BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

Sunday, 16 February 2014

ልጓም ያልተገኘለት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ

  • መንግስት የነዳጅ ዋጋን ማረጋጋት አለበት” (ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ ብሩህ ተስፋ)
  • ባለፉት 8 ዓመታት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ከአራት እጥፍ በላይ አድጓል
  • የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ መንግስት ለዜጎቹ ግድ ማጣቱን አመላካች ነው፡፡(የከተማዋ ነዋሪ)
የስምንት ዓመት የዋጋ ንረት
1998         2006
ቤንዚን             6.57        20.47
ነጭ ጋዝ            3.45        15.75
ታክሲ (አጭር ርቀት)        0.60ሳ        1.50
ታክሲ (ረዥም ርቀት)    1.25        3.00
አንበሳ አውቶብስ        0.50ሳ        300% ጭማሪ
አቶ መስፍን ወርቅነህ በመንግስት መ/ቤት የንብረት አስተዳደር ክፍል ውስጥ ተቀጥረው መስራት ከጀመሩ ወደ 18 ዓመት ገደማ አስቆጥረዋል፡፡ ሥራ ሲጀምሩ የወር ደመወዛቸው 720 ብር ነበር፡፡ በሥራ ዘመናቸው ለሦስት ጊዜ ያህል የደረጃ ዕድገቶችና የደመወዝ ጭማሪ ዕድሎችን አግኝተዋል፡፡ በ18 ዓመት ጊዜ ውስጥ ደሞዛቸው 1690 ብር ደርሷል፡፡

ከ15 ዓመት በፊት ትዳር የመሰረቱት በ280 ብር ከግለሰብ በተከራዩት ቤት ውስጥ ሲሆን ሦስት ልጆቻቸው የተወለዱትም እዚሁ ቤት ውስጥ ነው፡፡ የዛሬ 10 ዓመት ገደማ አከራያቸው ድንገተኛ የሃምሳ ብር ጭማሪ ሲያደርጉባቸው ክው ብለው ደነገጡ፡፡ የከተማው ዳርቻ አካባቢ አነስተኛ የኪራይ ቤት ማሰስ ጀመሩ።  በመጨረሻም አየር ጤና የተባለው ሰፈር በ200 ብር የኪራይ ቤት አገኙና ቤተሰባቸውን ይዘው ገቡ፡፡ አቶ መስፍን ከከተማ ወጣ ብለው ቤት የተከራዩት፣ወጪያቸውን በመቀነስ የሚያገኟትን ደሞዝ አብቃቅተው ሦስቱን የአብራካቸውን ክፋዮች ሳይርባቸው ሳይጠማቸው አሳድጋለሁ በሚል ነበር፡፡ ጊዜው ግን ከእሳቸው ጋር እልህ የተጋባ መሰለ፡፡ ከዓመት ዓመት ኑሮው ወደ ላይ ይተኮስ ጀመረ ይላሉ፤ አዛውንቱ፡፡
ከአየር ጤና ካዛንቺስ ሱፐር ማርኬት አካባቢ እሚገኘው መ/ቤታቸው ለመድረስ ሁለት አንበሳ አውቶቡሶችን መጠቀም ነበረባቸው፡፡ የአንድ ቀን የደርሶ መልስ ወጪያቸው 3 ብር ሲሆን በወር 80 ብር ገደማ ለትራንስፖርት ያወጣሉ፡፡ አንዳንዴ ከረፈደባቸው ወይ ከቸኮሉ  ከ5-6 ብር ለማውጣት ይገደዳሉ – በታክሲ ለመሄድ፡፡ የቤታቸውና የመሥሪያ ቤታቸው ርቀት ለምሣ ወደቤት መሄድን ፈፅሞ የሚያሳስብ አይደለም፡፡ መ/ቤታቸው አቅራቢያ ባለች አነስተኛ ምግብ ቤት ከ8-10 ብር እያወጡ  ምሳቸውን የሚመገቡት አቶ መስፍን፤ የምሳ ወርሃዊ ወጪያቸው ከ180-200 ብር ይደርስ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
በልጆች ት/ቤት በኩል የተገላገሉ ይመስላሉ። ሁሉም  በመንግስት ት/ቤት ነው የሚማሩት፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን በአመቱ መጀመሪያ ላይ ለትምህርት መሳሪያዎችና ለዩኒፎርም ማሰፊያ የሚጠየቁት ገንዘብ ወገብ ይቆርጣል። የቱንም ያህል ፈተናና ውጣ ውረድ ቢበዛባቸውም ሁሉን ተቋቁመው ወደፊት እንዲጓዙ የሚያደርጋቸው ተስፋቸው ነበር፡፡ መቼም ቢሆን የተሻለ ነገን ከማለም ቦዝነው አያውቁም፡፡ አስደንጋጩ የኑሮ ውድነት ግን ህይወታቸውን አጨለመባቸው፡፡ ህልምና ተስፋቸውን ነጠቃቸው፡፡
