BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!
Sunday, 9 November 2014
ኢትዮጵያ ፦ ለልጆቿ የተከለከለች ፍሬ
የፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሀተታ
ጥቅምት 19 ቀን 2007 ዓ.ም. የተላለፈ
ዕምቅና ተጨባጭ የሆነው የተፈጥሮ ሀብቷ ሞልቶ ተርፎ ፤ ዜጎቿን መመገብ ያልቻለች ምድር ሀገራችን ኢትዮጵያ
መሆኗ እስከ ዛሬ ደረስ ያልተገነዘበ ፍጡር ይኖራል ብለን አንገምትም ። እኛም ዛሬ ይህንን ለማውሳት የፈለግነው፤
ለድኅነታችን፤ ለችግራችንና ለረሀብ ጥማታችን ማስተዋወቂያ አዲስ ሰሌዳ ለመዘርጋት አይደለም ። ብሄራዊ ችግሮቻችንን
በአደባባይ ማውጣቱም ሀዘንን እንጅ፤ ደስታን ፤ ሀፍረትን እንጅ ኩራትን እንደማያመጣልን ደህና አድርገን እንገነዘባለን ።
ዘለዓለም ስለ ሀገራችን መከራና ችግር ብቻ እያወሳን ማነብነብ አንዳችም መፍትሄ እደማያስገኝ እንረዳለን ።
የሀገራችን ችግር መወገዱ ቀርቶ፣ እንዲያውም እየተባባሰ መሄዱ እስከቀጠለ ድረስ ግን፤ በቸልታ ልንመለከተው
አይገባንም። በመሆኑም፤ የችግሩን መሠረታዊ ምክንያቶችና ለችግሩም ተጠያቂዎች የሆኑትን ለይቶ በመፈረጅ
የሚወገዱበትን ዘዴ መፈለጉን እንቀጥልበታለን። በዕርግጥም፤ በችግሮቹ ነባር ምክንያቶች ላይ በማተኮር፤ የዘለቄታ
መፍትሄ ማግኘት አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር መሆኑንም እናምንበታለን ።
ማጀቷ ሞልቶ ተርፎ ልጆቿን የምታስርብ ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ ከሆነች ግን የችግሩን ምሥጢር አውቆ መፍትሄውን
መፈለግ፤ የዜጎቿ ኃላፊነት እንጅ በውጭ ርዳታ ላይ መተማመን የዘለቄታ መፍትሄን አያስገኝም ። የሦስተኛው ዓለም
ሀገሮች ተብለው ከተመደቡትና የውጭ ዕርጥባን ከሚያገኙት ሀገሮች መካከል፤ ኢትዮጵያ ከፍተኛውን ርዳታ የምታገኝ
መሆኑ ቢታወቅም፤ የዜጎቿ ኑሮ ግን ከድኅነት ደረጃ ክፍ ሊል አልቻለም። ዛሬም እንደወትሮው፤ የዕለት ጉርስና የዓመት
ልብስ ያጡ ዜጎች ቁጥር፤ በበርካታ ሚሊዮን እንደሆነ የታወቀ ሆኗል ።
በቅርቡ ይፋ ከሆነው የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ጥናት ሰንጠረጅ ( ስታትስቲክስ ) መርዳት እንደተቻለው፤ ሲሦ (1/3 )
