አራት ልጆች ያሉኝ ሲሆን ሁለቱ ልጆቼ የወለድኳቸውና ሌሎች ወላጅ አልባዎች በመሆናቸው የማሳድጋቸው ልጆቼ ዛሬ ለጎዳና አዳሪነት ሊዳረጉ ስለሆነ ለሚመለከተው ሁሉ ከጎኔ እንዲሰለፉ የድረሱልኝ ጥሪዬን አቀርባለሁኝ፡፡
No comments:
Post a Comment