BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

Saturday, 21 February 2015

ያ ትውልድ !

የካቲት 1966 ሲታወስ 
                                                                                (የካቲት 1966 ዓ.ም. 41ኛ ዓመት መታሰቢያ ምክንያት በማድረግ)

በምሥራቅ አፍሪካ ሊፈነጥቅ የድል ጮራ፤ ሕዝባዊ ጥያቄዎችን ከፍ አድርጎ በየአቅጣጫው የተንቀሳቀሰው ሕዝባዊ ዓመጽ፣ ለሕዝብ መብት ሕዝብ የጮኸበት፣ ብዝበዛ እንዲያበቃ ተበዝባዥ የተጠራራበት፣ ረሃብ ጩኸቱን ያሰማበት፣ የተራቡ ዓይኖች ማየት የጀመሩበት ድንቁርና መስማት የጀመረበት፣ ሀገሬ ኢትዮጵያ “ያገር ያለህ !” ያለችበት የካቲት 1966 ዓ.ም. ትውስታ አርባ አንደኛ ዓመት።


ኢትዮጵያ ሀገራችን የግዛት አንድነቷንና ሉዓሊዊነቷን በቆራጥ ልጆቿ ተጋድሎ ጠብቃ የኖረች መሆኗ ብቻውን ለሕዝቧ መብት፣ ለልጆቿ ዳቦ ሊሆን አልችል አለ። ለዘመናት ከፍ ብሎ የተውለበለበው የነፃነት አርማዋ የጀግኖች መኩሪያ ሰንደቅ ዓላማዋ ቀና ብለው ቢያዩት ወራሪን እንዳንበረከከው ግፍና መከራን ሊቋቋም አቃተው። ለአፍሪካ ጥቁር ሕዝቦች ኩራትና መመኪያ የሆነችው ሀገራችን ኢትዮጵያ ልጆቿን መንከባከብ አቃታት። ፍሬዋን ተመጋቢው፣ ሰብሉን ከታቹ፣ በዕንቁዋ ተዋቢው የሀገሪቷ እጅግ የተወሰነ ክፍል ሆነ። ሌላው በበይዎች መጎምጀትና የበይ ተመልካች ሆነ። ረሀብ ላጎሳቆለው “ደሀ በህልሙ ቅቤ ባይጠጣ ንጣት ይገለው ነበር” ተተረተለት። የሀገራችን አንድነት፣ ክብር፣ የሦስት ሺህ ዘመን ታሪክ የለገሰንን ተፈጥሮአዊ ሀብት ካልሰሩበት፣ ካልተጠቀሙበት ልማትና ዕድገትን አያመጣምና ኩራታችን በልመና፣ ክብራችን በረሃብ፣ መብታችን በረገጣ መሆኑ እየከፋ መጣ።

ኢትዮጵያ በውጭው ዓለም ያላት ታላቅነት የውስጥ ችግሯን ሊመለከት አቃተው። የአርሶ አደሩ ሞፈርና ቀንበር ከመሬት ራቁ፣ ከተሜው ዞር ቢል በሽታ፣ ቀና ቢል ረሃብ፣ ጎንበስ ቢል ዴንቁርና ከበውታል። የዜግነት መብት፣ ኢትዮጵያዊነት መብት፣ የሰውነት መብት አስፈላጊነታቸው ተዘንግቷል። ሴቶች ስለመብት መጠየቅ አስነዋሪ ነው። የሃይማኖት ልዩነት አስፈሊጊ ሆኗል። የብሔር/ብሔረሰቦች ጉድይ ተከርችሟል። ኢትዮጵያ ሀገራችን ወደ ልማትና ዕድገት ጎዳና ከመውሰድ ይልቅ ባላባትና ጭሰኛን መሠረት ያደረገ ኋላ ቀር ሥርዓት በሃይማኖትና በእምነት ማስፈራሪያነት ይቀጥል ዘንድ “ሰማይ አይታረስ ንጉስ አይከሰስ” “ስዩመ እግዚአብሔር” መልዕክቶች የንጉሡ አገዛዝ መመሪያዎች ሆኑ። ኢትዮጵያን በዓፄነት ከአስተድደሩት ነገስታት የየራሳቸው ጠንካራና ደካማ ጎኖች እንደተጠበቁ ከአንዱ ወደ ሌላው እየተሸጋገረ የመጣው ዘውዳዊ አገዛዝ በሕዝብ ዘንድ ምሬትን የወለደው፣ ዓመጽ አርግዞ ሕዝባዊ ዓመጽ የወለደው ልክ የዛሬ 41 ዓመት የካቲት ወር ነበር።