የሚሆነው የሀገሪቱ ነዋሪ የቀን ገቢው፤ ከአንድ ብር በታች እንደሆነ መዝግቦታል። አራት ነጥብ ስድስት ከመቶ ( 4.6 %)
የሚሆኑ ህጻናት ወላጆቻቸውን አጥተው ዕጓለ ምውታን ሆነዋል። ይህ ስሌት፤ ወላጆች የሌላቸው ህጻናት ፤ ዘጠና ( 90 )
ሚሊዮን ከሚሆነው የሀገሪቱ ነዋሪ ውስጥ አምስት ከመቶ ( 5 % ) እጅ ማለት ነው። ከያንዳንዱ ስድስት (6) ህጻናት
ውስጥ አንድ አንድ ነፍስ-ወከፍ ልጅ ዕድሜው አምስት ( 5 ) ዓመት ሳይደርስ ይሞታል ይባላል። ይህ ሃቅ፤
እንዲያው በደፈናው፤ ያለውን ስዕል ለማሳየት ቢጥርም፤ በበርካታ ሚሊዮኖች የሚቆጠረው የሀገሪቱ ዜጋ በርሃብ ፤
በበሽታና በዕርዛት እየተጎዳ ለመሆኑ አሊ የሚባል አይደለም ። በገጠርና በከተማ የሚኖሩት ዜጎች ድኅነታቸው ተመሳሳይ
ሆኗል። ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ደግሞ፤ በኢትዮጵያና በሕዝቦቿ ስም ከውጭ የሚመጣው ርዳታና ትብብር ፤
ከፍተኛውን ቅጥር የያዘ ሆኖ፤ ተጠቃሚዎቹ ግን የገዥው መደብ አባሎች ብቻ መሆናቸው ነው ። 2
የማነኛውም ሀገር ችግር የሚመነጨው ከተፈጥሮና ከሰው-ሰራሽ ጥፋቶች እደሆነ ይታመናል ። ከተፈጥሮ አደጋ
የሚመጡትን ችግሮች፤ የሀገሬው ነዋሪ ተባብሮ ለመቋቋም ይጥር ይሆናል ። በሰው ኅይል ትብብርም ሆነ በሳይንስና
ቴክኒዎሎጂ ርዳታ ሊያሰወግዳቸው ይችልም ይሆናል ። ሰው ሰራሽ ችጎሮችን ግን ለማስወገድ ቀርቶ ለመቋቋም
የሚደረገው ጥረት ቀላል አይሆንም። ችግሩን ለማስዋገድ የሚደረገው ጥረት ከባድ ሊሆን የሚችልበት ምክንያት፤ ሆን
ተብሎ በዕቅድም ሆነ ባለማወቅ በሰው ሰራሽ የሚፈጸሙ ጥፋቶች ውስብስብ ስለሚሆኑ ነው ።
የሀገራችንን ጂኦግራፊያዊ አቀማማጥ፤ በግምት ወስጥ አስገብቶ፤ የአየር ጠባዩን ተስማሚነት፤ የአፈሩን ለምነት፤ የታላላቅ
ወንዞቻችንን ብዛት፤ በዓመት የሚገኘውን የዝናብ መጠን፤ የኢትዮጵያ ገበሬዎች የሥራ ብርታትና ታታሪነት፤ የአዝርቱ፤
የአትክልቱ፤ የዕጽዋቱ፤ የዕህል ሰብሉን ትሩፋት፤ ስንገመግም ፤ የሀገራችን ሕዝብ የዕህል ዕጥረት ያጋጠመዋል ተብሎ ማሰብ
ቀርቶ መጠርጠር አይቻልም ነበር ። ያለመታደል ሆኖ ፤ ተጨባጩ ሁኔታ የሚያሳየው ግን ይህን ሃቅ ነው ። ረሀብና
ጠኔ፤ ድኅነትና ስደት፤ አሁንም የኢትዮጵያ ሀገራችን ብሄራዊ መለያ ሆኖ እንደቀጠለ ነው ። ይህንን ቅስም- ሰባሪ
መለያችንን በግድ መለወጥ አለብን !
