የብአዴን ከፍተኛ ካድሬዎች ባነሱት ጥያቄ ምክንያት
ንትርክ እና ጭቅጭቅ ተከስቶ እንደነበር ተጋለጠ
የብአዴን ከፍተኛ ካድሬዎች ባነሱት ጥያቄ ምክንያት ንትርክ እና ጭቅጭቅ ተከስቶ እንደነበር ተጋለጠ በሙስና ሰበብ ተለጥፎባቸው በእስር ላይ በሚገኙት የወያኔ ቱባ ባለስልጣናት ዙሪያ በተደረገ ውይይት ላይ በባለስልጣናት መሀከል ንትርክ ተፈጥሮ መሰንበቱን ከውስጥ አዋቂ ምንጮች ያገኘነው ጥቆማ ገለጸ፡፡
የብአዴን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዳይሬክተር በሆነው በመላኩ ፈንታ ዙሪያ በተነሳ ውይይት አንዳንድ የብአዴን ከፍተኛ ካድሬዎች ሞራል እና ስነ ምግባርን ያልተከተለ ክስ ነው በሚል ባነሱት ጥያቄ ምክንያት ንትርክ እና ጭቅጭቅ ተከስቶ እንደነበር ተጠቆመ፡፡ ከታሰረ ሁለት ወር በሁዋላ ክስ በተመሰረተበት በመላኩ ፈንታ ላይ ከቀረቡት ክሶች መሀከል የሰው ሚስት አፋትቶ አማግጦዋል በሚል የቀረበበትን ክስ ከፍተኛ የብአዴን ካድሬዎች ሞራልን የሚነካ ...ስነ ምግባርን
ያልተከተለ…ምክንያታዊ ያልሆነ….ከጀርባው ተልዕኮ ያለው….ክስ በመሆኑ እርማት ሊደረግ ይገባል በሚል ጥያቄ ያነሱ ቢሆንም ነባር እና በእድሜ የገፉት የህወሀት ባለስልጣናት ግን ይህን ማለት ሙስናን እንዋጋለን ብለን ቃል የገባነውን እንደመሻር የሚቆጠር በመሆኑ ጥያቄው ተገቢ ያልሆነ ከመሆኑም በላይ አንዳንዶቻችሁ በጥቅም የተሳሰራችሁ መሆናችሁን ደርሰንበታል በማለት የማስደንገጫ ምላሽ እንደሰጧቸው ከደረሰን ከውስጥ አዋቂ ምንጮች ጥቆማ ለመረዳት ተችሎዋል፡፡
መለስ ከሞተ በሁዋላ የሕወሀት ሰዎች እርስ በርስ ተከፋፍለው እየተፋለሙ በነበረበት ወቅት ብአዴን አንሰራርቶ ለጥቂት ግዜ የበላይነቱን ለመያዝ እየተንፈራገጠ የነበረ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ኢህአዴግ 9ኛ ጉባኤውን በባህርዳር ላይ ባደረገበትም ወቅት የብአዴኖች ሰዎች ልብ አግኝግተው አንዳንድ ጉዳዮችን ያለ ፍርሀት ሲናገሩ እንደነበር ይታወሳል።
የግብርና ሚኒስትሩ የብአዴኑ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ተፈራ ደርበው ግብርናን አስመልክቶ በአሁኑ ሰዓት የግብርና ፖሊሲ ብለን እየተንቀሳቀስንበት ያለው መንገድ ከአርሶ አደሩ ጋር ያልተመጣጠነና ተገቢ ያልሆነ ከመሆኑም በላይ የቀረጽነው ስትራቴጂ የተሳሰተ ነው በማለት በይፋ የወያኔን ግብርና መሪ ፖሊሲ እያብጠለጠለ በጉባኤው ላይ መናገሩ የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ የኤርትራ ተወላጁና የመለሰ ቀኝ እጅ የሆነው በረከት ስምኦንን ጨምሮ የወያኔ ባለስልጣኖች አባይ ጸሀዬ …አባይ ወልዱና ሌሎቹም ተረባርበው ተፈራ ደርበው ባቀረበው አስተያየት ላይ ውርጅብኝ ያዘነቡበት ከመሆኑም በተጨማሪ የቀረጽነውና በስራ ላይ እየተረጎምነው ያለው የግብርና መሪ ፖሊሲ የአስፈጻሚው ችግር እና የአርሶ አደሩ ስንፍና ነው በማለት መሳደባቸው ይታወሳል፡፡