ለኑሮ ውድነቱ መባባስ፣ ለሸቀጦች ዋጋ መናር፣ ለትራንስፖርት ዋጋ በሁለትና ሦስት እጥፍ መጨመር፣ ለነዋሪው ኪስ መራቆት፣ ለችግርና ጉስቁል መጋለጥ፣ ወዘተ… ሰበቡ ልጓም ያጣው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ነው። ሌላው ቀርቶ መንግስት እንኳ በሰፊ እጁ ስላለቻለው “ድጎማውን ትቼ አለሁ” ብሎ በይፋ እጅ ሰጥቷል። ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ በነዳጅ ዋጋ ላይ የተደረገው ተከታታይ የዋጋ ጭማሪ የአቶ መስፍንን ህይወት ብቻ አይደለም ያናጋው፡፡ እንደሳቸው ያሉ ሚሊዮኖችን ኑሮ አቃውሷል፡፡ የሚሊዮኖችን ከእጅ ወደ አፍ ኑሮም አዛብቷል፡፡ አቶ መስፍን፤ ከ10 ብር በማይበልጥ ዋጋ ምሳቸውን ይበሉበት የነበረው ምግብ ቤት፤ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ዓይናቸው እያየ 40 እና 50 ብር ገባ፡፡ የዛሬው ብቻ ሳይሆን የነገው ጭምር ያሳስባቸው ጀመር፡፡ “አንዳንዴ የምንኖረው በተአምር ነው የሚመስለኝ፤ ምኑ ተምኑ ተደርጐ ከወር ሊደርስ እንደሚችል ማሰቡም ከባድ ነው፡፡ ተዉኝ እባካችሁ… ለዜጎች ግድ ያጣ መንግስት ነው ያለን፡፡ ብናልቅስ ምን ገዶት ብላችሁ!” ይላሉ  አቶ መስፍን – የኑሮ ውድነቱ የወለደውን ብሶታቸውን ሲተነፍሱ፡፡
የአለማቀፉን የነዳጅ ዋጋ ውጣ ውረድ ተንተርሶ፣ የንግድ ሚኒስቴር በወሩ መጨረሻ የሚያወጣው የነዳጅ ዋጋ ክለሣ፣ በ8 አመት ውስጥ ከሶስት እጥፍ በላይ መጨመሩን ያመለክታል፡፡ ከሚኒስቴር መ/ቤቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ከግንቦት 1998 ዓ.ም ጀምሮ በፍጥነት እየጨመረ የመጣው የአለማቀፉ የነዳጅ ዋጋ፣ በኢትዮጵያ የነዳጅ አቅርቦትና የዋጋ ተመን ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳርፏል፡፡ በአለማቀፍ ደረጃ የበርሜል ነዳጅ ዋጋ መጨመሩን ተከትሎ በዚያው ዓመት በተደረገው የዋጋ ክለሣ፣ የአዲስ አበባ የተራ ቤንዚን መሸጫ ዋጋ፣ በሊትር 6 ብር ከ57 ሣንቲም ገደማ የነበረ ሲሆን ታሪፉ አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንደገና ተሻሽሎ  በታህሳስ 1999 ዓ.ም 7 ብር ከ75 ሳንቲም  ሆነ፡፡ በ8 ወር ጊዜ ውስጥ በሊትር እስከ 1ብር ከ20 ሣንቲም የሚደርስ ጭማሪ ተደርጓል ማለት ነው፡፡ በወቅቱ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው በህብረተሰቡ የእለት ተእለት ኑሮ ላይ የጐላ ጫና አሳርፏል ለማለት ባያስደፍርም፣ ጭማሪው ቀደም ካሉት አመታት አንፃር ሲታይ ከፍተኛ ነበር፡፡
ከአመት በኋላ በንግድ ሚኒስቴር በተደረገው ክለሳ፣ የነዳጅ ዋጋ ወደ 9 ብር ከ60ሣ. አድጓል፡፡ ከቀድሞው ዓመት 1 ብር ከ85 ሣንቲም ጭማሪ በማሳየት ማለት ነው። የ2001 ዓ.ም የነዳጅ ዋጋ ደግሞ ቀደም ካለው ዓመት 1 ብር ከ40 የሚደርስ ቅናሽ እንዳሳየ የሚኒስቴር መ/ቤቱ መረጃ ይጠቁማል፡፡ ሰኔ 2001 የተከለሰው የነዳጅ ዋጋ እንደሚያመለክተው፤ ቤንዚን በሊትር 8 ብር ከ95 ሣንቲም ገደማ ሲሆን ከሁለት ወር በኋላ በጳጉሜ 2001 በተደረገው ክለሳ፣ አዲስ አበባ ላይ በሊትር የ2 ብር ገደማ ጭማሪ በማሳየት ወደ 10 ብር ከ93 ሣንቲም ተመነደገ፡፡ ከአንድ አመት በኋላ በህዳር 2003 ዓ.ም በከፍተኛ ሁኔታ ያሻቀበው የቤንዚን ዋጋ፣ 14 ብር ከ87 ሣንቲም የደረሰ ሲሆን ከአምስት ወር በኋላ በአብዛኛው የክልል ከተሞች በሊትር ከ22 ብር በላይ ሲሸጥ፣ በአዲስ አበባ የ6 ብር ጭማሪ ተደርጐበት   በሊትር 20 ብር ከ94 ሣንቲም ገባ። ይህም በ8 አመት ውስጥ በጥቂት ወራት ልዩነት ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የታየበት ወቅት መሆኑን ያመለክታል፡፡
