BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

Monday, 31 March 2014

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች ምሬታቸውን ለፓርላማ አሰሙ

‹በሕይወቴ ያለምቾት የሠራሁበት ወቅት አሁን ነው›› የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሀብትና ንብረትን ለመጠበቅና ለማስተዳደር ሲባል ‹‹ራሳችንንና ቤተሰቦቻችንን ችግር ውስጥ ከተናል›› በማለት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች ለፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ምሬታቸውን ገለጹ፡፡


የኦዲት አገልግሎት ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢና በሥሩ የሚገኙ ተቋማት ላይ ከ1999 እስከ 2002 ዓ.ም. ባለው ሒሳብ ላይ ያካሄደውን ኦዲትና የኦዲት ግኝቶችን አስመልክቶ ማብራርያ እንዲሰጡ፣ ባለፈው ዕለት በፓርላማው የመንግሥት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተጠርተው በተወቀሱበት ወቅት ነው አመራሮቹ ምሬታቸውን የገለጹት፡፡

በዋናው ግቢ ከልዩ ልዩ የተሰብሳቢ ሒሳብ መሰብሰብ የሚገባው 80.7 ሚሊዮን ብር ለረዥም ጊዜ መንከባለሉን፣ የሚሰበሰብ ከሆነም ከማን እንደሚሰበስብ አለመታወቁ፣ በዋናው ግቢ በግዥ ቅድመ ክፍያ ተከፍሎ የመጀመርያው ሳይወራረድና ሳይረጋገጥ ድጋሚ የግዥ ቅድሚያ ክፍያ በተለያዩ አቅራቢዎች ተመዝግቦ መገኘቱና ለረዥም ጊዜ ያልተወራረደ ሒሳብ በድምሩ 29.8 ሚሊዮን ብር መገኘቱ፣ በአንዳንድ ሒሳብ መደቦችና አካውንቶች ጭራሹኑ የባንክ ማስታወቂያ ሒሳብ ያልተሠራላቸው መኖራቸውና የሒሳቡ ትክክለኝነትን ማረጋገጥ አለመቻሉን የኦዲት ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡
ለአብነት ያህል ከተጠቀሱት ውስጥ በዋናው ግቢ በጥሬ ገንዘብ በባንክ ሒሳብ 28 ሚሊዮን ብር መኖሩ የጥሬ ገንዘብ ቆጠራና የባንክ ሒሳብ ባለመዘጋጀቱ ስለትክክለኛነቱ ማረጋገጥ አለመቻሉ፣ እንዲሁም በገንዘብ ያዥ እጅ 10.4 ሚሊዮን ብር በጉድለት መታየቱና ምክንያት ሊቀርብለት አለመቻሉ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ እሸቱ ተሾመና ሌሎች የቋሚ ኮሚቴው አባላት እንዲሁም የዋናው ኦዲተር መሥሪያ ቤት ባለሙያዎችና ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዱቢሶ የኦዲት ግኝቱን አስመልክቶ የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበውላቸዋል፡፡
‹‹የአገሪቱን የፋይናንስ ሕግ፣ ደንብ፣ መመርያና አሠራር ለማክበር ችግራችሁ ምንድነው? ዩኒቨርሲቲው ሒሳቡን በወቅቱ ዘግቶ ኦዲት አለማድረጉና ችግሩን በወቅቱ አለማረሙ ምክንያቱ ምንድነው? ተጠያቂነቱን እንዴት ትዘነጋላችሁ›› በማለት ጠይቀዋቸዋል፡፡
በቀረቡት ጥያቄዎች ላይ የማጠቃለያ ምላሽ የሰጡት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አድማሱ ፀጋዬ፣ ‹‹በዋናነት መታወቅ ያለበት ችግሩን የማስተካከል ኃላፊነት እንጂ እኛ ተጠያቂ አይደለንም፡፡ ምክንያቱም አሁን ያለው አመራር ከመምጣቱ በፊት የተከሰተ ችግር ነው፤›› በማለት ግንዛቤ እንዲወሰድ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ይህ ማለት ግን ኃላፊነቱ አይመለከተንም ማለት እንዳልሆነ፣ አሁን