(ክፍል አንድ)
ናትናኤል ካብቲመር (ኦስሎ ኖርዌይ)
አርእስቴን በጥቂቱ ያልኩበት ምክንያት የተነሳሁበት ርእስ ምን ያህል ሰፊ እንደሆነ ስለማውቅ ነገር ግን ልንወያይበት እንደሚገባ በመረዳቴ ለውይይት መክፈቻ ይሆን ዘንድ እንጂ እኔ ባለኝ እውቀት ብቻ ሙሉ በሙሉ ልተነትነው እንደማልችል በማመኔ ነው። ይህም ቢሆን እንደዜግነቴ ሃገሬን ለዘመናት ለተቆራኛት የድህነት ችግር መንስኤና መፍትሄ ሊሆኑ ይችላሉ ብዬ ያሰብኳቸውን ዋና ዋና ነጥቦች በመጠኑ ለመተንተን ለመሞከር ነው።
በአንድ ሃገር ወይም አካባቢ የሚኖር ማህበረሰብ ለግላዊም ሆነ ማህበራዊ ፍላጎቶቹ በበቂ ሁኔታ መሟላት አጣጥሞና አስማምቶ በእኩልነት ሊያኖረው የሚችል ህግና ስርዓት በብዙሃኑ ፍላጎትና ስምምነት ላይ ተመስርቶ መቀረፅ አለበት። የሰውን ልጅ ከእንሰሳት የሚለየውና የተሻለ ያደረገውም አንዱ ሌላውን በእኩልነት ማየቱ እንዲሁም ሰው በጉልበቱ የበላይ መሆን የማይችልበት ሁናቴ መፈጠሩ ነው። ነገር ግን አንድ ጉልበተኛ ሌላውን አቅመ ደካማ በጉልበትና በማስፈራራት ፍላጎቱን ከተጫነው ከሰውነት ደረጃ ወርዶ በሰውና በእንስሳ መሃከል ሆነ ማለት ነው። ለዚህም ነው የሰብዓዊ መብት መነሻ ሃሳቡ ሰውን ሁሉ እኩል አድርጎ የማየት ላይ የተመሰረተው።
እንግዲህ ከላይ እንደጠቀስኩት ለአንድ ሃገር ወይም ማህበረሰብ የኑሮ ግብዓቶች መሟላት ማህበረሰቡን አንድ የሚያደርገው በብዙሃኑ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ህግና ስርዓት መኖሩ ነው። የእያንዳንዱ ግለሰብ ለተቀረፀው ህግና ስርዓት በመገዛት የሚያደርገው የግል አስተዋፅኦ የማህበረሰቡን አባላት ፍላጎት ከማሟላቱም ባሻገር በመተባበር ክድህነት ወደተሻለ የኑሮ ደረጃ ያሸጋግራል። ይህም ስኬት የሚገኘው ማህበረሰባዊ ወይም ሃገራዊ ህጉ በእኩልነት ላይ ሲመሰረት ነው። ጤናማ የሆነ እኩልነት መኖር በዜጎች መካከል የምርት ፣ የሞያና የክህሎት ፍሰት ፈጥሮ የዛን ሃገር ወይም ማህበረሰብ መሰረታዊ ፍላጎቶች ብቻ ሳይሆን የኑሮ እርካታን የሚፈጥሩ ተጨማሪ ፍላጎቶችንም ወደ ማሟላት ሊሻገር ይችላል።
ነገር ግን ልክ እንደ አሁኑ የአትዮጲያ መንግስት የወጡትና የሚወጡት ህጎች አቀራረፃቸው እንዲሁም አተረጓጎማቸው ለተወሰነ የማህበረሰብ አካል በአድሎአዊነት ከተንጋደዱ በዜጎች ወይም በጠቅላላ ማህበረሰቡ መካከል ፍትሃዊ የሆነ እኩልነት ከማስፈን ይልቅ የእርስ በእርስ ቂምና ግጭት በመፍጠር ሃገርን ከድህነት ለማውጣት ወሳኝ ግብዓት የሆነውን “በጋራ የማደግና የመግባባት እሴት” ያመነምናል። የዚህ የህግ አተረጓጎም መጣመም ጥቂቶችን ብቻ ጠቅሞ ብዙሃኑን ስለሚጎዳ የሃገር ሁለንተናዊ ብልፅግና ገላጭ የሆነው የወል እድገት ይቀጭጭና የድህነት አዙሪት ይፈጠራል።
አሁንም ሃገራችንን የተቆራኛት ይኸ ችግር ነው። ከዚህ አስከፊ ችግር ለመውጣት ወሳኝ ግብዓቶች ናቸው ብዬ ያሰብኳቸውን ዋና ዋና የ ሃገራዊ መዋቅር መሰረቶች በተናጠል እንደሚከተለው ለማስቀመጥ ልሞክር።
ማህበረሰባዊ አንድነት
ማህበረሰባዊ አንድነት በአንድ ሃገር የሚኖሩ ዜጎችን በመግባባትና በመዋደድ እርስ በእርስ የሚያስተሳስር እንደ ሀግ የተፃፈም ሆነ ያልተፃፈ ነገር ግን በዜጎች መካከል የመንፈስ አንድነት የሚፈጥር ጠንካራ የሆነ የሃገራዊ መዋቅር እሴት ነው።ማህበራዊ አንድነት በሃገራችን ከቅርብ ግዜ ወዲህ እየተገፋ ከሄደበት አዲስ የአመለካከት ጠርዝ ማለትም “ማህበረሰባዊ አንድነት የሚኖረው ተመሳሳይ ብሄር ፣ ዘር ወይም ሃይማኖት ላላቸው ሰዎች ነው” የሚባለው ውስን እይታ እንደ ኢትዮጲያ ያሉ የበርካታ ብሄርና ብሄረሰቦች ያሏት ሃገር ሁለንተናዊ ብልፅግና የማይበጅ በዜጎች መካከልም ተከባብሮና ተዋዶ አብሮ ሰርቶ የማደግን ትልም የሚንድ ፣ ምርታማነትን አቀጭጮ ሃገራችንን ጥልቅ የድህነት አዙሪት ውስጥ የሚጨምር ክፉ የአመለካክት ደዌ ነው።
