BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

Saturday, 22 February 2014

የዉህደት ሐሳብና ፈታኙ የብሄር ፖለቲካችን

Abraha Desta

ገዢው ፓርቲ የራሱ አማራጭ ሐሳብ መንገድ ያቀርባል። ተቃዋሚዎችም ሌላ አማራጭ መንገድ ያቀርባሉ። ከሁሉም አማራጮች የተሻለውን መንገድ ይመረጣል። የተሻለውን መንገድ የሚመርጠው አካል ማነው? መንገዱ የሚመርጠው ተጓዡ ነው። ተጓዡ ማነው? ህዝቡ ነው። ህዝቡ በነፃነት የተሻለውን መንገድ ለመምረጥ ዕድል ይሰጠዋል። ከዛ ሁላችን አብዛኝው ህዝብ በመረጠው መንገድ አብረን እንጓዛለን። የተሻለ ለውጥም እናመጣለን። ለውጥ ካላመጣን የመረጥነው መንገድ ትክክል አልነበረም ማለት ስለሚሆን በሚቀጥለው ምርጫ ሌላኛው መንገድ እንከተላለን።

ህዝብ የተሻለውን የሐሳብ መንገድ ለመምረጥ ስለ አማራጮቹ ሙሉ መረጃ ሊኖረው ይገባል። አማራጭ አቅራቢዎቹም (ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚዎች) የየራሳቸው የሐሳብ መንገድ ለህዝብ በነፃነት ማቅረብ ይኖርባችኋል። ገዢው ፓርቲ የመንግስት ስልጣንና ሃብት ስለተቆጣጠረ የመንግስት መዋቅርና ሃብት ተጠቅሞ ከህዝብ ጋር በቀላሉ መገናኘት ይችላል።
የሚፈተኑት ተቃዋሚዎች ናቸው። ተቃዋሚ ፓርቲዎች አማራጭ የሐሳብ መንገድ አቅራቢ እንዲሆኑ ከህዝብ ጋር ተገናኝተው አማራጫቸውን የሚያቀርቡበት ዓቅም ሊኖራቸው ይገባል። ተቃዋሚዎች ዓቅም እንዲኖራቸው መጀመርያ የህዝብ ድጋፍ ሊኖራቸው ይገባል። የህዝብ ድጋፍ ለማግኘት ወደ ህዝብ ወርደው መቀስቀስ አለባቸው።
የኢትዮጵያ ህዝብ በብሄር፣ በጎጥ ወዘተ የተከፋፈለ ነው። በጎጥና በብሄር የሚያስብ ሰው ለመቀስቀስ የግድ ስለ ጎጥና ብሄር ማንሳት አለብህ። “እኛ ለናንተ ጥቅም የቆምን ነን፣ እነ እገሌ ጠላቶቻችን ናቸው …ወዘተ” እያልክ የ“እኛና እነሱ” ፖለቲካ መጫወት አለብህ። ይህን ዓይነት ከፋፋይ ስትራተጂ ግን ትክክለኛ የሐሳብ መንገድ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም የመላው ሀገር ህዝብ ወደ አንድ አቅጣጫ መርቶ ሁላችን ተባብረን ለውጥ የምናመጣበት አማራጭ ሐሳብ አይደለም። “የኛና የነሱ ፖለቲካ” ከፋፋይ ነው።
ትክክለኛ የሐሳብ መንገድ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በአንድነት ወደ አንድ አቅጣጫ መርቶ ለውጥ የሚያመጣ እንጂ ኢትዮጵያውያን ከፋፍሎ እርስበርሳቸው እንዲጠራጠሩና እንዳይግባቡ የሚያደርግ መሆን የለበትም። ትክክለኛ የሐሳብ መንገድ ለማስተዋወቅ “ለሁሉም ህዝቦች የሚጠቅም ይሄ ነው፤ ይህ መንገድ ከተከተልን ሁላችን አንድ ላይ የተሻለ ደረጃ እንደርሳለን” ብለን ማለት አለብን። አንድ አቅጣጫ መከተል የራሳችን ወይ የየግላችን ማንነት፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት ወዘተ መርሳት አለብን ማለት አይደለም። በአንድ ሀገራዊ የፖለቲካ አቅጣጫ ለመራመድ የግድ አንድ ሃይማኖትና ቋንቋ መያዝ የለብንም። የየራሳችን ማንነት ይዘን ኢትዮጵያዊ በሆነ የጋራ ማንነታችን አንድ መሆን እንችላለን።
ግን የኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ንቃተ ህሊና አነስተኛ ነው (ፖለቲከኛ እንዲህ ብሎ መደምደም የለበትም አይደል? አንዳንዶቹማ “ለህዝብ ያለህ ንቀት የሚያሳይ ነው ይሉኛል”)። በዚህ ምክንያት ህዝብ ለመጀንጀን የሀገር (የጋራ ጉዳይ) ከምታነሳ የጎጥና የብሄር ጉዳይ ብትቀላቅል የአከባቢው ህዝብ የበለጠ ያምነሃል፣ ይደግፈሃል። ጎጥና ብሄር ለይተህ “እንዲህ አደርግላቸዋለሁ …” ስትላቸው የበለጠ ይደግፉሃል። ይህን ዓይነት የፖለቲካ ቅስቀሳ ድጋፍ ብታገኝበትም መርሁ ግን ስህተት ነው። ምክንያቱም ለሁሉም ኢትዮጵያውያን በጋራ የሚጠቅም አቅጣጫ መቀየስ ሲገባህ ለተወሰነ የሕብረተሰብ ክፍል ብቻ መቆምህ በራሱ ሀገራዊ የጋራ ጉዞው በአሉታዊ መልኩ ይጎዳዋል።