የሀገራችንን የተፈጥሮ መልከዐ ምድር ( የጂዖግራፊ አቀማመጥ ) ለነዋሪዎቿ ያደለውን ትሩፋት በአንድ በኩል፤ በሌላ
በኩል ደግሞ የፖለቲካ መልከዐ ምድር ( ላንድስኬፕ) አድረገን ስናነጻጽር፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በድኅነት መኖሩ
እንቆቅልሽ ይሆንብናል። የፖለቲካ መልከዐ ምድሩ፤ የሕዝብ፤ ለሕዝብና ፤ በሕዝብ መንግሥት እጅ እስካልሆነ ድረስ፤
የማንኛውም ሀገር የተፈጥሮ ሀብትና ንብረት ኖረ አልኖረ፤ የሚያመጣው ፋይዳ አይኖረውም። ከእኛ ተመክሮ አልፎ
የአያሌ ባለጸጋ ሊሆኑ የሚችሉ የነባር የአፍሪካ ሀገሮችን ዕጣ ይመለከቷል። የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ምኅዳር በሕዝባዊ መንግሥት
ማዕቀፍ ውስጥ አስካልተካተተ ድረስም፤ የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ለዜጎቿ ጠቀሜታ ይውላል ብሎ ማሰብ የዋኅነት
ነው። በሕዝብ ፈቃድና ውሳኔ ያልተመሠረተ ስርወ- መንግሥት፤ ለሕዝብ ጥቅም ደንታ ይኖረዋል ተብሎ የሚታሰብ
አይሆንም ። ሁሉ ሞልቶ ተርፎ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ እስከ ዛሬ ድረስ ከድኅነት ቀንበር ነጻ ያልወጣበት ዓይነተኛ
ምክንያት፤ በመንግሥት ሥልጣን ላይ የሚፈራረቁ ቡድኖች ሁሉ ለራሳቸው ጥቅም እንጂ ለሕዝቡ ኑሮና ህይወት ደንታ-
ቢሶች በመሆናቸው ብቻ ነው።፡
ሌላው ይቅርና ላለፉት ስባ አራት ( 74 ) ዓመታት በተፈራረቁት ሥር ዓቶች ውስጥ የመንግሥት ሥልጣን
የጨበጡትን የሦስት ገዥዎችን ድርጊት እንኳን ብንገነዘብ፤ ሕዝብን ከመበዝበዝና ከመጨቆን በቀር ያመጡት ፋይዳ
አልነበረም። አሁንም የለም። በነኝህ 74 ዓመታት ውስጥ እያደገ ያለፈው ትውልድ እንደተገነዘበው፤ ከአያት ቅድመ-አያቱ
የተወራረሱትን አስከፊ የኑሮ ደረጃ የሚለውጥ የመንግሥት አስተዳደር አልተከሰተለትም ። የሦስት ሥር ዓት ለውጦች፤
የኢትዮጵያን ሕዝብ መሠረታዊ ችግሮች መለወጥ ቀርቶ መቅረፍ እንኳን አልቻሉም ። እንዲያውም ችግሮቹ ሁሉ
እየተባባሱና እየከበዱ ከመሄድ አልተገቱም ።
ከስዩመ -መለኮት እስከ ደርግ ሶሻሊዝምና ከዚያም አልፎ የወያኔ ዘረኛ አገዛዝ ቢገለባበጡና ቢከረባበቱ፤ የኢትዮጵያ
ሕዝብ ሁለንተናዊ ችግሮች እየተባባሱ ከመሄድ በስተቀር ሊሻሻሉ የሚችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር አልተቻለም ። እያላት
እንደሌላት የሆነች፤ አግኝታ እንዳጣች፤ ታድሏት እንደተነፈገች፤ የሁሉ ጌታ ሆና፤ እንደ መንጢ ደሃ የምትልምን፤ ሞልቷት 3