ማህበረሰባዊ አንድነት ለብሄራዊ አንድነት የጀርባ አጥንት ነው። ቢሆንም የአንድን ሃገር አንድነት በማጠንከርም ሆነ በማበላሸት በኩል የዛ ሃገር መንግስታዊ አወቃቀር ወሳኝ ግብዓት መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ነፃ በሆነ የብዙሃን ህዝብ ምርጫ ስልጣን የጨበጠ መንግስት የሃገር አንድነት ስጋት እምብዛም አይኖርበት ይሆናል ነገር ግን በመፈንቅለ መንግስት ወይም በጦርነት ስልጣን ላይ የወጣ መንግስት አገራዊ አንድነትን በዘላቂነት ከማረጋግጥ አንፃር የከበደ ችግር ሊያጋጥመው ይችላል።
ይህንን የከበደ ችግር በሁለት አቅጣጫ ላስቀምጠው።
የመንግስት ስልጣኑን በጉልበት የያዘው ቡድን የተመሰረተው በርእዮተ አለም መመሳሰልና መግባባት ከሆነ ስልጣኑን ለማደላደል የተቀረውን ህዝብ በርእዮተ አለም በመከፋፈል የራሱን የተመረጠና ለዛች ሃገር ሁነኛ መሆኑን ለማሳየት ይጥራል ከቻለም በህዝቡ ውስጥ በማስረፅ ተከታዮችን ለማፍራት ይጥራል ወይም ከባሰበት በአምባገነናዊነቱ ይቀጥላል።
በሌላ መልኩ ደግሞ የመንግስት ስልጣኑን በጉልበት የያዘው ቡድን የተመሰረተው በዘር ላይ ከሆነ ስልጣኑን ለማደላደል የተቀረውን ህዝብ በዘር ላይ በተመሰረት የፖለቲካ አይዲዮሎጂ ይከፋፍላል። ይህኛው ከላይ ከጠከስኩት እጅግ የከፋ ሃገርን ሊከፋፍል የሚችል እንዲሁም የሃገራዊና ማህበራዊ አንድነት ፀር የሆነ አደገኛ አካሄድ ነው። ለምሳሌም በኢትዮጲያ የሰፈነው ዘር ላየ የተመሰረተው የፖለቲካ ፓርቲዎች አደረጃጀት ከተወሰነ ግዜ ወዲህ እየፈጠረ ያለው እንድምታ በሃገራችን እንጭጭ የፖለቲካ ባህል ከጅምሩ የጥላቻ ስሜት ከመፍጠሩም ባሻገር የሃገራችንን የወደፊት የፖለቲካ ባህል ወደ አሳሳቢ ደረጃ ምን ያህል እንደገፋው ልብ ይሏል።
በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ አንዱ ካንዱ የመማር እና በመከባበር ላይ የተመሰረተ የሃሳብ መለዋወጥ ሊኖር ግድ ነው። ይህም ደግሞ በዛ ማህበረሰብ ውስጥ እኔ አቅልሃለው እንዲሁም እኔ የምለውን በግድ ተቀበሉኝ የሚል የተፅእኖ ስሜት ሳይኖር ማንኛቸውም ውሳኔዎች የአብዛኛውን የማህበሩን አባላት ፍላጎት በሚዛናዊነት ሊያሟላ በሚችል መልኩ የውሳኔ ሃሳብ አመንጭዎችን እይታ (perspective) በአክብሮት ማስተናገድ አለበት። ነገር ግን የአንድ ግለሰብ ወይም ቡድን የበላይነት ከሰፈነ አስተዳደራዊ ውሳኔዎች ከዚሁ ቡድን ወይም ግለሰብ ጥቅምና ፍላጎት አንፃር ብቻ ይሆኑና የጋራ ብልፅግና በእጅጉ ይጎዳል።
በዚህ ዘመን የአለማችን ህዝቦች በልዩነት ተዋዶ አብሮ የመኖር መንፈስ ጠንካራ ደረጃ ላይ ያደረሱት ሲሆን እንዲሁም በርካታ ፍፁሞ የተለያየ ባህል ፣ ቋንቋና እሴቶች ያሏቸው ሃገራት በጋራ ፍላጎት ላይ የተመሰረቱ ህብረቶችን እየፈጠሩ ሃገራቸውንና ህዝባቸውን ተጠቃሚ እያደረጉ ይገኛሉ። በሚያሳዝን መልኩ ደግሞ እንደ ኢትዮጲያ ያሉ አምባገነናዊ ስርዓት የተጫናቸው ሃገራት ለስልጣን ቆይታ አንድነትን ከማጠናከር ይልቅ ህዝባቸውን በጎሳ እየለያዩ የስልጣን እድሜያቸውን ለማራዘም ሲጥሩ እየተስተዋሉ ነው።