ግን የፖለቲካ ፓርቲ የህዝብ ድጋፍ ያስፈልገዋል። የፖለቲካ ድርጅት ትክክለኛና ሀገርዊ የሐሳብ መንገድ ቢኖረው እንኳ የህዝብ ድጋፍ ከሌለው ዋጋ የለውም። እናም ብዙ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሀገራዊ አጀንዳ ይዘው በአከባቢና በብሄር የተደራጁ አሉ። ከነዚህ ፓርቲዎች ዉስጥ ዓረና ትግራይ፣ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ፣ ደቡብ ሕብረት ወዘተ ይገኙባቸዋል።
እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች ክልላዊ ወይ የብሄር ፓርቲዎች መሆናቸው የአከባቢው ወይ የብሄሩ ተወላጆች ድጋፍ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል። ወደ ሀገራዊ ፓርቲነት ሲሸጋገሩ የአከባቢው ህዝብ ድጋፍ ሊያጡ ይችላሉ። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ህዝብ በብሄርና በአከባቢ ተከፋፍለዋል። የብሄር ፖለቲካ ነጣጥሎናል። በኢትዮጵያዊነት ማሰብ እንደ ከሃዲና ለህዝቡ ጥቅም የማይቆም የከሰረ ፖለቲከኛ ያስቆጥራል። የኢትዮጵያዊነት ስሜት በብሄርና ጎጥ ተተክቷል። ስለዚህ የብሄር ፖለቲካ ፈተና ሁኗል።
ተቃዋሚዎች የብሄር ፖለቲካ በፈጠረው ችግር ምክንያት የህዝብ ድጋፍ የሚያገኙበት ስትራተጂ ነድፈው በብሄርና በክልል ተደራጅተዋል። ግን የህዝብ ድጋፍ ማግኘት ለፖለቲካ ፓርቲ አስፈላጊ እንጂ በራሱ ግብ አይደለም። ምክንያቱም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚታገሉት የህዝብ ድጋፍ ለማግኘት ብቻ አይደለም። የፖለቲካ ፓርቲ ዓላማ አማራጭ የፖለቲካ አቅጣጫ በመቀየስ በሀገሪቱ የተሻለ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ለውጥ ማምጣት መቻል ነው።
የተሻለ ለውጥ ለማምጣት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በትረ ስልጣን መጨበጥ አለባቸው። በትረ ስልጣን መጨበጥ በራሱ ግብ ባይሆንም አማራጭ ፖሊሲዎችን ተግባር ላይ ለማዋል የሚረዳ ስትራተጂ ነው። ምክንያቱም ስልጣን ካልተያዘ አማራጭ ፖሊሲህን በሀገር ደረጃ ተግባራዊ ማድረግ አይቻልም። ስልጣን ለመያዝ ደግሞ በሀገሪቱ ያለው ገዢ ፓርቲ ማሸነፍ የግድ ይላል። ገዢውን ፓርቲ ለማሸነፍ በሀገር ደረጃ መንቀሳቀስ የግድ ነው። በሀገር ደረጃ ለመደራጀት ከሌሎች ብሄሮች ወይ ክልሎች የመጡ ፓርቲዎች ጋር ግንባር ወይ ሕብረት ወይ ዉህደት መፈፀም ግድ ይላል። ከሌሎች ጋር ዉህደት መፈፀምም ፈተና አለው፤ “ከጠላቶቻችን ጋር አብረዋል” የሚል ስም የማጥፋት ዘመቻ ይከፈትብሃልና።
ዓረና ፓርቲ እንውሰድ። ዓረና ክልላዊ ፓርቲ ነው። በክልል ደረጃ እየተንቀሳቀሰ የትግራይ ህዝብ ድጋፍ እያገኘ ነው (ወይ ያገኛል ብለን እንገምት ሐሳብ ለመስጠት እንዲመቸኝ)። ዓረና የህዝብ ድጋፍ አግኝቶ ካሸነፈ የሚይዘው ወንበር የትግራይ ክልል ነው። ዓረና የትግራይ ክልል ፓርቲ እስከሆነ ድረስ የሚያሸንፈው በትግራይ ብቻ ይሆናል። ዓረና በትግራይ ክልል ካሸነፈ በኋላ ምን ያደርጋል? ሀገራዊ ስልጣን መያዝ አይችልም። ታድያ ምን ያድርግ? ትግራይን ይገንጥል???
