ሳውዲ አረቢያ ቢሻ እየተባለ የሚጠራ አነስተኛ ከተማ ውስጥ አንዲት ኢትዮጵያዊት የቤት ሰራተኛ በሳውዲያዊ አሰሪዋ ከተተኮሰባት ጥይት ከሞት መትረፏን ምንጮች አረጋገጡ። በዚህች ኢትዮጵያዊት ላይ ስለደረሰው የነፍስ ማጥፋት ጥቃት በኢህአዴግ ተመልምለው የተሰየሙት ዲፕሎማቶች ምንም ዓይነት መረጃ የላቸውም፡፡
አደጋው የደረሰባት ወጣት በ20ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ መሆኗን የሚናገሩ የዜናው አቀባዮች ወጣቷ እንደተራራ የገዘፈውን ህይወት በመጋፈጥ ቤተስቦቿን ከችግር ለመታደግ በወቅቱ ከነበሩ የኤጀንሲ ደላላዎች ጋር ተዋውላ ሳውዲ አረቢያ ለስራ መምጣቷን ይናገራሉ።
በተጠቀሰው ውል መስረት ወጣቷ አሰሪዋ የወር ደሞዝዋን በየወቅቱ እንዲከፍላት ለማስረዳት ብትሞክረም ከኢትዮጵያ ከመጣች ጀምሮ ላለፉት ሁለት አመት ያለደሞዝ ለመቆየት መገደዷን ለመረዳት ተችሏል። ሰሞኑን ኢትዮጵያዊቷ የቤት ሰራተኛ የሁለት አመት ኮንትራት ውሏን መጨረሷን ተከትሎ አሰሪዋ ደሞዝዋን በአግባቡ አስቦ እንዲከፍላት ጥያቄ ብታቀርብም በንግግሯ የተበሳጨው ሳዑዲያዊ ከመሳቢያ ሽጉጥ በማውጣት ኢትዮጵያዊቷን የቤት ሰራተኛ ለመግደል አከታትሎ እንደተኮሰባት የሚናገሩ እማኞች ወጣቷ በሁለት ጥይት ተመታ እንደወደቀችና በአካባቢው ሰዎች ትብብር በተለምዶ መሊክ አብደላ እየተባለ ወደሚጠራ ሆስፒታል በመውሰድ ህይወቷን ለማትረፍ ተችሏል ብለዋል።
ጅማ ውስጥ ተወልዳ እንዳደገች የሚነገርላት ይህች ወጣት ሳውዲ አረቢያ ውስጥ ጉዳዩን የሚከታተልላት ዘመድና ቀባሪ የሌላት በአሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ደላሎች እምነት ጥላ የሳውዲ አረቢያን ምድር ከረገጠች ወዲህ ከማንም ጋር በቴሌፎንም ሆነ በአካል እንዳትገናኝ በአሰሪዎችዋ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግባት ስለነበር ወጣቷ ከሃገር ይዛ የመጣቸው የቤተሰቦችዋ የስልክ አድራሻ በአሰሪዎቿ በመነጠቁ ረዳት የሌላቸውን እህት ወንድሞቿን መርዳት ቀርቶ በህይወት መኖራቸውን እንኳን በትክክል እንደማታውቅ ይነገራል።
በአሰሪዋ ጥይት ህይወቷ ከመነጠቅ ተርፋ ሆስፒታል የገባችው ኢትዮጵያዊት ወጣት በአሁኑ ሰአት ያለችበትን የጤንነት ሁኔታ የሆስፒታሉ የምርመራ ውጤት በትክክል ባይገልጽም የጥይት አረሩ ከሰውነቷ መውጣቱን ማረጋጋጥ ተችሏል። ወንጀሉን የፈፀመው ሳዑዲያዊ አሰሪ ላይ ምንም አይነት እርምጃ ባለመወሰዱ ወጣቷ ሊገለኝ ይችላል በሚል ስጋት በጭንቀት እንቅልፍ በማጣት ላይ መሆኗን እና “ከሆስፒታል አውጡኝ፤ ሃገሬ ውስዱኝ” እያለች በኦሮምኛ ቋንቋ ስትማጽን ተሰምታለች።
የኢትዮያዊቷን ትክክለኛ የሃገር አድራሻ ለማወቅ አስሪዋ ፓስፖርቷን እንዲሰጥ ቢጠየቅም እስካሁን ፈቃደኛ አለመሆኑ ከአካባቢው የመጡ መረጃዎች ጠቁመዋል። ይህ ዜና እስከ ተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ለዜጎች ህይወት ደንታ የሌላቸው ሪያድ እና ጅዳ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዲፕሎማቶች አደጋ ስለደረሰባት ወጣት ምንም አይነት መረጃ እንደሌላቸው ማረጋገጥ ተችሏል።
ቀደም ሲል በኤጀንሲ ደላሎች ወደ ሳውዲ አረቢያ ከገቡ በመቶ ሺህ ከሚቆጠሩ እህቶች ውስጥ ገሚሱ የወር ደሞዛቸው በአሰሪዎቻቸው ተነጥቆ ግፍ እና በድልን ተሸክመው ለአገራቸው ሲበቁ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ዜጎች ሳውዲ ውስጥ ያሉበትን ሁኔታ በትክክል መግለጽ እንደማይቻል ይነገራል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ከወራት በፊት ወደ ሳውዲ አረቢያ ለጉብኝት መጥተው እንደነበር የሚነገርላቸው አፈጉባዔ አባዱላ በኮንትራት ሰራተኞች ዙሪያ ከሳውዲ አረቢያ መንግሥት ባለስልጣናት ጋር ለመነጋገር ያደረጉት ሙከራ እንዳልተሳካ የሚገልጹ ታዛቢዎች የዜጎችን መብት የሚያስክብር ሁለትዮሽ «ኦፊሴላዊ» የጋራ ውል በሌለበት የኮንትራት ሰራተኞችን ወደ አረብ ሃገራት ለመላክ ለተወካዮች ምክርቤት እንደሚቀርብ የሚጠበቀው የሰራተኛ እና አሰሪ አገናኝ ረቂቅ ህግ ሃላፊነት የጎደለው ከዜጎች መብትና ጥቅም ይልቅ ቱባ ባለስልጣናትንና ተላላኪዎቻቸውን ኪስ ክቡር በሆነው የዜጎቻች ህይወት ለማደለብ የሚደረግ ሩጫ መሆኑን በጉዳዩ ላይ ቅርበት ያላቸው አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።
No comments:
Post a Comment