BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

Monday, 11 November 2013



ቋንቋ ማንነትን እንደማይገልጽ በብርቅዬ ኢትዮጵያዊት አርቲስት EPRDF እና ጀሌዎቹ ቢገባቸው .............

“ፍቅርን እንደወረደ እሰብካለሁ” አርቲስት ሃኒሻ ሰለሞን

የባላገሩ አይዶል ባለቤት አብርሃም ወልዴ በክህደት ተከሰሰ

hanishaለማዘንም ለመደሰትም የቀረበች ናት። ስለዘርና ስለቋንቋ ያላት እምነት የሚለካው በፍቅርና በፍቅር ብቻ እንደሆነ ደጋግማ ትናገራለች። ቋንቋም ሆነ ዘር የማንነት መለኪያ እንዳልሆነ አጥብቃ ትከራከራለች። ፍቅርን እንደወረደ ከመስበክና ወገኖቿን የመርዳት ዓላማዋን ከማሳካት የሚበልጥባት ጉዳይ እንደሌለ አበክራ ትናገራለች። ገና ጀማሪ ብትሆንም ሙዚቃዎቿ ተወደውላታል የሚሉ እየበረከቱ ነው። እኔ ዘር የለኝም በሚል የሰፋ ሃሳብ ያለው ሙዚቃ ተቀኝታለች። ኢትዮጵያ የፍቅር ምድር እንድትሆን አብዝታ እንደምትሰራ ቃል በመግባት ከጎልጉል ጋር ቃለ ምልልስ አደረገችው አርቲስት ሃኒሻ ሰለሞን የምትኖረው ሎንዶን ነው። እንደሚከተለው ቀርቧል።hanisha7
በቃለ ምልልሱ ሃኒሻ ላይ በደል ፈጽሟል የተባለው የባላገሩ አይዶል ባለቤት አብርሃም ወልዴ ለቀረበበት ውንጀላ ምላሽ መስጠት ከፈለገ ዝግጅት ክፍላችን በደስታ እንደሚያስተናግደው ከወዲሁ ለመግለጽ ይወዳል። በተመሳሳይ በደል የደረሰባቸው አርቲስቶች እንዳሉ መረጃዎች ስላሉ ተበዳዮችም ሃሳባቸውን ቢሰጡ እናበረታታለን።
ጎልጉል፦ ከቋንቋ እንጀምር?
ሃኒሻ፦ ከስርአቱ እንጂ ከቋንቋ ጋር የሚደረግ ጸብ ለእኔ ግልጽ አይደለም። አይገባኝም። ቋንቋ መግባቢያ እንጂ የዘር መለኪያ ሚዛን አይደለም። አንድ ቋንቋ ግን አለኝ። እሱም ፍቅር ነው። ቋንቋዬ ፍቅር ነው ብዬ የዘፈንኩትም ለዚህ ነው። በጥንቃቄ ከታሰበ ከፍቅር በላይ ምንም ቋንቋ የለም። ፍቅርን፣ እንደወረደ እሰብካለሁ።
ጎልጉል፦ ስለ ብሔር ምን ትያለሽ?

ሃኒሻ፦ ሁሉም ብሄር ብሄረሰብ በእኩልነት አንዱ አዛዥ ሌላው ታዛዥ ሳይሆን ተከባብሮ በፍቅር አብሮ መኖር ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ።
ጎልጉል፦ ሃኒሻ ሁለት ጉዳዮች ተደባልቀውባታል የሚሉ አሉ፤
ሃኒሻ፦ ግልጽ ብታደርገ ው?
ጎልጉል፦ “መንፈሳዊ ሰው ነበረች” ይላሉ፤
ሃኒሻ፦ ሳቀች! (ቃለምልልሱ በስልክ ስለነበር ፊቷን አላየሁትም።ማዘኗን ግን ተረድቻለሁ። ተነፈሰችና ቀጠለች።) እኔ ከመንፈሳዊ እምነቴ አልራቅሁም። የሚገርመው ሰዎች ስንባል ራሳችን የማናደርገውን ነገር በሌሎች ላይ እንደስህተት አድርገን እንገልጻለን። መጠቋቆም እንወዳለን። በዚህች ዓለም ላይ ሙሉ ነገር የለም። ለስጋህ ስትሮጥ መንፈሳዊ ነገር ይጎድልብሃል። ሁሌም በጉድለት ነው የምኖረው። በሌላ በኩል ደግሞ የተፈለገውን ያህል መልካም ነገር ቢደረግ ከወቀሳ መዳን አይቻልም።
ጎልጉል፦ መንፈሳዊ ህይወትሽ የበዛ ነበር?