ዓረና ፓርቲ ትግራይን የመገንጠል ዓላማ የለውም። አማራጭ ሐሳቡ ለህዝብ አቅርቦ በህዝብ ተመርጦ መንግስታዊ ስልጣን ከህዝብ ተቀብሎ ኢትዮጵያ ሀገራችን ወደ ተሻለ ለውጥ የምት ሸጋገርበት መድረክ ይከፍታል። ስለዚህ ዓረና የተደራጀው በክልል ሁኖ ዓላማው ግን ሀገራዊ ከሆነ ምን ማድረግ አለበት? ከሌሎች ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ዉህደት ወይ ሕብረት ወይ ግንባር መፍጠር የግድ ነው።
ዓረና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ዉህደት ለመፈፀም በሚዘጋጅበት ግዜ ህወሓቶች የከፈቱት የማጥላላት ዘመቻ አለ። “ዓረና ከትግራይ ህዝብ ጠላቶች፣ የደርግ ስርዓት ርዝራዦች፣ ደቂቀ ምኒሊክ ወዘተ በማበር የትግራይን ህዝብ ለመጨቆን እየተንቀሳቀሰ ነው” ይላሉ። ታድያ ዓረና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ካላበረ ትግራይን ማስገንጠል አለበት? አይሆንም። ወይስ ህወሓት እንዳደረገው ሁሉ ዓረናም የራሱ አሻንጉሊት ድርጅቶች መፈብረክ ይኖርበታል?
ህወሓት ትግራይን የማስገንጠል (ማሌሊት የመመስረት) ዓላማ ይዞ ታግሎ ካሸነፈ በኋላ ኢትዮጵያን መቆጣጠር ሲያምረው ከሌሎች ጋር (ራሱ የፈበረካቸው አሻንጉሊቶች ቢሆኑም) ማበሩ አልቀረም። እኛ ግን ህወሓት ከጠላቶቻችን ጋር አብረዋል ብለን አልተከራከርንም፣ ጠላትም የለንም። ህወሓት “ጠላቶቻችን” እያላቸው ያሉ ሰዎች የደርግና የኢህአፓ ፖለቲከኞች የነበሩ ናቸው። ህወሓት ራሱ ግን ከደርጎችና ከኢህአፓዎች ጋር ነው እየሰራ ያለው። ኦህዴዶች የተማረኩ የደርግ ወታደሮች ናቸው። ብአዴኖችም የኢህአፓ ተገንጣዮች ናቸው።
እኛ ሰው በድሮ ታሪኩ የመመዘን ባህል የለንም። የደርግ ኢሠፓ ወይ የኢህአፓ አባል ስለነበረ ብቻ የህዝብ ጠላት ነው አንልም። ማንም ሰው በህዝብ ላይ ወንጀል ሰርቶ ከሆነ በሕግ ይጠየቃል እንጂ ህወሓትን ሲቃወም እንደ ጠላት የሚታይ፣ ህወሓትን ሲያገለግል ግን ወዳጅ የሚባል ከሆነ ተቀባይነት የለውም። ለማንኛውም የህወሓት ታሪክ የሃይል ታሪክ ስለሆነ ህወሓት የጠመንጃ ጉልበቱ ተጠቅሞ፣ አሻንጉሊቶችን ፈብርኮ ህዝቦች ያለ መልካም ፍቃዳቸው እየገዛ ይገኛል። የህወሓት የሃይል አገዛዝ ለማንም አልጠቀመም።
ዓረና ግን የራሱን አሻንጉሊት ድርጅቶች በመመስረት ሌሎች ህዝቦችን በሃይል የመግዛትና የመጨቆን ዓቅም ይሁን ዓላማ የለውም። ምክንያቱም የዓረና መንገድ ሰለማዊ ትግል እንጂ እንደ የህወሓቱ የትጥቅ ትግል አይደለም። ዓረና የህወሓት/ኢህአዴግ መንገድ አይከተልም። ደኢህዴን በኢህአዴግ ተፈጠረ። ኦህዴድ በብአዴን ተፈጠረ። ብአዴን በህወሓት ተፈጠረ። ህወሓትም በጠመንጃ ተፈጠረ። ስለዚህ አራቱ የኢህአዴግ ድርጅቶች የጠመንጃ ውጤት ናቸው።
ዓረና የተፈጠረው በሐሳብ ነው። ስልጣን ለመያዝ የሚታገለውም በህዝብ ምርጫ (ሰለማዊ መንገድ) እንጂ በጠመንጃ አፈሙዝ አይደለም። ስለዚህ ህወሓት እንዳደረገው የራሱ አሻንጉሊቶች አይመሰርትም። ዓረና ራሳቸው ችለው፣ በራሳቸው መንገድና ዓላማ ከሚጓዙ ሌሎች ድርጅቶችን ነው ዉህደት መፍጠር የሚፈልገው።