የፍትህ ሚኒስትሩ ብርሀን ኃይሉም በበኩሉ የተደራጁ ክሶች በአግባቡ እንዳይወሰኑና እንዳይታዩ በአንዳንድ የወያኔ ከፍተኛ ባለስልጣናት ትዕዛዝ እንዲዘጉና እንዲዳፈኑ በመደረጉ ስራ መስራት አልቻልንም በማለት በጉባኤው ላይ በይፋ መናገሩም ይታወቃል፡፡
ዛሬ በቃሊቲ እስር ቤት ውስጥ የሚገኘው የብአዴኑ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባሉ መላኩ ፈንታም በበኩሉ በጉባኤው ላይ ባቀረበው ሰፊ አስተያየት በተለይ በገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን ውስጥ እጃቸው ረጅም የሆኑ ከበረሀ የመጡ የወያኔ ታጋዮች በአሁኑ ሰዓት በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች አላሰራ ብለውናል….በመሆኑም የመንግስትን ፖሊሲ በአግባቡ ለመፈጸም ከፍተኛ ችግር ላይ ወድቀናል በማለት በአዳራሹ ለተገኙት በይፋ አጋልጧል፡፡
ይሄንኑ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባሎች ያደረጉትን ግልጽ ውይይት እና ያቀረቡትን አስተያየት ተከትሎ በልዩነት ሲነገራገጭ የነበረው የወያኔ ቡድን አንሰራርቶ አንድ አቁዋም በመያዝ በብአዴኖች ላይ የጥቃት በትሩን ማሳረፍ የጀመረው በዚያው ሰሞን ነበር፡፡
በዚህም ሳቢያ ብርሀን ኃይሉ መፍትሄ ይሰጠኛል ብሎ እራሱ ባቀረበው አስተያየት ከፍትህ ሚኒስትርነት እንዲነሳ ሲደረግ የግብርና ሚኒስትሩ ተፈራ ደርበው ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲነሳና ወደ አዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ዝቅ እንዲል መደረጉና የገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣኑ መላኩ ፈንታ በበኩሉ በሙስና ሰበብ ዘብጥያ እንዲወርድ ተደርጎዋል፡፡
ከመለስ ሞት በሁዋላ አንሰራርቶ ነበር የተባለው ብአዴን አንዲት እርምጃ ወደፊት ሳይራመድ ባለበት ማጥ ውስጥ ሲዳክር እርስ በርስ ተከፋፍለው ሲቦጫጨቁ የነበሩት የወያኔ ባለስልጣኖች መልሰው አንድ አቁዋም በመያዝ የጥቃት በትራቸውን በመሰንዘራቸው የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴዎችን እያሽመደመዱ በአሁኑ ሰዓት ጨርሶ ድምጻቸው እንዳይሰማ እያደረጓቸው ነው፡፡
ብአዴንን ሊያጠናክር ነው ተብሎ በጡረታ ከተባረረበት ተመልሶ የስራ አስፈጻሚ እንዲሆን የተሾመው አዲሱ ለገሰ ገና አንዲት እንቅስቃሴ ሳያደርግ በተወሰደበት እርምጃ የካድሬዎች ማሰልጠኛ ማዕከል ኃላፊ በሚል አርፎ እንዲቀመጥ ቀጭን ትዕዘዝ ተሰጥቶት ስራ ጀምሮዋል፡፡ ዋናው የወያኔ እና የመለስ ቀኝ እጅ እንደነበር ሲነገርለት የነበረው የብአዴኑ ከፍተኛ ባለስልጣንና የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትሩ በረከት ስምኦን በአማካሪነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ እንዲቀመጥ ተደርጎ አፈ ጮሌው