ሃኒሻ፦ አዎ ምንም ጥርጣሬ የለኝም። ያደኩትም ቤተክርስቲያን ዙሪያ ነው። የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ዘማሪ ነበርኩ።
ጎልጉል፦ “ፍቅር ነው ቋንቋዬ” የሚለው ዜማ ዋናው መልዕክቱ ምንድ ነው?
ሃኒሻ፦ “እኔ አገር የለኝም፣ ዓለም ነው አገሬ፤ እኔ ዘር የለኝም የሰው ልጅ ነው ዘሬ” የሚል ሃረግ አለበት። ግጥሙ የተገጠመው ለኔ ነው። “ከቅን ጋር ዋል ቅን ሆነህ ትገኛለህ” እንደሚባለው ቀና የሆኑት የልቤን ገጠሙልኝ። አዜምኩትና ራሴንና እኔን መሰሎችን ገለጽኳቸው። ፍቅር ቋንቋ ይሆን ዘንድ፣ ፍቅር አገር ይሆን ዘንድ፣ ፍቅር ድንበራችን ይሆን ዘንድ ፍቅር መግባቢያባችን ይሆን ዘንድ የበኩሌን አደርጋለሁ። እኛን የራበን ፍቅር ነው። አይደለም?hanisha2
ጎልጉል፦ ኦሮሞ ሆነሽ “ለምን በአማርኛ ዘፈንሽ” በሚል ተቃውሞ አጋጥሞሻል? ካጋጠመሽ በዝርዝር ልታስረጂኝ ትችያለሽ?
ሃኒሻ፦ እንደዚህ የሚል ነገር አላጋጠመኝም። አልደረሰብኝም። ከአዘፋፈን ስልት አንፃር ግን በየትኛው ቋንቋ በይበልጥ ብጫወት ጥሩ እንደሚሆን ምክር አዘል አስተያየት የሰጡ አሉ።
ጎልጉል፦ ያጋጠመሽን ችግር አንባቢያን ቢያውቁትና ቢወያዩበት በሚል ነው? “ኦሮሞ ሆነሽ ለምን በአማርኛ ትዘፍኚያለሽ” በሚል የተቃወሙ የሉም ነው የምትይው?
ሃኒሻ፦ ያጋጠመኝ ችግር የለም። ግን ማወቅ ያለብን ነገር ቢኖር አንድ ነገር ስትሰራ በማንኛውም መንገድ የሚቃወሙና የሚደግፉ መኖራቸውን ነው። ትልቁ ነገር የሚደግፉትን እያመሰገንህ የሚቃወሙህን ደግሞ ቀና በሆነ መንገድ ተወያይቶ እንዲወዱኝ ማድረግ ነው። ፍቅር ነው ቋንቋዬ ብዬሃለሁ እኮ …። አንድ ሰው ደግሞ ብዙ ቋንቋ ከቻለ መልእክቱን በሚችላቸው ቋንቋዎች ሁሉ ማስተላለፉ ታላቅ ችሎታ ነው። ይህን ችሎታዬን እንድቀጥልበት እንዲያውም በርቺ ነው የሚሉኝ።
ጎልጉል፦ ስለ ዘር ፖለቲካ ምን ሃሳብ አለሽ?
ሃኒሻ፦ ፖለቲካውን ለፖለቲከኞች እተወዋለሁ። ዓለም ዛሬ ድንበር አፍርሶ አንድ እንሁን ባለበት ዘመን ዘርና ጎሳ መቁጠር በግል ያሳዝነኛል። ጎሳና ዘር ቆጥረን ለምን እንለያያለን? ተለያይትንስ መጨረሻው ወዴት? መድረሻውና ማቆሚያውስ? ግን ይህንን ስል አንዱ ከሌላው በላይ ሆኖ የሌሎችን መብት እኩልነት ነፍጎ ሳይሆን ማንኛውም የሰው ልጅ እኩል መሆኑ ታምኖ በእኩልነት ተከባብሮና ተፋቅሮ መኖር ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ።
ጎልጉል፦ በዘርና በጎሳ ሃሳብ ላይ የመስራት እቅድ አለሽ?