በጠነከረ ማህበረሰባዊ አንድነት ላይ ተመስርቶ ስለሚገኝ አመርቂ የሃገር እድገት አንድ ጥሩ ምሳሌ ላቅርብ በ1940ዎቹ የሁለተኛው የአለም ጦርነት በእጅጉ የጎዳትና በርካታ ወጣቶቿ በጦርነት ያለቁባት ጃፓን ማህበረሰብ በቁርጠኛነትና በፅኑ ሃገር ወዳድነት ላይ የተመሰረተ ሁሉን አቀፍ ሃገራዊ እቅድ ከጦርነቱ ማብቂያ ማቅስት ለማውጣት ተስማሙ። በ 1950 ያስቀመጡት እቅድ እስከ 10 አመት ግዜ ውስጥ በጨርቃ ጨርቅ ምርት ከአለም አንደኛ መሆን ነበር ሆነላቸው። እንደገና በ1960 ከአለም በብረታ ብረት ምርት አንደኛ ለመሆን አቀዱ በ 1970 ተሳካላቸው። እንደገና በ1970 ከአለም በመኪና ምርት አንደኛ ለመሆን አቀዱ ተሳካለቸው። እንደገና በ1980 በኤሌክትሮኒክስ ምርት አንደኛ ለምሆን አቀዱ ተሳካላቸው። ለነዚህ ሁሉ ተከታታይ አመታት በቁርጠኝነት ለፍተው ሃገራቸውን አሳደጉ። አሁን ጃፓን ምን አይነት የእድገት ደረጃ ላይ እንዳለች ሁላችንም እናውቃለን። በአንድ ወቅት የኢትዮጲያ ኢኮኖሚ ከጃፓን ኢኮኖሚ እኩል ነበር ሲባል ሰምቻለሁ ምንም እንኳን ይህ ነው የሚባል መረጃ ባይኖረኝም ሆኖም ከሆነ እኛ መላ ቅጥ በሌለው የፖለቲካና የርስ በርስ ጦርነት ስንታመስ እነሱ ግን ማህበረሰባዊ አንድነት ላይ በተመሰረት የሃገር እድገት ውጥን የት እንደደረሱ አሁን ያሉበትን ደረጃ አይቶ መረዳት ይቻላል።
የሃገር እድገት ያለውን ማህበረሰባዊ ጥቅም የገባቸው እንደ ጃፓን ያሉ ሃገራት እንደዚህ ሲያድጉ በአንፃሩ ደግሞ እንደ ኢትዮጲኣያ ያሉ የተወሰነ ቡድን ፍላጎት ማሟላት ላይ የተመሰረተ አምባገነናዊ ስርዓት ያላቸው ሃገራት በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ የሚሰነዘሩ አንፃራዊ አማራጭ ሃሳቦችን አለመቀበል ብቻ ሳይሆን የአንፃራዊ ሃሳብ አመንጪውን ቡድን ፣ ማህበር ወይም ግለሰብ ሰብአዊ መብትን በእጅጉ በሚጥስ መልኩ ማሰር ፣ ማንገላታት እንዲሁም ከሃገር ማባረርና ህይወትን እስከመንጠቅ ይደርሳሉ።
የዚህም የጉልበት ሚዛን ባለው ግለሰብ ወይም ቡድን በሌላው አማራጭ ሃሳብ አመንጪ ግለሰብ ወይም ቡድን ላይ ይዞት በተነሳው ሃሳብ ሳቢይ ጉዳት ሲደርስበት የሚመለከቱ የተቀሩት የማህበረሰብ አባላት ለጋራ እድገት የሚበጅ አመለካከት ቢኖራቸውም አንኳን ለሚደርስባቸው ነገር እርግጠኛ ስለማይሆኑ ያላቸውን አመለካከት በግልፅ ከማውጣት ይቆጠባሉ ለሃገር ከማሰብ ይልቅ ለግላቸው ወይም ለቡድናቸው ብቻ ማሰብ ይጀምራሉ። ለሃገር ቢያውሉት ከፍተኛ ጥቅም ሊያስገኝ የሚችለውን እውቀታቸውንና ጉልበታቸውን ወይ ለባዕድ ሃገር ያውሉታል ወይም ደግሞ ጥቅም ላይ ሳይውል ባክኖ ይቀራል።
በዚህም ሳቢያ አቅም ያለው የማህበረሰብ አካል ሌላውን ሊጠቅም የሚችልበትን እንዲሁም ሃገር ከዜጎቿ ልትጠቀመው የሚገባትን በእጅጉ ያስቀራል፡ ይህ ደግሞ ማህበረሰባዊ የሆነ የወል እድገትን ፣ ማህበረሰባዊ መተሳሰብና አንድነተን እንዲሁም ለሃገርና ለህዝብ የመቆርቆር ስሜትን ቀስ በቀስ ሸርሽሮ ሊያጠፋውና ሃገርና ህዝብን መጠኑ የሰፋ የድህነት አዙሪት ከመክተት ባለፈ የሀገርን ጨርሶ የመበታተን አደጋ ሊያስከትል ይችላል።
ሰብዓዊ መብትና እኩልነት
