ኦሎምፒያ አካባቢ የሚገኘውን የቀለም ባለሞያውን የጌታሁን ሄራሞን ቢሮ በጎበኘሁ ቁጥር በሁለት ነገሮች እደሰታለሁ፡፡ በአንድ በኩል ስለ ቀለማት በሚሰጠው ሕይወት ያለው ትንታኔ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ባከማቻቸው የኢትዮጵያውያን ሰዓሊዎች ሥራዎች፡፡ የእርሱ ወንበርና ጠረጲዛው የቢሮውን አንድ ሦስተኛ ብቻ ነው የያዘው፡፡ ቀሪውን የቢሮውን ክፍል ዋናው ባለ አክስዮን ስብስብ ሥዕሎቹ ይዘውታል፡፡ መቼም ሰው ሥራውን ለምንዳዕ ብቻ ሳይሆን በፍቅርም ሲሠራው ሕይወትን በሌሎች ላይ የመዝራት ዐቅም ይኖረዋል፡፡
እዚያ ከተሰበሰቡት ሥዕሎች ውስጥ በመጀመሪያው ክፍል ከጠረጲዛው ከፍ ብሎ ግድግዳው ላይ የተሰቀለው ካንቫስ የፈጠራ ሃሳብ ያስደንቀኛል፡፡ በመስተዋቱ ውስጥ ሁለት ጥቋቁር ካልሲዎች በጫማ አቀማመጥ ቅርጽ ተለጥፈዋል፡፡ አንደኛው ምንም ያልነካው ‹አዲስ› ካልሲ ነው፡፡ ሁለተኛው ግን ተረከዙ ላይ ተቀድዷል፡፡
የጥበቡ ርእስ ‹ጥንድ የመሆን ፈተና› ይላል፡፡ ምን ማለት ነው? ደጋግሜ አየሁት፡፡ ‹‹ወፍ ስትበር የሚያሳይ ሥዕል ሳሉ›› ተብለን በሥዕል ትምህርት ቀልደን ላደግን ሰዎች የሥዕልን ጥበብ ዘልቆ ምሥጢሩን መረዳት እንደ ዋድላ ቅኔ ከባድ ምርምርን ይጠይቃል፡፡ ለረዥም ሰዓት ነው አፍጥጬ ያየሁት፡፡ እንዲያውም በመሐሉ የሥዕሉን ምሥጢር ከመመርመር ወጥቼ እኛ ቤት የነበረች አንዲት የቤት ሠራተኛችን ትዝ አለችኝ፡፡ የምገዛቸው ካልሲዎቼ ሁሉ ከጥቂት ቀናት በኋላ ከትዳር ተፋትተው ላጤ ሆነው ነበር የማገኛቸው፡፡ ‹‹ምንድን ነው?›› ስላት ‹አይጦቹ ናቸው›› ትለኛለች፡፡
ግርም ይለኝ የነበረው የነዚህ የስምንተኛው ሺ አይጦች ጠባይ ነበር፡፡ የሀብታም ትምህርት ቤት እንደገባ ልጅ ‹ለአንድ ቀን አንድ ዓይነት› የሚል መርሕ ሳይኖራቸው አይቀርም፡፡ ቢሞቱ ሁለቱንም ካልሲዎች አይበሏቸውም፡፡ ከሁለቱ አንዱን ብቻ ነው የሚመገቡት፡፡ አንዳንዱን ካልሲ ወስደው ለሆቴላቸው በያይነቱ ያዘጋጁበትም እንደሁ እንጃ፡፡ አንዱ ጓደኛዬ ደግሞ የለም ልጂቱ ባለ አንድ እግር ወዳጅ ሳይኖራት አይቀርም ይለኛል፡፡ ከሁለቱ አንዱ ነው፤ ወይም ሌላም ሊሆን ይችላል፡፡
አሁን እዚህ ደግሞ ካልሲ ጥበብ ሆኖ በፍሬም ተሰቅሎ ሳየው ገረመኝ፡፡
‹‹ጥንድ የመሆን ፈተና››
በኋላ ጌታሁን አንድም እያለ ተረጎመልኝ፡፡ ‹‹እስኪ እየው፤ ይኼኛው ካልሲ ደህነኛ ነው፡፡ እንዲያውም ቅድም እንዳልከው አዲስ ይመስላል፡፡ ተጣማሪው ግን ተቀድዷል፡፡ ካልሲ ሊደረግ የሚችለው በጥንድ ብቻ ነው፡፡ በዚህ በተቀደደው ምክንያት ያልተቀደደው ካልሲም ከጥቅም ውጭ ሆኗል፡፡ ቤቴ ውስጥ በተደጋጋሚ ሲያጋጥመኝ ጊዜ ይህንን ሃሳብ አሰብኩት፡፡ የዚህ የደህነኛው ካልሲ ጥፋቱ ምንድነ ነው?አልኩ፡፡ ሳስበው ጥፋቱ አንድ ብቻ ነው፡፡ የቀዳዳው ካልሲ ተጣማሪ መሆኑ፡፡ በቃ ተጣማሪው ስለ ተቀደደ እርሱም ይጣላል፤ ያለበለዚያም ለልጆች ኳስ መሥሪያነት ይውላል፡፡ ጥንድ የመሆን ፈተና ይኼ አይደለም ታድያ?›› አለኝ፡፡