ሃኒሻ፦ አዲስና ታዳጊ አርቲስት ነኝ። በማህበራዊ ጉዳየች ላይ ብዙ እቅዶች አሉኝ። ዝም ብሎ ለመዝፈን ሳይሆን ትርጉም ያላቸው ስራዎች ለመስራት እፈልጋለሁ። ማናጀሬ ካሰብኩት ግብ እደርስ ዘንድ እንደሚረዳኝ የጸና እምነት አለኝ።
ጎልጉል፦ ለመሪዎቻችንስ ትዘፍኝላቸዋለሽ?
ሃኒሻ፦ እነሱም እኮ ሰው ናቸው። ለህዝብ ሲዘፈን እነሱንም ያካትታል። ለሚሰማ ሁሉ እዘፍናለሁ። የኔም ሆነ የሌሎች አቀንቃኞች ድርሻ የራሳችንን መወጣት ነው።
ጎልጉል፦ በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ አቋምሽ እንዴት ይገለጻል?
ሃኒሻ፦ አብሮ መኖር፣ መስራት፣ መከባበር፣ መፈቃቀር፣ የወደቀውን መደገፍ….
ጎልጉል፦ በተለይ የሚያስደስትሽ?
ሃኒሻ፦ የተቸገሩ ሰዎችን መርዳት በጣም ያስደስተኛል። ወደፊትም በዚህ ዙሪያ ሰፊ እቅድ አለኝ። የታመሙ ሰዎችንhanisha6 መጎብኘት ልዩ ርካታ ይሰጠኛል።
ጎልጉል፦ ሃብታም ነሽ?
ሃኒሻ፦ (ሳቅ…) ምነው አበድሪኝ እንዳትል ብቻ? የእኔ ገንዘብ ባካባቢዬ ያሉ ናቸው። የኔ ሃብት ህዝብ ነው። የኔ ሃብት የሰው ዘሮች ናቸው።
ጎልጉል፦ ጥሬ ገንዘብ አትወጂም ማለት ነው?
ሃኒሻ፦ ሆ ሆ ምነው? ማን ብር ይጠላል? ገንዘብ እኮ የፈለከውን ታደርግበታለህ። የሚያስደስትህን ነገር ለማድረግ ያለ ገንዘብ አይሆንም። ገንዘብ ጥሩ ነው። ግን ልዩና ከሁሉም በላይ ተደርጎ የሚቀመጥ አይመስለኝም።
ጎልጉል፦ እና ላንቺ ሃብት ምንድ ነው?
ሃኒሻ፦ ሃብት የሰው መውደድ ነው የእግዚአብሄር ፀጋ ነው። በእምነት፣ በፍቅር ተከባብሮ መኖርና ሃሳብን በነጻነት ማንሸራሸርም ትልቅ ሃብት ነው።
ጎልጉል፦ ድህነትን ጠንቅቀሽ ታውቂዋለሽ?
ሃኒሻ፦ በሚገባ!! ጥሩ የደሃ ልጅ ነኝ። የድህነት መገለጫዎች በህይወቴ አልፈዋል። ባደኩበት ገጠር አንድ የገጠር ደሃ ቤተሰብ ያሳለፈውን ህይወት አልፌያለሁ። አብዛኛው ህዝብ በድህነት ከሚኖርበት ማህበረሰብ የወጣን ሁላችንም ድሆች ነን። ለኔ ግን ትልቁ ድህነት ሌላ ነው።
ጎልጉል፦ ምንድነው?
ሃኒሻ፦ ሃሳብን እንደልብ መግለጽ አለመቻል ለኔ ትልቁ ድህነት ነው።
ጎልጉል፦ እስኪ ስለ “አፍሪካ ተባበሪ” ንገሪኝ?
