መርገምንና በርካታ ሊሎች የግጥም መድበሎችንና ድርሰቶችን ያቀረበው ኃይሉ በቤተ ክህነት ትምህርት
የላቀ ዕውቀት የነበረው፤ የቅኔም አባት ሆኖ የቆየ ታላቅ የአገር ቅርስ ነበር ።
ኃይሉ ለዘመናዊው ትምህርት ወደ ዩኒቨርስቲ ከገባ ተጀምሮ በተራማጅ አስተሳሰብን ያንጸባርቅ በነበረው
የተማሪ እንቅስቃሴ ግንባር ቀደም ሆኖ ሲታገል ከሌሎች ስምንት ተማሪዎች ጋር ከዩኒቨርስቲ ተባሮ
እንደነበር ይታወቃል ። ገሞራው በአጼው ዘመን ሲታገል በተደጋጋሚ ለበርካታ ጊዜዎች ተይዞ ታስሮ
የነበረ ሲሆን ጨካኝ በሆኑ የጸጥታ ሰራተኞች ድብደባና ስቃይን ተቀብሏል ።
ገሞራው ለሰፊውና ጭቁን ሕዝብ አለኝታ ሆኖ ገና ከወጣትነት ዕድሜው ጀምሮ የታገለ ጀግና ነበር ። ለኢሕአፓ ደግሞ
የማይታክት ደጋፊና ወዳጅ ሆኖ የቆየ በመሆኑ ኢሕአፓ በዚህ ታላቅ ሰው ዕረፍት የተሰማው ሀዘን
ትልቅ ነው። ቢሆንም ገሞራውን በስራውና በቅርሱ ለማክበርና አርአያነቱንም ለማስተጋባት እንጥራለን
እንጂ እሱ ራሱ በማይፈልገው መንገድ ራስ ልንደፋና ልንሸማቀቅ--ልንበሳጭ አንችልም ።
"ዛሬ ቢያወሩልኝ አልሰማም የሻገተ ወሬ የቀመለ
ድፍን አበሻ ቢቀላምድ እንዲህ እንዲህ እያለ
ገዳሙን ትቶ ኮበለለ
ይህ አባ ቆቡን ጣለ
ብሎ የጻፈውንም ግጥም በአንክሮ የምናስታውሰው ሲሆን በተለይም በረከተ መርገም የዚያን ጊዘውን
ወጣት ትውልድ የቃኘና ያነሳሳ ታሪካዊ ግጥም መሆኑንም የምንዘነጋው አይደለም ። ገሞራው
“ያሰብከው ዓላማ አልሆን ብሎ ሲከሽፍ/ሁናቴው ሲጠጥር/ጠጣሩ እንዲላላ የላላውን ወጥር” ብሎ
የቋጠረው መልዕክት እስክዛሬም ወቅታዊ ሆኖ ቅኝትና ግንዛቤ ሰጪ ሆኗል ።
ኃይሉ ገብረ ዮሐንስ ወደ ቻይና ለከፍተኛ ትምህርት ሄዶ በዚያም ብዙ መከራን ችሎ የቆየ ሲሆን ከዚያ
ሲለቅም ከ400 ገጾች በላይ የሆነ የቻይንኛ (ሀን) የእንግሊዝኛ የፈሊጣዊ አባባሎች መጽሃፍን ጽፎ
አሰራጭቷል ።
ገሞራው ከማረፉ በፊት የስራው ስብስቦች በቅጾች ደረጃ ይታታሙ ዘንድ ለኢሕአፓ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)ሰጥቶ በዚህም መሰረት ለህትመቱ ሀገር ወዳዶች ጭምር መዋጮ ለግሰው የህትመቱ ስራ በሂደት ላይ
ይገኛል ። ገሞራው በስደት ወደ ኖርዌይና ስዊድን በመጣበት ወቅትም በነዚህ ሀገሮች ያሉ ወያኔዎችና
ሻዕቢያዎች ፍዳ ያሳዩት ሲሆን ለወያኔዎችና ሻዕቢያዎች ተንኮል ግንባሩን ሳያጥፍ፤ ቃል ኪዳኑን ሳይሽር
ችግሮቹን ተቋቁሞ ሲታገል ቆይቷል ። ይህን የኢትዮጵያ ታላቅ ቅርስ የሆነውን ውድ ዜጋ ለመታደምና
ለመንከባከብ ከፈተኛ ርብርቦሽና ጥረት መደረገ የነበረበት ቢሆንም በዜጎች ችላ ተብሎ የከፋ ችግርና ስቃይ
የደረሰበት መሆኑንም ሳንጠቅስ ብናልፍ ጉድለት ይሆናል ። ገሞራው ውሾ (ወያኔ ወ ሻዕቢያ
ላይ)የኢትዮጵያ ሕዝብ ድልን እንደሚቀዳጅ ሙሉ እምነት የነበረው ሲሆን ለወያኔ ድለላና ግብዣም
ጆሮ አልሰጥ በማለቱ መከራው ተባሶበት ቆይቷል ። ገሞራው የኢሕአፓ ባለውለታ ነው--የኢትዮጵያ
ሕዝብ ጀግናና ጽኑ ልጅም ነው ። በወያኔው እንደተገደለው ወዳጁ ጸጋዬ ደብተራውም ፍርሓት አልባ፤
ጽኑና ታላቅ የኪነት ሰውም የነበረ ነውና በማረፉ ሀገራችን ትጎዳለች ። የተወው የጀግንነት ቅርስ ግን
ወጣቱን ትውልድ ለትግል ይቃኛልና ገሞራው ሁሌም አብሮን ነው፤ ሁሌም ለጸረ ኢትዮጵያ ሃይሎች
ሁሉ አንቀጥቃጭ ሆኖ የሚቆይም ነው ።
ኢሕአፓ ለገሞራው ቤተሰቦችና ወዳጆች ሁሉ ጽናቱን ይስጣችሁ ይላል።
የገሞራው ቅርስና አርአያነት ትግላችንን ያጅባል፤ ያጠናክራል ።
No comments:
Post a Comment