እርሱ ይሄንን ሲነግረኝ ባለትዳሮች፣ ጓደኛሞች፣ የንግድ ሸሪኮች፣ የጥበብ ወዳጆች፣ የሥራ አጋሮች፤ እንዲቀያየር ሆኖ እንደተጫነ የኮምፒውተር ስክሪን ሴቨር በዓይነ ኅሊናዬ ቦግ እልም እያሉ አለፉ፡፡ ምርጥ ባል፤ የባሎች ሁሉ መለኪያ ሊሆን የሚችል፤ አባትም ባልም ተብሎ የሚነገርለት ተጣማሪው ተበላሽታ ሲበጠበጥ፣ ሲታመስ፣ ሲመሳቀል፣ ዐቅሙ ሲደክም፣ ሥራው ሲበላሽ፣ አእምሮው ሲናወጥ፣ ይኖራል፡፡ አይቆርጠው አካል፣ አይተወው ሕመም ሆኖበት፤ አይናገር ምሥጢር፣ ዝም አይል ብሶት ሆኖበት፤ ከዕረፍት እንደተመለሰ እሥረኛ ቤቱ እያስጠላው፣ ጥንድ መሆን ፈተና ላይ ጥሎት ይኖራል፡፡
ምን የመሰለች ሚስት፣ ዐፄ ቴዎድሮስ ‹ሚስት ናት ገረድ› ያሏት ዓይነት፣ ልጆቿን አፍቃሪ፣ ባሏን አክባሪ፣ ትዳርዋን አሥማሪ የሆነች ሚስት፣ ባሏ ተበላሽቶባት፣ ይኼው
ትዳር ምን ዕዳ ነው፣ ጎጆ ምን ዕዳ ነው
ከገነት ተባርሮ ገሐነም መኖር ነው
እያለች ታንጎራጉራለች፡፡ ሥራዋ፣ ሀብቷ፣ መልኳ፣ ዕውቀቷ፣ ጠባይዋ፣ ሥልጣኗ፣ ክብሯ፣ ዝናዋ ከሰው በላይ ሆኖ የትዳር አጋሯ ግን የተቀደደ ጣራ፣ የፈረሰ ግድግዳ፣ የማይዘጋ በር፣ የሚዋጋ ጫማ፣ የሚኮሰኩስ ልብስ፣ የሚያቃጥል ወጥ፣ የሚኮመጥጥ እንጀራ ሆኖባታል፡፡ አትተወው ትዳር፣ አትኖረው ሲኦል ሆኖባት፤ ስንት ውስብስብ ችግር በቢሮዋ የፈታች ሊቅ፣ የአጋርን ችግር መፍታት ቸግሯት ተጣማሪ ካልሲ ሆናለች፡፡
በአምስት ጣት የሚበላ ሰው መቼም አብሮ መሥራትን አይጠላም፡፡ ‹ድር ቢያብር አንበሳ ያሥር›፣ ‹ለአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ›፣‹ለአንድ ጉርሻ ሠላሳ ሁለት ጥርስ› እያለ የሚተርት መቼም አብሮ ተባብሮ መሥራትን አይጠላም፡፡ ማበር የሚያስጠላው፣ ሽርክና የሚያስመርረው፤ ኅብረት፣ አንድነት፣ ማኅበር፣ ቡድን፣ ኮሚቴ፣ የሚያቅለሸልሸው እንደ ካልሲው ከተጣማጆቹ የሚቀዳደድ ካለ ነው፡፡ አብሮ ለመሥራት፣ አብሮ ለማደግ፣ አብሮ ለመልፋት፣ አብሮ ለመትጋት ወስነው አጋና ከመቱ በኋላ አንዱ ወገን እንደ ካልሲው የተቀደደ ከሆነ፣ የቀዳዳው ዕድል ፈንታ በደህናው መወሰን ሲኖርበት፣ የደህናው ዕድል በቀዳዳው መወሰን ከጀመረ፣ ያኔ ነው አብሮ መሥራት እሴት ከመሆን ይልቅ ዕዳ የሚሆነው፡፡