ሃኒሻ፦ መነሻው የኔ ባይሆንም “አፍሪካ ተባበሪ” የሚል ዜማ አለኝ። ቀደምት የአፍሪካ መሪዎች ፓንአፍሪአካኒዝም ብለው ሲጀምሩ፣ አፍሪካ በአንድ መሪ እንድትመራ ሳይሆን አፍሪካውያን ሰላም ፈጥረው ድንበር የለሽ ኑሮ እንዲኖሩ ነበር። አሁን በተጨባጭ የምናየው የአፍሪካውያን ዕጣ ስደት፣ ረሃብና እርዛት ነው። እንደምታየው አውሮፓውያን ሁለት ጊዜ የአለም ጦርነት አድርገዋል። አሁን ግን አዲሱ ትውልድ በሰላም በመከባበር በእኩልነት ይኖራሉ። ሀያ ስምንት አገሮች ለዜጎቻቸው ድንበር የለሽ ለመሆን ተስማምተው እየኖሩ ነው። እኛ አፍሪቃውያንም እንደነሱ የማንሆንበት ምክንያት የለም። አዲሱ ትውልድ መንቃት አለበት።hanisha1
ጎልጉል፦ “አዮ – እናት” የሚለው ዘፈን ለእናት ይከራከራል፤ ለምን?
ሃኒሻ፦ እናት ዘጠኝ ወር ተሸክማ፣ አምጣ ወልዳ፣ አጥብታ አሳድጋ፣ ልጇ የሚጠራው ወይም የምትጠራው በአባት ስም ነው። ለምን እናት አትካተትም? “ለኔ ስም ሲያወጡልኝ፣ ያንቺ ስም ወዴት ተፋቀ?” በማለት መብትን የሚጠይቅ ዘፈን ነው። በነገራችን ላይ በሴቶች ዙሪያ ከሰብአዊ መብት አንጻር ወደፊት ትኩረት ሰጥቼ የምሰራው ሌላው ስራዬ ነው።
ጎልጉል፦ ሙዚቃ አድጓል የሚሉትን ትደግፊያለሽ?
ሃኒሻ፦ ሙዚቃ እድገት የሚኖረው የሙዚቃ ድርጅት ሲኖር ነው። አለበለዚያ አርቲስቱ ለግጥም፣ ለዜማ፣ ለማቀነባበሪያ ለማሳተሚያ ወዘተ እያወጣ ሙዚቃው አድጓል ለማለት ያስቸግራል። እንዲያድግ ከተፈለገ የሙዚቃ ድርጅቶች ታላቅ ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል። ታላላቅ ችሎታ ያላቸው ከያንያን አሉ ግን በግላቸው ያለ ድርጅት እርዳታ እነሱም ለማደግ ይቸገራሉ የሙዚቃዉም እድገት በዓለም ደረጃ ውስን ይሆናል።
ጎልጉል፦ ሁሌም የሚያባንንሽ ድንጋጤ አለ ይባላል፣ እውነት ነው?
ሃኒሻ፦ አዎ! የመኪና አደጋ ደርሶብኝ ነበር።
ጎልጉል፦ በወቅቱ ሞተሽ የተነሳሽ ያህል ተሰምቶሽ ነበር?
ሃኒሻ፦ አዎ! እንቅልፍ እንኳ የሞት ታናሽ ይባል የለ። ከመኪና አደጋ በአሰቃቂ ሁኔታ መትረፍ፣ እውነት ለመናገር አሳዛኝ ጊዜ ነበር። አምላክ ምስጋና ይግባውና አለሁ።
ጎልጉል፦ የተለየ ክስተት ነበር?
ሃኒሻ፦ ቤቴ አካባቢ ከሚኒባስ ወርጄ መንገድ ሳቋርጥ መኪና መታኝ። እንደገጨኝ ተነስቼ በሩጫ ቤት ገባሁ።
ጎልጉል፦ መኪናውስ?
ሃኒሻ፦ እኔ እንጃ፤ የማውቀው ነገር የለም።
ጎልጉል፦ ሲገጭሽ ለምን ሮጥሽ?
ሃኒሻ፦ ደነገጥሁ በተጨማሪ ከገጨኝ መኪና ጋር መከራከር የማልችልበት ወቅት ላይ ነበርኩ። ስደት!! እቤቴ ስገባ እጄ፣ ጉልበቴ፣ ትከሻዬ ጀርባዬ ደምቷል። ተጎድቻለሁ። ከዓመት በላይ ህክምና ሳላገኝ ቆየሁ። ላገሩ አዲስ ስለነበርኩና የመኖሪያ ፈቃድ ስላልነበረኝ ህክምና ለማግኘት ተቸግሬ ነበር። አሁን ድረስ የሚሰማኝ ስሜት አለ። ችግሩ ብዙ ነበር እንለፈው።
ጎልጉል፦ ለንዶን የተሳካልሽ ይመስላል?