ወርሃ የካቲት በኢትዮጵያ ሕዝብ የትግል ታሪክ ሲዘከርና ሲታወስ ይኖራል። መሠረታዊ የሆኑ ለውጦች በሀገሪቷ ይሰፍን ዘንድ የሕዝቡ ብሶት ብሶቱ የሆነው የሀገሪቷ ተማሪ ግምባር ቀደም ሚና የተጫወተበትና ሰፊውን ድርሻ የያዘበት የየካቲት ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ሲነሳ ይታወሳል። ሴቶች እህቶቻችን ከማጀት ወደ አደባባይ በመውጣት ስለ ፆታ መብት የጮኹበት፤ የዓለም ሰብአዊ መብቶችን ህግጋት ሰነድ በመፈረም ቀዳሚ ሚና የተጫወተችው ሀገራችን የልጆቿንም ትመለከት፣ የፈረመችው ለዜጎቿም ያገልግል ተብሎ እስላሙና ክርስቲያኑ እጅ ለእጅ ለጋራ መብት የተያያዙበት፤ የከተሜው ላብ አደር፣ የመንግሥት ሠራተኛው፣ ታክሲ ነጂው፣ መምህራንና ወታደሩ በጋራ ለከፋው የኑሮ ውድነት መስተካከል የካቲትን ያደመቁበት፤ የሥርዓቱ መገርሰሻ ዋነኛ መፈክር “መሬት ለአራሹ” መሪ የሆነበት፤ እነሆ ወርሃ የካቲት 41ኛ ዓመት።

የዓፄ ኃ/ሥላሴ በአንፃራዊነት ከአሏቸው “ሰላማዊ” የአገዛዝ ዘመንና በውጭው ዓለም ከመሠረቱት ቀና የውጭ ግንኙነት አንፃር ሀገሪቱን ወደ ተሻለ የዕድገትና የልማት ጎዲና ለመውሰድ የነበራቸውን ሰፊ ዕድል ሊጠቀሙበት አልቻሉም። ኢትዮጵያ ያላትን ተፈጥሮአዊ ገጸ በረከት ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም ይውል ዘንድ መተለም ተሳናቸው። በባሊባቱና በአራሹ ገበሬ መሀል ያለው ልቅ ያጣ ብዝበዛንና ዘረፋን ከቶም መመልከት ተሳናቸው። የባላባቱና መኳንንቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ጋሻ መሬቶች ተቀራምተው የሚያደርጉት ዝርፊያ እንከን እንዳይገጥመው በሚያጉረመርሙና ይሻሻልን ጥያቄ በሚያነሱ አርሶ አደሮች ላይ የሚደርሰው ወከባና ስቃይ ሌላ ጥያቄን ይዞ ብቅ አለ። የሕግ የበላይነት፣ የመብት ጥያቄ። የሠራተኛው ክፍል ዝቅተኛ ደሞዝ ያለውን የኑሮ ውድነት መቋቋም አለመቻል የሚቀርቡ የደሞዝ መሻሻል ጥያቄዎች የጋራ ትግልን ጠያቂዎች በመሆናቸው ቀስ እያለ የመምህራን ማህበርንና የሠራተኛ ማህበራትን ማጠናከርን ተያያዙ። ተማሪዎች በዩንቨርስቲ ቅጥር ግቢያቸው ላነሱዋቸው መለስተኛ አስተዳደራዊ ጥያቄዎች ምላሽ ዱላ መሆኑ የተማሪዎቹን ማህበር እያጠናከረ መምጣት ብቻ ሳይሆን የሚነሱ ጥያቄዎች ፖለቲካዊ ይዘትን እየተላበሱ የሥርዓት ለውጥ ጠያቂዎች ሆኑ።