ያለው አመራር ሚና የተፈጠሩትን ችግሮች ማረም፣ ማስተካከልና በዛላቂነት ለመፍታት ሲስተም መፍጠር ነው፤›› ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ከተጀመሩ የሲስተም ዝርጋታዎች አንዱ ሕግን በተከተለ መንገድ አሥራ አምስቱን የዩኒቨርሲቲው ግቢዎች የንብረት ቆጠራ ማካሄድና የሀብት ግምታቸውን ማወቅ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የዩኒቨርሲቲው ንብረቶች የሚመዘገቡት በእርሳስ እንደሆነ፣ የንብረት ክፍል ኃላፊዎች ሲቀየሩና አዲስ ኃላፊ ሲመጣ በላጲስ ጠፍቶ የአዲሱ ኃላፊ ስም እንደሚመዘገብ አስታውቀዋል፡፡
የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴርን አስፈቅዶ ዩኒቨርሲቲው ገንዘብ ሲሰበሰብ የነበረው ራሱ በሚያሳትመው የገንዘብ መሰብሰብያ ሰነድ መሆኑን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ አሁን ግን ገንዘብ ሚኒስቴር በሚያውቀው ሰነድ መሰብሰብ አለበት በመባሉ ወደዚህ ሥርዓት እየተገባ ነው ብለዋል፡፡ ኦዲት መደረግና መሰብሰብ ባልቻሉት ሒሳቦች ላይ ዕርምት ተወስዶ በርካታ ሚሊዮን ብሮች ተሰብስባዋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ምክትል ፕሬዚዳንቱ ዶ/ር ጄሎ ዑመር፣ ‹‹ዩኒቨርሲቲው ከ50 ሺሕ በላይ ተማሪዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከ20 ሺሕ በላይ በግቢው ውስጥ ነው የሚኖሩት፡፡ እነሱን በቀን ሦስቴ መመገብ አለብን፡፡ ግቢው ውስጥ ኮሽ ሳይል የመማር ማስተማሩ ሒደት መቀጠል አለበት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የፋይናንስም ሆነ የግዥ ሕጉን ማስተናገድ መቻል አለብን፡፡ እነዚህን አጣጥሞ መሄድ ምን ያህል ፈተና እንደሆነ ካልገባን በስተቀር አስቸጋሪ ነው፤›› በማለት ያለውን ሁኔታ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ችግሩ በቀድሞዎቹ አመራሮች ጊዜ የተፈጠረና ሥር የሰደደ በመሆኑ አስቸጋሪ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
‹‹እውነት ለመናገር ራሴንም ቤተሰቦቼንም ለችግር አጋልጬ ነው የምሠራው፡፡ ታመኖብን ከገባን አይቀር ብለን እንጂ ምቾት ተሰምቶን አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹እኔ በሕይወቴ ምቾት ሳይሰማኝ ሥራ የምሠራበት ወቅት ቢኖር ባለፉት ሦስት ዓመታት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን ከተቀላቀልኩ በኋላ ነው፤›› በማለት ምሬታቸውን አሰምተዋል፡፡
የሚቻለውን ያህል ሕግ ለማስከበር እየሠሩ መሆናቸውን የተናገሩት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ የዩኒቨርሲቲውን መኖሪያ ቤቶች ተረክበው የነበሩ መምህራን ከዩኒቨርሲቲው ቢለቁም መኖሪያ ቤቱን ግን ለቤተሰቦቻቸው ሰጥተው ቤተሰቦቻው አከራይተው እየኖሩ መሆኑ እንደተደረሰበትና ሕገወጥነቱን ለማስቆም ግብግብ ውስጥ መግባታቸውን ጠቁመዋል፡፡
ፕሮጀክቶች ከተጠናቀቁ በኋላ ለዩኒቨርሲቲው መመለስ የሚገባቸው ተሽከርካሪዎች አሁንም በመምህራን ንብረትነት እየተቆጠሩ በመሆናቸው፣ ይህንን ሁኔታ ለመቀየር ንትርክ ላይ መሆናቸውን በማስረዳት ጥረታቸው በፈተና የታጀበ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

No comments:

Post a Comment