ከላይ በዝርዝር ያስቀመጥኩት የማህበረሰባዊ አንድነት ሙሉ በሙሉ በእኩልነት ላይ ተመስርቶ ባይሆንም እንኳን በ አንፃራዊ መልኩ የኑሮ ህበረት ያላቸው ሃገራት ቀጣይ አጀንዳቸው የሚሆነው ለሁለንተናዊ ማህበረሰባዊ እድገት ወሳኝ የሆነው በእኩልነት ላይ የተመሰረት የዜጎች ሰብዓዊ መብት ማረጋገጥ ነው። እንደው ለፅሁፌ ዝርዝር አቀራረብ እንዲሚቸኝ ብዬ ነው እንጂ ሰብዓዊ መብት መከበርና እኩልነት የህብረተሰባዊ አንድነት ቁልፍ አካል መሆኑን ልብ ይሏል። ምንም እንኳን እውነተኛ ዲሞክራሲ እጅግ ፍፁም የሆነና የጠለቀ መሆኑ እንዲሁም ትርጉሙና ፍፁም የሆነ ተግባራዊነቱ አሁን ባሉት የአለማችን መንግስታት “በዚህ ሃገር እንዳለው” ለማለት ሙሉ ለሙሉ የሚያስደፍር ባይሆንም በንፅፅር ከመጥፎ እስከ እጅግ በጣም የተሻለ እያልን መመዘን እንችላለን። ምንም እንኳን በዲሞክራሲ ተግባራዊነት ዙሪያ የጠለቀ ትንተና ባላቀርብም የተውሰኑ ግብዓቶቹን ለተነሳሁበት ወሳኝ የዲሞክራሲ አካል ለሆነው የዜጎች ሰብዓዊ መብትና እኩልነት ስል በመጠኑ ነካካዋለሁ።
ባለፈው ምዕተ አመት ማለትም ከ1900 እስከ 2000 ባሉት መቶ አመታት በጉልበትና ዕብሪት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ስልጣን ወይም ርእዮተ አለም የበላይነት ማግኘት ሳቢያ ወደ መቶ ሚሊዮን የሚጠጋ ህይወት እንደጠፋ የታሪክ መዛግብቶች ያስረዳሉ። የዚሁ ሁሉ መነሻ አንዱ ካንዱ በግድና በጉልበት የበለጠ ለመሆንና አንዱ ቡድን የሚከተለውን የፖለቲካ ርዕዮተ አለም በግድ በሌሎች ሃገራት ወይም ማህበረሰቦች ላይ ለማስረፅ በመነሳቱ ነው። አሁን በርካታ የአውሮፓ ሃገራት ያንን ሁሉ አልፈው የሚስማማቸውንና የሚያስማማቸውን የሃገር አስተዳደር ርዕዮተ አለም እንዲሁም የዜጎች ሰብዓዊ መብት የተረጋገጠበት እጅግ በጣም የተሻለ የሚባል የዲሞክራሲ ስርዓት ፈጥረዋል። ዜጎቻቸውም የዚሁ መልካም ስርዓት ፍሬ የሆነውን ከድህነት ነፃ የሆነ የኑሮ ደረጃ ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚያስደፍር ደረጃ ተጎናፅፈዋል።
እነዚህ ሰብዓዊ መብት በበቂ ሁኔታ የተረጋገጠባቸው ሃገራት ብዙ ነገር ካጠፋባቸው በውሃላ በብዙ ጥረት ያረሙትን ስህተት እንደ ኢትዮጲያ ያሉ በጉልበተኞች የሚተዳደሩ ሃገራት በፓርላማ ደረጃ እየተስማሙ ስህተቱን ሲደግሙት ይታያል። የተለመደው ብሂላችን “ብልህ ከስህተቱ ይማራል” ቢሆንም የተሻለ ብልህ ደግሞ ከሌሎች ስህተት መማር ይገባዋል እላለሁ። በኢትዮጲያ የሰብዓዊ መብትን ያዘቀጡትና የዜጎችን እኩልነት ጥያቄ ውስጥ የከተቱት ከብሄራዊ ጥቅም አንፃር የሚነሱ ጠቃሚ ሃሳቦችን ከቡድናቸው ወይም ከጎሳ ጥቅም አንፃር የሚመነዝሩ የሃገር አመራሮች ስልጣኑን መቆጣጠራቸውና የሃሳቡን አመንጪዎችንና የደጋፊዎችን ፍላጎት ማፈናቸውና መጫናቸው እንዲሁም ለተለያየ እስርና እንግልቶች መዳረጋቸው ነው።
የሰብዓዊ መብቱ የተጣሰና እኩልነቱ ያልተከበረለት ማህበረሰብ ሃገርን ከድህነት ለማውጣትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው የጋራ ጥረት ከመሳተፍ ይቆጠባል እንዲሁም የችግሩ ተጠቂ ያልሆነ የማህበረሰብ አካልም ቢሆን የሰውን ልጅ መሰረታዊ መብት ከሚጥስ መንግስት ጋር ለመተባበር አይነሳሳም። ዜጎችም የሃገር ልማት ላይ ከመሳተፍ ይልቅ መብታቸውን ለማስከበር ትግል ይጀምራሉ። መብት የማስከበር ትግሉ ዘርፍ እየበዛ ሲሄድ ተነጋግሮ መግባባት ጭራሽ ይጠፋና ዲሞክራሲያዊ የሆነ አሳታፊ የወል እድገት ህልም ሆኖ ይቀራል። ይህ ደግሞ ሃገርን ማለቂያ የሌለው የድህነት አዙሪት ውስጥ ይከታል።
የሚቀጥለውን በክፍል ሁለት ይመልከቱ . . . . .
