BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

Sunday, 2 February 2014

ሌንጮ ለታ – ታሪክ ሊሰሩ ወይንስ ታሪክ ሊጽፉ…?

ክንፉ አሰፋ

Former OLF chairman Lencho Leta
ኦቦ ሌንጮ ለታ
ኢትዮጵያዊው ቱጃር ለለውጥ ብለው በኮንትራት ታክሲ በመሄድ ላይ ናቸው። እሳቸውን የጫነው ታክሲ መስቀል አደባባይ ላይ ሲደርስ በድንገት ቀጥ ብሎ ቆመ። ሾፌሩ ተደናጋጠ። መኪናውን እንደገና ለማስንሳት ብዙ ሞከረ። ከብዙ ሙከራ በኋላ ጥረቱ ስላልተሳካለት ቱጃሩን ለትብብር ጠየቃቸው። እንዲህ ሲል። “ወጣ ብለው ይግፉ።”  ቱጃሩ በመገረም ሾፌሩን አዩት።  ”ይግዙ” ማለትህ ነው ሲሉም መለሱለት። እኚህ ሰው መኪናውን ከመግፋት ይልቅ አዲስ መኪና መግዛት ይቀላቸዋል።  የቤቶች ድራማ ላይ እከ ደከ አስር ጊዜ “እኔን ነው?” የሚለው ወዶ አይደለም። ማመን የሚቸግሩንን ነገሮች ማጣራት ስንፈልግ እንደጋግማለን።
በዚያን ሰሞን በኦቦ ሌንጮ ለታ የወጣው ዜና ብዙዎችን አስገርሟል።
“ሃገር ቤት ገብተን በመታገል አዲስ ታሪክ እንሰራለን።” የሚል ነበር የዜና እወጃው ርዕስ። ይህን ርዕስ እንዳየሁ አይኔን በደንብ ጠረግ ጠረግ አደረግኩና እንደገና አነበብኩት።..........
“ታሪክ እንሰራለን” የሚለው ሃረግ በስህተት የሰፈረ ነበር የመሰለኝ።  ሌንጮ ለማለት የፈለጉት “ታሪክ እናነባለን” ይሆናል በሚል ጥርጣሬ ደጋግሜ ያየሁት።  ያነበብኩት ነገር ትክክል ነው። ይህንኑ ቃል ከራሳቸው አንደበትም ሠማሁ።  በስህተት የሰፈረ ዜና አልነበረም።  ታሪክን ማንበቡም ሆነ መስራቱ ቀርቶ “ሃገር ቤት ገብተን አዲስ ታሪክ እንጽፋለን።” የሚል ቢሆን እንኳን ግርታውን ይቀንሰው ነበር።
በፍትህ ሳይሆን ይልቁንም በአዋጅ በምትተዳደር ኢትዮጵያ፤ እጅና እግራቸውን ብቻ ይዘው በመግባት ታሪክ መስራት የሚችሉ ከሆነ በምትሃት አልያም በመለኮታዊ ሃይል ብቻ መሆን አለበት። ሌንጮ ሃገር ቤት ገብተው ሰላማዊ ትግል ለማድረግ መወሰናቸው ላይ ምንም ችግር የለብኝም። የዚህ ውሳኔ ትክክለኝነት የሚዳኘው አስቀድመው በሚተቹ እና በሚተነብዩ የፖለቲካ ነብያት አይደለም። ፍርድ የሚሰጠው ሂደቱ በተግባር ሲፈተን ብቻ ይሆናል። ይህን ለማየት ደግሞ ብዙም ሩቅ አይሆንም።  በጎረበጠ የፖለቲካ መንገድ ላይ ጉዞ ለማድረግ ወደ ሃገር ቤት ለመግባት መወሰናቸው ግን አስመራ ላይ፤ በሻእቢያ ከታገቱት የኦነግ መሪዎች የተሻለ ውሳኔ ይመስላል።  ታሪክ ለመስራት አስመራ የመሸጉት እነ ዳውድ ኢብሳ ታሪክ ሆነው ቀርተዋል።
ችግሩ ያለው “ታሪክ እንሰራለን” ማለቱ ላይ ነው። እንደዚህ አይነት የፖለቲካ ትግል ውሳኔ ላይ መድረስ ቀላል ነገር አይደለም። ከመቅጽበት የመጣው ይህ ውሳኔ ልክ እንደ ኦሎምፒክ ውድድር ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ አትሌት ይመስላል። አትሌቲክስም ቢሆን የአካል ብቃትና በቂ ዝግጅትን ይጠይቃል።  ፖለቲካ ደግሞ ዘው ብለው ገብተው ታሪክ የሚሰሩበት በኦሎምፒክ የውድድር መድረክ አይደለም። እነ ሌንጮ እየነገሩን ያሉት አዲስ አበባ ገብተው በባላገሩ አይደል ላይ ለመወዳደር አይደለም። በባላገሩ የጫወታ ደንብ ጥሩ ስራ የሰራም፤ አስቀያሚ ስራ የሰራም ይሸለማል። ሌንጮ ታሪክ እንሰራለን የሚሉት “ስልጣን ወይንም ሞት!” የሚል መፈክር አንግቦ እስካፍንጫው የታጠቀ ሃይልን በመጋፈጥ ነው።
ታሪክን ለመስራት ብቃት ያላቸው ድርጅቶች በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ጠፍተው አያውቁም። ከኦሮሞ ድርጅቶችም ቢሆን እነ ኦቦ ቡልቻ ደመቅሳ እና ፕ/ር መረራ ጉዲና አሉ።  የኦሮሞን ህዝብ አደራጅተው በምርጫም፣ በፓርላማም፣ በሰልፍም፣ በእርግማንም፣ በጸሎትና ምልጃም፣  በወረቀትም … ብዙ ተጉዘዋል። የእነዚህ ድርጅቶች አባላት እንደጥጃ እየተለቀሙ እስር ቤቱን ከማጨናነቃቸው በቀር ታሪክ ሲሰሩ አላየንም። አንድ እርምጃ ወደፊት፤ አስር እርምጃ ወደኋላ እየተጓዙ ሄደው…ሄደው በመጨረሻ ራሳቸውም ታሪክ ከመሆን አላለፉም። ይህ ለአቶ ሌንጮ ለታ እንግዳ ነገር አይደለም። አቶ ሌንጮ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ በከባድ ሚዛን ደረጃ የሚመደቡ ናቸው።
በዛሬይቱ ኢትዮጵያ በፖለቲካ ታግሎ ታሪክ ከመስራት ይልቅ ነድጅ ቆፍሮ ታሪክ መስራት እንደሚቀል ለሌንጮም አዲስ ነገር አይደለም። እርግጥ ነው።  የታሪክ ትርጉም አሰጣጣችን ላይ እንለያይ ይሆናል። የገዥው ፓርቲ የታሪክ ትርጉምም ከልማት ጋር ይያያዛል። በዘመናችን ብዙ ታሪኮችን እየሰማን ነው። ልማታዊ አስተሳሰብ ያለው ሰው ሁሉ ዛሬ ታሪክ ሰሪ ይባላል። ታሪክ ሰርተው የሚሸለሙ የልማት አርበኞችን በቴሌቭዥን እናያለን።  በአነስተኛና ጥቃቅን እየተደራጁ የኮብል-ስቶን ድንጋይን እያናገሩ ያሉ ወጣት ምሁራንም በታሪክ መዝገብ ላይ እየሰፈሩ ይገኛል።
ኦቦ ሌንጮ ታሪክ የሚሉን እንዲህ አይነቱን ድራማ እንደማይሆን እርግጠኞች አይደለንም።  እኝህ የፖለቲካ መሪ ታሪክ መስራት ከነበረባቸው ግዜው አሁን አይደለም። በሽግግሩ ዘመን 20 ሺህ ጦር እና 20 መቀመጫ ይዘው በነበሩበት ጊዜ ለዚህ እድሉ ነበራቸው። ያንን እድል ይዘው ታሪክ ከመስራት ይልቅ ድርጅታቸው ጥቁር ነጥብ ጥሎ ነበር ያለፈው።  አቶ ሌንጮ ታሪክ መስራት ከነበረባቸው በሽግግሩ መንግስት የኢትዮጵያ መሪ ሆነው በተመረጡ ግዜ ነበር። በወቅቱ ምን ነበር ያሉት?  “በዚህ ላይ አልተዘጋጀሁበትም።” ሲሉ የእድሉን በር ራሳቸው ዘጉት። በርግጥ ያን ጊዜ ከኦሮሚያ የመገንጠል አዙሪት ውስጥ አልወጡም ነበር። ትልቅ ህዝብን ይዘናል እያሉ፤ የመገንጠል ጥያቄን ሲያነሱ በአለም ላይ የመጀመሪያዎቹ ብቻ አይደሉም። የኦሮሞን ህዝብ በፖለቲካ አናሳ ማድረጋቸው የታያቸውም ከ40 አመታት በኋላ መሆኑ ነው።  በዚያን ወቅት ኢትዮጵያን መምራት እንችላለን ለማለት በራስ መተማመን አልነበራቸውም።  አንድ ሰው አንድ ድምጽ በሚል መርህ ምርጫ አድርገው ከመጓዝ ይልቅ፤ እንደ አናሳ ጎሳ “መገንጠል አለብን” የሚል ያታሪክ ስህተት ውስጥ ነበሩ።
ከኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር ወጥተው የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ግንባርን መመስረታቸው ከታሪክ ተወቃጭሽነት ሊያድናቸው ይችላል ። ይህንን በማድረጋቸው የሰማይና የምድርን ያህል ርቆ የነበረውን የፖለቲካ መስመር ሊያጠበው እንደሚችል ግልጽ ነው። ዛሬ የመገንጠልን ጥያቄውን ውድቅ አድርገው ለዲሞክራሲና ለፍትህ መታገል መምረጣቸው ታሪክ ሰሪ ሊያደርጋቸው አይችልም። ይህ ሊሆን የሚችለው ለውጥ አምጥተው ፍትሃዊ ስርዓት ማስፈን ሲችሉ ብቻ ነው።
ሌንጮ ለታ አዲስ አበባ በመግባት ታሪክ እሰራለሁ ሲሉ ይህ የመጀመርያቸውም አይደለም። እ.ኤ.አ. 1993 የስራ ባልደረባቸውን ከከርቸሌ ለማስፈታት አዲስ አበባ ዘው ብለው ገብተው ነበር። እኝህ ሰው ሲገቡ ቦሌ ላይ ልዩ አቀባበል ተደረገላቸው። በብረት ተጠፍረውም ከርችሌ ተወረወሩ። በወቅቱ አዲስ አበባ ላይ ተካሂዶ በነበረው የግዮኑ የሰላም እና እርቅ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ሲገቡ የታሰሩ ልኡካንን እዚያው ተቀላቀሉ።
ሌንጮ በዚያ ሰዓት ታሪክ ይሰራሉ ብለን ጠብቀን ነበር። ግን ይቅርታ ጠይቀው ከእስር ለመውጣት አንድ ሳምንትም አልፈጀባቸውም።  በወቅቱ ከአቶ ሌንጮ ለታ ጋር ረጅም ቃለ-መጠይቅ አድርጌ ይህንን ታሪክ በማሳትመው ጋዜጣ ላይ ለህዝብ ይፋ አድርጌዋለሁ። እርግጥ ነው። የሌንጮ ለታ ፖለቲካ እውቀት የሚደነቅ ነው። በፖለቲካ ብስለታቸውና ትንተናቸው ከማደንቃቸው የፖለቲካ ሰዎች አንዱ ናቸው።  ፖለቲካ ማወቅ እና ህዝብን መምራት ግን በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ብዙውን ግዜ የሰዎችን የፖለቲካ ብቃት የምንለካው በንግግር ችሎታው ብቻ ነው። ጥሩ የፖለቲካ መሪ አስተዋይም መሆን አለበት። የመሪ አስተዋይ አለመሆን ደግሞ ችግር የመፍታት ብቃታ ማጣቱን ነው የሚያሳየን።  ኦነግ ከ40 አመታት በላይ በትግል ላይ እንደሆነ ይነገረን እንጂ ድርጅቱ ድል አድርጎ አይተን አናውቅም። የሽግግሩን መንግስት ላይም ቢሆን የተገኘው በድል አድራጊነት ሳይሆን ከህወሃት እና ከሻእቢያ ጥሪ ተደርጎለት ነበር።
በአሁኑ የአዲስ አበባ ጉዞ ሌንጮ እንደቀድሞው ልዩ አቀባበል ላይገጥማቸው ይችላል። በእርግጠኝነት ለመናገር ከጉዞው በፊት አንዳች ቅድመ ሁኔታዎች ወይንም ስምምነቶች ይኖራሉ።  ይህ ካልሆነ ግን እኝህን ሰው በቀይ መስመር ላይ ማስቆም ወይንም ደግሞ ማኖ ማስነካቱ አይቀሬ ነው። እሳቸውን ቀይ መስመር ላይ ለማቆስም በጣም ቀላል ነው። የበደኖው፣ የዋተሩና የአርባጉጉ ፋይሎች እየተመዘዙ ማውጣት ብቻ ይበቃል። አልያም ቦሌ ላይ እነ ዋልታ ብቅ ብለው በካሜራ ይቀበሏቸዋል። ልማቱን እንዲያደንቁ ይጠየቃሉ። በእስር ያሉ ወገኖችና “ሽብርተኞች”ን ማውገዛቸውም የግድ ነው። በዚህ መስመር ላይ ከሄዱ  ”አባ ጸበል ይርጩን” ብለው እንደገቡት እንደነ ስም አይጠሬ ተዋርደው ይመለሱና የፖለቲካ ሞትን ዳግም ይቀምሷታል።
ለእንደዚህ አይነቱ “ልማታዊ” የተቃውሞ አስተሳሰብ ሳይገዙ ታሪክ መስራት ከተቻለ ግን ተአምር ይሆናል።  ለማንኛውም መልካም ጉዞ…

No comments:

Post a Comment