በናትናኤል ካብቲመር (ኦስሎ ኖርዌይ) የካቲት 4 2006
ሁላችንም እንደምናውቀው ከግዜ ወደ ግዜ አሰቃቂነቱ እየጎላ የመጣው የሃገራችን ወጣት የስደት ጉዳይና ለዚህም ዋነኛ መነሾ ስለሆነው በሃገር ውስጥ የሚኖረው የኢትዮጲያ ወጣት ማህበረሰብ እጅግ የከበደ የኑሮ ሁኔታ በጨረፍታ አንዳንድ ነገር ለማለት አሰብኩ።
ለምንድነው ደሃ የሆንነው? ለምንስ ነው ደሃ ሆነን የምንቀጥለው? ለምንስ ነው ወጣቱ በሃገሩ ሰርቶ የመኖር ተስፋው መንምኖ ለህይወትአስጊ የሆነውን ስደት እየመረጠ ያለው? ተብለው ለሚነሱት ጥያቄዎች በርካታ መልሶች ሊነሱ ይችላሉ ነገር ግን ከሚነሱት መልሶች ሁላችንንምየሚያስማማውና ሚዛን የሚደፋው “የዜጎችን መብት አክብሮ የሚያስከብር እንዲሁም መሰረታዊነት ያለው የሃገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበሚዛናዊና ወጥ የሆን የኢኮኖሚ ስርዓት የሚገነባ ሁነኛ መንግስት ማጣታችን ነው” የሚለው ነው። በርካታ የሃገራችን ምሁራንም ሆነ በሞያው የበቃ ልምድ ያላቸው ግለሰቦች በሃገራቸው የኢኮኖሚ ስርዓት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ሃሳቦችን የሚያመነጩበት መድረክ እንዳይኖር የሚያደርግ ሌት ተቀን የስልጣን ዘመኑን ለማስረዘም ሲል ብቻ የኔ የሚላቸውን ግለሰቦች ከስልጣን ስልጣን እያቀያየረ የሚሾም ጎጠኛ ስርዓት እንደ እርግማን ተጭኖብናል። በዛው ፓርላማ ተብዬ እንኳን በተወሰነ መልኩም ቢሆን ተቃራኒ ሃሳብ እንዳይስተናገድበት ከላይ እስከታች ለሆነው ላልሆነው እጅ ሲያወጡና ሲያጨበጭቡ በሚውሉ የህዝብ ተወካዮች ነን ባይ አስገራሚ ግለሰቦች ሞልተውታል።
የወያኔ መንግስት እንደምንም ተብሎ በተገኘችው ቀዳዳ አንፃራዊ የሆን አማራጭ ሃሳብ ሲቀርብለት የሃሳብ አመንጪውን አካል ዘርና ማንነት በክፉ እየመነዘረ ሰርቶ የሚያሰራና በመጠኑም ቢሆን ሊያስተማምን የሚችል የኢኮኖሚ ስርዓት ተፈጥሮ ወጣቱ ተረጋግቶ ሃገሩ ላይ የሚኖርበትን እድል እያጨለመ የመብት ጥያቄዎችን እያፈነ ወጣቱን ለአስከፊው ስደት እየዳረገው ይገኛል።
ከዚህ ሁሉ እጅግ የሚያመው ደግሞ ለህይወት አስጊ መሆኑና ምንም አይነት የህይወት ዋስትና እንደሌለበት መዓት ግዜ የሚለፈፍለት የአረብ ሃገራት ስደት ያ ሁሉ ስቃይና ህይወትን የሚያሳጣ መከራ በተሰደዱ ዜጎች ላይ በተጨባጭ እየታየ አሁንም በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሲጎርፉ ይታያል። ወጣቱም ሃገሩ ላይ ከመኖር ይልቅ ከሞት የማይሻል የስደት አማራጭ ያስደፈረው ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው ህዝብን አስተዳድራለሁ ብሎ በስልጣን የተደላደለው የወያኔ መንግስት ነው።
ያደጉ ሃገሮች መንግስታት አብዛኛውን ግዜያቸውን የሚያጠፉት የሃገራቸውን የስራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ ብሎም ለማጥፋት ፣ ለሰራተኛው የሚከፈለው የደሞዝ ክፍያና ዝቅተኛ የክፍያ እርከን ላለው የኑሮ ሁኔታ የሚያስኖርና በቂ ስለመሆኑ እንዲሁም ዝቅተኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል አስተማማኝ የሆን የጤና ሽፋን መቅረቡን ለማረጋገጥ ነው። እንደው ዘለን እነሱን እንሁን ለማለት አይቃጣኝም ነገር ግን የመፍትሄ ሁሉ መጀመሪያ ችግሩን መለየት ስለሆነ ችግሩ አገዛዙ የፈጠረብን መላ ቅጡ የጠፋ የኢኮኖሚ ስርዓት መሆኑን ለመጠቆም ነው። ከዚሁ ጋር አያይዤ አንባቢያንን አንድ ነገር እንዲያስተውሉ የምጠይቀው የሃገራችን አነስተኛው የደሞዝ መጠን ስንት መሆኑን ፣ መጠኑን የሚያውቅ ካለም ከወቅቱ የኑሮ ሁኔታጋ እንዴት እንደሚጣጣም እንዲያሰላስሉ ነው።