የኢትዮጲያ የድህነት አዙሪት መንስኤና መፍትሄዎች “በጥቂቱ” (ክፍል ሁለት)
በክፍል አንድ ፅሁፌ ሃገርንም ሆነ ዜጎችን ከድህነት አዙሪት ለማውጣት አስፈላጊ ስለሆኑት ስለ ማህበራዊ አንድነት እንዲሁም ስለ ሰብዓዊ መብትና እኩልነት አንዳንድ ነገር ብያለሁ የቀሩትን ዋና ዋና ነጥቦች ደግሞ እነሆ።
የዜጎች ነፃነት
የዜጎች ነፃነት ዘርፈ ብዙ መገለጫ አለው። የዜጎች ነፃነት ለሃገር ሁለንተናዊ እድገት ሌላው ወሳኝ ግብአት ነው። በጥቅሉ የዜጎች ነፃነት ጥሩ የሆነ ደረጃ ላይ ደረሰ የሚባለው በፖለቲካዊም ሆነ በማህበራዊ ዘርፍ አንፃራዊ የሆነ ነፃነት ሲሰፍን ነው። በነዚህ ሁለት ዘርፎች ነፃነት አለው የመባል ደረጃ የደረሰ ማህበረሰብ ከሌሎች በእጅጉ የተሻለ ምርታማነትን የማሳደግም ሆነ ከድህነት የመላቀቅ እድል አለው። ለመተንተን እንዲመች ፖለቲካዊና ማህበራዊ ነፃነትን ለየብቻ ላስቀምጣቸው።
ሀ.ፖለቲካዊነፃነት
ዜጎች በሃገራቸው ፖለቲካ ውስጥ በግልም ሆነ በቡድን የሚንቀሳቀሱበት ፣ ለሃገራቸው ይጠቅማል ብለው ያመኑበትን ሃሳብ በተለያዩ መድረኮች ወይም ሚዲያዎች የሚገልፁበትን አሰራር እንደመንግስት የተቀመጠው ቡድን ወይም አካል የመቅረፅ ሃላፊነት አለበት። የዚህ አይነት አሰራር አለመኖርና የዜጎች የፖለቲካ ነፃነት ታፍኖ እንደወንጀል መቆጠር ለሃገር እድገትና ምርታማነት የመረባረብና የመጨነቅ ባህልን ከዜጎች አመለካከት ያጠፋና ከፍተኛ የሆነ የፍርሃት ስሜት በጠቅላላ ማህበረሰብ ላይ እንዲሰፍን ያደርጋል።
ከዚህ መሰል የአፈና ስርዓት ከሚፈጥረው ፍርሃት በመጠኑም ቢሆን የተላቀቁ የማህበረሰብ አባላት ለሃገር ምርታማነትና እድገት ቢውል ይህ ነው የማይባል ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚኖርውን አቅማቸውን ፣ እውቀታቸውን አንዲሁም ግዜና ገንዘባቸውን ባስ ሲልም ህይወታቸውን ለዜጎች የፖለቲካ ነፃነት መከበር ይሰዋሉ። በተቃውሞ ሰልፎችና የፖለቲካ ክርክሮች የበርካታ ዜጎች ውድ ግዜ ይባክናል። እንደ ኢትዮጲያ መንግስት ያሉ አምባገነኖችም የመብት ጥያቄዎችንና አማራጭ ሃሳቦችን የሚያመነጩ አካላት ማስራቸውን ፣ ማዋከባቸውን ባስ ሲልም እንደህዝብ ጠላት መቁጠራቸውን ይቀጥላሉ። እዚህ ደረጃ ላይ ነው እንግዲህ የፖለቲካ ነፃነት መጥፎ ደረጃ ላይ ደረሰ የሚባለው።
የዜጎች የፖለቲካ ነፃነት አለመከበር የአንድን ሃገር የፖለቲካ ምህዳር ያጠባል እንዲሁም ከፖለቲካ በተያያዘ የፍርሃት መንፈስ ያነግሳል። ይህ ደግሞ ሰፋ ካለ የፖለቲካ ምህዳር ከሚሳተፉ አቅም ያላቸው ዜጎች የሚመነጩ ሁነኛ የሃገር እድገት አምጪና ምርታማነትን አሳዳጊ እይታዎች ከናካቴው እንዲጠፉ ያደርጋል። ሃገርም በተወሰኑ ግለሰቦች ወይም ቡድን አመለካከትና ፍላጎት ብቻ መመራት ትጀምራለች። ከዚህ መሰል ሃገራዊ አመራር ዜጎችን ከድህነት አዙሪት መላቀቅ መጠበቅ በአንድ እጅ እያጨበጨቡ ድምፅ መጠበቅ ማለት ነው።
ለ.ማህበረሰባዊነፃነት
