
በኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም የሚመራው መንግስት ከናቅፋ እስከ ጉና ተራራ ያሉ ምሽጎቻቸውን ከሰማይ በጦር አይሮፕላን፣ ከምድር እሳት በሚያዘንቡ ቢ.ኤሞችና መድፎች ሳያቋርጥ ደበድብም፤ በሀገሪቱ ሰሜናዊ አካባቢ ከቀን ወደ ቀን ግዛታቸውን እያሰፉ የተጠናከሩት ‹‹ወንበዴዎች›› ራስ ምታት ሆነውበታል፡፡ የኤርትራ ‹‹ነጻ አውጪ›› ቤዝ-አምባው በተወሰነ መልኩም ቢሆን ለጥቃት የመጋለጥ እድሉ አናሳ በሆነው የሳህል በረሃ በመሆኑ አብዛኛው የአመራር አባል መሸሸጊያው አድርጎታል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ በትግራይ አካባቢ የሚንቀሳቀሱት የወያኔ መሪዎች ምሽጋቸው እንደ ሳህል ምቹ ባለመሆኑ፤ በርካታ ክፉ ቀናትን ያሳለፉት በተራራማ አካባቢዎች በሚገኙ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ገዳማት ውስጥ ተደብቀው እንደሆነና ከቦታ ቦታ መዘዋወር ሲፈልጉም የመነኮሳቱን አልባሳት ይጠቀሙ እንደነበረ በትግሉ ዙሪያ የተዘጋጁ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