2004 እና 2005 ዓ.ም ከሌሎቹ አመታት በንፅፅር የነዳጅ ዋጋ የተረጋጋበት ወቅት ነበር፡፡ መጠነኛ ቅናሽም አሳይቷል፡፡ በዚህ ጊዜ ከ18 ብር ከ75 ሣንቲም እስከ 19 ብር ከ45 ሣንቲም ባለው ዋጋ መካከል ሲዋልል ቆይቷል፡፡ ዘንድሮ በ2006 ዓ.ም የየካቲት ወር የቤንዚን ዋጋ በሊትር 20 ብር ከ47 ሣንቲም ተተምኗል፡፡
በዝቅተኛ ኑሮ ላይ የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል፣ እንደ እለት ተእለት ፍጆታው የሚጠቀምበት ነጭ ጋዝ (ላምባ)፤ በ1998 አዲስ አበባ ላይ በሊትር 3 ብር ከ45 ሲሸጥ፣ በየካቲት 2006 ዓ.ም 15 ብር ከ75 ሣንቲም እየተሸጠ ነው፤ በአምስት እጅ ጨምሮ፡፡
የንግድ ሚኒስቴር ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በየወሩ መጨረሻ ላይ የሚያደርገውን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ተከትሎ የመንገድ ትራንስፖርት ባለስልጣንም የትራንስፖርት ዋጋ ማሻሻያ እያደረገ ነው፡፡ የታሪፍ ጭማሪው በህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ሃይገር ባሶች፣ የከተማ አውቶቡሶችና ታክሲዎችን የሚመለከት ሲሆን አንበሳ አውቶቡሶች ከ0.50 ሳንቲም ታሪፍ ተነስተው እንደየርቀታቸው ከ300% በላይ ጭማሪ አድርገዋል፡፡ በ1998 ዓ.ም የአጭር ርቀት የታክሲ ተመን 65 ሳንቲም፣ የረዥም ርቀት 1.25 ሳንቲም የነበረ ሲሆን አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ክፍያው ወደ 95ሣ. እና 1.65 ሳንቲም ከፍ ብሏል፡፡ በየጊዜው በሚደረገው የዋጋ ማሻሻያ መሠረትም ታሪፉ እየጨመረ ሄዶ፣ በያዝነው የካቲት ወር የአጭር ርቀቱ 1.50 ሳንቲም፣ ረዥም ርቀቱ 3.00 ብር ሆኗል፡፡
በከፍተኛ ደረጃ እያሻቀበ የመጣው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በአገሪቱ ኢኮኖሚና በህብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ በተመለከተ ሙያዊ ማብራሪያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ የድህረ ምረቃ ፕሮግራም መምህር የሆኑት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ብሩህ ተስፋ፤ በየጊዜው በሚጨምረው የነዳጅ ዋጋ በይበልጥ የሚጐዳው በቋሚ ደመወዝ የሚተዳደረው የህብረተሰብ ክፍል ነው ይላሉ፡፡
የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ከአለም የነዳጅ ዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞ እንደሚከሰት የጠቆሙት ዶክተሩ፤ መንግስት ሌላውን ዘርፍ እየጎዳ በነዳጅ ላይ ድጎማ ያደርግ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ የነዳጅ ዋጋ በጨመረ ቁጥር በሁሉም ሴክተር ላይ የዋጋ ጭማሪ መታየቱ እንደማይቀር ጠቁመው፤ በዚህ ተጎጂ የሚሆነው በተለይ በቋሚ ደመወዝ የሚተዳደረው የህብረተሰብ ክፍል እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ “በዓለም የነዳጅ ዋጋ ስለጨመረ እኛም መጨር አለብን