BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

Thursday, 6 November 2014

መንግሥት የተቃዋሚ መሪዎችን እያደነ ማሰሩን ቀጥሎአል

ጥቅምት  (ሃያ አቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-ካለፉት ሁለት ቀናት ጀምሮ መንግስት በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የተቃዋሚ አመራሮችን በመያዝ እያሰረ ነው::  በትግራይ ክልል በምዕራባዊያን ዞን ቃፍታ ሁመራ ወረዳ ዳንሻ ከተማ የአረና ፓርቲ የማእከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ዘነበ ሲሳይ ጥቅምት 25፣ 2007 ዓም ከቤታቸው ተነጥለው በመወሰድ ሲታሰሩ፣  በተመሳሳይ ቀን በሁመራ የአረና የቁጥጥር ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ አማረ ተወልደ  ታስረዋል።
ከወራት በፊት የታሰሩትን አብራሃ ደስታንና አያሌው በየነን  ጨምሮ 7 የፓርቲው አመራሮች በእስር ላይ ናቸው።
በተመሳሳይ ቀን በአማራ ክልል ምዕ/ጎጃም ዞን ደጋ ዳሞት ወረዳ  የአንድነት ፓርቲ ሰብሳቢ አቶ ጥላሁን አበበ እና ሶስት የድርጅቱ አባላት ተይዘው ወዳልታወቀ ስፍራ ተወስደዋል።  ባለፉት ሶስት ቀናት ብቻ ከ10 ያላነሱ የአንድነት ፓርቲ አመራሮች በቁጥጥር ስር ውለዋል። የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች የሆኑት አንዱአለም አራጌ፣ ዳንኤል ሺበሺ፣ ናትናኤል መኮንንና ሃብታሙ አያሌው  በእስር ላይ መሆናቸው ይታወቃል።

የሰማያዊ ፓርቲ የብሔራዊ ምክር ቤት አባል እና የሰሜን ጎንደር የዞን ሰብሰቢ አቶ አግባው ሰጠኝም  እንዲሁ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ወዳልታወቀ ስፍራ ተወስደዋል። ሶስት የሰማያዊ ፓርቲ  የአርባምንጭ አመራሮች አሁንም ድረስ በእስር ላይ ናቸው።
በምእራብ ጎጃም  በፍኖተሰላም ከተማ  የወረዳው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ( መኢአድ) ሰብሳቢ የሆነው  ዘሪሁን ብሬ ረቡዕ ጥቅምት 26፣ 2007 ዓም ተይዞ ወዳልታወቀ ስፍራ ተወስዷል።
መንግስት መጪውን ምርጫ ተከትሎ ከአሁኑ የሚወስደው እርምጃ ተቃዋሚዎች በምርጫው ላይ ጠንካራ አቋም እንዲይዙ ሊያደርጋቸው ይችላል የሚሉ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ነው።
ትናንት 9 የፖለቲካ ድርጅቶች ‹‹ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ›› በሚል ለአንድ ወር የሚቆይ የመጀመሪያ ዙር የህዝባዊ ትግል ፕሮግራም ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ፓርቲዎቹ   በመጀመሪያ  የአንድ ወር ፕሮግራም ከሚፈጽሟቸው ጉዳዮች መካከል  በቤተ እምነት ጸሎት እንዲደረግ ጥሪ ማቅረብና አማኞች እንደየ እምነታቸው ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማድረግ ፣  የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባዎችን መጥራት፣ በሰላማዊ ሰልፍ የተቃውሞ ድምጾችን ማሰማት፣ በምርጫ ዙሪያ የፓናል ውይይቶችን ማድረግ እንዲሁም የህዝብን ተሳትፎ ማበረታታትና ድጋፍ ማሰባሰብ የሚሉት ይገኙበታል።

No comments:

Post a Comment