በዓፄው አገዛዝ ሥርዓት ውስጥ ያገለገለና የሥርዓቱን ብልሹነት የተረዳ የመጀመሪያውን የማስጠንቀቂያ ደወል በ1953 ዓ.ም. ወርሃ ታህሳስ ደወለ። በወንድማማቾቹ በብርጋዴል ጄነራል መንግሥቱና ገርማሜ ነዋይ እንዱሁም ላለች የእንቅስቃሴው መሪዎች መገደልና መታፈን ወቅቱን በድል የተወጡት የመሰሏቸው መኳንንትና ባላባት እንኳ በቀጣይነት “ምን መደረግ አለበት?” በሚል የሕዝብን ብሶትና ጥያቄ ለመመልከት ከመሻት ይልቅ መፍትሄው እመቃና አፈና ብቻ መሆኑን ቀጠለበት። ስለ ሕዝብ መብት ቀዳሚ በመሆን የተገደለው የጥላሁን ግዛው ደም ለየካቲት 1966 ዓ.ም. ሕዝባዊ አብዮት እርሾ ሆነ። የነማርታና ዋለልኝ የነ አሳምነውና አቤ ጉበኛ ራቅ ሲልም የነበላይ ዘለቀ ዓጽም ከመቃብር ጮኸ ! ለዓፄው አገዛዝና ለባላባቱ አሻፈረኝ አለ። እምቢኝ ለሀገሬ! እምቢኝ ለሕዝቤ! እንቢኝ ለሰንደቅ ዓላማዬ! ተጮኸ። እኔም ሀገር አለኝ፣ እኔም ባለሀገር ያለ ጀግና የዘውዲዊ ሥርዓቱን ነቀነቀው።
“ፋታ ስጡን” የመጨረሻው ሰዓት ሊይ አድማጭ አጣ፣ ደሞዝ ጭማሪው ደም ካፈሰሰ በኋሊ አላረካ አለ። የንጉሣዊ አገዛዝ መጨረሻው በየካቲት 1966 ተበሠረ።

የካቲት ይዞ የተነሳውን ሀገራዊና ሕዝባዊ ጥያቄ፣ የያ ትውልድ ጩኸት፣ ዕምቡጥ አበባ በሞት እና ሕይወት መካከል ተቀንጥሳ መጠውለግ ጀመረች። የዳሞክራሲ መብት የተጠየቀ መንግስት የመግደል መብት ሰጥቶ የየካቲትን እንቅስቃሴ መሪ ትውልድ በላ። የካቲት ጥይት ወለደ፣ የካቲት ደም አፈሰሰ፣ የካቲት ለሀገር የጮኹትን በሀገር ስም ቀበረ። የህብረብሔራዊነት ካባ መለያው ያደረገ ፋሺዝም ነገሰ። የየካቲትን አበባ አጠውልጎ ቀበረ። ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለበ ሀገሬ እየዘመረ ኢትዮጵያንና ልጆቿን የቀበረ የ17 ዓመት ወታደራዊ አገዛዝ ብርቅዬ ትውልድ ጨረሰ።

መሪ አልባ የነበረውን የየካቲት 66 ሕዝባዊ እንቅስቃሴ የወታደሩ ክፍል በመረከብ አቅጣጫውን እንዱስት ሲያደርገው ወራትም አልፈጁበትም። የፊውዳልን አገዛዝ በሰላም አስወገደ ተባለ “ያለ ምንም ደም…” የተዘመረለት አብዮት ቀጣይ አገዛዙን በደም ማዕበል ቀዘፈው። የዓፄ ኃይለሥላሴን ባለሥልጣናትንና ንጉሡን ያለፍርድ በመግደል የተጀመረው የደም ጠብታ ለማንም አላሳሳም። የደርግ ወጠጤ መለያ ዝማሬው “የፍየሌ ወጠጤ” ሆነ። በ120 መኮንንኖች የተመሠረተው ደርግ በውስጡ ያሉትን ለየት ያለ ሀሳብ አቅራቢዎችና ቅን ሀሳቢዎችን እየበላ የአንድ አምባገነን ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ግራዚያኒ መንግሥቱ ኃ/ማርያምን ወለደ። ያጨበጨቡለትን ሳይቀር እየቀበረ ሀገርና ልጆቿን የደም መሬት አድርጎ ፈረጠጠ። ትምህርትና ኑሮውን ለድሃው በመጮህ ፋና ወጊ የሆነውን አንድ ትውልድ በፋሺስት መንግሥቱ መሪነት በጥይት ተደበደበ። የኢትዮጵያ ተስፋ መነመነ።
የኢትዮጵያ ልጆች የሀገር ትርጉሙ እስኪጠፋቸው ታሠሩ፣ ተደበደቡ፣ ተሰቃዩ፣ በክላሽ ተረፈረፉ።

“ዳቦ ለተራበ !” ያለ ትውልድ ጥይት ተመገበ። “የሕዝብ መንግሥት? የጠየቀ ትውልድ የጥይት መንግሥት ተቸረው። “የዲሞክራሲ መብት” ብል የጮኸ ትውልድ የመግደል መብት በተቸራቸው ካዴሬዎች በየሜዳውና በየዱሩ ለአሞራና ለጅብ ተጣለ። የብሔር/ብሔረሰቦች መብት ይከበር ያለ ዜጎች እስከ ቄያቸው ቦንብ ዘነበሊቸው። “ልጄን” ብላ የተከተለች እናት አብራ ተገደለች። የካቲት ለሞት የታደለ ትውልድ ትዝታው ሆነ። “ቢወቀጥ አጥንቴ ቢንቆረቆር ደሜ” ያለ ትውልድ በጨካኝ ፋሽስቶችና ባንዲዎች የዘመረው ሰመረለት። አጥንቱን ወቀጡት ደሙንም ጠጡት።