በአንድ ሃገር ወይም አካባቢ ተሰብስበው የሚኖሩ ማህበረሰቦች በሃገር ወይም መንግስት ደረጃ ከተደነገገው ህግ ባሻገር ሲወርድ ሲዋረድ የኖረ ያልተፃፈ ህግ አላቸው። ማህበረሰባዊ ነፃነት በጥቅሉ የዛ ማህበረሰብ አባላት ውስጥ አንዱ ያንዱን አመለካከት፣ ግላዊ ማንነት እንዲሁም እምነት የሚያከብርበት የተፃፈም ሆነ ያልተፃፈ የነፃነት መርህ ነው። ይህ የማህበረሰብ ነፃነት ለፖለቲካ ነፃነት እንደ አይነተኛ ግብዓትም ያገለግላል። ዜጎች የተለያዩ ፖለቲካዊም ሆነ ማህበራዊ አጀንዳዎችን እያነሱ በተዘጋጁም ሆነ ባልተዘጋጁ የማህበራዊ የውይይት መድረኮች ተቃራኒ ሃሳቦችን በመከባበር ላይ በተመሰረተ ሁኔታ ሃሳቦችን የሚያንሸራሽሩበትና የሚከራከሩበት ፍላጎታቸውን በነፃነት ሌላውን ባለመጫን ወይም መብቱን ባለመጋፋት የሚገላለፁበትን ባህል ካጎለበቱ ፡ ይህም ባህል ሃገራዊ መልክ ከያዘና ወደ መንግስት ደረጃ ካደገ በውይይትና በበሳል ክርክር የተፈተነ ሃሳብ ነጥሮ ይወጣና ሃገርን የማሳደግ ህልም እውን ይሆናል።
ይህ ተቃራኒ ሃሳብን የማዳመጥና የማንሸራሸር ባህል ከማህበረሰብ ወደ መንግስት ደረጃ የማደግ ወይም ከመንግስት ወደ ማህበረሰብ የመስረፅ እድል አለው። ከማህበረሰብ ወደመንግስት የሚያድገው የዛ ማህበረሰብ አባላት ሁለንተናዊ ማህበረሰባዊ እድገት ለማምጣት በሚል ተነሳስተው በነፃነት የራሳቸውን መንግስታዊ አካል ሲያዋቅሩ ወይም በቀላል ቋንቋ መንግስታቸውን ሲመርጡ ነው። በዚህ መልኩ ለስልጣን የበቃ መንግስት የመረጠውን ህዝብ ለማገልገል ስለተነሳ የህዝቡን ነፃነት አያፍንም ባህሉን እንደጠበቀ ይቀጥላል። ነገር ግን እንደ ሃገራችን ኢትዮጲያ አይነት በህዝብ የተመረጠ መንግስት ማለት ምን አይነት እንደሆነ በታሪካቸው አጋጥሟቸው የማያቁ ሃገራት መንግስት ላይ የማህበረሰባዊ ነፃነት ባህልን ማሳደር እጅግ ከባድ ይሆንባቸዋል።
በጦርነት ወይም በመፈንቅለ መንግስት ወደ ስልጣን የመጣ መንግስት አብዛኛውን ግዜ በማንነትም ሆነ በሃሳብ ልዩነት ላይ የተመሰረቱ ነፃ የሆኑ ማህበራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ውይይቶች ባህልን አሳድጎ ወደ ህዝብ ሲያሰርፅ አይታይም። የሃገራችን መንግስት የሚያደርጋቸው የሃሳብ ነፃነትን የማፈን ሂደትና እንዲሁም አማራጭ ሃሳብ አመንጪና የመብት መከበር ጠያቂ አካላት ላይ የሚያደርገው ኢሰብአዊ ተፅዕኖ በተጠቂዎች ላይ ከሚፈጥረው የአካልና የስሜት ጉዳት ባሻገር እጅግ አሳሳቢ የሆነው በተለያየ የማንነት ወይም የርዕዮተ አለም ልዩነት የሚፈጠሩ ማህበራት አባላትና ደጋፊዎች መካከል አንዱ አንዱን እንደጠላት የማየት እንድምታን ባስ ሲል ደግሞ የርስ በርስ ግጭትን መፍጠሩም ነው። ይህ ደግሞ በዜጎች መከባበርና መዋደድ ላይ የተመሰረተ መተባበር ብቻ ሊገኝ የሚችለውን የምርታማነት መጨመርና እድገትን እንዲሁም ከድህነት አዙሪት የመውጣት ጥረትን በከፍተኛ መልኩ ያቀጭጨዋል።
ዘላቂነት ያለው የፖለቲካ ስርዓት
ሁነኛ የፖለቲካ ስርዓት ማለት በጥቅሉ አንድን ሃገር ወይም ማህበረሰብ የአገዛዝና አስተዳደራዊ መዋቅር በአለማቀፍ ደረጃ ከተቀመጡት ስርዓቶች ጋር በማዛመድ ለዛ ሃገርና ማህበረሰብ እንዲመች ተደርጎ የተቀረፀ ማለት ነው። በፖለቲካ ስርዓት ዜጎች መንግስት እንዲሆን በመረጡት ወይም መንግስት ሆኖ በተቀመጠው አካል ጤናማና ሚዛናዊ የሆነ የህግና ስርዓት ፣ የኢኮኖሚ ስርዓት ፣ የባህላዊና ማህበረሰባዊ ስርዓት የማዋቀርና የማስተዳደር ሃላፊነት ሲሰጡት ያም መንግስት ዘላቂነት ያላቸው ህግጋትና ፖሊሲዎችን ለመረጠው የፖለቲካ መንገድና ለማህበረሰቡ እሴቶች በሚስማማ መልኩ ቀርፆ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ የአገዛዝ ስርዓት ሲመሰርትና ይህንንም ለማስከበር በአግባቡ ሃላፊነቱን ሲወጣ ማለት ነው።
