ባለሃብቱ ተወዳድሮ ተገቢና ፈጣን አገልግሎትን ለህዝብ ያቀርባል፡፡ ህዝብም በዋጋም ሆነ በጥራት የተሻለውን አገልግሎት
አማርጦ ይገዛል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መንግስት ኢኮኖሚውን በቀጥታም ሆነ በእጃዙር በተቆጣጠረባቸው አገራት መሰረታዊ
አገልግሎትን ለህዝብ ማዳረስ ዋነኛው የመንግስት ስራ ይሆናል፡፡ በአገራችን ኢኮኖሚው ከመንግስትም ወርዶ በገዥው ፓርቲ
ቁጥጥር ስር ከዋለ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ገዥው ፓርቲ የስልጣን መከታ ያደረገውን የአገሪቱን ኢኮኖሚና አገልግሎት
ሰጭ ድርጅቶችን ለግል ባለሃብቶች ለመልቀቅ ፈቃደኛ አለመሆኑ ህዝብ ተገቢውን አገልግሎት እንዳያገኝ እንቅፋት ፈጥሯል፡፡
መንግስት ኢኮኖሚውን እመራለሁ በሚልባቸው ሌሎች አገራት የግል ባለሀብቶች እንደ መብራት፣ ውሃና ቴሌኮሚኒኬሽን ያሉትን
አገልግሎቶች ከግል ባለሃብቶች አሊያም ከራሱ ከመንግስት ጋር በመወዳደር ለህዝብ ያቀርባሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እነዚህ ቁልፍ
የህዝብ አገልግሎቶች በመንግስት ቁጥጥር ስር ብቻ ይገኛሉ፡፡ እነዚህን አገልግሎቶች ሞጭጮ የያዘው መንግስት ህዝብ ከአመት
አመት የተሻለ የመብራት፣ የውሃና የቴሌኮምኒኬሽን አገልግሎት እንደሚያገኝ ቃል ከመግባት ባይቆጠብም አገልግሎቶቹ ግን
አመት አመት ህዝብን እያማረሩ ቀጥለዋል፡፡
በተደጋጋሚ የኃይል ማመንጫዎች እንደተሰሩና እየተሰሩ
እንደሆነ ቢነገርም መብራት እስካሁን ከነበረውም በባሰ አዲስ አበባን ጨምሮ በመላ አገሪቱ በአንዴ ጠፍቶ እያደረ ስለመሆኑ
ሰሞነኛ ክስተት ነው፡፡ ህዝብ ጨለማ ውስጥ በሚኖርበት በአሁኑ ወቅት ጂቡቲን ጨምሮ ለጎረቤት ሀገራት መብራት እየተሸጠ
መሆኑ የመንግስትን ግድ የለሽነት የሚያሳይ ነው፡፡ ህዝብ ጨለማ ውስጥ ሆኖ በቀጣይ የተሻለ መብራት እንደሚያገኝ
ቃል ለመግባት የማይታክተው መንግስት አሁንም ለአባይ ግድብ የመንግስት ሰራተኞች፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ
ኢትዮጵያውያንና ተማሪዎች ላይ ገንዘብ እየሰበሰበ ይገኛል፡፡ ከዚህም ባሻገር በመብራትና በሌሎች አገልግሎቶች መቆራረጥና
መጥፋት ምክንያት ንግድ ቤቶች እየተዘጉ ነው፡፡ በውሃ እጥረት ምክንያት ተማሪዎችና አዛውንቶች ካለ አቅማቸው
ከሰፈር ሰፈር እየተንከራተቱ በጀርባቸው ለመሸከም ተገደዋል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የቴሌኮሚኒኬሽን አገልግሎት
ምክንያት ህዝብ ስልክና ኢንተርኔት መጠቀም አልቻለም፡፡ ባልታቀዱ ግንባታዎች ምክንያት የሚፈራርሱት መንገዶች
