ሱዳን መዲና ካርቱም ውስጥ በ6 ጋጠወጦች የተደፈረችው ኢትዮጵያዊት ስደተኛ፣ ወጣት፣ ነፍሰጡር ለአንድ ወር እስር ቤት እንድትቆይ እና 950 ዶላር እንድትቀጣ ትናንት ተበየነባት። ወጣቷ ኢትዮጵያዊት ስትደፈር 7ኛው ወንጀለኛ ድርጊቱን በሞባይል ቀርፆ በማኅበራዊ መገናኛ ዘርፍ ማሰራጨቱም ተነግሯል። ወጣቷ በአሁኑ ወቅት እስር ቤት ነው የምትገኘው።
የ18 ዓመት ወጣት የሆነች ኢትዮጵያዊት ስደተኛ ሱዳን መዲና ካርቱም ውስጥ በ6 ጋጠወጦች ተደፍራ ድርጊቱ በማኅበራዊ መገናኛ ዘርፍ ቢሰራጭም፤ ወጣቷ በጥፋተኝነት ቅጣት ተበየነባት። ወንጀሉ ሲፈጸምባት የሶስት ወር ነፍሰጡር የነበረችው ኢትዮጵያዊቷ ወጣት 950 ዶላር ገደማም እንድትከፍል ተፈርዶባታል። ወጣቷ እስር ቤት ውስጥ ነው የምትገኘው። የሴቶች መብት አስከባሪ ተቋም በእንግሊዘኛ ምኅፃሩ SIHA የአፍሪቃ ቀንድ ኃላፊ የሆኑት ወይዘሪት ሐላ ኧልካሪብ።
«እስር ቤት ውስጥ ለአንድ ወር እና ከእዛ በላይ ቆይታለች። የደረሰች ነፍሰጡር በመሆኗ በማንኛውም ጊዜ ልትገላገል ትችላለች። የፈፀምሽው ኢ-ግብረገባዊ ድርጊት ነው በሚል ለአንድ ወር እንድትታሰር ትናንት ተፈርዶባት ነበር። ሆኖም እስር ቤት ወስጥ አስቀድም አንድ ወር ስለቆየች ያ ተነስቶ ለእዛ ተመጣጣኝ የተባለ ወደ 950 ዶላር ግድም እንድትከፍል ተበይኖባታል። ገንዘቡ ቢከፈልም፣ አሁንም ድረስ አልለቀቋትም»
ወጣቷ በግፍ ስትደፈር የሚያሳየው ቪዲዮ ውስጥ ደፋሪዎቹ በአረቢኛ ቋንቋ ሲነጋገሩ፣ ሲስቁ እና በየመሀከሉም ሁለት ጣቶቻቸውን በድል አድራጊነት ምልክት፣ የመሀል ጣታቸውን ደግሞ ለስድብ ካሜራው ፊት ሲቀስሩ ይታያሉ። ለመሆኑ ወጣቷ እንዲህ ጭካኔ በተሞላበት ሁናቴ በ6 ጋጠወጦች እንዴት ልትደፈር ቻለች? ወጣቷ ይላሉ ወይዘሪት ሐላ ኧልካሪብን፤ ወጣቷ ካርቱም ውስጥ መኖሪያ ቤት ለመከራየት ትፈልጋለች። እናም አንድ ደላላ ነኝ ያለ ሰው የሚከራይ ቤት ሊያሳያት ይዟት ይሄዳል። ወጣቷ ክፍሎቹን ስትመለከት እሱ 6 ጓደኞቹን በስልክ በአፋጣኝ ይጠራና ወጣቷን አስገድደው በመድፈር በስልክ ይቀርፃታል።
«ድርጊቱ የተፈፀመው በመስከረም ወር ውስጥ ነው። ይሁንና ግን ከወንጀለኞቹ አንዱ፤ ሰባተኛው ሰው እንደሆነ ይታመናል የአስገድዶ መድፈር ድርጊቱን በእጅ ስልኩ ቀርፆ WhatsApp በተሰኘ የማኅበራዊ መገናኛ አማካኝነት ይለቀዋል።»
እናም ትናንት በጥፋተኝነት የተፈረደባት ኢትዮጵያዊቷ ወጣት ከአንድ ወር በፊት በቁጥጥር ስር ትውላለች። ወንጀሉ በተፈፀመባት ወቅት ግን መንገድ ላይ አንድ ፖሊስ አግኝታ ለማነጋገር ሞክራ ነበር። ወጣቷ ስለተፈፀመባት ወንጀል ለመግለፅ ብትሞክርም የቋንቋ ችግር ስለነበረባት ፖሊሱ አውራ ጎዳናው ላይ ጥሏት እንደሄደም ኃላፊዋ ጠቅሰዋል። ወጣቷ ሱዳን ውስጥ ብዙም እንዳልቆየች፣ የተሰባበረ አረብኛ የምትናገር ከኢትዮጵያ የመጣች ስደተኛ እንደሆነችም ገልፀዋል።
«ልጅቷ ስደተኛ ናት፤ ከኢትዮጵያ ነው የመጣችው። ሱዳን ውስጥ የገባችው ምናልባትም የተሻለ ህይወት ፍለጋ ብላ ነው።»
በሱዳን ሕግ አንዲት ሴት ተደፍራ እንኳን ብትገኝ ድርጊቱ በዝሙት ወንጀል እንደሚያስቀጣ፤ ደፋሪዎቹም ሆኑ ተደፋሪዋ ባለትዳር ከሆኑ ደግሞ በድንጋይ እስከመወገር እንደሚያደርስ ጠቅሰዋል። ደፋሪዎቹ ያላገቡ ወጣቶች በመሆናቸውም በጅራፍ ብቻ ተገርፈው ወደቤታቸው ተለቀዋል።
የአስገድዶ መድፈርን በመቃወም ሰልፍ
የአስገድዶ መድፈርን በመቃወም ሰልፍ
«በደንብ ሊፈረድባቸውና በድንጋይ ሊወገሩ ይችሉ ነበር። ሆኖም ወንጀለኞቹ በሙሉ ያላገቡ መሆናቸውን በማረጋገጣቸው እያንዳንዳቸው 100 ጅራፍ ተገርፈው ወደቤታቸው ሄደዋል።»
በመደነቅ «እና የተደፈረችዋ ወጣት 950 ዶላር እንድትከፍል ተደርጋ እስር ቤት ስትወረወር ወንጀለኞቹ በቃ በ100 ጅራፍ ተሰናበቱ ማለት ነው?» ስል ጥያቄዬን አቀረብኩ። የሴቶች መብት አስከባሪ ተቋም የአፍሪቃ ቀንድ ኃላፊ ወይዘሪት ሐላ ኧልካሪብ ቁጭትን በሚያንፀባርቅ ድምፀት መልስ ሰጡ። «አዎ 100 ጊዜ ገርፈው ለቀቋቸው።» መሰል ፍርድ ሱዳን ውስጥ የተደፈሩ ሴቶችም ሆኑ ወንዶች ለበደላቸው ፍትኅ ሳያገኙ እንዲደበቁ ሲያደርግ የወንጀለኞቹ ድርጊት ደግሞ እንዲባባስ አድርጓል አሉኝ። አክለውም ወጣቷ ኢትዮጵያዊት ሱዳን ውስጥ የገባችው በሕገወጥ መንገድ ነው በመባሉ እስር ቤት ትገኛለች ሲሉ ጠቅሰዋል። ወጣቷ የደረሰች የ9 ወር እርጉዝ ናት።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ተክሌ የኋላ
No comments:
Post a Comment