በሰለማዊ ትግል አንድ ፓርቲ ከሌሎች ፖለቲከኞች ጋር አብሮ ሲሰራ ወይ ዉህደት ሲፈጥር ዉህደቱ የሚከናወነው ከፖለቲከኞቹ ጋር ሳይሆን ከመራጭ ህዝቡ ነው። ምክንያቱም ሰለማዊ ታጋይ ስልጣን የሚይዘው በህዝብ ፍቃድ (ምርጫ) ነው። ያለ ህዝብ ፍቃድ ስልጣን አይዝም። ስልጣን ካልያዘ ህዝብ የሚጎዳበት ወይ የሚጠቅምበት አጋጣሚ አይኖርም።
በትጥቅ ትግል ስልጣን የሚያዘው በሃይል ነው። የህዝብ ፍቃድ መጠየቅ አያስፈልግም። ለዚህም ነው ህወሓት ኦህዴድን ለኦሮሞ ህዝብ፣ ብአዴን ደግሞ ለአማራ ህዝብ ራሱ መርጦ የሸሞላቸው። የኦሮሞ ህዝብ ምርጫ ኦህዴድ ሳይሆን ኦነግ ሊሆን ይችላል። ግን ኦነግ በህወሓት ስላልተወደደ ኦህዴድ ተመረጠላቸው። ኦህዴድ የተመረጠበት ምክንያት ለኦሮሞ ህዝብ የተሻለ ስለሆነ ሳይሆን ለህወሓት (ከኦነግ) የተሻለ ታዛዥ ስለነበረ ነው። የአማራ ህዝብ ምርጫም ብአዴን ላይሆን ይችል ነበር። ግን ብአዴን በህወሓት ስለተመረጠ የአማራ ህዝብ ገዢ ተደርጎ ተሾመ። ደኢህዴንም እንደዚሁ። ስለዚህ በትጥቅ ትግል በህዝብ ያልተመረጡ (‘የህዝብ ጠላቶች’ ልበለው በህወሓትኛ ቋንቋ) ገዢዎች ስልጣን የሚይዙበት ዕድል አለ።
በሰለማዊ ትግል ግን በህዝብ ያልተመረጠ ፖለቲከኛ ስልጣን የሚይዝበት አጋጣሚ አነስተኛ ነው። ምክንያቱም ስልጣን የጠመንጃ ሳይሆን የህዝብ ነው። ስለዚህ ዓረና ፓርቲ ከሌሎች ድርጅቶች (በህወሓት ቋንቋ መሰረት ‘የትግራይ ህዝብ ጠላቶች’) ዉህደት ቢፈጥር እንኳ ፖለቲከኞቹ በህዝብ ሊመረጡ ወደ ህዝብ ስለሚቀርቡ በህዝብ የማይፈለጉ ግለሰቦች ስልጣን የሚይዙበት ዕድል አይኖርም።
ዓረና ከአንድነት ፓርቲ፣ ከኦፌኮ፣ ከድቡብ ሕብረት፣ ከሰማያዊ ፓርቲ፣ ከኢዴፓ፣ ከመኢአድ ወዘተ ዉህደት ቢፈጥር በነዚህ ድርጅቶች ያሉ ፖለቲከኞች በሚቀጥለው ምርጫ ለህዝብ ይቀርባሉ። ህዝብ ከመረጣቸው ህዝብ ወክለው ይመጣሉ፣ በህዝብ ድምፅና መልካም ፍቃድ ስልጣን ይይዛሉ። ዓረናም በህዝብ ከተመረጠ ህዝብ ወክሎ ሐላፊነት ይሸከማል። ከተመረጡት ፖለቲከኞችም አብሮ ይሰራል።
በህዝብ ከተመረጡና ዓረናም ከነሱ ጋር አብሮ ከሰራ “ዓረና ከትግራይ ህዝብ ጠላቶች ጋር …” ገለመሌ ብሎ ነገር አይሰራም። ምክንያቱም ዓረና አብሮ የሚሰራው በህዝብ ከተመረጡ (ወይ ለምርጫ ከሚቀርቡ) ፖለቲከኞች ጋር ነው። በህዝብ ከተመረጡ (ወይ ከሚመረጡ) ሰዎች ጋር አብሮ መስራት ከህዝብ ጋር አብሮ እንደመስራት ነው። ምክንያቱም አንድ ፖለቲከኛ ከህዝብ ጋር አብሮ መስራት አለበት። ከህዝብ ጋር አብሮ ለመስራት ህዝብ ከመረጣቸው ወይ ከሚመርጣቸው ፖለቲከኞች ጋር አብሮ መስራት ይጠይቃል። ህዝብ የሚሳተፈው በተወካዮቹ በኩል ነውና።
ስለዚህ “የትግራይ ጠላቶች” ምናምን ብሎ ነገር የለም። ምክንያቱም ግለሰቦቹ ወይ ድርጅቶቹ የትግራይ ህዝብ ባይመርጧቸው እንኳን ሌላ የመረጣቸው (የሚመርጣቸው) ህዝብ አለ። የአማራ ህዝብ መኢአድ ወይ ኢዴፓ ወይ ብአዴን ወይ ግንቦት ሰባት (ከተወዳደረ) ሊመርጥ ይችላል። መብቱ ነው። የህዝብ ድምፅ መከበር አለበት። የኦሮሞ ህዝብ ኦፌኮ ወይ ኦህዴድ ወይ ኦነግ (ከተወዳደረ) ሊመርጥ ይችላል። መብቱ ነው፤ የህዝቡ ድምፅ ማክበር አለብን። የትግራይ ህዝብ ዓረና ወይ ህወሓት ወይ ዴምህት (ከተወዳደረ) ሊመርጥ ይችላል። ድምፁ ማክበር አለብን።