ሃኒሻ፦ ፈጣሪ ምስጋና ይግባው ሰላም ነው።
ጎልጉል፦ ለእድገትሽ በስራሽ ላይ መሰናክል የሆኑ ነገሮችስ አጋጥሞሻል?
ሃኒሻ፦ አዎ! ግጥም እንሰራለን ዜማ እንደርሳለን እያሉ ገንዘብ ከተቀበሉ በኋላ በቃላቸው በማይገኙ ስዎች የተነሳ ጊዜየ ባክኗል፡፡
ጎልጉል፦ “አብርሃም ወልዴ የባላገሩ አይዶል ባለቤት አጭበርብሮሻል” ይባላል ምንድነው ያጭበረበረሽ? እውነት ነው?
ሃኒሻ፦ በዚህ ጉዳይ ላይ ውሉን የተዋዋለው ማኔጀሬ ስለሆነ መናገር የሚችለው ማኔጀሬ ነው እና እሱን ብትጠይቀው ይሻላል፡፡ አለችኝ።
ጎልጉል፦ እኔም መልካም በማለት የሃኒሻን የሙዚቃ ሃላፊ ጋዜጠኛ ድልነሳውን ስለ አብርሃም ወልዴ ማጭበርበር እንዲያብራራልኝ ጠየቅሁት::
abraham wolde
(ፎቶ: Abraham Wolde Facebook, Sept. 14, 2009)
ጋዜጠኛ ድልነሳው፦ እኔ የምኖረው ሎንዶን ነው። እና አብርሀም ወልዴን እዚህ በመጣበት ወቅት አፈላልገን አግኝተነው ስንስማማ ፍትህ ወዳድ፣ ጥሩ ሰው፣ ሀቀኛና እውነተኛ ሙያውን የሚያከብር እንደሆነ አጫወተኝ። እኔም አመንሁት ለሃኒሻ ሙዚቃ ስራ መሳካት እኔ ገንዘብ ስለከፈልኩት ብቻ ሳይሆን እሱም በተጨማሪ እንደሚረዳት አብረን በሙዚቃ ሙያዋ እንደምናሳድጋት ቃል ገባ። እኔም አመንሁት 8 ዘፈኖችን ለማዘጋጀት 5ሺህ ፓውንድ ወሰደ። በተጨማሪ ደግሞ ሁለት ዘፈኖችን በሌላ ሰው ሊያስራላት 12ሺህ የኢትዮጵያ ብር መስማማቱን ገለጸልኝ። ገንዘቡ ተከፈለው። በጣም ተከራክሮ ዋጋ እንዳስቀነሰም ነገረኝና አመንኩት። እሱ የሚሰራቸውን ስምንት ዘፈኖችና በሌላ ሰው የሚያሰራቸውን ሁለት ዘፈኖች በጥቅሉ 10 ዘፈኖችን በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ግጥምና ዜማውን እሰጣለሁ ብሎ ቃል ገብቶ ተስማማን። እንኳን በሶስት ወር ቀርቶ አምስት አመት ጠብቀን አላገኘነውም። አብርሃም የውሃ ሽታ ሆነ። እምነቱን አጎደለ። የተረዳሁት ነገር ቢኖር ከአብርሃም ወልዴ ጋር ስትወያይ በብርጭቆ ድንጋይ እሰብራለሁ ብሎ የሚያሳምን ምላስ ያለው ሰው መሆኑን ነው። የሚገርመው በተገናኘንበት ወቅት አብርሀም እንዲያዉም “ፕሮጀክቴን ቀድተው ኢህዴጎች ለራሳቸው ሰዎች ሰጡብኝ” በማለት በሙያዬ ሁሉ እንድረዳው ጠይቆኛል። ከዛሬ አስር ዓመት በፊት እንግዲህ ተጭበረበርሁ ያለ ሰው እራሱ አጭበርባሪ ሲሆን በጣም ያሳዝናል። 5ሺህ ፓውንድ ቀላል ገንዘብ አይደለም። ከሁሉም በላይ ደግሞ የምታድገዋን ልጅ እድል መግደል ወንጀል ነው። በስልክ የተነጋገርናቸው ጉዳች በሙሉ ተመዝግበው ተይዘዋል። በተጨማሪ ሌሎችም ያጭበረበሩና ዘፈን የሰረቁን ሁሉ አሉ። ያም ሆነ ይህ ወደፊት ትልቅ አርቲስት እንደምትሆን ስለተረዳሁ የሁለት ልጆች አባት እንደመሆኔ ሶስተኛ ልጄ ትሆኛለሽ በማለት ልረዳት ቃል በገባሁላት መሰረት ሃኒሻን ትልቅ ቦታ ለማድረስ ጥረቴ ይቀጥላል።
ጎልጉል፦ ሃኒሻ የምትጨምሪው አለ?