ይህንን ካልሲ ሳይ መኪና ታወሰኝ፡፡ አራት እግር ያለው መኪና አንዱ ጎማ ሲተነፍስ የሚቆመው ለምንድን ነው? ጥንድ የመሆን ፈተና ገጥሞት አይደል፡፡ ያልተነፈሱት ሦስት ጎማዎች በተነፈሰው አንድ ጎማ ምክንያት መቆማቸው የግድ ነው፡፡ ስንት የተጣመሩ ፓርቲዎች ከመካከላቸው እንደ ካልሲው የተቀደደ፣ እንደ ጎማው የተነፈሰ ሲያጋጥማቸው አይደል ቆመው ወይም ፈርሰው የቀሩት፡፡
አንዳንዴ ምንም ያህል ብንፈልገው ብቻችንን ልንሆነው የማንችለው ነገር አለ፡፡ ብቻችንን ብንሠራው እንኳን ከማናውቅ አካል ጋር የምንጣመርበት ጉዳይም አለ፡፡ ‹አይ የታክሲ ሾፌር፣ አይ አስተናጋጅ፣ አይ ነጋዴ፣ አይ ቀበሌ፣ አይ ተቃዋሚ፣ አይ ደጋፊ፣ አይ ጋዜጠኛ፣ አይ ፖሊስ› እየተባልን በምናውቀውም በማናውቀውም፤ ባደረግነውም፣ ባላደረግነውም የምንወቀሰውኮ ‹ጥንድ በመሆን ፈተና› ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ እኛ ብቻችንን መልካም ብንሠራ፣ ንጹሕና ጻድቅ ብንሆን እንኳን፣ የሆነ ቦታ በሚገኙ ሳናውቅና ሳንፈቅድ በተጣመርናቸው የሞያ አጋሮቻችን ጥፋት መወቀሳችንና ሕዝባዊ አመኔታ ማጣታችን አይቀሬ ነው፡፡
ጥቂት የዚያ ብሔረሰብ ሰዎች፣ የተወሰኑ የዚያ ቡድን አባላት፣ እፍኝ የማይሞሉ የዚያ ሀገር ዜጎች፣ በጣት የሚቆጠሩ የዚያ ሃይማኖት አማኞች፣ ውክልና የሌላቸው የዚያ ማኅበር አባላት፣ ለራሳቸው ብቻ ሲሉ ወጥ በረገጡ የዚያ ሞያ ባለቤቶች፣ ከሁለት ወንበር በማይበልጡ የዚያ መሥሪያ ቤት ባልደረቦች ጥፋት ‹እንደ አህያ ጆሮ እንደ ጦር ጉሮሮ‹ ሁሉንም አንድ አድርጎ የመኮነን አባዜ የመጣው ጥንድ ከመሆን ፈተና ነው፡፡ በተቀዳደዱ ካልሲዎች ምክንያት የሚያገለግሉትም አብረው እንደሚጣሉት፡፡
ምርጥ የባለሞያ ወጥ፣ በስሕተት በበዛ ጨው ምክንያት ተመጋቢ የሚያጣው ጥንድ የመሆን ፈተና ገጥሞት ነው፡፡ ‹በጨው ደንደስ በርበሬ እንደሚወደሰው› ሁሉ በጨው ጥፋትም በርበሬ ከጥቅም ውጭ ሊሆን ይችላል፡፡
ዘመናዊ ኑሮ የጉርብትና ሥርዓት ነው፡፡ ዐውቀነውም ይሁን ሳናውቀው ከብዙ ነገሮች ጋር ተጣምረንና ኅብረት መሥርተን ነው የምንኖረው፡፡ ሰው ብቻውን መጥፎ፣ ብቻውንም ጥሩ መሆን አይችልም፡፡ ብቻውን ንጹሕ፣ ብቻውንም ቆሻሻ ለመሆን አይችልም፡፡ እኛ ቤት የምትመጣው ዝንብ ከየት መነሣት እንዳለባት ልንወስንላት አንችልም፡፡ አንዳንድ ጊዜ በአንድ መንደር መብራት፣ ውኃና መንገድን ለማስገባት፤ ጸጥታ፣ ንጽሕናና ውበትን ለመጠበቅ መንደሩ ሁሉ ይስማማና ጥቂት ጎረቤቶች ግን እምቢ ይላሉ፡፡ አልከፍልም፣ አልሠራም፣ አልሰበሰብም፣ አልተባበርም፣ አያገባኝም ይላሉ፡፡ የስንት ጎበዞችን ዕቅድ የጥቂት ቀዳዳ ካልሲዎች ችግር ከጥቅም ውጭ ያደርገዋል፡፡
ጥንድነት የማይቀር የኑሮ ሥርዓት ከሆነ ከባዱ ነገር ጥንድ የመሆንን ፈተና እንዴት እንለፈው ነው፡፡
‹‹ትንሽ በር በሬ ብደቁሰው፣ ብደቁሰው
ሀገሩን ሁሉ አስነጠሰው፣ አስነጠሰው››
የተባለው ይህንን ይነግረናል፡፡ ለማስነጠስ በርበሬ መደቆስ አያስፈልገንም፡፡ የሌላው ጎረቤት በርበሬ በቂ ነው፡፡ በቢሯችን ውስጥ መልካም ሽቱ የተቀባ ሰው ካለ ለሁላችን መዓዛው እንደሚተርፈው ሁሉ፣ የጫማውን ጠረን ማስወገድ ያልቻለውም የቢሯችን ባልደረባም በተቃራኒው እንዲያ ነው፡፡
ጥንድነት የሚያመጣውን ፈተና ለመወጣት አንድም የዳበረ የኑሮ ጥበብ ያሻል፣ አንድም የታሰበበትና ተገቢ የሆነ የጥንድነት ልማድና ሕግ ያስፈልጋል፤ አንድም ደግሞ ከፈተናው የመውጫ ውጤታማ የአደጋ ጊዜ በር ሊሠራ ይገባል፡፡ ጥንድነት የሚያመጣውን ፈተና ለመከላከል፣ ካልሆነም ለመፍታት የሚያስችል ከማኅበረሰቡ ጋር የተዋሐደ የኑሮ ጥበብ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን የኑሮ ጥበብ ለመገንባት ደግሞ የሃይማኖት ትምህርቶች፣ ሥነ ቃል፣ ሚዲያና ዘመናዊ የኑሮ ዘዴ ትምህርቶች ታላቅ አስተዋጽዖ ያደርጋሉ፡፡
አብሮነት የሚያስከትላቸውን ፈተናዎች ማራቂያ፣ ሲመጡም የከፋ ጉዳት ሳያደርሱና እንደ ቀዳዳው ካልሲ ለመጣል ሳያበቁ፣ ማስወገጃ የዳበረ ሀገራዊ ልማድና ሕግም ወሳኘው ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ፈተናውን አምቀን ብቻ እንድንይዘው፣ ያለ መውጫ እንድናስበው፣ የዐርባ ቀን ዕድል አድርገን እንድንቆጥረው፣ መፍትሔው አብሮ መውደቅ ብቻ አድርገን እንድናየው የሚያደርግ ሀገራዊ ልማድና ሕግ ካለ ጥንድነት እሴት ሳይሆን ዕዳ ብቻ ይሆናል፡፡
ፍየል ቀንዷ ለምን ወደ ኋላ ዞረ? ሲባል፤ ስትገባ መውጫ መውጫውን ለማየት ነው አሉ፡፡ የምንገባበት ነገር ሁሉ አንዳች የመውጫ የአደጋ ጊዜ በር ሊኖረው ይገባል፡፡ የአደጋ ጊዜ በር በማናቸውም ጊዜ፣ በፈለገው ሰው፣ ለማናቸውም ዓይነት ምክንያት አይከፈትም፡፡ የሚከፈትበት ምክንያት፣ ጊዜ፣የመክፈት ሥልጣን ያለው አካል አለ፡፡ በጥንድነት ፈተናም እንዲሁ ነው፡፡ እንደ መግቢያው በር ሁሉ የመውጫ የአደጋ ጊዜም በር ያስፈልጋል፡፡ መግቢያ ብቻ ያለው ባለ አንድ በር ቤት ለጥንድነት አይመከርም፡፡ ዐውቀን የዘጋነው፤ በአደጋ ጊዜ ግን ልንከፍተው የምንችለው፣ የመጨረሻው አማራጫችን እርሱ ሲሆን ዘለን የምንወጣበት የአደጋ ጊዜ በር ያስፈልጋል፡፡ ‹እኔ በዚህ አልስማማም፣ የእኔ ሃሳብ የተለየ ነው፣ እኔ በዚህ መኪና ተሳፍሬ እስክገለበጥ ድረስ አልጓዝም› ብለን ልንናገርበት የምንችለው በር፡፡ ጥንድነት ዕድልና መብት እንጂ ዕዳና ግዴታ እንዳይሆን፡፡
No comments:
Post a Comment