የካቲት ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በቅርቡ በህገወጥ መንገድ በታገደው የአንድነት ለፍትሕና ለዲሞክራሲ አመራሮች ላይ ደህንነቶች ዛቻ፣ ማስፈራሪያና ማዋከብ እየፈጸሙ ነው።
የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የነበሩት አቶ አስራት አብርሀ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ባለፈው እሁድ ማታ መናኛ አለባበስ የለበሱ ሁለት ወጣቶች የተከራዩበት ቤት ድረስ በመሄድ “እንፈልገሃለን” እንዳሏቸው በመጥቀስ፤ “በዚህ ሰዓት የምትፈልጉኝ እናንተ ደግሞ እነማናችሁ?” ብለው ሲጠይቋቸው “ከደህንነት መስሪያቤት ነው የመጣነው ” እንዳሏቸውና መታወቂያ አውጥተው እንዳሳዩዋቸው ገልጸዋል።
መሽቶ ስለነበር በዚያ ሰዓት ሊያናግሩዋቸው ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ሲገልጹላቸውም መረጃ ፈልገው እንደመጡ መናገራቸውን የጠቀሱት አቶ አስራት፤ ምን ዓይነት መረጃ እንደፈለጉ ሲጠይቋቸውም “አቶ በላይ ፍቃዱ ከሀገር ስለወጣበት ሁኔታ የምታውቀው ነገር ካለ እንድትነግረን ነው።” እንዳሏቸው ገልጸዋል።
ይህን ተከትሎ የአንድነት ሊቀ-መንበር አቶ በላይ ፈቃዱ በአሜሪካን ሀገር ጥገኝነት ጠየቁ የሚል ዜና በሶሻል ሚዲያ በስፋት የተሰራጨ ሲሆን፤ ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት አቶ አስራት ግን በጉዳዩ ላይ መረጃ እንደሌላቸው፤ሆኖም ወሬው እውነት ነው ብለው እንደማይገምቱ ተናግረዋል።
አንድነት- በሀይል ለነ ትእግስቱ አወል ከተሰጠ በሁዋላ አቶ በላይን አግኝተዋቸው እንደማያውቁ የጠቀሱት አቶ አስራት ለደህንነቶቹም ይህንኑ እንደነገሯቸው ጠቅሰዋል።
<ጉዳዩ ግን በዚህ ብቻ አላበቃም>> የሚሉት አቶ አስራት፤ከቀናት በሁዋላ የቀበሌ ካድሬዎች የተከራየሁበት ቤት ድረስ ሄደው የቤቱን ባለቤት “የኪራይ ውል አለህ ወይ? መታወቂያውን ኮፒ አድርገሀዋል ወይ?” በማለት እንዳዋከቧቸው የገለጹት የቀድሞው የ አንድነት የሕዝብ ግንኙነት ሀላፊ፤ ከዚያም ስማቸውን መዝግበው መመለሳቸውን ተናግረዋል።
በሁኔታው የተበሳጩት አቶ አስራት፦ <<ፓርቲ መስርተህ ስትታገል ሊያጠፉህ ይፈልጋሉ፤ ቤትህ አርፈህ ስትቀመጥ ቤትህ ድረስ መጥተው ሰላም ይነሱሃል፤ ይሄን መዓት አውርድ እንጂ ሌላ ስም ልሰጠው አልችልም፤ መዓቱን ያውርድላቸው>> ብለዋል።
No comments:
Post a Comment