ህዝብ በሰዓት ወዳሰበበት ቦታ እንዳይደርስ አድርገዋል፡፡ እነዚህ አገልግሎቶች የሰማይ ያህል በራቁበት ወቅት ሙስና፣ የመልካም
አስተዳደር እጦት፣ ህዝብ ሊያገኘው በሚገባው አገልግሎት ላይ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆነውበታል፡፡
ያለ መብራት፣ ውሃና ቴሌኮሚኒኬሽን ህዝብ ሰርቶ ለማትረፍ ይቅርና የራሱን ህይወት ለማሰንበትም እየተቸገረ ነው፡፡ ተግባሩን
በሚገባ የማይወጣው መንግስትና ደካማ ተቋማቱ ህዝብ ለእነዚህ የሚቆራረጡና የሚጠፉ አገልግሎቶች ክፍያ አንድና ሁለት
ቀን ዘግይቶ ሲከፍል ተገቢ ያልሆነ ቅጣት ይጥላሉ፡፡ ሃይ ባይ ያጣው መንግስትና ተቋማቱ የህዝብን አገልግሎት ሲያቆራርጡና
ሲያጠፉ ግን ህዝብ ምንም አይነት ካሳ እያገኘ አይደለም፡፡ ደንበኞች የአገልግሎት ክፍያ የሚከፍሉት በሚሰጣቸው
አገልግሎት ሳይረኩና አንዳንዴም ጭራሽ አገልግሎቱን ሳይጠቀሙ ነው፡፡ ይህም መንግስት ያለምንም ሌላ አማራጭ
ብቸኛ የአገልግሎት ሰጭ ተቋማቱ ተቆጣጣሪና ባለቤት በመሆኑ ነው፡፡ ህዝብ አማራጭ ተነፍጎታል፡፡ የውሃ ያለህ እያለ ነው!
የመብራት ያለህ እያለ ነው! የስልክ ያለህ እያለ ነው! በአጠቃላይ የአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ህዝብ እየጮኸ ነው፡፡ በተለያየ
መልኩም እሮሮውን እያሰማ ነው፡፡ መንግስት ግን ለዚህ የህዝብ ጩኸት ምላሽ መስጠት ተስኖታል፡፡
ነገረ-ኢትዮጵያ ህዝብ እያለቀሰ መቀጠል የለበትም ትላለች፡፡ ስለሆነም መንግስት ለህዝብ ጨኸት ጆሮ መስጠትና በተደጋጋሚ
ህዝቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች አስቸኳይ ምላሽ መስጠት እንዳለበት አበክራ ታሳስባለች!
‹‹እውነት ምን ያህል ትቢያ ላይ ብትጣል ትቢያዋን አራግፋ በድል የምንቆምበት የመኸር ዘመን ይመጣል፡፡ ያን ጊዜም የነጻነት
ብርሃን እንደ ማለዳ ፀሐይ የሚፈነጥቅ ይሆናል፡፡››አንዱዓለም አራጌ፣ ያልተሄደበት መንገድ‹‹ደርግ የሚፈልገውን በጠራራ ፀሐይ ደጃፍ ላይ ገድሎ ‹‹የፍየል ወጠጤን......›› እያስዘፈን ይፎክራል፣ ኢህአዴግ የሚፈልገውን ጨለማ ውስጥ በስውር ገድሎ ይቀብርና ጧት ‹‹እከልዬን ምን ነካብኝ ኧረ የት ገባ ኑ አፋልጉኝ እስኪ ይላል፡፡››ሻምበል አስረስ ገላነህ፣ የካድሬው ማስታወሻ
‹‹እኔ የእናንተን ሞት አያለሁ፤ እናንተ ግን የእኔን ሞት አታዩም፡፡››ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃ/ማርያም
‹‹የኢትዮጵያ ህዝብ በሌላው ዓለም የሌለ ትልቅ ትዕግስት አሳይቷል፡፡ ይህ ህዝብ የታገሰውም ከቀን ወደ ቀን መሻሻል ይኖር
ይሆናል በሚል ነበር፡፡›› አልጋ ወራሽ ልዑል አስፋው ወሰን
No comments:
Post a Comment