-ተርፏት ለሌሎች መለገስ ስትችል፤ ርጥባንና ምጽዋዕት የምትጠይቅ ሀገር፤ ኢትዮጵያ እንደሆነች ዜጎቿ ገና አልተረዱትም
ማለት አይቻልም ። " አብዛኛው ዜጋ ፤ ስለ ሀገሩ ጉዳይ ጆሮው ዕቅጩን ለመስማት ስለማይፈልግ፤ እውነትን እየሸሻት
ይሄዳል ። ይኅንን ማድረግ ደግሞ ፤ ኢትዮጵያዊ ኩራት ስለሚመስለው ራሱን እያታለለ ይኖራል ። " የሚል
ምጸትና ሽሙጥ እንዳይሰነዘርብን ከፈለግን፤ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን/ያት ለችግራችን ዘላቂ መፍትሄ ለማግኘት
ቆርጠን መነሳት አለብን ።
እስካሁን ድረስ፤ በሥልጣን ኮረቻ የተቀመጡ ገዥዎች ሁሉ፤ ነገር እንደበላ ጠበቃ ሕዝብን ከማታለል ያለፈ መልካም
ሥራ ሰርተው አይታወቁም። የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ፤ የራሄልን ጩኸት እያሰማ ቢኖርም፤ ገዥዎቹ ግን የናቡከደነጾርን
ኅልም እየመገቡት ይኖራሉ። በሽክላ እግር ላይ የተመሰረተ የመንግሥት ሥርዓት፤ እንደሚንኩታኮት ግን ከታሪክ ሊማሩ
አልቻሉም ። በሥልጣናቸው በሚቆዩበት ጊዜ ሲስግድላቸው የነበረው ሁሉ፤ ነገ ቀን ሲከዳቸው፤ ስቀሎ ! ስቀሎ ! እያለ
እንደሚሳለቅባቸው አይረዱትም ።
ይኽም የሚሆነው፤ በአመዛኙ፤ የሥልጣን ወንበር፤ ጣዕሟ ከማር ወለላ የበለጠ ጣፋጭ በመሆኑ ነው። ሥልጣን፤ ቀናተኛ
ስለምታደርግ፤ የሥልጣን ጥመኛው ሁሉ አብሮ ከሥልጣኑ ጋር ይጠፋል እንጅ፤ በህይወቱ እያለ በፈቃዱ ከሥልጣኑ
ሊወርድ አይችልም ። ይህንን ሀቅ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለፉት 74 ዓመታት በሚገባ ተረድቶታል ። የዐጼው ሥር ዓት
እድሜ ጠግቦ ሲሄድ፤ የደርግ አገዛዝ ደግሞ፤ እንዳበደ ውሻ ተክለፍልፎ ጠፋ ። ወያኔም የእነርሱ ዕድል እንደሚገጥመው
አያጠራጥርም።
ደግሞ፤ የቁልቁለት መንገድ ቀላል መሆኑ ቢገመትም፤ ብዙ ጊዜ፤ እያንደረደረ ወደ ጉድጓድ የሚያስገባ መሆኑን መገንዝብ
ይገባል ። የወያኔ ጉዞ የቁልቁለት መንገድ ነው። በኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ግፊት፤ ወደ ማይቀርለት ጉድጓድ መግባቱ
አይቀርም ። የኢትዮጵያም ሕዝብ ትግል አቀበቱን ወጥቶ የድል አክሊሉን እንደሚጨብጥ ታጋዮች ሁሉ ያምናሉ። እዚህ
ግብ ለመድረስ ግን፤ ትግሉ፤ ምሉዕ- በኩለሂ ማለት፤ፈርጀ- ብዙ ችሎታ ባላቸው አመራሮች መመራት ይኖርበታል ።
ሁለንተናዊ ችሎታንና ብቃትን፤ የሕዝቡንም ተዓመኔታና ትብብር ያገኘ የነጻነት ትግል፤ ግቡን የማይመታበት ምክንያት
ሊኖር አይችልም ። " ዕግረኛ ያወራውን ወሬ፤ ፈረሰኛ አይደርስበትም" እንዲሉ፤ በወያኔ ፕሮፓጋንዳ ሳይፈቱ፤ አንድነትን