የትግራይ ህዝብ የአማራ ህዝብ ድምፅና ፍላጎት ማክበር አለበት። የአማራ ህዝብም የኦሮሞ ህዝብ ድምፅ ማክበር አለበት። ሁሉም ህዝቦች የየራሳቸው ምርጫ (ተወካዮች) ይልካሉ። የሁሉም ተወካዮች ደግሞ ለህዝብ ሲሉ አብረው፣ ዉህደት ፈጥረው ይሰራሉ። “ይሄ ጠላታችን ነው፣ ይሄ ወዳጃችን ነው” ምናምን የለም። ምክንያቱም ጠላትህ ከሆነ አትምረጠው። በሌሎች ህዝቦች ከተመረጠ ግን አክብረው። ምክንያቱም አንተ ባትፈልገው እንኳ ሌሎች ይፈልጉታል። የራስህ ምርጭ እንዲከበርልህ ደግሞ የሌሎችን ምርጫ ማክበር አለብህ።
ሌላው መሰረታዊ ጉዳይ ደግሞ ድርጅታዊ ዉህደት ሲፈፀም የፓርቲዎቹ አይድዮሎጂ፣ ፖሊሲና ፕሮግራም መሰረት ያደረገ እንጂ የፖለቲከኞች ያለፈው ታሪክ መሰረት ያደረገ መሆን የለበትም። ምክንያቱም ዉህደት የሚፈጥሩት ግለሰቦቹ (ፖለቲከኞቹ) ሳይሆኑ የድርጅቶቹ ራእይ፣ ዓላማ፣ ፕሮግራም ወዘተ ነው። ስለዚህ ፓርቲዎች በዓላማ ከተስማሙ ቢዋሃዱ መልካም ነው። ህዝብ ጠንካራ አማራጭ የፖለቲካ ድርጅት ያስፈልገዋልና።
የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስም (ኦፌኮ) ቢሆን ብሄር መሰረት አድርጎ የተደራጀ ነው። የኦሮሞ ህዝብ ድጋፍ ለማግኘት ‘ለናንተ ጥቅም የቆምኩ ነኝ’ ብሎ መቀስቀስ አለበት። ይህን ካላደረገ ግን ድጋፍ የሚያገኝበት ዕድል ይጠባል። ምክንያቱም ባሁኑ ግዜ የኦሮሞ ህዝብ የኦነግ የ‘ተበድለናልና እንገንጠል’ ሐሳብ እየቀረበለት ነው። የኦሮሞ ህዝብ ‘ያለፈው በደል እንርሳውና አሁን ስለ ኢትዮጵያ አንድነት እናስብ’ በሚልና ‘በደሉ ይብቃን፣ እንገንጠል’ በሚል መስቀለኛ መንገድ ቁሟል።
ኦፌኮ የኦሮሞ ህዝብን የመገንጠል ሐሳብ ሳይደግፍ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በአንድነት የመንቀሳቀስ አማራጭ ቢከተል የኦነግና የኦህዴድ የማጥላላት ሰለባ ይሆናል። ‘ኦፌኮ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን፣ ደቂቀ ምኒሊክ … በማበር የኦሮሞን ህዝብ ጭቆና ለማራዘም እየተንቀሳቀሰ ነው’ ብለው በህዝብ ፊት ይከሱታል። የኦሮሞ ህዝብ ያለፈው በደል በመቀስቀስ የህዝብ ድጋፍ ያሳጡታል። ኦፌኮ የኦሮሞ ህዝብ ድጋፍ ከሌለው ደግሞ ዋጋ የለውም።
ኦፌኮ ከሌሎች የኢትዮጵያ ድርጅቶች ጋር ሕብረት መፍጠር የማያዋጣው ከሆነ ምን ማድረግ አለበት? ለብቻው መንቀሳቀስ? ለብቻው ተንቀሳቅሶ የኦሮሞን ህዝብ ድጋፍ አግኝቶ በኦሮምያ ከተመረጠና የክልሉ ስልጣን ከተቆጣጠረ ለብቻው መንግስትነት መመስረት ይችላል? በኦሮምያ ክልላዊ መንግስት መመስረት ይችላል (በፌደራላዊ የመንግስት አወቃቀር መሰረት)። ሀገራዊ ወይ ማእከላዊ መንግስት ግን መመስረት አይችልም። ሀገራዊ መንግስት ለመመስረት የግድ ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ግንባር ወይ ዉህደት መመሰረት ይኖርበታል።
ሌላው አማራጭ ህወሓት እንዳደረገው ሁሉ ኦፌኮም ኦሮምያን ከተቆጣጠረ በኋላ በሌሎች ክልሎች የራሱ አሻንጉሊቶች መስራት ይኖርበታል። ይህ አሻንጉሊቶችን የመፈብረክ ስትራተጂ ግን አያዋጣውም። ምክንያቱም (አንድ) ግዜው ያለፈበትና ተቀባይነት የሌለው ነው። ህወሓትም አሻንጉሊቶች በመፈብረኩ አልተመሰገነምና። (ሁለት) ኦፌኮ በሰለማዊ ትግል የሚያምን እስከሆነ ድረስ በሌሎች ክልሎች የራሱ አገልጋይ ፓርቲዎች የማቋቋም ዓቅም አይኖረውም። አሻንጉሊቶችን መመስረት የሚቻለው በጠመንጃ ሃይል ብቻ ነው።
ታድያ ይህን ሁሉ ፈተና ካለ ኦፌኮ ለብቻው መንቀሳቀሱ ምን ይፈይዳል? ኦሮምያን ለመገንጠል? አይመስልም። ምክንያቱም የመገንጠል ጥያቄ ቀላል መልስ የለውም። (አንደኛ) እኔ እስኪገባኝ ድረስ ኦፌኮ ኦሮምያን የማስገንጠል ዓላማ የለውም። (ሁለተኛ) ኦሮምያን የማስገንጠል ዓላማ ቢኖረው እንኳ በቀላሉ አይሳካም። ምክንያቱም ኦፌኮ ሰለማዊ ታጋይ ነው። ሀገር የማስገንጠል ጉዳይ በቀላሉ በሰለማዊ ትግል የሚሳካ አይደለም። ሀገር ማስገንጠል የሚቻለው በሃይል እርምጃ ነው።
(ሦስተኛ) የኦሮሞን ህዝብ ጥያቄ ጭቆናን የማስወገድ ጥያቄ እንጂ የመገንጠል ጥያቄ ላይሆን ይችላል። ምክንያቱም (ሀ) የኦሮሞ ህዝብ የኢትዮጵያ መሰረት ነው። ማን ከማን ሊገነጣል? (ለ) የኦሮሞ ህዝብ የመገንጠል ሐሳብ ቢደግፍ ኑሮ ኢትዮጵያ በፈራረሰች ነበር።
ስለዚህ ኦፌኮ ኦሮምያን የማስገንጠል ሐሳብ ይኖረዋል የሚል ግምት የለኝም። እናም የማስገንጠል ዓላማ ከሌለው፣ አሻንጉሊቶችም መፈብረክ ካልቻለ፣ መንግስታዊ ስልጣን ለመቆጣጠር አማራጭ ሐሳብ ካቀረበ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በጋራ መስራት ግድ ይለዋል።
የህዝብ (ወይም የፖለቲከኞች) የመገንጠል ሐሳብ ወደ ኢትዮጵያዊ የአንድነት ሐሳብ ማሸጋገር ይቻላል። ህዝብ የመገንጠል ጥያቄ ለምን ያነሳል? በአንድነት መኖር ስላልተመቸው ነው ሊሆን የሚችለው። አንድ ህዝብ ከሌሎች ጋር በአንድነት የመኖሩ ጉዳይ ካንገሸገሸውና መገንጠልን ከመረጠ በቃ ጭቆና አለ ማለት ነው። ፍትሕ፣ እኩልነትና ነፃነት የለም ማለት ነው። ምክንያቱም ፍትሕ፣ እኩልነትና ነፃነት ቢኖር ኑሮ በአንድነት መኖርን የሚጠላበት ምክንያት አይኖርም ነበር። ስለዚህ ጭቆናን በማስወገድ፣ ፍትሕ በማንገስ፣ እኩልነት በማስፈን፣ ነፃነት በመስጠት የህዝቦች የመገንጠል ጥያቄ ማስቀረት ይቻላል። የኦሮሞ ህዝብ የሚገባውን ያህል ካገኘ መገንጠልን የሚመርጥበት ሁኔታ አይታየኝም።
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲም (አንድነት) እንውሰድ። የአንድነት ፓርቲ ሐሳብ ኢትዮጵያውያን ሳንከፋፈል በአንድነት መቆም እንድንችል ጥረት ማድረግ ነው። ጥሩ ሐሳብ ነው። ግን ስለ አንድነት ስናወራ ስለ መከፋፈላችንም ማሰብ አለብን። ሀገራዊ አንድነት ለማምጣት ጥረት የምናደርገው ስለተከፋፈልን ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን ባንከፋፈል ኑሮ ስለ ሀገራዊ አንድነት ባልተጨነቅን ነበር። ስለ የአንድነት አስፈላጊነት ካወራን መከፋፈሉ አለ ማለት ነው። ስለዚህ አንድነት ፓርቲ ስለ ሀገራዊ አንድነት መዘመር ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ተከፋፍለን እንዳለንም መገንዘብ አለበት።
እንበልና አንድነት ፓርቲ ከሌሎች የጎሳ ድርጅቶች መዋሃድ አይፈልግም። ግን እንደ ፓርቲ በምርጫ ይወዳደራል። በሀገር ደረጃ ተወዳድሮ አሸንፎ ስልጣን ለመያዝ በአማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮምያ፣ ደቡብና ሌሎች ከተሞች ዘልቆ መግባት አለበት። ግን አንድነት ፓርቲ ከኦፌኮ ሳይግባባ ኦሮምያ ለመግባት ይከብደዋል። ፓርቲው (አንድነት) የሀገርና የህዝብ አንድነት የመጠበቅ ዓላማ ካለው መጀመርያ የተለያዩ በጎሳ የተደራጁ ፓርቲዎች ወደ ዉህደት እንዲመጡ ጥረት ማድረግ አለበት።
በብሄር የተከፋፈለ ህዝብ ወደ አንድነት ለማምጣት ምን መደረግ አለበት? በብሄር የተደራጁ ፓርቲዎች መተቸት፣ መንቀፍ? አይሆንም። ምክንያቱም ሀገራዊ አንድነት ለማምጣት በብሄር የተደራጁ ፓርቲዎች ሕብረት ወይ ግንባር ወይ ዉህደት የሚፈጥሩበት (ወደ አንድ የሚመጡበት) ሁኔታ ማመቻቸት እንጂ በብሄር ስለ ተደራጁ ብቻ ከነቀፍናቸው መከፋፈሉን እያጠበብነው ሳንሆን እያሰፋነው ነው። ‘በብሄር ስለተደራጁ ከነሱ ጋር አንወሃድም’ የሚል አቋም ከተያዘ ሌላ መከፋፈል መፍጠር ነው።
የኢትዮጵያውያን አንድነት ለመጠበቅ መጀምርያ ልዩነታችንን መቀበል አለብን። አንድነት ለማምጣት መከፋፈላችንን እንወቅ። መከፋፈላችን አንደግፈውም። ግን ተከፋፍለናል። መከፋፈላችን ስህተት ነው። ምክንያቱም መከፋፈል አልነበረብንም። ክፍፍላችን ግን እውነታ ነው። ስለዚህ ችግሩ ለመፍታት መጀምርያ እውነታው እንዳለ መቀበል አለብን። ክፍፍሉ ስለማንደግፈው ብቻ እውነታው በመካድ መፍትሔ ማምጣት አንችልም።
እንበልና! መኪኖች በሚንቀሳቀሱበት መንገድ ላይ ቦምብ ተጠምዷል። መንገዱ ተሽከርካሪዎች ስለሚተላለፉበት በመንገዱ ላይ ቦምብ መጠመዱ ስህተት ነው። ምክንያቱም በመንገድ ላይ ቦምብ ከተጠመደ ተሽከርካሪዎች ሊረግጡትና ቦምቡ ሊፈነዳ ይችላል። ከፈነዳ ደግሞ ጉዳት ያደርሳል። ስለዚህ በመንገድ ላይ ቦምብ መጠመዱ ተቀባይነት የለውም። ይሄ ጥሩ ሐሳብ ነው። በመንገድ ላይ ቦምብ መጠመዱ ስህተት መሆኑ ስለተስማማን ብቻ መኪና ይዘን እያሽከረከርን ቦምቡ ረግጠን ማፈንዳት አለብን ካልን ግን ሌላ ተጨማሪ ስህተት መስራት ነው።
የቦምቡ መንገድ ላይ መጠመድ ተቀባይነት የለውም። ግን ቦምቡ ተቀብሯል። የቦምቡ መቀበር ስህተት ቢሆንም የቦምቡ መቀበር (መጠመድ) ግን እውነታ ነው። አሁን ጉዳዩ መሆን ያለበት የቦምቡ መቀበር ስህተትነት መስበክ ሳይሆን መፍትሔ መፈለግ ነው። መፍትሔ ለመፈለግ መጀመርያ እውነታው መቀበል አለብን። እውነታው ቦምቡ ተቀብሯል። ቦምቡ ከረገጥነው ይፈነዳል። ጉዳት ያደርሳል። የቦምብ አጥማጁ ዓላማ ይሳካል። ታድያ ምን ማድረግ አለብን? ቦምብ መጠመዱ አውቀን መኪናችን እናስቁም (ቆም ብለን እናስተውል)። ከዛ የተጠመደው ቦምብ የሚመክንበት መንገድ እንፍጠር። ቦምቡ ይምከን። ከዛ ጉዟችን እንቀጥል። የብሄር ጉዳይ የቦምብ ጉዳይ ነው። ችግሩ እስካለ ድረስ ስለማንፈልገው ብቻ የሌለ ያህል ቆጥረን የብሄር ቦምቡ ረግጠን ማፈንዳት የለብንም። ኢትዮጵያዊነታችንን ለማስቀጠል የብሄር ቦምቡ ማምከን ይኖርብናል።
