ሚያዝያ 17 እና 18 ቀን በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩ ሦስት ጋዜጠኞችና ስድስት ጦማርያን (Bloggers) በዕለተ እሑድ ሚያዝያ 19 ቀን 2006 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ጋዜጠኞች ተስፋዓለም ወልደየስ፣ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ፣ ኤዶም ካሳዬ፤ ጦማሪያኑ ደግሞ በፍቃዱ ኃይሉ፣ ማህሌት ፋንታሁን፣ አቤል ዋበላ፣ ዘለዓለም ክብረት (አምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህር)፣ አጥናፉ ብርሃኔና ናትናኤል ፈለቀ ናቸው፡፡
ሚያዝያ 19 ቀን 2006 ዓ.ም. በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል (ማዕከላዊ) መርማሪ ፖሊስ ያቀረባቸው በፍቃዱ ኃይሉ፣ ማህሌት ፋንታሁን አቤል ዋበላ በአንድ መዝገብ፤ ዘለዓለም ክብረት፣ ተስፋዓለም ወልደየስና አስማማው ኃይለጊዮርጊስ በአንድ መዝገብ እና አጥናፉ ብርሃኔ፣ ናትናኤል ፈለቀና ኤዶም ካሳዬ አንድ ላይ፣ ዘጠኙም ተጠርጣሪዎች ሦስት ሦስት ሆነው ቀርበዋል፡፡
ፖሊስ ተጠርጠሪዎቹ የተጠረጠሩበትን ወንጀል ለፍርድ ቤቱ ሲያስረዳ የመብት ተሟጋች ነን ከሚሉ የውጭ ኃይሎች ጋር በሙሉ ሐሳብና በገንዘብ በመስማማት፣ ሕዝብን የሚያተራምስና አገርና መንግሥትን የሚያፈርስ ዘገባ በኢንተርኔትና በማኅበራዊ ድረ ገጾች ያልሆነ መረጃ በማስተላለፍ መጠርጠራቸውን ማስረዳቱ ታውቋል፡፡ ምርመራውን ባለመጨረሱም 15 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቆ የ10 እና 11 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ተፈቅዶለታል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ መቼና እንዴት ሊታሰሩ እንደቻሉ ማብራሪያ የተጠየቁት በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሸመልስ ከማል ‹‹የማውቀው ነገር የለም›› ብለዋል፡፡
No comments:
Post a Comment