BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

Tuesday, 5 November 2013

ሰማያዊ ፓርቲ 

Semayawi Party


Semayawi party
One more chance to unite Ethiopians for Democracy::

ራዕይ፣ ተልዕኮና ዓላማ


የሰማያዊ ፓርቲያችን ፕሮግራም የፓርቲያችንን ራዕይ፣ ተልዕኮና ዓላማ እንደሚከተለው በዝርዝር አስፍሯል፡፡


ራዕይ



የዜጎች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ የተከበሩባት፤ ለሕዝብ ፍላጎት መሟላት በኃላፊነትና በተጠያቂነት መንፈስ የሚሰራ መልካም አስተዳደርና የህግ የበላይነት የተረጋገጠባት፤ የኢኮኖሚና ማሕበራዊ ብልፅግና የሰፈነባት፤ ለዜጎቿ ሁሉ አለኝታና መኩሪያ የሆነች፤ለዓለም ሕዝብ መልካም ግንኙነት የበኩሏን አስተዋፅዖ የምታደርግ ኢትዮጵያን ማየት ነው፡፡

ዓላማ



ሀ.     የዜጎች ዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩና ተፈፃሚም ኢንዲሆኑ በጽናት መቆም፡፡
ለ.     ለዜጎች አስተማማኝ የማሕበራዊ ደህንነት ዋስትና አገልግሎት ማቅረብ፡፡
ሐ.     በኢትዮጵያ ፈጣንና ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት ማረጋገጥ፡፡
መ.    የፖለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ነፃ፣ ፍትሃዊና ትክክለኛ በሆነ መንገድ ተወዳድረው የፖለቲካ  ሥልጣን የሚይዙበት የምርጫ ሥርዓት መመስረት፡፡
ሠ.     ራዕዩን ተግባራዊ ለማድረግ በነፃና ፍትኃዊ ምርጫ በህዝብ ድምፅ የፖለቲካ ሥልጣንመያዝ
ረ.     ሀቀኛ፣ ብቃትና ተጠያቂነት ባለው አመራር አማካኝነት ታታሪና የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ዜጎች መፍጠር፡፡
ሰ.     የሕብረተሰቡን የፖለቲካ ግንዛቤ በማሳደግ ዜጎች በሃገራቸው ጉዳይ በንቃት እንዲሳተፉ፣ ግዴታቸውንና ኃላፊነታቸውንም እንዲወጡ ማድረግ፡፡
ሸ.     የእያንዳንዱን ዜጋ ችሎታ በማሳደግ በሃገርና በዓለም ደረጃ ብቁ ተወዳዳሪ ለመሆን ያለውን  ምኞት ማሳካት፡፡
ቀ.     ከሀገራቸው ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊና ቁሳዊ አቅማቸውን ለሃገራቸው ልማት እንዲያውሉና ለሕዝብም ቁሳዊና መንፈሳዊ ሕይወት መሻሻል የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ማበርከት የሚችሉበት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማሕበራዊ ሥርዓት መመስረት፡፡
በ.     ዓለምን ለመረዳትም ሆነ የዓለም ሕብረተሰብ በአግባቡ እንዲረዳው ማድረግ የሚችልና በነፃነት የሚያስብ ሕብረተሰብ መመስረት፡፡
ተ.     የኢትዮጵያ ወጣት ትውልድ በራሱና በወረሰው መልካም ነገር እንዲኮራና በሕይወቱ ውስጥ ተስፋ እንዲኖረውና ለከፍተኛ ግብ እንዲሰራ ማደፋፈር፡፡

ተልዕኮ



ተልዕኮአችን ዓላማችንን ማሳካት ሆኖ በተለይ በሀገራችን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍንና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ዋስትና የሚሰጥ ከሕዝብ፣ በሕዝብ፣ ለሕዝብ የቆመ መንግስት በሰላማዊ መንገድ መመስረት ነው፡፡