የህወሃት መንግስት ባለስልጣናት ግን ስር ስለሰደደው የስራ አጥነትና ተያይዞ ስለሚመጣው የህይወት መመሰቃቀል ሲጠየቁ “ወጣቱ ስራፈጣሪ መሆን አለበት” የሚል መሰረት አልባ ለንግግር የቀለለ ለመተግበር ግን እጅግ የከበድ ብሂል እየተቀባበሉ ያስተጋባሉ።
ከወራት በፊት አቶ ቴውድሮስ አድሃኖም በአንድ የህክምና ዶክተሮች ምረቃ በዓል ላይ ተገኝተው ለተመራቂዎቹ ሃገራቸውን በፍፁም ጥለውእንዳይሄዱ ሲደሰኩሩ ነበር። እውነታው ሁሉም ግድ ሆኖበት እንጂ ማን ሃገሩን ጥሎ መሄድ ይፈልጋል ነው። በዘመነ ወያኔ እየተንሰራፋ ያለውበትዕቢት የተሞላ የመብት ረገጣ ፣ መረን የለቀቀ የኑሮ ልዩነት ፣ ልጓም ያጣው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት እንዲሁም የስርአቱን ተጠቃሚዎችንእንጂ የማህበረሰቡን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበው የኢኮኖሚ ስርዓት የሃገራችንን ወጣቶች የወደፊት የኑሮ ተስፋና እድል ምን ያህል ጥያቄ ውስጥእንዳስገባው ለዚህም የተቀመጠ መሬት የወረደ መፍትሄ እንደሌለ የምናውቀው ገሃድ የወጣ ሃቅ ነው።
የተገኘው ስራ ተሰርቶ እንኳን ኑሮን ለማሸነፍ እንደ አማራጭ የሚታየው የቁጠባ ባህልም ባልተረጋጋውና ጠንካራ መሰረት በሌለውየኢኮኖሚ ስርዓት ምክንያት በሚፈጠረው መላ በሌለው የምንዛሬና የዋጋ ከመጠን ያለፈ ግሽበት ሳቢያ ከጨዋታ ውጪ ሆኗል። ማህበረሰቡለአመታት ቆሎ ቆርጥሞ የቆጠበው ገንዘብ ዋጋ እያጣበት ኑሮውን ለእለት ብቻ ካረገው ሰነባብቷል። ወጣቱም ከዛችው ከአነስተኛ ደሞዙ ቆጥቦየወደፊት ኑሮውን እንዲሁም ቤተሰብ እንዳይመሰርት ይኸው ችግር እንቅፋት ሆኖበታል።
የስርዓቱ አመራሮችና ባለስልጣናትም የደሃውን ህዝብ ገንዘብ በአግባቡ ስራ ላይ ከማዋል ይልቅ ለግል ጥቅማቸው ወደ ውጪ ሃገራትማሸሸት ስራዬ ብለው ይዘውታል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ነፍሰ ጡር ሚስቶቻቸውን ሳይቀር ምዕራባዊ ሃገራት ላይ እየወሰዱ ማስወለድመጀመራቸው በግልፅ የሚታይ በሃገር ላይ ተስፋ የማጣት አሳፋሪ ስነ ምግባር የተለመደ ሆኗል። ሃገር እንመራለን እያሉ ነገር ግን ወጣቱ ሃገራዊስሜቱ እንዲዳብርና ሃገሩ ላይ ተስፋ እንዲኖረው ምሳሌ የመሆንን ሃላፊነት አሽቀንጥረው በመጣል በሃገር የመኩራትን ስሜት እንደሁዋላቀርነትሲቆጥሩት ማየት እጅግ ያሳዝናል።
መልካም አስተዳደር ከሚፈጥራቸው መልካም እንድምታዎች አንዱ ይኸው በሃገር ላይ ተስፋ ማሳደርን ከሁሉም ሃገርን ማስቀደምን ነው። መልካም አስተዳደር ሰርቶ ያሰራል እንዲሁም የዜጋው ጉዳት ይቆረቁረዋል። ነገር ግን የሃገራችን ጉዳይ የተገላቢጦሽ ነው “መልካም አስተዳደር መስርተናል” የሚሉት ባለስልጣናትና ቤተሰቦቻቸው ጭምር አካላቸው እንጂ መንፈሳቸው ሃገራቸው ላይ የለም። የወያኔ ስርዓት ለአመታት እያምታታና የተለያዩ ምክንያቶች እየደረደረ ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች እንዲሁም በሚሊዮን ለሚቆጠሩ የሃገራችን ወጣቶች ስደትና ተያያዥ እንግልቶች የተድበሰበሰ ሰበብ ሲሰጥ ቆይቷል። አሁን ግን ወጣቱ የችግሩ ዋና መንስኤ የመንግስት ተብየው ብልሹ አስተዳደርና መሆኑን ተረድቶ ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት መታገል አለበት።
አሁንም ቢሆን የወያኔ ስርዓት ካልተወገደ ህዝባችን መቸገሩን ወጣቱም ውድ ሃገሩን እየተወ መሰደዱን አያቋርጥም። የወያኔን ስርአት መወገድ ለችግራችን ሁሉ የመፍትሄ ጅማሮ ቁልፍ እርምጃ ነው።
No comments:
Post a Comment