BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

Wednesday, 12 February 2014

የግብፅ እና የኢትዮጵያ ውይይት ከጅምሩ ተቋረጠ

የካቲት ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የግብፅ የውኃና መስኖ ሚኒስትር መሐመድ አብዱል ሙታሊብ ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ለማድረግ በጠየቁት መሠረት ባለፈው ሰኞ አዲስ አበባ ቢገቡም፣ የዓባይ ግድብ ግንባታ እንዲቆም በመጠየቃቸው ውይይቱ በሰዓታት ውስጥ ተቋረጠ፡፡

ሪፖርተር እንደዘገበው  የግብፅ ሚኒስትር ከኢትዮጵያ አቻቸው አቶ አለማየሁ ተገኑና ከባልደረቦቻቸው፣ እንዲሁም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተወከሉ ባለሙያዎች ጋር ባለፈው ሰኞ  ተገናኝተዋል።
ይዘዋቸው የመጡት አጀንዳዎችም ከዚህ ቀደም ተቀባይነት ሊያገኝ ያልቻለውን የዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ቡድን ተጨማሪ ጥናት እንዲያከናውን የሚጠይቅ፣ እንዲሁም በግንባታው ላይ መተማመንን ማጐልበት የሚሉ ጉዳዮች ናቸው።

በግድቡ ግንባታ ላይ መተማመንን ማጐልበት በሚል በግብፅ በኩል በቀረበው ሐሳብ ውስጥ የቀድሞው የግብፅ የውኃ መጠን እንደማይቀንስ ኢትዮጵያ እንድታረጋግጥ የሚጠይቅ ነው፡፡
ይህንን በተመለከተ በሰኞው ስብሰባ የግብፁ ሚኒስትር በድጋሚ አንስተው ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው ግልጽ እንደተደረገላቸው አቶ አለማየሁ በውይይት መድረኩ ላይ ለተገኙ ጋዜጠኞች ገልጸዋል፡፡
የግብፅ የውኃ ሀብት ሚኒስትር ዓለም አቀፍ ውይይቱን ለመቀጠልና ከሦስቱ አገሮች በሚወከሉ ባለሙያዎች የቀድሞዎቹ ባለሙያዎች ያቀረቧቸው ምክረ ሐሳቦች ተግባራዊ እንዲደረጉ፣ የግድቡ ግንባታ ይቁም ብለው መጠየቃቸውን አቶ አለማየሁ ተገኑ ገልጸዋል።፡፡
‹‹ያነሷቸው ጥያቄዎች በጭራሽ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት እንደማይኖራቸውና የግድቡ ግንባታም ለሰከንዶች እንደማይቆም ካስረዳናቸው በኋላ ምሳ ጋብዘናቸው በሦስት ሰዓታት ውስጥ ተለያይተናል፤›› ሲሉ አቶ አለማየሁ  ተናግረዋል።

No comments:

Post a Comment