BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

Sunday, 23 March 2014

ሰበር ዜና – የማኅበረ ቅዱሳንን አመራርና አባላት በአክራሪነት የሚከስ ዶክመንተሪ ሊዘጋጅ ነው ተባለ

(ፋክት፤ ቅጽ ፪ ቁጥር ፴፰፤ መጋቢት ፳፻፮ ዓ.ም.)
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሲኖዶሱን ይኹንታ አግኝቶ በመላው አገሪቱ የሚንቀሳቀሰውን የማኅበረ ቅዱሳንን አመራርና አባላት በአክራሪነት የሚከስ ነው የተባለ ዶክመንተሪ ፊልም ለማዘጋጀት መታቀዱ ተጠቆመ፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አንዳንድ ሓላፊዎች አቀብለውታል በተባለ መረጃ እንደሚታገዝና በመንግሥት አካል እንደሚሰናዳ የተገለጸው የዶክመንተሪ ዝግጅቱ በማኅበሩ ኻያ አመራሮች እና አባላት ላይ እንዳነጣጠረ ተገልጧል፡፡
መንግሥት በምርጫ – 97 ውጤትና በተከታይ ኹኔታዎቹ ላይ ባካሔደው ግምገማ፣ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ናቸው የሚባሉ ግለሰቦች በተለይ በገጠር ቀበሌዎች ለተቃዋሚዎች ተሰሚነት ማግኘት በምክንያትነት መጥቀሱ በዜና ጥቆማው የተመለከተ ሲኾን ‹‹የአክራሪነትና የጽንፈኛ ፖሊቲከኞች ምሽግ ነው›› በሚል የሚያቀርበው ክሥም ከዚኹ የሚነሣና ለመጪው የ2007 ሀገራዊ ምርጫ የሚደረግ ቅድመ ዝግጅትም አካል እንደኾነ ተነግሯል፡፡

በቅድመ ዝግጅቱ የሚወሰዱ ርምጃዎች የማኅበሩን አቅሞችና እንቅስቃሴዎች በመቆጣጠር በተለይም የማኅበሩ መሠረቶች ናቸው የሚባሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያትን ‹‹በሴኩላሪዝም መርሖዎች የመግባቢያ ሰነድ›› ጠርንፎ ‹የአገልግሎት ቅኝቱን የማስተካከል› ዓላማ እንዳላቸው የገለጸው የዜና ምንጩ፣ ይህም ካልተሳካ በተከታታይ አስተዳደራዊ ርምጃዎችና የተቃውሞ ቅስቀሳዎች ማኅበሩን በማወከብ ተቋሙን ለዘለቄታው የማፍረስ ውጤት ሊኖረውም እንደሚችል አመልክቷል፡፡
ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት አብያተ ክርስቲያናት የተጠሩ ናቸው የተባሉ አስተዳዳሪዎችና ሠራተኞች የሚሳተፉበት እንደኾነ የተገለጸና ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በማኅበሩ አገልግሎት ላይ ቁጥጥሩን እንዲያጠብቅ የሚጠይቅ ስብሰባ በዛሬው ዕለት በቤተ ክህነቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እንደሚካሔድ የተዘገበ ሲኾን ዓላማውም ‹‹በአክራሪዎችና ጽንፈኛ ፖሊቲከኞች ምሽግነት፣ የቤተ ክህነቱን አሠራር ባለማክበርና ከቤተ ክህነቱ በላይ ገዝፎ በመውጣት›› ማኅበሩ የሚከሰስባቸውን ኹኔታዎች በማጠናከር ለታቀዱት ርምጃዎች የሚያመቻች ነው ተብሏል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን÷ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ላይ በማተኮር የተማረው ትውልድ ሃይማኖቱን የሚወድ፣ ግብረ ገብነት ያለው፣ ሀገሩንና ቤተ ክርስቲያኑን በዕውቀቱ፣ በሞያውና በገንዘቡ የሚያገለግል ብቁ ዜጋ ይኾን ዘንድ በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ በተሰጠው መተዳደርያ ደንብ መሠረት በመሥራት ላይ እንዳለ የሚገልጹ የማኅበሩ አባላትና ደጋፊዎቹ፣ ማኅበሩ ለቀረቡበት ክሦች የሚመች አደረጃጀት ይኹን ባሕርይ እንደሌለው በመግለጽ ተጠሪ ከኾነለት ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጋራ በአሠራር ሒደት የሚፈጠር ክፍተትን በማጦዝ የሚሰነዘሩ ውንጀላዎች ተቀባይነት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡
የተጠቀሱትን ክሦች ለሚያቀርቡት አካላት ‹‹የሚነገረውና የሚጻፈው እኛን የሚገልጸን ስላልኾነ ማስረጃ አቅርቡና እንነጋገርበት›› የሚል ጥያቄ ቢቀርብላቸውም ለሠለጠነ ውይይት ፍላጎት እንደሌላቸው አባላቱ አስረድተዋል፤ በምትኩ ‹‹ርምጃ እንወስዳለን›› በማለት በተለያዩ መድረኮች ማኅበሩን ማሳጣትና መክሠሥ እንደሚመርጡም ለፋክት መጽሔት አስታውቀዋል፡፡ ታቅዷል የተባለው የዶኩመንተሪ ዝግጅት እውነት ከኾነም ማኅበሩን ብቻ ሳይኾን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የማዳከም አጠቃላይ ዘመቻ አንድ አካል አድርገው እንደሚቆጥሩትና በቀላሉ እንደማይመለከቱት አሳስበዋል፡፡

No comments:

Post a Comment