በአለማችን በርካታ ሃገራት ለዜጎቻቸውና ለነባራዊ ሁኔታቸው በሚመች መልኩ የፖለቲካና የአገዛዝ ስርዓት ገንብተዋል ለአብነት ለመጥቀስ ያህልም የአሜሪካ መንግስት የሚከተለው የፖለቲካ ስርዓት ከሁለት ምዕተ አመት በላይ መሰረታዊ መርሁን ሳይለቅ ሊቀጥል ችሏል። ከዚህም ወጥነት ካለው የፖለቲካ ስርዓቱ የመነጩት የኢኮኖሚና ማህበራዊ ስርዓቶች ከትውልድ ወደ ትውልድ እየጠነከሩ አሁን ላሉበት ደረጃ ደርሰዋል። በአንፃሩ እንደ ኢትዮጲያ ያሉ ያላደጉ ሃገራት ለአለማደጋቸው እንደምክንያት ከሚጠቀሱት ውስጥ ዋነኛው የሆነው በየግዜው የሚቀያየር ስርዓት መኖሩ እንዲሁም ጭራሽ ይህ ነው የሚባል ስርዓት አለመኖሩ ነው። በኢትዮጲያ የሚመጣው መንግስት ሁሉ የራሱን ስርዓት እንደ አዲስ መጀመሩ ከፖለቲካው ስርዓት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸውን የኢኮኖሚና ማህበረሰባዊ ስርዓቶች እንደገና ፈርሰው እየተሰሩ የተወሰኑትም “የቀደመው መንግስት አሻራ አለባቸው” በሚል ምክንያት እየፈረሱ አጠቃላይ የሃገር እድገትን ባለበት እንዲሄድ አርጎታል።
የአሁኑ የኢትዮጲያ መንግስት ስልጣኑን በእርስ በርስ ጦርነት አግኝቶ ያዋቀረው የአገዛዝ ስርዓት ስልጣኑን ያገኘው በህዝብ ምርጫ ስላልሆነ ስርዓቱ ለተወሰኑ የማህበረሰቡ አካላት ብቻ ሲያደላ ቆይቷል። በዚህም ሳቢያ መጠነ ሰፊ የሆን የፍትህ መጓደል ይስተዋላል። ከማህበረሰብ ውይይትና ይሁንታ ውጪ ስልጣኑን ለማደላደል የሚያወጣቸው የተለያዩ ህግጋት በህዝብ ዘንድ በግድ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ሲያደርግ የለየለት አምባገነን ሆኗል።
እንደ ኢትዮጲያ መንግስት አይነት አምባገነናዊ ባህሪይ ያላቸው መንግስታት በተለየ መልኩ አማራጭ የፖለቲካ ስርዓት ወይም በተመሳሳይ ስርዓት የተለዩ ዝርዝር ፖሊሲዎችን ይዘው ለተነሱ የፖለቲካ ማህበራት በግልፅ ውይይትና ክርክር ማንኛቸው ለህዝብ እንደሚሻሉ ከማሳየት ይልቅ አማራጭ ሃሳብ አመንጪዎችን ይዘው የተነሱትን አላማ ለህዝብ እንዳያስተዋውቁ በማፈን ፣ በማዋከብ ፣ በማሰርና ውድ ህይወትን እስከመንጠቅ ይደርሳሉ።
የኢትዮጲያ መንግስት የራሱን ፖሊስዎችና መርሆች በግልም ሆነ በህዝብ ሚዲያ እንደልቡ እያስነገረ ነገር ግን አማራጭ የፖለቲካ ማህበራትን መሰብሰብ እስከመከልከልና ብሎም እንደ ህዝብና ሃገር ጠላይ ይፈርጃል። ይህ መረን የወጣ አምባገነናዊ ስርዓት ዜጎች ሃገራዊ እድገት ላይ ሊኖራቸው የሚገባውን ተሳትፎ አሳንሶ በገዛ ሃገራቸው ባይተዋር የሚያደርግ እንዲሁም ሃገርን ከድህነት የማውጣት ጥረት እጅግ ጠቃሚ ተሳትፎ እንዳያረጉ የሚያስቀር ለተወሰኑ ቡድንና ግለሰቦች የስልጣን ጥምና ጥቅም ሲባል ሃገርን የድህነት አዙሪት ውስጥ የመዝፈቅ ሃላፊነት የጎደለው ስርዓት ነው።
አስተማማኝ የኢኮኖሚ መዋቅር