አጠንክሮ፤ የጠላትን ማንነት መርምሮ፤ የራስን ምሥጢር ጠብቆ ፤ ከባዕዳን ሰላዮች ተጠንቅቆ ፤ በዓላማ ጽናት ተማምኖ
ከታገሉ፤ የመጨረሻውን ግብ መምታት ይቻላል ። ተጋጋዥ የሆኑ ትብብሮችን ማቀናጀት አስፈላጊ እንደሆኑም ማመን
አስፈላጊ ነው ። ግብታዊና አመራር - አልባ ትግል የትም አያደርስም ። ብሶትህ ብሶቴ ፤ ችግርህ ችግሬ፤ ሀገርህ አገሬ
ወዘተርፈ... ብሎ መነሳት የዓላማ አንድነትን ለማግኘት ይረዳል ። ከጨለምተኝነት ይልቅ ፤ ብሩህታዊነትን (
ኦፕቲምዝም)ን አንግቦ መታገል የውስጥ ጥንካሬን ይሰጣል ። በዓላማቸው ጸንተው የሚታገሉ ሁሉ፤ መቸውንም ጊዜ
ቢሆን ፤ "ጨለማ ከዋጠው ሸለቆ መጨረሻ ፤ የብርሃን ወገግታ እንደሚኖር " ያምናሉ ። ተስፋ መቁረጥ፤ የልፍስፍስነትን
ባኅርይ የሚያስተናግድ ሰው ጠባይ በመሆኑ፤ ዓላማን አንግቦ መጓዝ ፤ የቁርጠኝነትን ስብዕና የያዘ ሁሉ ያውቀዋል ። "
ወይ ፍንክች ያባ ቢላዋ ልጅ ! " እንዲሉ። 4
ሀገራችንን አሁን ከገባችበት የድህነት አዘቅት ለማውጣት፤ ምሰሶና ማገር የሆኑትን ሀብቶች መጅመሪያ እንድ ታሳቢነት
መመልከት ይገባል ። እነርሱም የሀገሪቱ የተፈጥሮ/ እምቅና ተንቅሳቃሽ ሀብቶችን ተብለው ሊጠቀሱ ይቻላሉ ።
1. ከላይ በዝርዝር እንደሰፈሩት፤ የሀገሪቱ ጂኦግራፊ ያቀፈው ልዩ ልዩ የደለበ ሀብት አለ። ይህ ያልተነካና ያለተቀመሰ ዕምቅ
ሀብት ለዘመናት የበይ ያለህ! የተጠቃሚ ያለህ ! በማለት ሲጮህ ኖሯል ። አሁንም ይህንን ጩኸቱን እንደቀጠለ ነው። ይህ
በከርሰ ምድሯና ከመሬቷ በላይ ያለው ተዝቆ የማያልቅ ሀብት ለነዋሪዎቿ ጥቅም ሊውል ይገባል ።
2. ኢትዮጵያ ፤ ቁጥሩ ዘጠና ( 90 ) ሚሊዮን የሚገመት የሰው ኅይል/ ሀብት አላት። ይህ ግዙፍ ኀይል የማይናቅና
የማይነጥፍ ሀብት ነው ። ሰራተኛና ታተሪ ሕዝብ ደግሞ ፤ ዕምቅም ተንቀሳቃሽም ሀብት በመሆኑ፤ ሀገሪቱን ከድኅነት ደረጃ
አውጥቶ፤ ከባለፀጋዎቹ የዓለም ሕዝቦች ተርታ የማያሰልፍበት አንዳችም ምክንያት ሊኖር አይችልም ። ስለ አንድ ሀገር
ሕዝብ፤ ሀብትም ሆነ ኅይል በሚጠቀስበት ጊዜ፤ የሀብቱ አንድ አካል አንድ አምሳል ሆኖ የሚሰላው፤ የሕዝቡ ታሪክ፤
ባኅል፤ ዕምነት፤ ሥልጣኔ፤ ቋንቋ፤ ፊደልና ሥነ ጽሁፍ፤ ሙዚቃና የመሳሰሉትን ሁሉ ያካትታል ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ፤
የእነኝህ ዝርዝር ሃብቶች ሁሉ ባለቤት በመሆኑ፤ ለብልጽግናው ዋስትና ብቻ ሳይሆኑ፤ ለወደፊት ዕድገቱም እመርታ ሰጭና
አንቅሳቃሽ ኀይል ናቸው ።
3. ሀገሪቱ፤ ትክክለኛ ቁጥሩ በአሃዝ ሊነገር የማይቻል፤ የተማረ የሰው ኀይል አላት። የኢትዮጵያ ምሁራን ፤ በልዩ ልዩ
