(ዘ-ሐበሻ) ራሳቸው በጠሩት ግምገማ፣ ራሳቸውን አስገምግመው ከፓርቲው ሊቀመንበርነታቸው መነሳታቸው የንጽህናቸው ውጤት መሆኑን ሲናገሩ እንደነበረ የሚነገርላቸውና በአንድ ወቅት በጋምቤላ ስለነበረው ጭፍጨፋ ተጠያቂ ነህ ሲባሉ “መሳሪያውን ያቀበለው መለስ ዜናዊም መጠየቅ አለበት” ብለዋል የተባሉት የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንትና የአሁኑ የፌዴል ጉዳዮች ሚ/ር ደኤታ አቶ ኦሞት ኦባንግ ከሃገር መፈርጠጣቸው ተሰማ።
በስልጣን ዘመናቸው ፕሬዚዳንቱ የክልሉን ደን እያስጨፈጨፈና ህዝቡን እያፈናቀለ ስላለው የመሬት ሽያጭና ነጠቃ የክልሉ እጅ የለበትም በሚል የተናገሩት ኦሞት ሂይውማን ራይትስ ዎች ባወጣው ሪፖርት ላይ በክልሉ ስለሚካሄደው የመሬት ነጠቃ አቶ በረከት ስምኦን በበኩላቸው ምላሽ ሲሰጡ በክልሉ ከሶስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ ባለቤት የሌለው መሬት መኖሩን መናገራቸው አይዘነጋም።........
ኦሞት ኦባንግ ከሃገር እንዳይወጡ ከፍተኛ የሆነ ጥበቃ ሲደረግባቸው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን በተለይም በጋምቤላ ክልል ስለተፈጸሙት የጅምላ ጭፍጨፋዎች በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ምስክር ይሆናሉ በሚል ፍራቻ በሕወሓት/ኢሕአዴጎች ከሃገር እንዳይወጡ ይፈራ እንደነበርና የፌደራል ጉዳዮች ሚ/ር ደኤታ የተደረጉትም “ጠላትህን አታርቀው፤ አቅርበውና እንስቅቃሴውን ተከታተለው” በሚለው የፖለቲካ አካሄድ እንደነበር የውስጥ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ይህን በማስመልከትም አዲሲቷ ኢትዮጵያ ለጋራ ንቅናቄ በአንድ ወቅት ባወጣው መረጃ “አቶ ኦሞት ካገር ከወጡ አቶ መለስና መንግስታቸው ላይ ምስክር ይሆናሉ። አቶ ኦሞት ከተሰደዱ በአካል ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ምስክርነታቸውን መስጠት ግዳጃቸው በመሆኑ የህወሃት ሰዎች ስጋት አለባቸው። ስለዚህ አቶ ኦሞት በተቀመጠላቸው የስድስት ወር የሃላፊነት ዘመናቸው አድርጉ የተባሉትን እየፈጸሙ ይኖራሉ። የህወሃት ሂሳብ ይህ ቢሆንም በመጨረሻ ያልታሰበ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል እገምታለሁ። ምክንያቱም ነገሮች ተነካክተዋል” የሚል አስተያየት አስነብቦ እንደነበር ይታወሳል።
የሚኒስትር ዲኤታውን ኩብለላ በተመለከተ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የተጠየቁት የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም አቶ ኡመt በስራ ገበታቸው ላይ እንደሌሉ ማረጋገጣቸውን ገልጸው መስሪያ ቤታቸው ጉዳዩን እያጣራ እንደሚገኝ ሲናገሩ አቶ ኡመትም ወደ ሃገራቸው መመለስ እንደማይፈልጉ መናገራቸውን ጨምሮ የመጣው መረጃ ሲጠቁም፤ አሁን ግን የት ሃገር እንዳሉ ለጊዜው ማረጋገጥ እንዳልተቻለ ተጠቁሟል።
በጋምቤላ በተፈፀመው ጭፍጨፋ የሚከተሉት ሰዎች በዋነኝነት ለፍርድ መቅረብ አለባቸው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሉ።
1. አባይ ፀሀዬ (በጊዜው የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር የነበረ)
2. ዶ/ር ገብረአብ ባርናባስ (በጊዜው ሚኒስትር ደኤታ የነበረና በቦታው በመገኘት ጭፍጨፋውን ያስተባብር የነበረ)
3. ኮለኔል ፀጋዬ (በጊዜው በቦታው የነበረው ወታደራዊ ሀይል አዛዥ)
4. ኡመት ኦባንግ (አሁን ከሃገር የፈረጠጡት የቀድሞው የጋምቤላ ክልል አስተዳዳሪ)።
No comments:
Post a Comment