BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

Thursday, 27 February 2014

አቶ አለማየሁ አቶምሳ ከክልሉ ፕሬዚዳንትነትና ከኦሀዴድ ሊቀመንበርነት ለመልቀቅ ደብዳቤ እንዳሰገቡ ተደርጎ በክልሉ መንግስት የተሰጠው መግለጫ ሃሰት ነው ተባለ



የካቲት ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የኦህዴድ ከፍተኛ አመራር በክልሉ ፕሬዚዳንት በአቶ አለማየሁ አቶምሳ ቢሮ ውስጥ የተፈጠረውን ጉዳይ በዝርዝር ለኢሳት አስረድተዋል።

አቶ አለማየሁ ከኦህዴድ ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ጋር የካቲት 10 ቀን፣ 2006 ዓም በክልሉ ውስጥ ስለሚታየው የመልካም አስተዳደር መበላሸትና የህዝብ ሮሮ፣ ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ በመጣው ሙስና እንዲሁም በድርጅቱ ጎጠኛ አሰራር ዙሪያ እርሳቸውን ከሚቃወሙዋቸው ሌሎች የኦህዴድ ባለስልጣናት ጋር  ከጧት ጀምሮ  እስከ ምሽቱ 3 ሰአት ድረስ ግምገማ ሲያደርጉ ውለዋል፡፡

ብዙዎቹ የድርጅቱ አባላትና አባ ዱላ ስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ከፍተኛ ቦታዎችን ይዘው የነበሩት ባለስልጣናት በአቶ አለማየሁ ግምገማ ባለመደሰት ከአቶ አለማየሁ ጋር ውዝግብ ውስጥ የገቡ ሲሆን፣ አቶ አለማየሁም ህመማቸው ከሚፈቅደው በላይ ድምጻቸውን እያወጡ ከአንዳንዶች ጋር ሲጨቃጨቁ ውለዋል።
በማእከላዊ ከሚቴ አባላት መካከል የተነሳው ውዝግብ እየከረረ ሄዶ አቶ አለማየሁ ስብሰባውን ምሽት ላይ ለመበተን የተገደዱ ሲሆን፣ ስብሰባው እንደተጠናቀቀም ሁሉም የምክር ቤት አባላት ቢሮውን በፍጥነት ለቀው ሲወጡ የኦህዴድ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊና የህወሃት የኦህዴድ ወኪል ተደርገው የሚቆጠሩት ወ/ሮ አስቴር ማሞ  ብቻ በጽህፈት ቤታቸው ቀርተዋል።
ወ/ሮ አስቴር አቶ አለማየሁን ” አትወጣም እንዴ?” ብለው ሲጠይቋቸው አቶ አለማየሁ ምንም ምላሽ ባለመስጠታቸው፣  ወ/ሮ አስቴር በድንጋጤ፣ አምቡላንስ በማስጠራት ገርጂ ወደሚገኝ አንድ ሆስፒታል እንዲላኩ አድርገዋል። ሆስፒታሉም በአስቸኳይ ወደ ውጭ መላክ እንዳለባቸው በመግለጹ፣ አቶ አለማየሁ ወዲያውኑ ወደ ውጭ ለህክምና ተልከዋል።
የአቶ አለማየሁ ህመም ለህይወታቸው አስጊ መሆኑ እንደታወቀ የኦህዴድ ማእከላዊ ኮሚቴ  በማግስቱ ተሰብስቦ አቶ አለማየሁ ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው እንደለቀቁ አድርጎ ደብዳቤ በመጻፍ፣ ለመንግስት የመገናኛ ብዙሀን በትኗል።
አቶ አለማየሁ በከፍተኛ ህመም መሰቃየታቸው እውነት ቢሆንም፣ ከስልጣን ለመልቀቅ ያስገቡት ደብዳቤ ግን የለም።
ቀድሞውንም  በግለሰቡ አመራር ያልተደሰቱት ሰዎች ቦታውን ለመያዝ ከፍተኛ ሩጫ ካደረጉ በሁዋላ፣ የአባዱላ ደጋፊ እንደሆኑ የሚታመኑት አቶ ሙክታር ከድር ስልጣኑን ተረክበዋል።
አቶ አለማየሁ ስልጣን በያዙ ማግስት በምግብ መመረዛቸውን አንዳንድ የኦህዴድ ባለስልጣናትን በመጥቀስ ኢሳት በወቅቱ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣  የእርሳቸው የግል ጠባቂ የሆነው ግለሰብም፣ እርሳቸው ከታመሙበት ቀን ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ በተመሳሳይ ህመም እየተሰቃየ እንደሚገኝና ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ህመሙ ጸንቶበት ገርጂ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ውስጥ እየታከመ ይገኛል።
አቶ አለማየሁ ስልጣን በያዙ ማግስት በክልሉ የሚታየውን ሙስና አጻዳለሁ በሚል አዲስ እንቅስቃሴ ቢጀምሩም ረጅም ርቀት ሳይጓዙ ለበሽታ ተዳርገዋል። እርሳቸው ከታመሙበት ጊዜ ጀምሮ ክልሉን ምክትሉ አቶ አብዱላዚዝ መሐመድ ሲመሩት ቆይተዋል።
የአቶ ሙክታር ከድር የድርጅቱ ሊቀመንበር ሆኖ መመረጥ ለህወሃት ትልቅ እፎይታ መሆኑን የውስጥ ሰዎች ይናገራሉ።
አቶ አለማየሁ ተሽሎአቸው ወደ አገር የሚመለሱ ከሆነ፣ በአዲሱ ሹም ሽር ግራ ሳይጋቡ እንደማይቀሩ ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ።

No comments:

Post a Comment