BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

Thursday, 13 March 2014

በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ ከ60 በላይ ቤቶችና ድርጅቶች ይፍረሱ መባሉ ውዝግብ አስነሳ

ማጋቢት ፬ (አራት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በንፋስ ስልከ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ ፣ ከለቡ አካባቢ ተነስቶ በቱሉ ዲምቱ አድርጎ አዳማ ድረስ ይሠራል በተባለው መንገድ ምክንያት፣ ከ60 የሚበልጡ መኖሪያ ቤቶችና የንግድ ድርጅቶች እንደሚፈርሱ በመገለጹ፣ ነዋሪዎችና ክፍለ ከተማው እየተወዛገቡ መሆናቸውን ሪፖርተር ዘገበ።

የመኖሪያ ቤቶችና የንግድ ተቋማትን ለመገንባት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር   በ1994 ዓ.ም ያቀረቡት  ጥያቄ  ተቀባይነት አግኝቶ በ1997 ዓ.ም.  የአካባቢውን የልማት ዕቅድ በጠበቀ ሁኔታ እንዲሠሩ  በተሰጣቸው መሬት ላይ ከባለአንድ እስከ ባለአራት ፎቅ የሚደርሱ ከ60 በላይ የመኖሪያና የንግድ ድርጅቶች ሕንፃዎችን ገንብተው እየኖሩና እየሠሩበት እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ለቡ አደባባይ ባለው ኃይሌ ጋርመንት አካባቢ እንደሚገኙና እስከ 500 የሚደርሱ ቤተሰቦችና ሠራተኞች እንዳሏቸው የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፣ በኑሮ ውድነት ወቅት  ተበድረውና ያላቸውን ጥሪት ጨርሰው የገነቡትን ቤት ‹‹መንገድ የሚያልፍበት ነው›› በሚል ማፍረስ ተገቢ አለመሆኑን እየገለጹ ነው፡፡
መንገዱን  በሌላ በኩል አድርጎ መገንባት እንደሚቻል የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፣ ይሁንና የክፍለ ከተማው አስተዳደር ለመንገዶች ባለሥልጣን  ይህንኑ አማራጭ በአግባቡ ማስረዳት እየቻለ በዝምታ በማለፉ ለከፋ ጉዳት እየተጋለጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ያለባቸውን ችግር በማብራራት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ያስገቡት ደብዳቤ ለጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ አሰግድ ጌታቸው መመራቱን  ያመለከቱት ነዋሪዎቹና ባለ ድርጅቶቹ፣ እርሳቸውም፦ “ክፍለ ከተማው አጣርቶ ምላሽ ይስጥ” በማለት ጉዳዩን ወደ ክፍለ ከተማው መምራታቸውን ጠቁመዋል፡፡
የነዋሪዎቹን  ተቃውሞ አስመልክቶ  የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደስታ ፍጹምን ለማነጋገር የተደረገው ጥረት አልተሳካም።

No comments:

Post a Comment