በማለት መንግስት በየጊዜው በነዳጅ ዋጋ ላይ የሚያደርገው ጭማሪ አያዋጣም” የሚሉት ባለሙያው፤ የነዳጅ ዋጋው በጨመረ ቁጥር የዋጋ ግሽበቱ እየጨመረ መሄዱ በህብረተሰቡ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ምን ያህል እንደሆነ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ተሰብስበው እንዲመክሩበትና መፍትሄ እንዲፈልጉለት ማድረግ ተገቢ ነው” ሲሉም ይመሰክራሉ፡፡ በዋናነት የነዳጅ ዋጋን የማረጋጋት ኃላፊነት የመንግስት መሆኑንም ያሰምሩበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአብዛኛው ህብረተሰብ አቀፍ ዘርፍ በመሆኑ መንግስት ሊቆጣጠረው የሚችለው ነው ያሉት ዶክተሩ፤ የነዳጅ ዋጋ በጨመረ ቁጥር ነጋዴው በሚሸጠው ዕቃ ላይ ዋጋ ጨምሮ በመሸጥ ጭማሪውን ሊቋቋመው እንደሚችል ጠቅሰው፣ ሸማቹ በተለይም ቋሚ ገቢ ያላቸው የመንግስት ሰራተኞችና ጡረተኞች ግን ለጉዳት እንደሚጋለጡ ተናግረዋል፡፡ የመንግስት ሰራተኞች ሲባልም የጦር ኃይሎችና የፖሊስ አባላትን እንደሚያካትት፣ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎችም በዋጋ ንረቱ እንደ ሚጎዱ በመግለፅ ጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሊታይ ይገባዋል ብለዋል፡፡
አገሪቱ በዓመት ወደ ሶስት ቢሊዮን ዶላር የሚፈጅ ነዳጅ እንደምታስገባ የጠቆሙት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ በነዳጅ ዋጋ ላይ የሚደረገውን ጭማሪ ለመግታት ሌላው አማራጭ የነዳጅ ፍጆታን መቀነስ እንደሆነ ጠቁመዋል። በከፍተኛ መጠን ነዳጅ የሚጠቀሙት የመንግስት መስሪያቤቶች ሲሆኑ መኪኖች፣ ጄኔሬተሮች፣ ግድቦችና መሰል ነገሮች የሚሰሩት በነዳጅ በተለይም በናፍጣ በመሆኑ ይህንን ፍጆታ መቀነስ የሚቻልበት መንገድ ሊታሰብበት ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡ ሌላው ምሁሩ አማራጭ ነው ያሉት ጉዳይ የነዳጅ ፍለጋውን አጠናክሮ መቀጠል ሲሆን ነዳጅን እየደጎሙ መቀጠሉ አዋጪ ነው የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡
የነዳጅ ዋጋ ማሻቀቡ ሌላው ምክንያት ነው ያሉት የፍጆታ መጠን መጨመሩ ሲሆን አሁን አገሪቱ ውስጥ ባለው ሁኔታ እየተሰሩ ያሉት መሰረተ ልማቶች፤ ማሽኖችና መሳሪያዎች የሚወስዱት የነዳጅ ፍጆታ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ አገራችን በአብዛኛው ነዳጅ የምታስገባው ከኩዌት መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ በአሁኑ ወቅት የሚታየውን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ለመግታት መንግስት ሊያስብበት ይገባል ይላሉ። የልማት ስራዎች ሲሰሩም የህዝቡን ጥቅምና ፍላጎት ሳይነኩ መሆን እንዳለባቸው ጠቁመው፤ “ከአቅም በላይ የሚሰራ ልማት ጫናው በህብረተሰቡ ጫንቃ ላይ ያርፍና ህብረተሰቡ ይበልጥ እየተቀየመ ከመጣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶችን ይፈጥራል” ብለዋል፡፡ በእሳቸው ዘመን ከንጉሱ ጊዜ ተቃውሞ ለለውጡ ዋንኛ መንስኤ የነበረው የታክሲ ነጂዎች በነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ምክንያት ያስነሱት ተቃውሞና ያደረጉት ሰላማዊ ሰልፍ መሆኑንም ዶክተር ቆስጠንጢኖስ አስታውሰዋል፡፡

No comments:

Post a Comment