የኢኮኖሚ መዋቅር ወይም ስርዓት ማለት በጥቅሉ በአንድ ሃገር ወይም ማህበረሰብ ውስጥ ያለ ምርትና አገልግሎትን የማምረትና የማሰራጨት እንዲሁም የተለያዩ ግብዓቶችን በተገቢው መልኩ የማዳረስ ስርዓት ማለት ነው። በዚህ ስርዓት ውስጥ የማህበረሰቡን የተለያዩ ምርትና አገልግሎቶች አቅራቢ ተቋማት ፣ ማህበራትና ድርጅቶች እንዲሁም ተጠቃሚዎች መካክል ጤናማ የሆን ፍሰት እንዲኖር የሚያደርግ ስርዓት ማለት ነው። ይህም ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር የተስተካከለና ጤናማ እንዲሆን መንግስት የተለያዩ ህግጋቶችንና ድንጋጌዎችን በማውጣት ከአለማቀፍ ኢኮኖሚ ስርዓቶች ጋር የማጣጣም ሃላፊነት አለበት።
ጤናማ የኢኮኖሚ ስርዓት መኖር የአንድን ማህበረሰብ ወይም ሃገር የኑሮ ደረጃ በማሳደግ በኩል ቀጥተኛ አስተዋፆ አለው። ኢኮኖሚያዊ መዋቅሩ በተገቢው መልኩ እንዲቀጥል ሰላማዊና በፍላጎት ላይ የተመሰረተ ሃገራዊ አንድነት መኖር ወሳኝ ሚና አለው። አንድ መንግስትም የሃገርን ኢኮኖሚ በተገቢ መልኩ እየመራ ነው የሚባለው አጠቃላይ ፍሰቱን ለሁሉም ዜጋ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ሲያስተዳድር ፣ ሲዳኝ እንዲሁም ሲያበረታታ ነው።
ፍሰቱ ሚዛናዊ አደለም የሚባለው ለተወሰኑ የንግድ ተቋማት መንግስታዊ የሆነ አድልዎ በማድረግ የተቀሩትን የመጫን ሂደት ሲኖር እንዲሁም ኢኮኖሚውን የማስተዳደር ሃላፊነት የተሰጣቸው መንግስታዊ ተቋማት በገለልተኝነት በማስተዳደር ፈንታ በአድሎአዊነት ጣልቃ ሲገቡና በጥቅማ ጥቅም ሲያዙ ነው። ይህ ሚዛናዊነቱን የማሳት ተግባር ለተወሰኑ ግለሰቦች ጥቅም ሲባል በሃገር ኢኮኖሚ እድገት ላይ ከፍተኛና ቀጥተኛ ሚና የሚኖራቸውን ድርጅቶችን ለክስረትና ለመዘጋት ይዳርጋል ፣ ሃገርና ህዝብ ከንግድ ፍሰቱ የሚያገኙትን ጥቅማ ጥቅሞች ያሳጣል ፣ ወደ ንግድ ስራዎችና መሰል እንቅስቃሴ ለመግባት ያቀዱ ሃገራዊም ሆነ አለማቀፋዊ ድርጅቶችን ፍላጎት ይገታል ፣ የስራ አጡን ቁጥር ይጨምራል እንዲሁም በርካታ መሰል ችግሮችን በመፍጠር ሃገር ወይም ማህበረሰብ ከድህነት አዙሪት ለመውጣት የሚያረገውን ጥረት ያቀጭጨዋል።
ለምሳሌ በሃገራችን ኤፈርት የተባለው የንግድ ተቋም በመንግስት በሚደረግለት ግልፅና ቀጥተኛ ድጋፍ በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚንቀሳቀስ ፣ ከዛ ሁሉ የኢትዮጲያ ብሄርና ክልል አንድ ክልልና ብሄርን ለማልማት በሚል የተዋቀረ ድርጅት አለ። የዚህ ድርጅት በተለያዩ ውድድር በሚያሻቸው የንግድ ዘርፎች ተሰማርቶ ነገር ግን በመንግስት ድጋፍ በሞኖፖል መንቀሳቀሱ ሌሎች ቀድመው የነበሩ እንዲሁም አዲስ የሚፈጠሩ የንግድ ተቋማትን ምን ያህል እንደጎዳ በዘርፉ ባለሞያዎች ብዙ ተብሏል። መሆን የነበረበት ግን የኢትዮጲያ መንግስት እከተለዋለው ያለውን የኢኮኖሚ ስርዓት በአግባቡ ቢያስተዳድር ፣ ጤናማ የውድድር መንፈስ ቢፈጥር እንዲሁም የሁሉንም ሃገራዊ ድርጅቶች ምርቶች ከአድልዎ ውጪ በሆነ መልኩ አለማቀፍ ገበያ ውስጥ እንዲታወቁ በቅንነት ቢጥር ሃገራችን በቅርቡ ከድህነት አዙሪት ትወጣ ነበር።
እንግዲህ ከተነሳሁበት ሃሳብ ስፋትና ጥልቀት አንፃር በእኔ አቅም ይህችን ብያለው። አንባቢዎች የማይስማሙባቸው ወይም የቀረ የሚሉት ብዙ ሊኖር ይችላል ነገር ግን እኔ ሃገር የምትገነባው በጎ መሰረት ያለው ግልፅ ውይይት ሲኖር ነው ብዬ ስለማምን እንደ አንድ ተቆርቋሪ ዜጋ ይህችን አዋጥቻለሁ።
ሃገራችን ከአምባገነናዊ ስርዓት የምትላቀቅበትን ህዝቦቿም ከድህነት አረንቋ የሚወጡበትን ቀን ቅርብ ያርግልን !!
No comments:
Post a Comment