የካቲት ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአማራ ክልል ቋሪትና ጃቢጠህናን ወረዳዎች ይካሄድ የነበረው መረን የለቀቀ ህገወጥ የአራጣ ብድር ስርዓት በአስከተለው ቀውስ ከ250 በላይ ጠንካራ ነጋዴዎች ተሰደዋል ተባለ፡፡
ከፍተኛ ማታለል የነበረበት ይህ ህገወጥ የአራጣ ብድር ስርዓት ነጋዴዎችን ባዶ ያስቀረና ያሰደደ ከመሆኑ ባለፈ ብዙዎችን ለእብደትና ለቤት መፍረስ ዳርጓል ሲሉ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉና ከ121 ሺህ ብር በላይ ተወሰደብኝ ያሉ አንድ የገነት አቦ ነዋሪ ጎልማሳ ተናግረዋል፡፡
ይህ አይን ያወጣ ዘረፋና ማታለል ሲፈጽም ከመንግስት ዕይታ ወጭ አልነበርም ያሉት ጎልማሳው መንግስት አራት ግዙፍ ጥፋቶችን ፈጽሟል ብሏል፡፡
መንግስት ኢንቨስትመንት ደረጃ ላይ ያልደረሱ ወጣቶችና ጀማሪ ባለሀብቶች ከንግድ ባንክ ብድር እንዳይወስዱ በመከልከላቸው ወደ ሌላ አማራጭ ፍለጋ እንዲዛወሩ ማስገደዱ፣ህገወጥ ዘራፈው በድብቅ ተካሄደ ቢባልም ከመንግስት እይታ ውጭ እንዳልሆነ እየታወቀ አስቸኳይ ዘረፋን የመከላከል መፍትሄ አለመውስዱ፣ዘራፊዎች በህግ እንዲጠይቁ በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ የህዝብን ሀብት ዘረፈው የወሰዱና የገንዘብ ጡንቻቸው የፈረጠመ ግለሰቦች የህጉን ፍትሐዊነት ጥያቄ ውስጥ ሲያስገቡት መንግስት ለተጎጂዎች እገዛ አለማድረጉና ገና ከጅምሩ ህዝብ እንዳይታለል የግንዛቤ ማስጨበጫ ተከታታይ ስልጠና እንዲሰጥ አለማድረጉ ናቸው በማለት አስረድተዋ፡፡
ከአስር ሚሊዮን ብር በላይ ሊመዘበር እንደሚችል እገምታለሁ ያሉት ጎልማሳው የክርክር ሂደቱ አዲስ አበባ ላይ መካሄዱን ቢያውቁም የትኛው ምድብ ችሎት እንደሆነ እውቅና የለኝም ካሉ በኋላ ከአንድ አመት በላይ በተካሄደው በዚህ ክርክር ግን የመጣ ምንም ለውጥ አለመኖሩን ስንመለከት መንግስትና ፍትሐዊነት ስለመኖሩ እንደንተራጠር አድርጎናል ሲሉ አማረው ተናግረዋል፡፡
ነጋዴዎቹ ቤተሰቦቻቸውን በትነው ለቀን ስራ ወደ ባህርዳርና ሌሎች ከተሞች በመሰደዳቸው የአካባቢው ንግድ ስርዓት ተሸመድምዷል፣ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ ተከስቷል ያሉት ጎልማሳው ፣ ከተሰደዱት መካከል አቶ ሞላልኝ አበበ፣አቶ አበባው፣አቶ ካሳ እንዳላማውን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል ብለዋል፡፡
“እንደ ቋሪቷ ገነት አቦ በመቅሰፍቱ የተመታ ይኖራል ለማለት አልደፈርም እንጂ” በሁሉም የአማራ ክልል ከተሞች የአርሶ አደሩንና የነጋዴውን ሀብት የዘረፈ ህገወጥ የአረጣ ብድር ተፈጽሟል የሚሉት ፣ ጎልማሳው መንግስት አሁንም መፍትሄ እንዲያመጣለን እንጠይቃለን ብለዋል፡፡
No comments:
Post a Comment