አንድ ተግባር ለመፈፀም ስናስብም በመራጩ ህዝብ ሊፈጠር ስለሚችል ስሜት መገንዘብ ይኖርብናል። ፖለቲካ ስለ ‘ትክክለኛነት’ ብቻ አይደለም፤ ስለ የህዝብ አስተያየት ጭምር እንጂ። ስላለፈው ጭቆና ማንሳት ተገቢ ባይሆንም በህዝቦች ትውስታ እስካለ ድረስ ጭቆናው መካድ የለብንም። አንድ ምሳሌ ልስጥ። ሰማያዊ ፓርቲ ‘የአጤ ምኒሊክ መቶኛ የሙት ዓመት’ አስታውሷል። ማስታወሱ በራሱ ችግር የለበትም። ጉዳዩ አጤ ምኒሊክ ጥሩ ነገር ማበርከታቸው ወይ ህዝቦች ክፉኛ መጨቆናቸው አይደለም። የአንድ መንግስት ተግባር ላንዱ ጥሩ ሲሆን ለሌላው መጥፎ ስሜት ሊፈጥር እንደሚችልም መረዳት ጥሩ ነው።
የአጤ ምኒሊክን ታሪክ ማስታወስ ለሰማያዊ ፓርቲ ሰዎች ጥሩ ስሜት ሊፈጥር ይችላል። የምኒሊክ ስም ማንሳት የማይፈልጉ ህዝቦች ግን አሉ። ሰማያዊ ፓርቲ የፖለቲካ ድርጅት እስከሆነ ድረስ መራጭ ህዝቦችን በማያስቀይም መልኩ መንቀሳቀስ ይገባው ነበር። ‘የምኒሊክ ስርዓት ለመመለስ የሚቋምጡ ሃይሎች አሉ’ የሚል ፕሮፓጋንዳ በሚነዛበት ወቅት ስለምኒሊክ ታላቅነት ማውራት ከጥቅሙ ኪሳራው ያመዝናል። በፖለቲካ የመራጭ ህዝብ ስሜት ቅድምያ ሊሰጠው ይገባል።
ኢህአዴግ ህዝቦችን የመከፋፈል ስትራተጂ ለስልጣኑ ማራዘምያ ስለሚጠቅመው ይከተለዋል። እናም በመከፋፈል ስትራተጂው ተቃዋሚዎች አንድነትና ጥንካሬ ፈጥረው ከስልጣን እንዳያወርዱት ይከላከላል። ተቃዋሚዎች ይህ የኢህአዴግ የመከፋፈል ስትራተጂ በንቃት ተከታትለው ማሸነፍ ካልቻሉ ኢህአዴግን ከስልጣን ማውረድ አይችሉም። ኢህአዴግ በተቃዋሚዎች ጠንካራ ሕብረት ከስልጣን ባይወርድ እንኳ በራሱ ግዜ በስብሶ ከጥቅም ዉጭ ይሆናል።
ኢህአዴግ በስልጣን ለመቆየት ሲል ህዝቦች መጨቆኑ ይቀጥላል። ምክንያቱም አሁን ባለው ሁኔታ መሰረት ገዢው ፓርቲ ህዝብ ከማፈን አልፎ ፍትሕ በማንገስ ህዝብ መግዛት ይችላል የሚል ግምት የለኝም። ህዝቦችም ፀረ ጭቆና መነሳታቸው አይቀርም። ህዝቦች ተቃውሟቸውን በሰለማዊ መንገድ መግለፅ እንዳይችሉ ከታፈኑ ሌላ አማራጭ የተቃውሞ መንገድ መከተላቸው አይቀርም። እናም ህወሓት በዴምህት ይፈተናል። ኦህዴድ በኦነግ ይፈተናል። ብ አዴን በግንቦት ሰባት ይፈተናል። ኢህአዴግ ስልጣኑ ለህዝብ ሳይሆን ለሌሎች ባለጠመንጃዎች ለማስረከብ ይገደዳል።
ግን ስልጣን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለህዝብ ቢሰጥ ጥሩ ነው። ገዢዎቻችንና የትጥቅ ትግል የመረጡ ወንድሞቻችን ሳይገድሉና ሳይገደሉ በሀገራችን በሰላም የሚኖሩበት ሁኔታ ቢመቻች መልካም ነው።
ለስልጣን ተብሎ መገዳደል ይብቃ።

No comments:

Post a Comment