BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

Monday, 28 April 2014

ጥቂት ስለ ማዕከላዊ!

አክመል ነጋሽ

ማዕከላዊን በከፊል አውቀዋለሁ፡፡ ከትናንት በስቲያ ሰባት የሚሆኑ ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮችና አክቲቪስቶች መታሰራቸውን ተከትሎ ወደ ማእከላዊ መወሰዳቸውን ሰምተናል፡፡ በቀጣዮቹ ቀናት ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ጨለምተኛ ልመስል እችል ይሆናል፤ እውነታው ግን ይኸው ነው፡፡
መጀመሪያ ክሱ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው አጓጊ ጥያቄ ነው፡፡ ይህን ለማወቅ ወሳኝ ፍንጭ የሚሰጠው የቤት ፍተሻው ነው፡፡ የታሰሩትን ሰዎች ቤት የሚፈትሹት ፖሊሶችና መርማሪዎች ቤቱን የሚፈትሹት ለጥቂት ሰዓታት (ቢበዛ ለሁለት ሰዓታት) ከሆነና በጣም ብርበራ ያልበዛበት ከሆነ አለቆች በጸረ ሽበር ሕግ ለመክሰስ እንዳላሰቡና አስፈራርተው ብቻ በዋስ ለመልቀቅ እንዳሰቡ ፍንጭ ይሰጣል፡፡ በተቃራኒው ፍተሻው በትንሹ ከስድስት ሰዓታት በላይ የሚረዝምና በቤቱ የተገኘውን ወረቀት፣ መጽሐፍ፣ ሲዲ፣ ኮምፒውተርና ሞባይሎች ምንም ሳይስቀሩ ሰብስቦ የሚያስኬድ ከሆነ ጉዳዩ በጸረ ሽብር ሕግ ከመክሰስ ጋር የተያያዘ እንደሆነ መጠርጠር ያሻል፡፡
ይሄ የቤት ፍተሻ የቤቱን ኮርኒስ መቅደድና ወለሉን እስከመቆፈር ይደርሳል፡፡ በዚህ ጉዳይ ውስጥ ዋናው ግንዘቤ መወሰድ ያለበት ነገር ሰዎቹ የሚያስሩት ማስረጃ በመያዝ ሳይሆን፤ ማስረጃ ሊሆን የሚችል ማንኛውም ነገር በፍተሻው አግኝቶ እሱን ቀባብቶና አሳምሮ መክሰስ መቻላቸው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መርማሪዎች፣ አቃቢ-ሕጎችና ተሰያሚ ዳኞች ተገናኝተው እንዲያወሩ ስለሚደረግ ነገሩን ፍርድ ቤት አድርሶ የሚፈለገውን ውሳኔ ለማስወሰን መንገዱ ጨርቅ ነው፡፡
በማእከላዊ ከተወሰዱ በኋላ ቢያንስ ለሦስት ቀን ያህል ከቤተሰብም ሆነ ከማንም ጋር መገናኘት የማይተሰብ ነው፡፡ ይህ ታሳሪዎቹንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን የበለጠ ለማደናገጥና የሥነ-ልቦና ጫና ውስጥ ለመክተት ወሳኝ ነው፡፡ ታሳሪዎቹ በቀጥታ የሚወሰዱት ‹‹ጣውላ ክፍል›› ወደሚባሉ የእስር ክፍሎች ነው፡፡ በዚህ ክፍል የሚታሰሩ ሰዎች በ24 ሰዓት ውስጥ ለ15 ደቂቃ ያህል የሚቆይ ጸሀይ መሞቂያና መጸዳጃ ቤት መሄጃ ፈቃድ ይሰጣቸዋል፡፡ እነዚህ ከፍሎች በግምት አራት በአራት ስፋት ያላቸውና ወለላቸው ከጣውላ ጣሪያና ግድግዳቸው ከኮንክሪት የተሠራ ሲሆን፤ ቦታው ሻል ካለው የእስር ኮሪደር ‹‹ሸራተን›› እጅግ ያነሰ ነጻነት ያለውና፤ በጣም ከባሰው ጨለማ ክፍል ‹‹ሳይቤሪያ›› የተሻለ ቦታ ነው፡፡ ምርመራው ለእስር በገቡበት ምሽት ይጀመራል፡፡ የኢ-ሜይልና ሌሎችም አካውንቶች ፓስወርዶች በግድ እንዲሰጡ ይደረግና የኮምፒውተር ሀ ሁ በማያውቁ ‹‹መርማሪዎች›› አካውንታቸው ይበረበራል፡፡
ከዚሁ ጎንለጎን ቀለል ያለ ምርመራና ጥያቄና መልስ ይካሄዳል፡፡ በቀጣዮቹ አምስት እና አስር ቀናት ‹‹ጠቃሚ ውጤት በምርመራ አላገኘንም›› ብለው ካሰቡ ወደ ሌላኛው የእስር ክፍል ወደ ‹‹ሳይቤሪያ›› ያዘዋውሯቸዋል፤ በዚህ ወቅት የምርመራ ስልቱና አጠቃላይ ሁኔታውም ይለወጣል፡፡ ታስረው መቆየት ‹‹አለባቸው›› ወይም ‹‹የለባቸውም›› የሚለውን የሚወስኑት በዚህ ጊዜ ነው፡፡ ውሳኔው ይፈቱ ከሆነ ወደ ‹‹ሸራተን›› የእስር ክፍል ያዘዋውሯቸዋል፡፡ ይህ ከቤተሰብ ጋር መገናኘት የሚያስችል የእስር ቦታ ሲሆን፣ በጊቢው ካሉት የእስር ክፍሎች ሁሉ የተሻለ አንጻራዊ ‹‹ነጻነት›› ያለው ነው፡፡
በጥቅሉ ሳይቤሪያ ከአንድ ሜትር ስኩዌር ብዙም የማይበልጥ፣ ጨለማ፣ በጣም ቀዝቃዛና አምስት ቀናት ቢቆዩቡት መላው አካልን ወደ አመድነት (ነጭነት) የሚለውጥ ዘግናኝ ቦታ ነው፡፡ በዚህ እስር ክፍል ውስጥ ሰዎች የሚታሰሩት ያላደረጉትን ነገር አድርገናል ብለው እንዲያምኑ ወይም የያዙትን ‹‹ሚስጥር›› ‹‹እንዲያወጡ›› ነው፡፡ በዚህ ክፍል የሚታሰሩ እስረኞች አንዳንዴ ያልተቋረጠና እስከ 14 ሰዓት የሚደርስ ምርመራ በፈረቃ በሚቀያየሩ መርማሪዎች ይደረግባቸዋል፡፡ በምርመራው እንደ እስረኛው ሁኔታ የሚላላና የሚጠነክር ድብደባና ቶርች መጠቀም የተለመደ ‹‹አሠራር›› ነው፡፡ ቶርች የተደረጉ ሰዎች ቁስላቸው እስከሚያገግም ከቤተሰብም ሆነ ጠበቃ ጋር ማገናኘት የማይታሰብ ነው፡፡ በእነዚህ ሁሉ ወቅቶች ቤተሰብ ምግብ ለማድረስ፣ ጠበቆች ደንበኞቻቸውን ለማግኘት የሚደርጉት ጥረት ውጤት አልባ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ይቺ ነች፡፡

No comments:

Post a Comment