ሀገራዊ ዕይታ



ሀ.     ኢትዮጵያ ሀገራችን በኢትዮጵያ ህዝብ ሙሉ ገዥነት ስር የሚገኘውን መሬት፣ ውሃ፣ የአየር ክልል፣ በከርሰ ምድርና በከርሰ ውኃ የሚገኘው ሃብት፣ በአየር ክልሉ ያለው የድምፅና የምስል ሞገድ ባለቤት ሉዓላዊ ሀገር ናት፡፡
ለ.     የኢትዮጵያ ያልተመለሱ የድንበርና የይገባኛል ጥያቄዎች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ የአስተዳደር ወሰን አሁን በኢትዮጵያ መንግስት ሥር የሚገኘውና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተመዘገበዉ ክልል ነው፡፡
ሐ.     በኢትዮጵያ ውስጥና በውጭ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአንድነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ናቸው፡፡
መ.    የኢትዮጵያ ሕዝብም በኢትዮጵያ ጉዳይ ባለሙሉ የሥልጣን ባለቤት ነው፡፡ ሃገሪቱን የማስተዳደር ሥልጣን ከሕዝብ ይመነጫል፡፡
ሠ.     የኢትዮጵያ አንድነትም ሆነ ሉዓላዊነት አይነጣጠሉም፤ለሌላም አይለቀቁም፡፡
ረ.     ኢትዮጵያውያን በግል ያላቸው የዜግነት መብትም ሆነ በወል የሚጋሩት የህግ፣       የፖለቲካ  የማህበራዊና የባህል መብት የአንድነታቸው ዓይነተኛ መሰረት ነው፡፡
ሰ.     ኢትዮጵያ ሀገራችን የረጅም ጊዜ አኩሪ ታሪክ፣ የበርካታ ገፀ-ምድርና  ከርሰ-ምድር ሃብት ባለቤት፣ አስደናቂ የተፈጥሮ ውበትና የሰው ልጅ ቀደምት ሥልጣኔ መገለጫ
የሆኑ ቅርሶች ያሏት ታላቅ ሃገር ናት፡፡
ሸ.     ሃገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ ባህል፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋ፣ ወግና ሥርዓት አሸብርቃ የኖረች፣ በብዙ ዓይነት ሃረጎች ተሳስረውና በታሪክ ተቆራኝተው የጋራ አመለካከትና ኢትዮጵያዊ ማንነትን በማዳበር ለዘመናት ተቻችለውና ተከባብረው በአንድነት የኖሩ ዜጎች ሃገር ናት፡፡ እነዚህ ዜጎች በየዘመናቱ የተለያዩ አስተዳደራዊ በደልና ጭቆና ደርሶባቸዋል፡፡ ዛሬም ቢሆን የዜጎች የአስተዳደርና የፍትህ ጥያቄ በአግባቡ አልተፈታም ወይም መብታቸው አልተከበረም፡፡ በመሆኑም ሁሉም ዜጎች የዜግነት መብታቸው እንዲከበርና በሃገር ጉዳይ ላይ ተገቢው ድርሻና ተሳትፎ እንዲኖራቸው አሁንም ፅኑዕ ትግል የሚያስፈልጋት ሃገር ናት፡፡

ርዕዮተ ዓለም



እጅግ ውድ የሆነው የሰው ልጅ ሃብት ነፃነቱ በመሆኑ ሰማያዊ ፓርቲ ለግለሰብ ነፃነት ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ ዜጎች በቡድን ሊያከናዉኗቸው የሚፈልጓቸው እንደ ሃይማኖት፣ ልማዶች፣ ቋንቋ፣ ማህበሮች እና የመሳሰሉት የጋራ መብቶች የግለሰብን በነፃነት የመወሰን መብት ሳይሸረሽሩ እንዲከበሩ የህግ ጥበቃ እንደሚያስፈልጋቸው ያምናል፡፡ በመሆኑም ሰማያዊ ፓርቲ በለዘብተኛ ሊብራል ዲሞክራሲ መሰረታዊ መርሆች ይመራል፡፡

No comments:

Post a Comment