የሙያ መስክ ሠልጥነው ሰፊ ተመክሮን በማካበት ያሉ ናቸው ። ብዙዎቹ ችሎታውን በዓለም አቀፍ መድረክ
አስመስክረው ባዕዳንን በማገልገል ላይ እንደሆኑ ይታወቃል :፡ የተማረ የሰው ኅይል ያለው ሕዝብ፤ ለዕድገቱና
ለሥልጣኔው በሚያደርገው ግስጋሴ ፤በልዩ ልዩ የሙያ መስክ የሰለጠኑ ምሁራን ከፍተኛ ዕመርታ እንደሚያመጡ
የሚያከራክር አይሆንም ። ማነኛውም ኢትዮጵያዊ ምሁር፤ በሠለጠነበት ሙያ ፤ ከባዕድ ሀገሮች ይልቅ፤ የራሱን ሀገርና
ሕዝብ ማገልገሉን ይመርጥ ነበር ። ግን ይህን ዕድል አላገኘም ። የወቅቱ የሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ እንደሚያሳየው፤
የኢትዮጵያ ምሁራን ፍልሰት በሚያስደነግጥ ፍጥነት እየጨመረ በመሄድ ላይ ይገኛል ። ሁኔታው እስካልቆመ ድረስ ደግሞ፤
ሀገሪቱ ሠላምና መረጋጋትን አግኝታ፤ ረሃብንና ችግርን ማስወገዱ ላይ ትኩረት ታደርጋለች ተብሎ የሚታሰብ አይሆንም ።
የተማረው ኅይል፤ ዕድል አግኝቶ ሀገሩን ማገልግል የሚችልበት ሁኔታ ከተመቻቸለት፤ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ችግሮች
ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት ፤ የተባ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይታመናል ።
እነኝህ በሦስት ረድፍ የተካተቱትን ብሄራዊ ሀብቶች አስተባብሮና አቀናጅቶ፤ በተግባር የሚተረጉም፤ ለሕዝብ የቆመ
ሥርዓት ከተመሠረተ፤ ረሀብና ድኅነት በሀገሪቱ ወስጥ ሊከሰቱ አይችሉም ። ይህ ዕውን ሊሆን ከተፈለገ ደግሞ፤ በቅን
ለሀገርና ለሕዝብ አሳቢ የሆነ መንግሥት የመመስረት ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ። የሀገሪቱ ብሄራዊ ሀብትና
ንብረት የሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች በዕኩል የመጠቀም መብታቸው እስከተረጋገጠ ድረስ፤ የበይ- ተመልካች ዜጋ ሊኖር
አይችልም። ሁሉ ሞልቶ ተርፏት ዜጎቿን የማታስርብ ሀገር ለማግኘት ከተፈለገ፤ በዘር ላይ የተመሰረተውን የወያኔን ሥርዓት
ማስወገዱ፤ የሁሉም ዜጎች የቅድሚያ ዓላማ ሊሆን ይገባል ። የኢትዮጵያ አንድነትና ነጻነት አስተማማኝ ሊሆን
የሚችለውም፤ በሁሉም ዜጎች ሙሉ ፈቃድና ትብብር የተመሰረተ መንግሥት ሲመጣ ብቻ ነው ።
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኖራለች
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment