ማጋቢት ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አንዳንድ ሾፌሮች ለኢሳት እንደገለጹት በባህርዳር ከተማ ወደ ሌሎች ክልሎች ወይም ተዘዋውረው በመስራት ላይ ያሉ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ የታክሲ አሽከርካሪዎች ታስረው 10 ሺ ብር የሚደርስ ቅጣት እንዲከፍሉ እየተደረገ ነው።
በአገራችን እንደልባችን ከክልል ክልል ተዘዋውረን እንዳንሰራ በፖሊሶች ታግደናል የሚሉት ሾፌሮች፣ ለምን ብሎ የጠየቀ ሰው ድብደባ እንደሚፈጸምባቸው ይናገራሉ
በሌላ በኩል ደግሞ በሸዋ ሮቢት ከተማ የሚገኙ የባጃጅና የታክሲ አሽከርካሪዎች ከአማራ ክልል ውጭ በመሄድ በሌሎች ክልሎች መንጃ ፈቃድ በማውጣታቸው፣ ክልሉ በህጋዊነት ሊቀበለው እንደማይችል በመግለጹ ስራ ማቆማቸውን ተናገሩ። ካለፉት 4 ቀናት ጀምሮ ተቃውሞዋቸውን እያሰሙ የሚገኙት የታገዱ ሾፌሮች ጉዳያቸውን ከክልል እስከ ፌደራል ባለስልጣናት ቢያቀርቡም መፍትሄ ሊያገኙ አልቻለም።
ሾፈሮቹ ችግራቸው በአስቸኳይ የማይፈታ ከሆነ የረሀብ አድማ እንደሚጀምሩ ተናግረዋል ።
አንድ የክልል ሾፌር ወደ ሌላ ክልል ሄዶ መንጃ መፈቃድ ለማውጣት እንደማይችል የሚደነግግ ህግ አለመኖሩን ለማወቅ ተችሎአል። የኢትዮጵያ ህገመንግስት ሰዎች ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው መስራት እንደሚችሉ ቢደነግግም ይህ መብት በብዙ ክልሎች እየተጣሰና ክልሎች ራሳቸውን እንደ አገር በመቁጠር ማስተዳደር መጀመራቸውን የሚመለከቱ ትችቶች ይቀርባሉ።
መንግስት በበኩሉ በቋንቋና በዘር ላይ የተመሰረተው የፌደራል ስርአት የአገሪቱን አንድነት አስጠብቋል፣ ግጭቶችንም ለማስወገድ አስችሎአል ብሎ ይከራከራል።
No comments:
Post a Comment