ሃኒሻ፦ ወደ ሙዚቃው ዓለም ስገባ አንድ የኦሮምኛና አንድ የአማርኛ ሲዲ ለማሳተም ነበር የመጀመሪያ አላማዬ። ግን ያው ማኔጀሬ እንዳለው በደረሰብን ችግር የተነሳ ስድስት የአማርኛና ስድስት የኦሮምኛ ዘፈኖችን ለማሳተም ሲወሰን እንዴት አማርኛውና ኦሮምኛው ተቀላቅሎ ይቀርባል? ግማሽ ኦሮምኛ ግማሽ አማርኛ ያልተለመደ ስራ ይዘጋጃል በሚልና አንድ አማርኛ አስራ አንድ ኦሮምኛ ወይም አንድ ኦሮምኛ አስራ አንድ አማርኛ ዘፈን መሆን አለበት የሚለው ጉዳይ በሙዚቃ አሳታሚዎች ዘንድ አነታራኪ ሆነ። ለምን አንድ ኦሮሞኛ ወይም አንድ አማረኛ ይሆናል በማለት ማኔጀሬ ድልነሳው ሲጠይቃቸው የሰጡት መልስ ያልተለመደ ስራ ነው የሚል ነው። በመጨረሻ ማናጀሬ ጋዜጠኛ ድልነሳው “እኔ እራሴ አሳትመዋለሁ” በማለት ጠንካራ አቋም በመውሰድ አልበሙ ታተመ።hanisha5
ጎልጉል፦ ማናጀርሽን ድልነሳውን እንዴት አገኘሽው?
ሃኒሻ፦ እዚህ እግሊዝ አገር ፊልም ለመስራት ምልመላ በነበረበት ወቅት እሱም አንዱ መላማይ ሆኖ ተገኝቶ ነበር። እዛ ኩኩ የምትባል ጓደኛዬ አብራኝ ነበረች፤ ጎበዝ ናት እና እሷ ስትዘፍን በዕረፍት ጊዜአችን እሷን እየተቀበልሁ ስጫወት ሰማኝና ዘፋኝ መሆን የሚያስችል ድምጽ እንዳለኝና ዘፋኝ መሆን እንደምችል ሲነግረኝ “የሚረዳኝ ካለ” አልኩት። “ሁለት ሴት ልጆች አሉኝ ሶስተኛ ልጄ ትሆኛለሽ” አለኝ። በዚሁ አባቴም፣ ማናጀሬም፣ የህይወቴ አዲሱ መንገድ መሪ ሆነ።
ጎልጉል፦ የአዘንሽበት ቀን አለ?
ሃኒሻ፦ ማናጀሬ ድልነሳው ታሞ የቀዶ ጥገና ለማድረግ ሆስፒታል ገብቶ ነበር። በቅርቡ እንደገና መልሼ የማላገኘው መስሎኝ ነበር። በህይወቴ ያዘንኩበትና በጣም የተጨነኩበት ጊዜ ነው። አምላክ ቸር ነውና በሚገባ ድኖ … (አለችና … አለቀሰች። ከቆይታ በኋላ እንደመሳቅ ብላ) … ሰሞኑን በባህር የሰመጡ ምስኪን ወንድሞችና እህቶች ዜና ክፉኛ ልቤን ነክቶታል አለችኝ። ዳግም አለቀሰች …
ጎልጉል፦ ዘፋኝ እሆናለሁ ብለሽ ግን አስበሽ አታውቂም ነበር?
