BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

Monday, 17 November 2014

ኢትዮጵያ በሰብዓዊ መብቶች ላይ የምትፈጽመውን ጥሰት ካላቆመች የአፍሪካ ህብረት መቀመጫውን ከአዲስ አበባ መቀየር አለበት ተባለ።


Imageኢትዮጵያ በሰብዓዊ መብቶች ላይ የምትፈጽመውን ጥሰት ካላቆመች የአፍሪካ ህብረት መቀመጫውን ከአዲስ አበባ መቀየር አለበት ተባለ። በደቡብ አፍሪካ ዊትስ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደ የአፍሪካ የምርመራ ጋዜጠኝነት ጉባኤ ላይ አንጎላዊው ጋዜጠኛ ራፋኤል ማርኩዌዝ ደ ሞራይዝ የኢትዮጵያ መንግስት ያሰራቸውን ጋዜጠኞች መፍታት አለበት ብሏል።

ራፋኤል ማርኩዌዝ ደ ሞራይዝ አንጎላዊ ጋዜጠኛ ነው። በሙያው በሃገሩ አንጎላ በርካታ ክስ እና እስር እንደገጠመው ይነገራል። ባለፈው ወር በደቡብ አፍሪካ ዊትስ በተካሄደው የአፍሪካ የምርመራ ጋዜጠኝነት ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽን ጨምሮ በሰብዓዊ መብቶች ላይ ጥሰት በመፈጸም ከአፍሪካ ህብረት ህልም በተቃራኒ ቆማለች በማለት ተችቷል። ''የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ በቀዳሚነት የመላ አፍሪካውያንን ህልም ይወክላል። የሰው ልጅ ክብር እና የሰብዓዊ መብት ክብር ደግሞ የሁሉም አፍሪካውያን የጋራ ህልም ነው። ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ የሰዎችን ሰብዓዊ መብት በመጣስ በተቃራኒው መንገድ እየተጓዘች ነው። ይህ ደግሞ የአፍሪካውያንን ህልም አይወክልም። የኢትዮጵያ መንግስት ያሰራቸውን ጋዜጠኞች በመፍታት ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ነጻነትን እንዲያከብር እና ዜጎች እና ጋዜጠኞች ህገ-መንግስታዊ መብታቸውን በተግባር እንዲያውሉ እንዲፈቅድ የአፍሪካ ህብረት ጫና ማድረግ ይኖርበታል። ''

ራፋኤል በጉባኤው የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎችን እስር እና ክስ እንዲሁም የቀድሞው ፍትህ ጋዜጣ አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝን የሶስት አመት ብያኔ በማሳያነት አንስቷል። አፍሪካውያን ጋዜጠኞችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ በቸልታ አልፈዋል ሲልም ተችቷል። ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብትን ማክበር ካልቻለች የአፍሪካ ህብረት ከአዲስ አበባ መነሳት ይኖርበታል ብሎ ያምናል።

''የተወሰኑ ጋዜጠኞችን አውቃለሁ። በ2005 ተኩስ ሲጀመር እና ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ሲታሰሩ በአዲስ አበባ ነበርኩ። አሁን በሃገሪቱ ስላለው ሁኔታ በቂ ግንዛቤ አለኝ። ከኢትዮጵያውያን ምሁራን እና አሁን ባለው መንግስት የተለያየ ጫና የደረሰባቸውን ሰዎች አገኛለሁ። የአፍሪካ ህብረትን ለመወከል በመጀመሪያ ሰብዓዊ መብትን የሚያከብር ሃገር እንፈልጋለን። ኢትዮጵያ ይህንን ማድረግ ካልቻለች እንደ አፍሪካዊነታችን የአፍሪካ ህብረት መቀመጫውን ዜጎች ራሳቸውን የመግለጽ እና ሰብዓዊ መብት ወደ ተከበረበት ሃገር እንዲዛወር መጠየቅ ይኖርብናል። ምክንያቱም ግለሰቦች የሚከበሩባት መንግስታት የህዝብ አገልጋይ እንጂ ከህግ በላይ ያልሆኑባት አጋርነት የጠነከረባት አፍሪካን እንሻለን። ኢትዮጵያ ደግሞ በአሁኑ ወቅት ይህን እያደረገች አይደለም። ''''

ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ባለፈው ሳምንት ባወጣው ዘገባ ባለፈው አመት ብቻ በኢትዮጵያ ስድስት የህትመት ውጤቶች ሲዘጉ ከ ሰላሳ በላይ ጋዜጠኞች መሰደዳቸውን ይፋ አድርጓል። በምህጻሩ ሲፒጄ ተብሎ በሚጠራው የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ተቋም መሰረት ደግሞ ቢያንስ 17 ጋዜጠኞች በኢትዮጵያ በእስር ላይ ይገኛሉ። ራፋኤል ማርኩዌዝ በእስር ላይ ያሉ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ አፍሪካውያን ሊተባበሩ ይገባል ሲል ይናገራል።

''አፍሪካውያን በሙሉ በተለይም ጋዜጠኞችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በትብብር ከሰራን የኢትዮጵያ መንግስት ቆም ብሎ ራሱን እንዲፈትሽ ማድረግ እንችላለን። አላማችን ኢትዮጵያን ማግለል አይደለም። አላማችን ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን እንድታከብር ሃሳባቸውን በነጻነት የመግለጽ መብታቸውን በመጠቀማቸው የታሰሩትንም እንድትፈታ ነው።''

 source http://www.dw.de/%E1%8A%A2%E1%89%B5%E1% ... a-18051929

No comments:

Post a Comment