መጋቢት ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአዲስአበባ የመጠጥ ውሃ እና የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲሁም የሞባይልና የኢንተርኔት አገልግሎቶች መቆራረጥ በያዝነው መጋቢት ወር ተባብሶ በመቀጠሉ ነዋሪዎች ለአላስፈላጊ ኪሳራ ከመዳረጋቸው ጋር ተያይዞ በነዋሪው ዘንድከፍተኛ ምሬት መፍጠሩን ዘጋቢያችን ገልጿል።
በያዝነው ወር የኤሌክትሪክ ኃይል ቢያንስ በሁለት ቀን አንድ ጊዜ ለሰዓታት የሚጠፋበት ሁኔታ በተደጋጋሚ መስተዋሉን ዘጋቢያችን ተዘዋውሮ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች የገለጹ ሲሆን በዚህም ምክንያት ለአንድ ፍሬ ሻማ ወጪ ከአራት አስከ አምስት ብር ለማውጣት ተገደዋል፡፡
በተጨማሪም አንድ ጄሪካን የመጠጥ ውሃ በአንዳንድ አካባቢዎች እስከ10 ብር እየተጠየ መሆኑን የጠቀሱት ነዋሪዎች መንግስት በቴሌቪዥን የሚናገረውና በተግባር የሚታየው ሊጣጣም አልቻለም ይላሉ።