ሃኒሻ፦ በፍጹም። ሰዎች በተደጋጋሚ ድምጽሽ ጥሩ ነው ይሉኝ ነበር። እናቴ ሃኒሻ ብላ የቤት ስም ሰጠችኝ። ማናጀሬ የቤት ስሜን አደባባይ አወጣውና ታዋቂ አደረገኝ። በዚህ አጋጣሚ ስለ መልካምነቱና ስላደረገልኝ ሁሉ ምስጋናዬ ትልቅ ነው።
ጎልጉል፦ ለመጀመሪያ ጊዜ መድረክ ላይ የታየሽው የት ነው?
ሃኒሻ፦ በተለያዩ የርዳታ ማሰባሰቢያ ድራማዎች ላይ ተሳትፌያለሁ። በ2001 ለንደን በተካሔደ የኢትዮጵያዊያኖች የቁንጅና ውድድር ተሳትፌ 3ኛደረጃ አግኝቻለሁ። ግን በመዝፈን ደረጃ ከሆነ በ23ኛውና በ24ኛው በሎንደን የገለስፒ የሙዚቃ ዝግጅት ላይ ነው። በ2012 ደግሞ በቦትስዋና የነፃነት ክብረ በኣል ላይ ተጋብዠ ተጫውቻለሁ። እና አሁን በቅርቡ ደግሞ በ11ኛው የአፍሪቃ አገሮች የሙዚቃ ዝግጅት ላይ ተጫውቻለሁ።
ጎልጉል፦ ተስፋ ስለመቁረጥ አስበሽ ታውቂያለሽ?
ሃኒሻ፦ ብዙ ተፈትኛለሁ። ብዙ የህይወት ውጣ ውረድና ክህደት አዳክሞኝ ነበር። ግን ሁሌም አንድ ትልቅ እምነት አለኝና እዚህ ደረስኩ። እምነቴ በማንኛውን ሁኔታ ውስጥ ማለፍ የምችልበት ሃይል እንዳለኝ ማመኔ ነው። አሁን በጥሩ ጅምር ላይ ነኝ። አሰብኩበት እደርሳለሁ የሚል ሙሉ እምነት አለኝ። ከእግዚአብሔር ሳልርቅ!!hanisha8
ጎልጉል፦ ከዘፈንሻቸው ዘፈኖች ውስጥ ባልዘፈንኩት የምትይው ዘፈን አለ?
ሃኒሻ፦ ገና መቼ ዘፈንኩና!
ጎልጉል፦ ሞዴል አድርገሽ የወሰድሽው ዘፋኝ አለ?
ሃኒሻ፦ የለም።
ጎልጉል፦ እንዴት ነበር የምትለማመጂው?
ሃኒሻ፦ ድምጽሽ ረበሸኝ የምትል ምቀኛ ጎረቤት ብትኖረኝም ጭር ሲልልኝ ቤቴን ዘግቼ በቴፕሪኮርደር እየቀዳሁ እለማመድ ነበር። እድሜ ለማናጀሬ እያረመኝ እዚህ ደርሻለሁ። ስለቅላጼ እንኳን የማውቀው ነገር አልነበረኝም። ቅላጼ ምን እንደሆነ የተረዳሁት ሲዲው ከታተመ በኋላ ነው። እኔን በማነጽ ማናጀሬ ድልነሳው ታላቅ ስራ ሰርቷልና ሁሌም ለምስጋናው ከፊት ለፊት ረድፍ የሚገኝ ይሆናል።
ጎልጉል፦ ባንድ አለሽ?
ሃኒሻ፦ አዎ፤ አለኝ ሙሉ ባንድ። የባንዱ ማለትም የሙዚቃ ቡድኑ ኃላፊ ጋናዊ ነው። አዲስ ጅምር ነው እናድጋለን።
ጎልጉል፦ በካፒታል ምን ያህል ይገመታል?
ሃኒሻ፦ ስለገንዘብና ሃብት መጠየቅ ታበዛለህ። አዲስ ነን። ግን በቅርቡ እናድጋለን። አብረን ለመስራት ቃል ገብተዋል።
ጎልጉል፦ በአስራ አንደኛው የአፍሪቃ ሙዚቃ ዝግጅት ፌስቲቫል ላይ ተሳትፈሽ ነበር ተሳካልሽ?
