BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

Saturday, 7 February 2015

ኤርትራ ያቀረበችው የ‹‹ድንበር ይከለልልኝ›› ጥያቄ በአፍሪካ መሪዎች ውድቅ ተደረገ።


 ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ሲካሄድ በሰነበተው የአፍሪካ ኅብረት 24ኛ መደበኛ የመሪዎች ጉባዔ መጠናቀቂያ ላይ የኤርትራ መንግሥት አጀንዳ አስይዞ ነበር፡፡ በኮሚሽኑ ውሳኔ መሠረት የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር እንዲካለልና የኢትዮጵያ ወታደሮችም በኃይል ከያዙት የኤርትራ ግዛት እንዲለቁ ኤርትራ ጠይቃለች፡፡

በአፍሪካ ኅብረት የኤርትራ ተወካዮች ጥያቄውን በአምባሳደር አርዓያ ደስታና በአቶ ቢኒያም በርሄ አማካይነት ስታቀርብ፣ ከኢትዮጵያ ተወካዮች ምላሽ ተሰጥቶበት መጠነኛ ውይይት እንደተደረገበት፣ ስብሰባው ከተገኙት ምንጮች ለማወቅ መቻሉን ሪፖርተር ጽፏል፡፡
ኤርትራ ቀድማ አጀንዳ አስይዛ ያነሳችው ጥያቄ የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲሆን ነው፡፡ በተጨማሪም ድንበሩ እንዲከለልና የኢትዮጵያ ወታደሮች የኤርትራን ግዛት ለቀው ኤርትራ በሕግ የተሰጣትን መሬት እንድታገኝ ኅብረቱ ጫና እንዲፈጥር ጠይቃለች፡፡
የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ተወካዮች በጉዳዩ ላይ መጠነኛ ክርክር ያካሄዱ ሲሆን በዚሁ 24ኛ መደበኛ የኅብረቱ ጉባዔ ላይ የኅብረቱ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡ የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያን አቋም በመደገፍ ሁለቱም አገሮች ችግራቸው መፍታት ያለባቸው በውይይትና በመተሳሰብ መሆን እንዳለበት፣ እንዲሁም የነጮችን ይሁንታ መጠበቅ እንደሌለባቸው ገልጸው፣ ለኅብረቱ የቀረበው ጥያቄ አግባብነት የሌለው መሆኑን መናገራቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
‹‹ጉዳያችሁን ለሦስተኛ ወገን አሳልፋችሁ አትስጡ፡፡ ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የሰላም ሐሳብ በአዎንታ እንቀበለዋለን፡፡ መፍትሔውም እሱ ብቻ ነው፤›› በማለት ያቀረቡት ሐሳብ በመሪዎች ሙሉ ድጋፍና ከፍተኛ ጭብጨባ ተቀባይነት አግኝቶ ጉዳዩ መቋጨቱ ተገልጿል፡፡
የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ውዝግብ ይፈታል ተብሎ የተቋቋመው ዘሔግ የሚገኘው ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ ፍርደ ገምድል ነው በማለት በኢትዮጵያ ተቀባይነት ያላገኘ ሲሆን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የቀረበው ባለአምስት ነጥብ የሰላም ሐሳብ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተቀባይነት አግኝቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡

No comments:

Post a Comment