ጥር ፳፱(ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኦሮሞ ፌደራሊስ ኮንግረስ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ሙላቱ ገመቹ ፣ የክልል ምክር ቤት አባላትንና የተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ለማስመዝገብ በተንቀሳቀሱበት ወቅት አልጋና ምግብ እንዳያገኙ ተከልክለው እንደነበር ገልጸዋል።
ከደምብቢ ዶሎ ወደ ጊምቢ ሲሄዱ አይራ በሚባል ቦታ ላይ ለማደር አንድ ሆቴል ውስጥ አልጋ ለመያዝ ሲሞክሩ፣ ፖሊሶች ለሆቴሉ ባለቤት በመደወል አልጋ እንዳይሰጡዋቸው፣ ምግብም እንዳይሸጡላቸው ማዘዛቸውን ተናግረዋል። የሆቴሉ ባለቤት ከደህንነት መስሪያ ቤት ተደውሎ “ወንጀለኞች ናቸውና አባሩዋቸው” ተብሎ እንደተነገራቸው አቶ ሙላቱ አክለው ተናግረዋል።
ባለሆቴሉ ” ንግድ ቤቴን ይዘጉብኛል ብለው በመማጸናቸው” 4ቱም ሰዎች መኪና ውስጥ ለማደር መገደዳቸውን ገልጸዋል። በማግስቱ ጉሊሶ ወደምትባል ከተማ ሄደው ሆቴል ከያዙ በሁዋላ ምሽት ላይ የታጠቁ ፖሊሶች ወደ ክፍላቸው ገብተው ፍተሻ እናካሂዳለን በማለት ውዝግብ ፈጥረው እንደነበር አውስተዋል። ምርጫው ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ይሆናል የሚባለው ተረት ነው ያሉት አቶ ሙላቱ፣ ጉዳዩን ለምርጫ ቦርድ ማሳወቃቸውን ቢገልጹም፣ ኢህአዴግ ይህ የድርጅት ጉዳይ ሳይሆን ግለሰቦች ያደረጉት ነው በማለት ለማጣጣል መሞከሩን ተናግረዋል በሌላ በኩል ደግሞ በደቡብ ክልል የአንድነት የአመራር አባላት ታሰረዋል።
የምርጫ ቦርድ በአንድነት ፓርቲ ላይ የወሰደውን እርምጃ የተቃወሙ የቁጫ የአንድነት ሰብሳቢ አቶ ኢሳያስ ቱሉ ና አቶ ጌታቸው ኩየራ ተይዘው ሲታሰሩ፣ የስልጤ ዞን ሰብሳቢ አቶ ኢብራሂም ከድር ደግሞ ከስራ ተባረዋል። በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ የአንድነት ፓርቲ አባላት የምርጫ ቦርድን ውሳኔ በመቃወም ፔትሺን ተፈራርመው ለምርጫ ቦርድ አስገብተዋል። ሰማያዊ ፓርቲ እንደገለጸው ደግሞ ፤ምርጫ ቦርድ በአንድነት ፓርቲ ላይ ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ የቀድሞ የአንድነት አባላት በስፋት ሰማያዊ ፓርቲን እየተቀላቀሉ ይገኛሉ፡፡
ትናንት ጥር 28/2007 ዓ.ም በአምስት የምርጫ ወረዳ የተደራጁት የቀድሞው አንድነት ፓርቲ የቦረና ዞን መዋቅር ሙሉ በሙሉ ሰማያዊ ፓርቲን መቀላቀላቸውን የአንድነት መስራች፣ የምክር ቤት አባልና የዞኑ የፓርቲው አደራጅ የነበሩት አቶ ጌታቸው በቀለ ገልጸዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር የቡርጅና የሰሜን ቀጠና አስተባባሪዎችን ጨምሮ የቀጣናው መዋቅር በሙሉ ሰማያዊ ፓርቲን መቀላቀሉ ተመልክቷል፡፡ እንደ ፓርቲው ገለጻ፤ ጥር 26/2007 ዓ.ም የቀድሞው የአንድነት አመራሮች ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር መቀላቀላቸውን በመግለጫ ካሳወቁ በኋላ በአዲስ አበባና በሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ የቀድሞው የአንድነት አመራሮችና አባላት ያለማቋረጥ ሰማያዊ ጽ/ቤት ድረስ እየመጡ የአባልነት ቅጽ እየሞሉ ይገኛሉ፡፡
ሰማያዊን የተቀላቀሉት የአንድነትአመራሮችና አባላት፤ ገዥው ፓርቲና ምርጫ ቦርድ ፓርቲያቸውን አሳልፈው መስጠታቸው የተፈጠረባቸው ቁጭት፤ ይበልጥ ሰላማዊ ትግሉን አጠናክረው እንዲቀጥሉ እንደገፋፋቸው ተናግረዋል፡፡ ሙሉ መዋቅራቸውን ይዘው ወደ ሰማያዊ ፓርቲ የተቀላቀሉት የቦረናው አደራጅ አቶ ጌታቸው በቀለ፤ ገዥው ፓርቲና ምርጫ ቦርድ በፈጸሙት በደል ተስፋ ሳይቆርጡ እንደሚታገሉ በመጥቀስ ህዝቡም ተስፋ ሳይቆርጥ የቻለውን ሁሉ በማድረግ ከጎናቸው እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
No comments:
Post a Comment