ሃኒሻ፦ በጣም ውብ ዝግጅት ነበር። ኢትዮጵያ አገሬን ወክዬ ነበር የተሳተፍኩት። የፌስቲቫሉ መዝጊያው ላይ ሙሉ ስራዬን አቅርቤ ተወዶልኛል። መድረክ ላይ ሆኜ የተሰጠኝ ምላሽ ግሩም ነበር። ከመድረክ ስወርድም ዘወትር እንደማደርገው የማናጀሬን ፊት ሳየው ጥሩ እንደሰራሁ አመንኩ። እኔ ሲቀናኝ መደሰቱን ፊቱ ላይ አነበዋለሁ። ሳቅ …
ጎልጉል፦ ወደ እንግሊዝኛው ዘፈን ለማምራት ታስቢያለሽ?
ሃኒሻ፦ ለጊዜው ሀሳብ የለኝም። የአገሬን ባህልና ወግ መልቀቅ አልፈልግም። ብዙ ውብ መልክና ገጽታ አለን። አገሬን በሙያዬ አጎላለሁ ብዬ አስባለሁ እንጂ ሎንዶን ስለምኖር እንግሊዘኛ ልዝፈን ብዬ ከኔ ከሚበልጡት ተወላጆች ጋር ግፊያ ውስጥ አልገባም። የማሊ፣ የካሜሮንና የሴኔጋል ዘፋኞች በውጪው ዓለም በራሳቸው ቋንቋ በከፍተኛ ደራጃ ተደማጭ ሆነዋል ። እኔም ባገሬ ቋንቋ ዘመንን ተከትዬ መግፋት ነው ፍላጎቴ።
ጎልጉል፦ በጣም የሚያስደስትሽ ምንድ ነው?
ሃኒሻ፦ ማይክ ይዞ መድረክ ላይ መውጣት ያስደስተኛል። የሰዎችን ጭንቀት መጋራት፣ በሰዎች ሃዘን ውስጥ መሳተፍና ራሴን በተጎዱ ሰዎች ቦታ በማስቀመጥ ለተወሰነ ጊዜ ማሰብ እጅግ ያስደስተኛል።
ጎልጉል፦ የምትጠየፊው ነገር አለ?
ሃኒሻ፦ ቃሉ ከበደ። የምትጠይው ነገር ለማለት ከሆነ ግን ሰው ማማት አልወድም። ሰው የማያከብር ሰው አልወድም። በደልን ማድረግ አግባብ አይደለም ብየ አምናለሁ። በደልን በጠየከኝ ቃል መጠን አልወድም።hanisha4
<
ጎልጉል፦ ምኞትሽ?
ሃኒሻ፦ በሴቶች ጉዳይና በሰብአዊ መብት ዙሪያ የመስራት እቅዴ እውን ሆኖ ማየት እፈልጋለሁ። የርዳታ ስራ ላይ ለመሰማራት የጀመርኩት ስራ አለ። እሱም እንዲጠናቀቅልኝ እመኛለሁ። ከሁሉም በላይ የፍላጎቶቼ ሁሉ መሰረትና የህልሞቼ ቁልፍ በሆነው ሙያዬ ታላቅ ስም መትከል እፈልጋለሁ። የማናጀሬ ድልነሳው ፍላጎትና ህልም በእግዚአብሔር አርዳታ ይሰካ ዘንድ ጸሎቴ ነው። የሚወዱኝም በሃሳብ እንዲተባበሩኝ እፈልጋለሁ።
ጎልጉል፦ በምን እንጨርስ?
ሃኒሻ፦ ስራዬን ለተከታተሉልኝ፣ ሃሰብ ለሰጡኝና መልካም ለተመኙልኝ ሁሉ የልብ ምኞታቸው እንዲደርስላቸው እመኛለሁ። ክህደት መልካም አይደለምና የክህደት ልብ ያላቸውን ተግባራቸውን እንጂ እነሱን እንደማልጠላቸው በዚህ አጋጣሚ ለማሳወቅ እፈልጋለሁ። ወደልባቸው በመመለስ ህሊናቸውን አጽድተው እንዲኖሩም እመክራቸዋለሁ። ለሁሉም የአገሬ ሰዎች ቋንቋቸው ፍቅር፣ አገራቸው ፍቅር፣ ህይወታቸው ፍቅር እንዲሆን እመኛለሁ። አመሰግናለሁ!! (የሃኒሻ ፎቶዎች በሙሉ የተወሰዱት ከHanisha Solomon Facebbok ነው)

No comments:

Post a Comment