የተባለውና የከተማ ታጋዩ የደኢህዴኑ ካድሬ ሬድዋን ሁሴን በሚኒስትር ማዕረግ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሆኖ የበረከትን ቦታ እንዲረከብ ተደርጎዋል፡፡
ዛሬ ሀገሪቱን በሙሉ ከመከላከያ እስከ ፌዴራል ፖሊስ….. ከሚኒስትር እስከ ደህንነት መስሪያ ቤቶች… በስውርም ሆነ በይፋ እየመሩና እያንቀጠቀጡ የሚገኙት የወያኔ ሰዎች ሲሆኑ በተለይ መለስ ከሞተ በሁዋላ ከፍተኛ የሀገሪቱን ቁንጮ ስልጣን በስውር ተቆጣጥሮ ያለው የወያኔው ባለስልጣን ደብረጽዮን ወ/ሚካኤል መሆኑንም ያገኘውነው መረጃ ይጠቁማል፡፡
ዶ/ር ደብረጽዮን ወ/ሚካኤል የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ተብሎ መለስ ከመሞቱ አስቀድሞ የተሾመ ሲሆን ይህ ሚኒስትር መስሪያ ቤት የደህንነቶቹን ተቁዋማት ሙሉ ለሙሉ የሚቆጣጠር እና የባለስልጣናቱን የስልክ ልውውጦች እንዲሁም እንቅሰቃሴያቸውን ሁሉ የሚከታተልና የሚቆጣጠር ሲሆን መለስ ከሞተ በሁዋላም በምክትል ጠቅላይ ሚነስትር ማዕረግ የፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ ተብሎ ከፍተኛ ስልጣን እንዲይዝ ተደርጎዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በሀገሪቱ የሚገኙ የገንዘብ ተቁዋማት ማለትም ብሔራዊ ባንክንና ሌሎችንም ባንኮች….. የፋይናንስና ገንዘብ ሚኒስትርን….በአጠቃላይ ገንዘብ ነክ ጉዳዮችን ሙሉ ለሙሉ በበላይነት የሚመራው ይሄው የህወሀቱ ደብረጽዮን ሲሆን በሀገሪቱ የሚገኙ የደህንነት ተቁዋማቱንም በበላይነት እየመራ እንደሚገኝ ታውቆዋል፡፡
በእነ መላኩ ፈንታ ክስ መዝገብ ውስጥ ከሕዝብ የተዘረፈው የህወሀት ንብረት የሆነው መስፍን ኢንጂነሪንግ ከባለሀብቶች እና ከባለስልጣናት ጋር በሞዳሞድ ያለ ቀረጥ እቃዎችን በማስገባት በፈጸመው ወንጀል ተከስሶዋል ተብሎ እየተነገረ ቢገኝም ድርጅቱን ስትመራ የነበረችው የመለስ ዜናዊ ሚስት አዜብ መስፍን ልትጠየቅ ሲገባ ይበልጥ ድጋፍ እና እንክብካቤ እየተደረገላት መገኘትዋ የብአዴን መሽመድመድ እና የወያኔ የበላይነት መንገሱን የሚያሳይ በመሆኑ የእነ መላኩ ፈንታ የሙስና ሳይሆን የፖለቲካ በቀል መሆኑንም ያረጋገጠ ነው የሚል አስተያየት የሚሰጡ አሉ፡፡
በመከላከያ ስር የተቁዋቁዋመው የብረታ ብረት እና ኢንጅነሪንግ ድርጅትም በስም ተጠቅሶ የተከሰሰ ሲሆን ዋና ስራ አስኪያጁና እንዲሁም ሳሞራ የኑስ እና ብ/ጄ/ል ተብየው ክንፈ ሳይጠየቁ መቅረታቸው የብአዴን ባለስልጣናት ለጭዳ የቀረቡበት ክስ ድራማ መሆኑንም ውስጥ አዋቂዎች ያጋልጣሉ፡፡ የወያኔ ቡድን ፍርሀት በእጅጉ ጨምሮዋል የአንድነት ፓርቲ አመራሩ በሶስት ደሕንነቶች ተደብድቦ ለከፋ ጉዳት ተዳረገ የህዝብ ተቃውሞ ይነሳብኛል በሚል በፍርሀት እየራደና ወባ እንደያዘው ሰው እየተንቀጠቀጠ የሚገኘው የወያኔ ዘረኛው ቡድን በተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ላይ ማስፈራሪያ ከመሰንዘሩም በተጨማሪ ድብደባና የግድያ ሙከራ ማድረጉ ተጋለጠ፡፡
የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ለሁለት ወራት በጎንደር…. በደሴ…በአዲስ አበባ…በአዳማ…በወላይታ ሶዶ እና በሌሎችም ከተሞች የሚሊዮኖች ድምጽ በሚል ተከታታይ ባደረገው የአደባባይ ተቃውሞን ተከትሎ በአመራሮቹና በአባሎቹ ላይ ከፍተኛ የማዋከብ ስራ እየተደረገ መሆኑ ታውቆዋል፡ የተቃውሞ ሰልፉን ሲያስተባብሩና ሕዝቡን ሲያንቀሳቅሱ ነበር የተባሉ የአንድነት ፓርቲ አመራሮችን እና አባሎችን ከየመንገዱ እያፈኑ ሰዋራ ቦታ እየወሰዱ ከፍተኛ ድብደባ ከመፈጸማቸውም በላይ የከፋ የአካል ጉዳት
ደርሶባቸው በየቤታቸው ተኝተው የሚገኙ ዜጎች ከቀን ወደ ቀን ቁጥራቸው እየበዛ መምጣቱ ተነግሮዋል፡፡
ሰሞኑን የተቃውሞ ሰልፉን ሲያስተባብሩ ከነበሩት መሀከል አንዱ በደህንነቶች ታፍኖ ተወስዶ ጫካ ውስጥ ተደብድቦ ተጥሎ የተገኘ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በከባድ ጉዳት እቤቱ ተኝቶ እንደሚገኝም ለቤተሰቦቹ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ተናግረዋል፡፡
መምህር አበበ አካሉ የተባለው የአንድነት ፓርቲ አመራር እና የተቃውሞ ሰልፉ አስተባባሪ የነበረው አርብ ጥቅምት 14 ቀን 2006 ዓ.ም ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ኮተቤ ኪዳነ ምሕረት መሳለሚያ አቅራቢያ በደህንነቶች ታፍኖ ወዳልታወቀ ስፍራ ተወስዶ እስከ ምሽቱ 1 ሰዓት ተኩል ድረስ ድብደባ ተፈጽሞበት ተጥሎ መገኘቱን ለቤተሰቦቹ ቅርበት ካላቸው ወገኖች ያገኘውነው መረጃ አስረድቶዋል፡፡
ሶስት የደህንነት ሰዎች ዘመናዊ ቪ8 በተሰኘ ላንድ ክሩዘር መኪና ኮተቤ ኪዳነ ምህረት መሳለሚያ አቅራቢያ አፍነው ወደ ጫካ በመውሰድ እንዳይጮህ እና የድረሱልኝ ጥሪ እንዳያሰማ አፉን በስፖንጅ ጠቅጥቀው አየር ከማሳጣታቸውም በተጨማሪ እራሱን እንዲስት አልኮል በመጋት ይህ ቀረሽ የማይባል ድብደባ ከፈጸሙበት በሁዋላ ወደ አስፓልት ዳር ጥለው መሄዳቸውን ተከትሎ በሕብረተሰቡ ርብርብ ወደ ቤቱ ሊገባ እንደቻለ ይሄው የደረሰን ጥቆማ አስረድቶዋል፡፡
ባለትዳር እና የሶስት ልጆች አባት የሆነው የአንድነት ፓርቲ አመራር መምህር አበበ አካሉ ከአንድነት ጋር ለምን ትሰራለህ….ከእንግዲህ በዚህ ፓርቲ ውስጥ ብትገኝ ጀምረንሀል እንጨርስሀለን በማለት ወደል እና ጠብደል አፋኝ የደህንነት ሰዎች እንዳስጠነቀቁትም የደረሰን ጥቆማ አብራርቶዋል፡፡
ለወያኔ ቡድን በጥቅም ተታልሎና አሸርግዶ ለአራት ዓመታት ሲያገለግል የነበረው ወጣት ከድቶ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን በመቀላቀሉ ወከባ እየደረሰበት መሆኑን አጋለጠ፡፡ የወያኔ የወጣት ፎረም አባል ከመሆን ጀምሮ እስከ ሊቀመንበርነት የደረሰው ወጣት ሀብታሙ አያሌው በወያኔ ቡድን ውስጥ የሚሰራው የሀገር አፍራሽ እና ሕዝብን የመነጣጠል ሴራ ስላልተመቸኝ በማለት ቡድኑን ከድቶ ወደ ተቃዋሚ ጎራ በመቀላቀሉ በደህንነቶች እና በባለስልጣናት ወከባ እና እንግልት እየደረሰበት መሆኑ ተጋለጠ፡፡
የወያኔን ስርዓት አውግዞ እራሱን አግልሎ ከአንድነት ፓርቲ ጋር አብሮ መስራት በጀመረው በዚሁ ወጣት ላይ የተለያዩ የጥቃት እርምጃዎችን ሊያደርሱበት ሞክረው የነበረ ቢሆንም ይህ አልሳካ ሲላቸው በቅርቡ የሀሰተኛ ክስ መስርተው ፍርድ ቤት እንዳቆሙት ተናገረ፡፡
አንድነት ፓርቲ የሚሊዮኖች ድምጽ ብሎ ባዘጋጀው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ከፍተኛ ሚና ሲጫወት የነበረው እና የወያኔን ገመና አብጠርጥሮ የሚያውቀው የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ አባሉ ወጣት ሀብታሙ አያሌው በባለስልጣናት ላይ ዛቻ ሰንዝረሀል በሚል ፍርድ ቤት ተከስሶ መቅረቡ ታውቆዋል፡፡
አቁዋሙን ቀይሮ ወደ ወያኔ እንዲያድር የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅመው እያባበሉት እምቢ በማለቱ የወያኔ ባለስልጣን የሆነ ግለሰብ አንገትህን እቆርጥሀለሁ ብሎ ዝቶበታል በሚል በተከፈተበት የሀሰተኛ እና የፈጠራ ክስ ተከስሶ ፍርድ ቤት እየተመላለሰ እንደሚገኝም ከፓርቲው ውስጥ አዋቂ ምንጮች የደረሰን ጥቆማ አስረድቶዋል፡፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስከያጅ ከሀገር ኮበለለ ተባለ ዓመታዊ የሲኖዶሱ ስብሰባ በጳጳሳት መሀከል በጭቅጭቅ እና በንትርክ ተጠናቀቀ ዓመታዊ ጉባኤውን ከጥቅምት 9 ቀን ጀምሮ እስከ ጥቅምት 19 ቀን 2006 ዓ.ም ድረስ ሲያደርግ የሰነበተው አፍቃሪ ወያኔ የሆነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሶኖዶሱ ስብሰባ ያለመግባባት በንትርክ እና በጭቅጭቅ መጠናቀቁ ታወቀ፡፡
ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር በተወከሉ ሁለት ከፍተኛ ካድሬ ባለስልጣናት በተገኙበት በተደረገው በዚሁ ዓመታዊ የሲኖዶሱ ስብሰባ ላይ ጳጳሳት ሕልውናችንን አሳልፋችሁ በሰጣችሁበት ጉባኤ ላይ መነጋገር የለብንም በማለት ስብሰባ ረግጠው ለመውጣት ሞክረው እንደነበርም የቤተክህነት የውስጥ አዋቂ ምንጮች ገለፁ፡፡ ሲኖዶሱ የጥቅምቱን ዓመታዊ ጉባዔ ለማድረግ ጥቅምት 9 ቀን ከጠዋቱ 3 ሰዓት ተኩል ላይ በጸሎት የጀመረ ሲሆን በመሀከላቸው የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ከፍተኛ ባለስልጣናት መገኘታቸው ስብሰባውን ሲመሩ ከነበሩት ከአቡነ ማትያስ በመገለጹ ጳጳሳቱ በውስጥ ችግሮቻችን እኛ ብቻ መነጋገር ሲገባን የመንግስት ተወካዮች ጣልቃ ገብተው መገኘታቸው ተገቢ አይደለም በማለት ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡
ምንም እንኩዋን ጳጳሳቱ ባለስልጣናቱ ከጉባኤው እንዲወጡና የስብሰባውን ሂደት ከፈለጉ ተቀርጾ እንዲሰጣቸው በመግለጽ የተቃወሙ ቢሆንም አቡነ ማትያስን ጨምሮ ጥቂት ጳጳሳት ተቀርጾ ተሰጣቸውም ሆነ ተቀምጠው መከታተሉ ለውጥ ስለሌለው በዚሁ ይቀጥሉ በማለት አስተያየት በመስጠታቸው በጳጳሳት መሀከል ከፍተኛ ጭቅጭቅ እና ንትርክ ተፈጥሮ እንደነበር ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡
በአራት ኪሎ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች ጥያቄ ዙሪያም ጳጳሳቱ አጀንዳ ቀርጸው የተነጋገሩበት ቢሆንም አንዳንድ ጳጳሳት በተለይ ተማሪዎቹ ላይ ባላቸው ጥላቻ የስም ማጥፋት እና ጨርሶም ከሽብርተኝነት ጋር እስከመፈረጅ የደረሰ ሀሳብ በማቅረባቸው በብዙሀኑ ጳጳሳት ዘንድ ቁጣን ቀስቅሶ ሲወዛገቡ እንደነበርም የቤተክህነት ውስጥ አዋቂ ምንጮች ገልፀዋል፡፡
በሁለት ባለስልጣናት የተወከለው የወያኔ ቡድን ጨርሶ ሕዝበ ክርስቲያኑ አንገቱን ደፍቶ እንዲኖርና እንዳይተነፍስ ለማድረግ የተጀመረ እቅድ መኖሩን ገልፀው ለዚህ ተግባራዊ እንቅስቀሴ ደግሞ የእምነት አባቶች ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ቢናገሩም ጳጳሳቱ በዚህ ላይም ትችት እና ወቀሳ ሰንዝረዋል፡፡ የጳጳሳቱ ዓመታዊ ጉባኤ ከመጀመሩ አስቀድሞ የመላ ሀገሪቱ አብያተ ክርስትያናት የደብር አለቆች እና የቤተክህነት ስራ አስኪያጆች የተገኙበት ዓመታዊ ስብሰባ የተደረገ ሲሆን በዚህ ስብሰባ ላይም የወያኔ ቡድን በእምነት ተቁዋማት ውስጥ ጣልቃ እየገባ የሚፈተፍተውን እንዲያቆም በማለት በሙሉ ድምጽ አቁዋም
እንደተወሰደበት የውስጥ አዋቂ ምንጮች ጥቆማ ገልጾዋል፡፡
የተለያዩ ሰበቦች እየተለጠፉባቸው ሕዝበ ክርስቲያኑን ከማስተማር እንዲርቁ የተደረጉ…. ማስፈራሪያ የተሰነዘረባቸው …..እምነታቸውን የሚሰብኩ ከቅርብ ግዜ ወዲህ እንዳያስተምሩ የተከለከሉ ብዙ ምሁራን የእምነት አባቶች አሉ ….ይሄ ደግሞ ነጻነትን የሚጋፋ በመሆኑ ሊታረም ይገባል ያሉት የስብሰባው ተሳታፊዎች መንግስት በእምነታችን ውስጥ ጣልቃ እየገባ የሚፈጥረውን ደንቃራ ሊያቆም ይገባል ብለዋል፡፡
በተለይ በዚሁ ስብሰባ ላይ የወያኔን ቡድን እያብጠለጠለና ምስጢር እያጋለጠ ሲናገር የነበረው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ መጋቤ ሀዲስ ይልማ በተሰብሳቢው ዘንድ አድናቆትን ያገኘ ከመሆኑም በተጨማሪ በስብሰባው ላይ የወያኔን ሴራ በማጋለጡ በጭብጨባ ሲታጀብ እንደነበር የውስጥ አዋቂ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በስብሰባው ላይ ለረጅም ሰዓት የወያኔን ገመና ሲያጋልጥ እና ምስጢሩን ይፋ ሲያደርግ የነበረው መጋቤ ሀዲስ ስብሰባው ከመጠናቀቁ አንድ ቀን አስቀድሞ ቤተሰቦቹን ተሰናብቶ ለስራ ጉዳይ በሚል ከሀገር እንደወጣም ምንጮቹ ገልፀዋል፡፡
የአዲስ አበባው ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ ከሀገር መውጣቱን ተከትሎ ምክትል ስራ አስኪያጁ ምክንያቱ ሳይገለጽለት ከኃላፊነቱ ላይ የተነሳ መሆኑ ተነግሮት ቢሮው መታሸጉን እነኚሁ የቤተክህነት ውስጥ አዋቂ ምንጮች አጋልጠዋል፡፡
ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ
Finote Democracy Voice of Ethiopian Unity
ጥቅምት 23 ቀን 2006 ዓ.ም.
No comments:
Post a Comment