«ያ ትውልድ ተቋም» የየካቲት ሕዝባዊ እንቅስቃሴን 41ኛ ዓመት ስንዘክር ወቅቱ ይዟቸው የተነሳውን ምላሽ ያላገኙትን የህዝብና የሀገር ጥያቄዎች በማስታወስ ነው። ለህዝባቸው መብት መከበርና ለሀገራቸው ክብር ሲለ “የትግል ነው ሕይወቴ” ብለው ክቡር ሕይወታቸውን ለቆሙለት ዓላማ የሰዉ ወገኖቻችንን በማስታወስ ነው። በ17 የደርግ አገዛዝ የስቃዩ ሰለባ የሆኑ እናቶች አባቶች ሕፃናትን በአጠቃላይ በከተማም በገጠር ያለ ቤተሰቦችን ስቃይና ሰቆቃ በመጋራት ነው። “ፋኖ ተሰማራ” ብላችሁ በዱር በገደሉ ለምትወዷት ወገናችሁና ሀገራችሁ ስትታገሉ የወደቃችሁ ወገኖች ሁሌም እናስታውሳችኋለን። ታሪካችሁ ምንጊዜም ህያው ነው። ሕይወታችሁ ውስጣችን አለና የካቲትን ስናስታውስ እናንተን ከተራራው ጫፍ አድርገን ነው። የትግል ችቦዎች ናችሁ። እንኮራባችኋለን።

ያ ትውልድ አነባ 
ታግለን እንዳልታሠርን 
ጥለን እንዳልወደቅን 
ሞተን አፈር ጭረን 
ቧጠን እንዳልወጣን 
ግርፉ ሽ….ባ አዴርጎን 
ቅርጫ ሁነን ቆስለን 
ለሕዝብ ነው ትግለ! 
ለሕዝብ ነው ዴለ! 
እያልን እንዳልነጎድን 
በጽናት የቆሙት እናጅሬ እገሌ
እንደው እንዳለሌ? 
ምንም እንዳልሰራን፤ ሳልስት አልባ አርጋችሁ 
የአርበኞቹን ሥራ ታሪክ ቀደዳችሁ 
እነማን ነበሩ? ታሰኙናላችሁ። 
“ቢወቀጥ አጥንቴ፤ ቢንቆረቆር ደሜ”ን 
በፋሺስቶች አረር፤ ወይ ግንባር ደረትን 
ተራራ አንቀጥቅጡን የከፍቶች ራሥ 
ከኢትዮ ጅቡቲ እስከ ሱዲን ድረስ 
ያ! ታላቁ አድማ፤ ያ! ታላቁ ሤራ 
ከራስ ካሣ አንስቶ እስከ ራስ ዱሜራ 
ጥልቅ ዓላማ ይዘን መሪው ኮከብ ጠፍቶ 
ያለ ግብ ዓላማ ይቀራል ወይ ከቶ? 
ወይ እንደ መርከቡ ኮምፓስ እንደሌለው 
መሀል ውቅያኖስ አቅጣጫ እንዳሳተው 
ያውሎ ነፋስ ውዥቀት ማዕበል ያሰከረው 
ውሉ እንደጠፋበት የት እንዲሁ መድረሻው 
የዛ የህልም ዓለም ይህ ነው መጨረሻው? 
ዑ…ዑ….ዑ...እውነትም ! አ…መ…ጽ…ካ…ጋ…ተ…ው…ጡ…ት…ሽ…የ…ጠ…ባ… የ…ወ…ለ…ድ…ሽ…ው…ያ…ት….ው…ል…ድ…አ…ነ…ባ….ዑ…ዑ…ዑ… 
ስንቱን ያሳየናል ዘመንና ዕድሜ 
እንዲህ ሆኖ ቀረ “ቢወቀጥ ! አጥንቴ፤ ቢንቆረቆር ! ደሜ” ። 

አባሪውን ግጥም በድምጽ ያድምጡ https://www.youtube.com/watch?v=FCGcSRpa_a4 «ያ ትውልድ ተቋም» ድረ ገጽ ፡ www.yatewlid.org, www.yatewlid.com ኢሜሌ ፡ yatewlid@yahoo.com, yatewlid@gmail.com, yatewlid@hotmail.com

No comments:

Post a Comment