የካቲት ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ባለፉት 10 ዓመታት ሲካሄደው የቆየውና የቤት ልማት ፕሮግራሙ ለኪራይ ሰብሳቢነትና ብልሹ አሰራሮች የተጋለጠ እንደነበር ኢህአዴግ “አዲስ ራዕይ” በተሰኘ ልሳኑ አምኗል፡፡አዲስ ራዕይ በህዳር – ታህሳስ 2006 ዕትም “የመኖሪያ ቤት ፖሊሲያችንና ለዜጎች የሀብት ክፍፍል ፋይዳው” በሚል ርእስ ባሰፈረው ሐተታ “እስከአሁን በነበረው የቤት ልማታችን ሂደት የተፈጠሩ ክፍተቶች አሉ” ብሏል፡፡
ክፍተቶቹን ሲዘረዝርም “በክልል ከተሞቻችን ቀደም ሲል ግንባታቸው የተጀመሩ ቤቶች ተጠናቀው ለተጠቃሚዎች በማስተላለፍ በኩል ሰፊ የባለቤትነት መጓደል ይታያል፡፡ የግብዓት አጠቃቀምና የግንባታ ሂደቱም በአግባቡ ባለመመራቱ ለቤቶቹ ማጠናቀቂያ ሊሆን ይችል የነበረ ሀብት ባልተቀናጀ መንገድ ሥራ ላይ ውሏል፡፡ አንዳንድ ቦታ፣ ትርፍ ከፍተኛ መጠን ያለው ብረት ሲኖር የሲሚንቶ እጥረት የሚታይበት፣ የጠጠር ትርፍ ክምችት ሲኖር የአሸዋ እጥረት የሚታይበት እንዲሁም ከኮንትራክተሮችና የሱፐርቪዥን ኮንሰልታንቶች ጋር በመመሳጠር ያልተገባ ጥቅምም እያገኙ የነበሩ በሂደቱ የተጠየቁ እንዲሁም የችግሩ ባለቤት የሆኑና በአግባቡ ያልተጋለጡ ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል፡፡” ብሎአል።
በአዲስ አበባ ደግሞ ከእነዚህ ችግሮች በተጨማሪ የመጀመሪያ የምዝገባ ቋት በአግባቡና በጥራት መያዝም ላይ የነበረው ሁኔታ ተጨማሪ ክፍተት ተደርጎ የተወሰደና ለማስተካከል ጥረት እየተደረገበት ያለ ጉዳይ ነው የሚለው ልሳኑ፣ እነዚህ በቀድሞ የመኖሪያ ቤት ግንባታዎች የተለዩ ችግሮች አንድ ባንድ የተለዩ በመሆናቸው የማይደገሙ መሆኑን በሚያረጋግጥ መልኩ ጥብቅና በዲስኘሊን የሚሰጥ አመራር ማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ ነው” ሲል አስፍሮአል፡፡
የመንግስት የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል እያካሄደ ያለው የቤት ልማት ፕሮግራም አነጋጋሪ መሆኑንና በዜጎችም የሚነሱ ስጋቶች ትክክል መሆኑንም ጹሁፉ ያስረዳል፡፡
የኪራይ ሰብሳቢነት ኃይሎች መንግስት አንድ ሚሊዮን ቤት የመገንባት አቅም በፍጹም ስለማይኖረው ከጥንቆላ ለይተው እንደማያዩትም እየተናገሩ ነው የሚለው ልሳኑ፣ በሕብረተሰቡም ውስጥ ቤቶቹ በፍጥነት ተገንብተው መቼ ሊደርሱ ይችላሉ በሚል በቀላሉ የማይታይ ስጋት የሚታይበትና አነጋጋሪ አጀንዳ መሆኑን እንዲሁም ችግሩ በከፊል አንዳንድ ዜጎች እንደሚያነሱት የቤቶቹ ግንባታ ሂደት ከዚህ በፊት እንደታየው መንቀራፈፍና በሂደቱም የሚስተዋሉ የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባራት ምልክቶች ከመኖራቸው ጋር ተያይዞ ስጋቶች ቢነሱ ተገቢነት የላቸውም አይባልም….” ብሎአል፡፡
የግንባሩ ከፍተኛ አመራሮች ይጽፉበታል ተብሎ የሚገመተው ይህው መጽሔት አንድ ሚሊየን ቤት ፈላጊ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቤት ሰርቶ ማስረከብ እንደማይቻል የሚገልጹ ወገኖችን በጅምላ“የኪራይ ሰብሳቢ ሃይሎች” በሚል ከመፈረጅ ባለፈ ለቤት ፈላጊው ወገን በምን መልኩ ቤቶቹ ተሰርተው ሊሰጥ እንደታቀደ፣ ይህን ያህል ቤቶችን ለመገንባት የገንዘብ፣ የአደረጃጀት መዋቅርና የባለሙያ አቅም ስለመኖሩ በዘገባው ያሰፈረው ነገር የለም፡፡
No comments:
Post a Comment